በአፋር፣ አዳል ወረዳ ʻኤደስ ኤጂፕታይʼ በተባለ ትንኝ አማካይነት በየቀኑ 20 ሰዎች የችኩንጉኒያ በሽታ እንደሚጠቁና እስካሁንም ከ300 በላይ ሰዎች በወረርሽኙ ምክንያት ሕይወታቸው አደጋ ውስጥ መግባቱ ተነገረ።
ወረርሽኙ እንደተከሰተ ከታወቀበት የካቲት 2011 ጀምሮ በአስቸኳይ የሕክምና ቡድን ወደ ሥፍራው እንደተላከ የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ለአዲስ ማለዳ አሳውቋል።
ኢንስቲትዩቱ በሽታው በወረርሽኝ መልክ መከሰቱ ከታወቀበት ጊዜ አንስቶ በሽታውን ለመከታተልና ለመቆጣጠር የሚያስችል ሥራ እየሠራ እንደሆነ የኅብረተሰብ ጤና አደጋዎች ምላሽ ቡድን መሪ የሆኑት ድሪባ ሱፋ ተናግረዋል። ከክልሉ መረጃው ሲደርሰው 30 ሰዎች በበሽታው ተጠቅተው እንደነበር አክለዋል።
ከዚህ ቀደም እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር 2016 በሶማሌ ክልል ዶሎ አዶ አካባቢ ወረርሽኙ ተከስቶ የነበረ ሲሆን ምልክቶቹም ከመጠን ያለፈ ትኩሳት፣ ከተለያየ የሰውነት ክፍሎች ደም መፍሰስ (በአብዛኛው ከአፍንጫ)፣ የመገጣጠሚያ ህመምና ለመንቀሳቀስ በሚከብድ መልኩ ህመም መሰማት ናቸው።
ʻኤደስ ኤጂፕታይʼ የተባለችው የሰውን ደም የምትመገብ በመሆኗ ስትናደፍ የበሽታውን መንስኤ የሆነው ተህዋሲያን ከበሽተኛ ሰው ወደ ጤነኛ ሰው በቀላሉ ይተላለፋል እንደ ሕክምና ባለሙያዎች ገለፃ።
ተህዋስያኑ ወደ ሰው ደም ከገባ በአማካኝ ከ3 እስከ 7 ቀናት ውስጥ የበሽታው ምልክት በታማሚዎች ላይ መታየት እንደሚጀምር ማወቅ ተችሏል።
ለዚህም ለመከላከል ሥራዎች እየሠራን ነው ያሉት ድሪባ ትንኟ የምታጠቃው ጠዋትና ማታ በመሆኑ ሙሉ ልብስ እንዲለብሱ እንመክራለን ያሉ ሲሆን፤ ምልክት ያለባቸው በአፋጣኝ ወደ ጤና ተቋማት በመሔድ እንዲታከሙ ማድረግ፣ በሕዝቡን ማስተማር፣ አጎበር መጠቀም፣ መድኀኒት ቤት ለቤት በመርጨት ሥራዎችና ትንኝ መራቢያ እርጥበት አዘል ጉድጓዶችን የመድፈን ሥራ እየሠራን ነው ብለዋል።
ወረርሽኙ መድኀኒት የሌለው በመሆኑ ጊዜያዊ ሕመም ማስታገሻ መድኀኒቶች ለታማሚዎች በመስጠት እንዲያገግሙ እየተደረገ ነው ሲል ኢንስቲትዩቱ አስታውቋል። ነገር ግን የበሽታው መነሻ እንዴት እንደሆነና ሌሎች ጉዳዮች ጋር ተያይዞ ጥናት መጀመሩንም ኢንስቲትዩቱ ይፋ አድርጓል።
በተጨማሪ፤ የኩፍኝ በሽታ ወረርሽኝ በኦሮሚያ በሱማሌ ብሔራዊ ክልሎች የተከሰተ ሲሆን ኢንስቲትዩቱ በሽታው በወረርሽኝ መልክ መከሰቱ ከታወቀበት ጊዜ አንስቶ የመቆጣጠር ሥራዎች እየተከናወነ ነው ሲል ተቋሙ ገልጿል።
በኦሮሚያ ክልል በባሌ ዞን በ11 ወረዳዎች፣ በምዕራብ ሐረርጌ ዞን በ4 ወረዳዎች ፣ በምሥራቅ ሐረርጌ ዞን ደግሞ በ2 ወረዳዎች በሚገኙ ቀበሌዎች ወረርሽኙ የተከሰተ ሲሆን በሱማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ደግሞ በ8 ዞኖች በሚገኙ 41 ወረዳዎች ተከስቷል።
Average Rating