ለ5 ሺሕ የመምህራን የጋራ መኖሪያ ቤቶች ማደሻ የሚሆን 121 ሚሊየን ብር በአዲስ አበባ መስተዳደር ቢመደብም ሙሉ በሙሉ ዕድሳት የተደረገላቸው 250 ቤቶች ብቻ መሆናቸውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መምህራን ማኅበር አስታወቀ።
በጀቱ የተመደበው በ2009 ለአዲስ አበባ ቤቶች ግንባታ ፕሮጀክት ፅሕፈት ቤት ሲሆን በከፊልም ታድሰው ለመምህራኑ የተላለፉት 2 ሺሕ 882 ቤቶች ሲሆኑ የተቀሩት ምንም ዓይነት ዕድሳት አልተደረገባቸውም። ቤቶቹ ለመምህራኑ ከተላለፉ በኋላ አብዛኞቹን ራሳቸው አድሰው እንደገቡ ያስታወሰው ማኅበሩ ለማደሻ ይውል ዘንድ የፀደቀው 121 ሚሊዮን ብር የት እንደገባ ሊጣራ ይገባል ሲል አክሏል።
ይሁን እንጂ፤ የፕሮጀክት ፅሕፈት ቤቱ ሥራ አስኪያጅ ኪሮስ እንደተናገሩት የከተማው አስተዳደር ለቤቶቹ እድሳት የሚሆነውን በጀት መመደቡን ተከትሎ ገንዘቡን ሙሉ ለሙሉ ለ 5 ሺሕ ቤቶች ዕድሳት አውለነዋል ብለዋል። ቤቶቹን አድሰው ለአዲስ አበባ የቤቶች አስተዳደር ኤጀንሲ እንዳስረከቡም ለአዲስ ማለዳ አብራርተዋል።
በሌላ በኩል፤ መንግሥት ለመምህራን እንዲተላለፉ ከወሰነባቸው የጋራ መኖሪያ ቤቶች ቤቶች መካከል 131 የሚሆኑት ክፍት እንደሆኑ አዲስ ማለዳ ከምንጮቿ ማረጋገጥ ችላለች። በከተማዋም ለመምህራን ከተዘጋጁት የጋራ መኖሪያ ቤቶች ውስጥ 251 ቤቶች ባለቤታቸው ሳይታወቅ ተቆልፈው የተቀመጡ፣ 91 ቤቶች ከመምህራን ውጪ ለሌላ ወገን ተላልፈው የተቀመጡ እንዲሁም ባለቤት የሌላቸው 131 ቤቶች እንዳሉ ለማወቅ ተችሏል።
በስድስት ክፍለ ከተሞች የተገነቡትና ክፍት የሆኑት የጋራ መኖሪያ ቤቶቹ ለሌሎች መምህራን እንዲተላለፉ ለኤጀንሲው እና ለትምህርት ቢሮ ጥያቄ ማቅረቡን የመምህራን ማኅበሩ ገልጿል።
የማኅበሩ ፕሬዝዳንት ደበበ ገብረፃዲቅ ለአዲስ ማለዳ እንደገለፁት ለጥያቄያቸው ምንም ዓይነት ምላሽ ከሚመለከታቸው አካል አልተመለሰም። ቤቶቹ ለ2 ዓመታት ክፍት ሆነው በመቆየታቸው ተገቢ አይደለም ብለው ለተቋሞቹ ላነሱት ጥያቄም ‹በተገቢው መንገድ ዕድሳት ባለመደረጉና መምህራኑ ውሉን በጊዜው ስላልተዋዋሉ ነው የሚል አጥጋቢ ያልሆነ ምላሽ› እንደደረሳቸው የማኅበሩ ፕሬዝዳንቱ ገልፀዋል። ጉዳዩን በተመለከተ ለትምህርት ቢሮ ጥያቄ ብናቀርብም አይመለከተንም ሲሉ የቢሮው የኮሙዩኒኬሽን ኃላፊ አበበ ገልፀዋል።
አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው መምህራን የቤቱ ዕጣ ከተላለፈ ጀምሮ ከቤት ኪራይ አከፋፈል ጋር እንዲሁም ከዕድሳት ጋር በተያያዘ ተደጋጋሚ ጊዜ ጥያቄ ቢያቀርቡም ምላሽ ባለማግኘታቸው አብዛኞቹ አድሰው እንደገቡ ገልፀዋል። አንዳንድ በፅህፈት ቤቱ የተቀጠሩ አዳሽ የጥቃቅንና አነስተኛ ማኅበራት ‹ቤቱን አድሰን እንዳስረከብናችሁ ፈርሙልን በሚል የማጭበርበረያ ሰነድ በመያዝ ሲያስፈራሩን ቆይተዋል› ሲሉም መምህራኑ ተናግረዋል።
በተያያዘም የቤት ኪራይ ውል ከተዋዋሉበት ጊዜ ጀምሮ ቤት ውስጥ መኖር ባለመጀመራቸው የተነሳ በተለያየ ምክንያት ቤቱን ተረክበው ያልኖሩበት ኪራይ እንዲከፍሉ እየተገደዱ መሆናቸውን ማኅበሩ ገልጿል። በተለይ ደግሞ በየካ ክፍለ ከተማ የሚያስተምሩ 600 መምህራን ለማኅበሩና ለኤጀንሲው ጥያቄ ሲቀርቡ መቆየታቸው ተገልጿል።
በአዲስ አበባ ከተማ በአጠቃላይ ከ15 ሺሕ በላይ መምህራን ቤት ፈላጊ ናቸው ተብሏል።
የከተማ አስተዳደሩ በ2009 ለመምህራን እጣ ያወጣባቸው የጋራ መኖሪያ ቤቶች ቁጥር አራት ሸሕ 920 ቢሆኑም አስተዳደሩ ግን አምስት ሺሕ ቤቶች ላይ እጣ እንዳወጣ አድርጎ በመገናኛ ብዙኃን ዘገባ ሲያሰራና ሪፖርት ሲያቀርብ እንደነበር ይታወሳል። በወቅቱ የእድለኞቹን ዝርዝር ይዞ የወጣው አዲስ ልሳን ጋዜጣም ብዛታቸው 4920 ብቻ መሆኑን አረጋግጧል።
Average Rating