ሲፒኦ በመጠቀም ግብርን መክፈል ተከለከለ
የገቢዎች ሚኒስቴር በአዲስ አበባ በአራቱም ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶቹ ኢ-ታክስን ተግባራዊ ማድረጉን ተከትሎ ሲፒኦን በመጠቀም ግብር መክፈልን ከልክሏል።
የሐሰተኛ ሰነዶችን ለመከላከልና የሚገኘውን ገንዘብ ቀጥታ ወደ መንግሥት ካዝና ለማስገባት በማሰብ ደንበኞች ግብር ለማሳወቅ ሲፒኦን መጠቀም እንደማይችሉ ሚኒስቴሩ ከልክሏል።
ከሚንስቴሩ የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው ከመጋቢት 2011 መጀመሪያ አንስቶ የኢ-ታክስ ወይም በኤሌክትሮኒክስ መንገድ ግብር የመክፈልን ስርዓት የጀመረ ሲሆን፤ በአዲስ አበባ በምዕራብ፣ በከፍተኛ ግብር ከፋዮች ፅሕፈት ቤት፣ በምሥራቅ ቅርንጫፍ እና በመካከለኛ ግብር ከፋዮች ፅሕፈት ቤት ተግባራዊ ሆኗል። ይህንም ተከትሎ በተጠቀሱት ቅርንጫፍ ፅሕፈት ቤቶች ሲፒኦን በመጠቀም ግብርን ማሳወቅ ደንበኞች እንደማይችሉ ታውቋል።
በዚህም መሰረት የገቢዎች ሚኒስቴር ለደንበኞቹ እንዳስታወቀው በሲፒኦ ፋንታ በባንኮች በሚዘጋጀው የአገር ውስጥ ግብር ክፍያ ማዘዣ መጠቀም እንዳለባቸው አሳስቧል። የኢንተርኔት አገልግሎትን በመጠቀም ቅፁን በመሙላት የግብር አከፋፈል ሒደቱን ማሳለጥ እንደሚቻል ከገቢዎች ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
ይህም በሚኒስቴሩ ድረ ገፅ ላይ በተዘጋጀው ቅፅ ላይ ግብር ከፋዮች የሚጠቀሙበትን ባንክ፣ ቅርንጫፍ፣ የባንክ ሒሳብ ቁጥር እና እንዲሁም ገንዘቡ የሚተላለፍበት ተቋም የባንክ ሒሳብ ቁጥር በትክክል መሞላት ይኖርበታል። ከዚህም በተጨማሪ ግብር ከፋዩ መክፈል ያለበትን የገንዘብ መጠን በፊደልና በአሃዝ በቅፁ ላይ ይሞላል።
የገቢዎች ሚኒስቴር ይህን ይበል እንጂ፤ ከግብር ከፋይ ደንበኞች ግን አሉታዊ ምላሾች ገጥሞታል። አዲሱ የግብር አከፋፈል ስርዓት መዘመኑ መልካም ነው ሲሉ ይጀምራሉ ከከፍተኛ ግብር ከፋዮች ጎራ የሚመደቡት ቃልአብ አባተ፥ ባለው የኢንተርኔት መጨናነቅ በተፈለገው መንገድ ተግባራዊ ይሆናል የሚል እምነት የለኝም ይላሉ።
ሌላው ደግሞ በተሸከርካሪ መለዋወጫ ዕቃ ማስመጣት ሥራ የተሰማሩት ሳሙኤል ሓፍተ እንደሚናገሩት ˝ሲፒኦ ለማሠራት በባንክ ውስጥ የምናጠፋውን ጊዜ በእጅጉ ይቀንስልናል˝ ብለው፤ ነገር ግን ሳሙኤል ሌላ ፍራቻ አላቸው። ˝መንግሥት ባሻው ጊዜ ኢንተርኔቱን ሲከፍትና ሲዘጋ በሚኖርበት አገር ኢንተርኔትን መሰረት ያደረገ የግብር አከፋፈል ስርዓትን መከተል ከጥቅሙ ጉዳቱ እንደሚያመዝን ነው እኔ የሚገባኝ˝ ብለዋል።
የገቢዎች ሚኒስቴር ለአዲስ ማለዳ እንዳስታወቀው በአዲስ አበባ በአራቱም ቅርንጫፍ ፅሕፈት ቤቶች ተግባራዊ የተደረገው የኢ-ታክስ ስርዓት በዚህ ወር መጨረሻ ላይ አንድ ወር እንደሚያስቆጥር እና እስካሁን የጎላ ችግር እንዳላጋጠመው ታውቋል።
ሚኒስቴሩ ይህን ይበል እንጂ አዲስ ማለዳ በስልክ ያነጋገረቻቸው ግብር ከፋይ ደንበኞች አዲሱ የግብር ማሳወቂያ ስርዓት በትክክል ካለመትግበሩም በላይ የተለመደውን በግብር መሳወቂያ ጊዜ የሚታየውን ረጃጅም ሰልፍ ማስቀረት እንዳልተቻለ ገልፀዋል።
Average Rating