በአዲስ አበባ ከተማ 74 ጊዜያዊ የደረቅ ቆሻሻ ማጠራቀሚያ እና መለያ ቦታዎች ቢያስፈልጉም ግንባታቸው እየተካሔደ ያለው የ18ቱ ብቻ መሆኑ ታወቀ፡፡
በከተማዋ ደረቅ ቆሻሻ ከምንጩ ሳይለይ ወደ ጊዜያዊ ማቆያና መለያ ቦታዎች መከመሩ ጥቅም ላይ ሊውሉ የሚችሉትን ጥሬ እቃዎች ከማስቀረቱም ባሻገር ከ60 ዓመታት በላይ የከተማዋን ቆሻሻ በመሸከም እያገለገለ ላለው ረጲ መጨናነቅን እየፈጠረ መሆኑ በተደጋጋሚ ይነሳል። በዚህም ባለፈው ዓመት 85 ጊዜያዊ የቆሻሻ ማከማቻና መለያ ቦታዎችን ለመገንባት የመሬት አቅርቦት ይጠበቅ እንደነበር በወቅቱ የነበሩት የጽዳት አስተዳደር ኤጀንሲ ሥራ አስኪጆች ሲናገሩም ነበር፡፡
አዲስ ማለዳ ከከተማዋ የደረቅ ቆሻሻ አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ሥራ አስከያጅ እሸቱ ለማ እንደተረዳችው የማዕከላቱ ብዛት ወደ 74 ዝቅ ተደርጎ ታቅዷል፡፡ ይህም ቀድሞ ከ630 በላይ የነበሩትን ደረቅ ቆሻሻ አንሺ ማኅበራት ወደ ሽርክና በመቀየር ቁጥራቸውን 74 ለማድረግ ከተጀመረው እንቅስቀሴ ጋር በተያያዘ ነው፡፡ ያም ሆኖ ለእነዚህ ማዕከላት ግንባታ ከአስተዳደሩ 74 ቦታዎች የሚስፈልጉ ቢሆንም የተገኘው ቦታ 36 ብቻ መሆኑን ሥራ አስኪያጁ አሳውቀዋል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ 18 ቦታዎች ላይ ጊዜያዊ ማዕከላቱ እየተገነቡ ሲሆን የሦስቱ ግንባታዎች በቅርቡ ተጠናቀው አገልግሎት መስጠት ይጀምራሉ ተብሎላቸዋል፡፡
ለእያንዳንዱ ማዕከላት ግንባታ በነፍስ ወከፍ ሦስት ሚሊዮን 17 ሺሕ ብር መመደቡም ተሰምቷል፡፡
ሁሉም ቆሻሻ ሳይለይ ወደ ረጲ ስለሚሔድ በቦታው ጫና እየፈጠረና ለአደጋ ሥጋትም እየሆነ ነው የተባለ ሲሆን፣ ለመልሶ ጥቅም የሚሆኑ የተለያዩ የፕላስቲክ ጠርሙሶች፣ ወረቀቶች፣ ካርቶኖች እና ጨርቃ ጨርቆችን በየፈርጁ በመለየት ከሚመነጨው ቆሻሻ 15 በመቶ የሚሆነው ጥቅም ላይ እንዲውል ማድረግ እንደሚቻልም ሥራ አስኪያጁ አስገንዝበዋል፡፡
በተያያዘ ዜና መጋቢት 2/2009 በረጲ ደረቅ ቆሻሻ ማስወገጃ ቦታ በተከሰተውና ከ113 በላይ ዜጎችን ሕይወት የቀጠፈው የቆሻሻ መደርመስ አደጋ ዳግም እንዳይከሰት ለማድረግ ያስችላል የተባለ ሥራ መከወኑ ተነግሯል፡፡ ይህም በጃፓን መንግሥት ኹለት ሚሊየን ዶላር ድጋፍ እና በከተማ አስተዳደሩ 100 ሺሕ ዶላር ድጎማ ችግሩ በድጋሜ እንዳይከሰት በጃፓን የፋኩውካ ቴክኖሎጂ የተሰኘን ዘዴ በመጠቀም ሥፍራው ማስተካከልና ከአደጋ ሥጋት የማራቅ ሥራ ተሰርቶ ከሰሞኑ መጠናቀቁን አዲስ ማለዳ ከኤጀንሲው ሥራ አስኪያጅ ሰምታለች፡፡
የመከላከያ ፕሮጀክቱ ቆሻሻው እንዳይናድና እንዳይንሸራተት ጋቢዎኖችን በመሥራት በተወገደው ቆሻሻ ውስጥ ኦክሰጂን እስከ ታች ድረስ እንዲገባ እና እንዲበሰብስ በማስቻል የቆሻሻው መጠን እንዲቀንስ እና ከዚህ በፊት በሜቴን ጋዝ ታምቆ እየወጣ እሳት ይፈጥር የነበረውን ሒደት ኦክስጂን በማስገባት ካርቦንዳይ ኦክሳድ እንዲመረት የሚያደርግ መሆኑ ተነግሮለታል፡፡
Average Rating