በአፋር ክልል ገዋኔ አካባቢ በዛሬው ዕለት ታጣቂዎች በትግራይ ዋልታ ፖሊስ እግር ኳስ ቡድን ላይ ተኩስ ከፍተው አንድ ተጫዋች ሲገድሉ ሌሎች አምስት አቆሰሉ።
እግር ኳስ ተጫዋቾቹ ትናንት ከደብረ ብርሃን ከነማ ጋር የነበራቸውን ጨዋታ አጠናቀው ዛሬ ጠዋት ከአዲስ አበባ በመነሳት በአፋር በኩል ወደ መቐለ እየተጓዙ ነበር። የትግራይ ክልል ፀጥታ እና አስተዳደር ጽህፈት ቤት የኮምኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሀፍታይ መለስ ጥቃቱ በዛሬው ዕለት ጠዋት 3 ሰዓት ተኩል ገደማ ላይ መፈፀሙን ለዶቼቬሌ የገለጹ መሆኑን ራዲዮ ጣቢያው ገልጧል። በጥቃቱ ከቆሰሉ ስድስት ሰዎች መካከል የአንዱ ሕይወት ማለፉንም ገልጸዋል።
አቶ ሀፍታይ መለስ «የትግራይ ፖሊስ እግር ኳስ ቡድን ከጨዋታ እየተመለሰ መንገድ ላይ ማንነታቸው እስካሁን ድረስ ማንነታቸው በግልፅ ማን እንደሆኑ ያላወቅናቸው ታጣቂዎች ጥቃት አድርሰዋል። በደረሰው ጥቃት ወደ ስድስት የቡድኑ አባላት ቆስለዋል። ከቆሰሉት ሁለቱ ከበድ ያለ ጉዳት ደርሶባቸው ነበር። አንደኛው ሕይወቱ ሊያልፍ ችሏል። በጣም የሚያሳዝን እና እጅግ የሚያስቆጭ አደጋ ነው» ሲሉ ተናግረዋል።
የትግራይ ክልል የጸጥታ እና አስተዳደር ጽህፈት ቤት ጥቃቱን “በምንም መልኩ ተቀባይነት የሌለው አረመኒያዊ ድርጊት ነው” ሲል አውግዞታል። የጥቃቱ ፈፃሚዎች ማንነት እንደማይታወቅ የገለጸው ጽህፈት ቤቱ “ማንም ሽፍታ እየተነሳ በአውላላ ሜዳ ላይ ዜጎችን ለአደጋ እንዲያጋልጥ እያደረገው ያለው የፌዴራል እና የክልል መንግስታት የዜጎችን በነፃ የመንቀሳቀስ መብት ላይ ብቁ ስራ መስራት በሚችሉበት ቁመና ላይ አለመገኘታቸው ነው” ሲል ወቅሷል። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ቀደም ብሎ ባወጣው አጭር መግለጫ ጥቃቱ መፈፀሙን አረጋግጧል።
Average Rating