Views: 41
የመገናኛ ብዙኀን አውታሮች የታላቁ ኅዳሴ ግድብ ግንባታን በተባራሪ ዘገባ ከመሸፈን ባለፈ የብሔራዊ መግባቢያ አጀንዳ ማድረጉን ረስተውታል የሚል ወቀሳ ቀረበባቸው። የግድቡ ግንባታ ሕዝባዊ አስተባባሪ ምክር ቤት ጽሕፈት የተጣራ መረጃን ይዞ ወደ መገናኛ ብዙኃን ለመቅረብ ወራትን ስለፈጀሁ የፕሮጀክቱ የዘገባ ሽፋን እንዲቀንስ አንድ ምክንያት ሆኗል ያለ ሲሆን፣ የተቀዛቀዘውን የሕዝብ ተሳትፎ ለማነቃቃትና ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር እየሠራሁ ነው ብሏል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ኅዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት ከተበሰረ በመጪው መጋቢት 24 ስምንት ዓመቱን ይደፍናል። ፕሮጀክቱ በመጋቢት 24/2003 የመሰረት ድንጋይ ከተቀመጠለት ጀምሮ በነበሩት ሰባት ዓመታት የአገር ውስጥና የውጭ መገናኛ ብዙኀን አውታሮች ዋነኛ የዘገባ አጀንዳ ሆኖ መክረሙን የሚያነሱ የጋዜጠኝነት ዘርፍ ምሁራን ዘለግ ካሉ ወራት ወዲህ ግን ፕሮጀክቱ እንደቀደሙት ዓመታት የመገናኘ ብዙኀን አውታሮችን ሽፋን ከማግኘት አሽቆልቁሎ በተባራሪ ዘገባ ብቻ እየተነሳ መምጣቱን ይናገራሉ።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ተግባቦት መምህሩ ተሻገር ሽፈራው (ዶ/ር) ግድቡ እንደሚገነባ ይፋ የሆነበትን 8ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ ከመገናኛ ብዙኀን አውታሮች ጋር በተደረገ ምክክር ˝ታላቁ የኅዳሴ ግድብና የመገናኛ ብዙኃን ሚና˝ በሚል ርዕስ ጽሑፍ ያቀረቡ ሲሆን፣ ባለፉት ወራት በሕዳሴ ግድብ ላይ የነበረው የዘገባ ሽፋን እያሽቆለቆለ መምጣቱና ቸል መባሉን አስገንዝበዋል።
የግድቡ ጉዳይ መዘገብ ያለበት ግንባታው ሲፋጠን ብቻ ሳይሆን ሲቀዛቀዝም ጥፋቶችን እየነቀሱ በማውጣት መሆን እንዳለበት ያስገነዘቡት መምህሩ የልማታዊ ጋዜጠኝነት አረዳድም መስተካከል እንደሚገባው መክረዋል። ሕዝብ መስማት የሚፈልገው ስኬትን ብቻ ሳይሆን መታረም ያለባቸውን ውድቀቶችም ጭምር እንደሆነም አስምረውበታል።
እንደተሻገር ማብራሪያ ግድቡ የፖለቲካ፣ የምጣኔ ሀብትና የዲፕሎማሲ አጀንዳ ከመሆኑም ባሻገር በኢሕአዴግ መራሹ መንግሥት የ28 ዓመታት ጉዞ ከተቀረፁና ብሔራዊ መግባባት ከፈጠሩ ጥቂት አጀንዳዎች መካከል አንዱ መሆኑን አስታውሰዋል። ስለሆነም በመገናኛ ብዙኃን በኩል ትኩረት ሊያገኝና የሕዝብ ገንዘብ እየፈሰሰበት ያለ ፕሮጀክት መሆኑ ሊዘነጋ እንደማይገባ መክረዋል።
˝ግድቡ ላለፉት ዓመታት ችግር ሳይገጥመው ሲገነባ ነበር˝ የሚለው የግድቡ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት፣ በቅርብ ባጋጠሙ የግንባታ መጓተትና ተያያዥ ችግሮች የሕዝቡ ድጋፍና ተሳትፎ መቀዛቀዙን አሳውቋል። የጽሕፈት ቤቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ፍቅርተ ተዓምር አሁን ላይ የምክር ቤቱ ቀዳሚ ዓላማ ገቢ ማሰባሰብ ሳይሆን የተቀዛቀዘውን ʻግድቡ የእኔ ነውʼ ባይነት ሕዝባዊ ተሳትፎ ማነቃቃትና ብሔራዊ መግባባትን መፍጠር ነው ብለዋል። ለዚህም የታሰቡ ኹነቶች መኖራቸው ተገልጿል።
ከዘገባ ሽፋን መቀዛቀዝ ጋር በተያያዘ ከመገናኛ ብዙኀን በኩል ያለው መረጃን ቆፍሮ የማውጣት ችግር እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ጽሕፈት ቤቱ ለመረጃ በሩን ዘግቶ ከርሟል በሚልም ተወቅሷል። ፍቅርተ በበኩላቸው ከመገናኛ ብዙኀን ጋር መራራቁ የተፈጠረው የተጣራ መረጃን አደራጅቶ ለመቅረብ ሲሠራ ነው ብለዋል።
የጋዜጠኝነት መምህሩ ተሻገር በበኩላቸው መንግሥት መረጃን ባይሰጥ እንኳን የመገናኛ ብዙኀን አጀንዳ በመፍጠር የግድቡ ጉዳይ መዘንጋቱንና መንግሥት ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ማንቃት ይችሉ ነበር ብለዋል።
በቅርቡ በፕሮጀክቱ ላይ የተፈፀሙ ችግሮች በመጋለጣቸው የሕዝቡ ተሳትፎ ቀንሷል ቢባልም ሕዝቡ አሁንም ለግድቡ ከማዋጣት አልተቆጠበም ያለው ጽሕፈት ቤቱ እስከ ታኅሣሥ 2011 ድረስ 12 ነጥብ አራት ቢሊዮን ብር መሰብሰቡን እና ከ400 ሚሊዮን ብር በላዩ ባለፉት ስድስት ወራት መሰብሰቡን አስረድቷል። በተደረገ የዳሰሳ ጥናት ሕዝቡ መንግሥት ቃሉን አልጠበቀም በሚል ቅሬታ እንደገባውም ፍቅርተ አልሸሸጉም።
በተያያዘም በምክትል ጠቅላይ ሚንስትሩ የሚመራው የሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት ሕዝብን በይፋ ይቅርታ መጠየቁ አስፈላጊነት ላይ ካመነበት ይቅርታ የመጠየቂያ መድረክ በመፍጠር የሕዝቡን የግድቡ ባለቤትነት ለማረጋገጥ ወደኋላ እንደማይልም አሳውቋል።
ለግድቡ እስካሁን 98 ቢሊዮን ብር ወጪ መደረጉንና 66 ነጥብ 24 በመቶ መገንባቱን የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት አሳውቋል። ግንባታውን በቀጣይ አራት ዓመት ውስጥ ለማጠናቀቅም እቅድ ተይዟል።
Average Rating