www.maledatimes.com ኤርትራና ስደት ተወራራሽ ቃላት (synonymous) እየሆኑ መጥተዋል። - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

ኤርትራና ስደት ተወራራሽ ቃላት (synonymous) እየሆኑ መጥተዋል።

By   /   November 3, 2012  /   Comments Off on ኤርትራና ስደት ተወራራሽ ቃላት (synonymous) እየሆኑ መጥተዋል።

    Print       Email
0 0
Read Time:30 Minute, 37 Second

ኤርትራ፣ የብሔር ራስን በራስ ማስተዳደር እስከመገንጠል መብትና አንቀጽ 39

በአውሮፓና በአሜሪካ፣ በአፍሪካና መካከለኛው ምሥራቅ፣ በሩቅ ምስራቅና በአውስትራልያ ሳይቀር እያደር ኤርትራና ስደት ተወራራሽ ቃላት (synonymous) እየሆኑ መጥተዋል። እገሌ/ እገሊት እኮ ኤርትራዊ ነው/ነች ሲባል ስደተኛ ነው/ነች እንዴ? – ብሎ መጠየቅ የተለመደ አነጋገር ሆኗል። እዚህ አገር ስደተኞች በዝተዋል ሲባል ሱማሌና ኤርትራውያን በዝተዋል የሚል – ድምዳሜ ላይ ይደረሳል። ኢትዮጵያውኖችም በዝተዋል ሊባል ትንሽ ቀርቷል።
በቅርብ ዘመናት የነበሩት የኢትዮጵያ ነገስታት ከአውሮጵውያኖች ዘመናዊ መሳርያና ጥቅማጥቅሞችን ይፈልጉ ነበርና ከባህረ ነጋሹ መሬት (ቦገስ፣ሠሃጢን) ቆንጠር እያደረጉ ለባእዳኑ ኃይላት እንደ መወዳጃነት ይሰጡ ነበር። የስዊዝ ቦይ ሲከፈት ታድያ የቀይ ባህር ቀጠናነቱ እየጎላ በመሄዱ የአውሮጳ ቅኝ ገዝዎችን ቀልብ እየሳበ መጣ። በመሆኑም እንግሊዝ ግብጽን – ነጭ አባይን ራሷ መቆጣጠር ፈልጋ ለጥቁር አባይ ቃፊር በመፈለጓ ይህንኑ ኃላፊነት ኢጣልያ ላይ ወረወረች። ኢጣልያ ይህንኑ ተልዕኮ ተግባራዊ ለማድረግ ስትቅበዘበዝ የአድዋው ጦርነት ተከስቶ የውርደት ሸማ ተከናነበች። ይሁንና ግን በወቅቱ በነበረው አስቸጋሪ ነባራዊ ሁኔታ ኢጣልያ ከመረብ ወድያ ያለውን የኢትዮጵያ መሬት በቁጥጥሯ ሥር አደረገች።
በመሆኑም ባህረ ነጋሽን – ኤርትራ የሚል መጠርያ ሰጥተዋት ከእናት ሀገርዋ ነጠሏት።ኤርትራውያን ከስድሣ ዓመታት በላይ በእጣልያ አገዛዝ በነበሩበት ወቅት የኢጣልያን ስልጣኔ እጅግ ቀስመዋል። በእጃቸው ከመብላት ይልቅ ሹካና ማንኪያን መጠቀምን ለምደዋል። የቤት ቁሳቁሶችን አጠቃቀምና በንጽህና አያያዝን ያውቁበታል። አለባበሳቸው ይማርካል። አነጋገራቸውና ዘበናይነታቸው ደስ ያሰኛል። ጓደኝነታቸው በወረት አይደለም፣ በችግርም ይሁን በደስታ ጊዜ ከወደዱት አይለዩም።
ኤርትራውያን በክልልላቸው ጉዳይ ላይ ድብቅ ቢሆኑም እንኳን በተለያዩ ቁምነገሮች ላይ ለወዳጆቻቸው ግልጽ ናቸው። ብዙውን ጊዜ ከሸጋዋ ኤርትራዊ ቆንጆ ጋር የተፈጸመ ትዳር እንደ አበባ የፈካ ነው። ከትዳር አክባሪዋ ኤርትራዊ ጋር የሚመሰረት ጋብቻ ጽናትን ይወልዳል።
ኤርትራውያን ወንድምና እህቶቻችን “ኤርትራን” እንደማትታየዋ “ሠማያዊዋ ሀገራቸው” ሲያመልኳት ሌሎቹን የአለም አሕጉራት ደግሞ እንደ “ምድራዊ ሀገራቸው” ይቆጥራሉ። ብዙዎች ኤርትራን በሩቅ ሆነው እንደ መካና መዲና ያከብሯታል፣ ይጨፍሩላታል፣ የጀግኖች ሀገር እያሉ ያወድሷታል እንጂ ጎጇቸውን ከእሷ ዘንድ መቀለሱን አይመርጡም። በእድሚአቸው የገፉት እንኳን ሳይቀሩ ሀገራቸውን ትተው በውጭ ሀገር መኖር አይከብዳቸውም። መሰደዱ አላንገሸገሻቸውም። ይህን አስመልክቶ አቶ መለስ “ኤርትራውያን እግር እንጂ ሀገር የላቸው” – አሉ እየተባለ ይቀለዳል።
ኤርትራውያን አስመራን ንጹሂቷ ትንሿ ሮማ ይሏታል። ሥዕሏ እንደ መላዓከ ሚካኤል ሥዕል ከቢታቸው ግድግዳ ተለጥፋለች። ነግደው ያተረፉባትን – ተምረው የከበሩባትን አዲስ አበባ ግን ቆሻሻ ይበዛባታል ሲሉ ያንቋሽሿታል። አፋቤትን፣ ምጽዋን፣ ከረንን፣ ደቀመሀሪን ያንቆላጵሷቸዋል – ረብጣ ነዋይ የዛቁባቸውን ድሬዳዋን፣ ናዝሬትን፣ አዋሳንና ጅማን አያስታውሷቸውም።
የኤርትራና ስደት መወደጃጀት እክልላቸው መኖር ካለመፈለግ ምክንያት የመነጨ ይመስላል። ስደት ይቀናቸዋል – ያሳምራቸዋልም። ስለ መሪያቸው አቶ ኢሳይያስ አንዳች ክፉ ነገር ለመናገር የማይፈልጉት እነዚሁ ኤርትራውያን ይልቁንም በሳቸው ፈላጭ ቆራጭ ባላባታዊ አገዛዝ ምክንያት የመሰደዱ በር ዳግም ክፍት ስለሆነላቸው በውስጣቸው ያከብሯቸዋል። አቶ ኢሳያስም ቢሆን በበረኸኝነት እልሃቸው ፈረንጆቹን መናቃቸውና ፊት መንሳታቸው በሌላ በኩል ለኤርትራውያኑ የምዕራቡ ሀገር የመግቢያ ቪዛ መገኛ ስልት ሆነ።
የኤርትራ የነጻነት ትግል – “ሕዝቡን ነጻ የማውጣት ትግል” – ወይንስ – “መሬቱን ነጻ አውጥቶ ለአቶ ኢሳይያስ መሸለም”? – የሚለው ጥያቄ አዲስ የማህበራዊ ሳይንስ ንድፈ ሃሳብን ፈንጥቋል። ብዙ ሰዎች ምትክ የሌላት ሕይወታቸውን ሰውተውላቸው፣ በመድፍና በታንክ እየተታኮሱላቸው የትልቅ ጋሻ መሬት ብቸኛ ባለቤት እንዲሆኑ በማድረግ – ባለርስቱ ፕሬሲደንት ኢሳያስ በጣት ከሚቆጠሩት የዓለም ሰዎች አንዱ ናቸው። ግናስ ሕዝቡ አካባቢውን እንደ ኒውክለር ራድየሽን ብክለት እየፈራ የሚፈረጥጠው ለምን ይሆን? ይህም ጥያቄ አዲስ የማህበራዊ ሳይንስ ምርምርን መፈንጠቁ አልቀረም።
በቅርቡ ሃያ አንድ ዓመት የነጻነታቸውን በዓል ያከበሩት ኤርትራውያን ታሪክ በቅጡ የመዘገበው የግማሽ ምዕት ዓመት የጦርነትና የስደት ታሪክ አላቸው። ከሃያ አንድ ዓመት በፊት የተጎናጸፉት ነጻነት በየሀገሩ በስደት የወጡትን ዜጎች ሊመልስ አልቻለም። ይህ ከናቅፋ የተተኮሰው የፋኖ መራዒው የነጻነት ጥይት - “የመንፈሱን ነጻነት” – ማምጣት አልቻለም። ይልቁንም ከነጻነቱ ማግስት ጀምሮ የሚሰደደውን ሕዝብ ብዛት ባለፈው ሰላሳ ዓመት ከተሰደደው በመብለጥ ኤርትራውያን ከሶማሌያ ቀጥሎ ምዕራቡን ዓለም ኢትዮጵያን ጨምሮ እንዲያጨናንቁ አድርጓል። ከባለእርስቱ አቶ ኢሳይያስ ጋር የውስኪ ብርጭቆ የሚያነሱት የግል አውሮፕላን ነጂዎቻቸው ሳይቀሩ በቅርቡ አውሮፕላኑን ሰርቀው ወደ ሳውዲ መኮብላላቸው ራሱ አቶ ኢሳይያስ ወዳጅ አልባ መሆናቸውን ያስመሰክራል።
ኤርትራውያኖችን የስደቱ ሰለባ ያደረገው የብሔር ብሔረሰቦችን ጥያቄ አስመልክቶ ንድፈሀሳባዊ ግንዛቤን ለማግኘት የማርክስንና ኤንግልስን ሥራዎች በጥሞናና ስነምግባራዊ በሆነ መንገድ መረዳትን ይጠይቃል። በተጨማሪም የራሽያ የጥቅምቱ አብዮት ክስተትንና ተያይዞ የመጣውን የብሔር ጥያቄ ጽንሶችን በጽሞና መመርመርም ከውዥንብር ያድናል። በእርግጥ የብሔር ብሔረሰብ ጥያቄ አቀንቃኞች ማርክስና ኤንግልስክ ብቻ ሳይሆኑ ቦልሸቪኮች፣ ሮዛ ሉክሰምበርግና ካርል ካውትስኪም ተጠቃሾች ናቸው።
ማርክስ እ/ኤ/አ በ 1848 ዓ/ም ወደ ተሻለ ማህበራዊ ብልጽግና ደረጃ የሚያሸጋግሩት የምርት ኃይሎች እድገት (productive forces) ወሳኝ እንደሆኑ አትቶ ይኸው ሂደት በተለያዩ የብሔር ጥያቄዎች ላይ እንኳን ቢሆን ተጽዕኖ እንደሚያሳርፍ ገልጿል። በመሆኑም በሰራተኛው መደብ (working class) ትግል ውስጥ የብሔር ጥያቄ የሞተ ነው ሲል ማርክስ ጨምሮ አብራርቷል። የሰራተኛው ትግል መደቦችንና (classes) ብሔሮችን (nationalities) ስለሚያጠፋ የብሔሮች ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ ቦታ አያገኝም ብሎ ነበር። የማርክስ ዋነኛ መፈክር የዓለም ሠራተኞች ሁሉ ተባበሩ ነበር። (workers of all countries unite)
ማርክስና ኤንግልስክ ከ እ/ኤ/አ 1850 በፊት ስለ ብሔር ጥያቄ በቂ ንድፈሃሳቦችን ያልቀረጹ ቢሆንም ቅሉ እ/ኤ/አ – በ 1863 በተከሰተው የፖላንድ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን ብሔራዊ ጥያቄ ላይ አስተሳሰባቸውን በመለወጥ አየርላንድ ከእንግሊዝ ተገንጥላ ራሷን ማስተዳደር ትችላለች የሚል ጠበቅ ያላለ፣ ብዥታዊ መደምደምያ ላይ ሊደርሱ ቻሉ። ሌኒንም በተመሳሳይ በሠራተኛው መደብ ልዕልና ላይ በማተኮር የአርመንያኑ ሶሻል ደሞክራሲ የመገንጠልን ጥያቄ በሠራተኛው መደብ ነጻ መውጣት ይፈታል ቢልም ቅሉ ሀሳቡን በመለወጥ የተጨቆነ ብሒረ እስከ መገንጠል ሊያደርስ የሚችል መብት አለው ሲል ድንብርብር ያለ ጽሁፍ ሞነጫጭሯል። በሌላ በኩል ደግሞ ስታሊን – ሌኒንን መሠረት በማድረግ አንድ ሕዝብ ተመሳሳይ ቋንቋ ከተናገር፣ ባንድ አካባቢ ሳይነጣጠሉ የሚኖሩ ከሆኑ፣ አካባቢአቸው ድንበር ሊበጅለት የሚችል ከሆነ፣ ሕዝቡ በቂ የምጣኔ ኃብት ክምችት ካለው፣ ተመሳሳይ ስነልቦናዊ አመለካከት
እንዲሁም ተመሳሳይ ባህላዊ ትስስር ካለው ብሔር ሊባል የሚያስችለውን መስፈርት ስለሚያሟላ የመገንጠል ጥያቄ ሊያቀርብ ይችላል የሚል መደምደምያ ሰጠ። ሆኖም ግን ስታሊን ከነዚህ ስድስቱ መስፈሮቶች አንድ እንኳን ለተጓደለ ብሔር ስለማይባል መገንጠል እንደማይቻል አስጠንቅቋል።
ይህ ከላይ የተመለከትነው የፈረንጆቹ አኳኋን፣ ፖለቲካ፣ ፍልስፍና፣ ርዕዮተ ዓለም፣ ብዥታ፣ አመለካከትና ነባራዊ ሁኔታን ያላገናዘበ ትምህርት ወደ ኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ ውስጥ ዘልቆ በመግባት -“የብሔረሰቦች ስታሊናዊ ራስን በራስ ማስተዳደር እስከመገንጠል” – በሚል አጉል ሀሳብ ተቀሽሮ ቀረበ።
ሻዕቢያ ከዚህ ንድፈሃሳብ በመነሳት – “አረብ ነኝ” – የሚለውን ጀብሃ ካስወገደ በኋዋላ በመገንጠሉ ጥያቄ ጸንቶ ሲያበቃ ኦነግን በራሱ አምሳያ በመፍጠር መከረኛይቱን ኢትዮጵያ በእርስ በእርስ ጦርነት አናውጦ ሲያበቃ ተገነጠለ።
ሻዕቢያ አስቀድሞም ቢሆን ኤርትራን ለመገንጠል ያመቸው ዘንድ በንጉሡ ዘመን የተሰነዘሩትን የኢትዮጵያን ጭቁን ሕዝብ ጥያቄዎች በራሳቸው ስውር ዓላማ ሥር ሸሽገው ላይ ላዩን ኢትዮጵያዊ ተቆርቋሪዎች መስለው በደጋፊዎቻቸው በመታገዝ በጥንቃቄ ሲንቀሳቀሱ ቆይተዋል። ከቀዝቃዛው ጦርነት ማክተም በኋላ የማርክሲዝም ሌኒኒዝም ሃሳቦች በሚካኤል ጎርባቾቭ ፔሪስትሮይካና ግላስኖስት ተሀድሶ አዲስ መልክ ቢይዝም ቅሉ ሻዕቢያ፣ ሕወሀትና ኦነግ በመገንጠሉ ርዕዮት ላይ ጽናታቸውን አሳዩ።
ሻዕቢያ በገሀድ፣ ሕወሀት በዘዴ ኦነግ በተቀጽላነት። እንዴት?
የኃይለሥላሴ ንጉሳዊ መንግስት በድንገት መገርሰሱ “ለማርኪሲዝም ሌኒኒዝም” ርዕዮተ ዓለም መስፋፋት ጥርጊያ መንገድ እንዳዘጋጀ ሁሉ፣ የደርግ በራሱ የውስጡ ቅራኔ ምክንያት መፈረካከሱ ደግሞ ለብሔረሰቦቹ “የራስን በራስ መወሰን እስከመገንጠል” ዓላማ ተግባራዊነት እጅግ ምቹ ሆነ። ድንገት ሳይታሰብ የሚኒልክ ቤተ መንግስቱን የተቆጣጠሩት በሕወሀቱ ውስጥ የነበሩት ታጋዮች – “የታላቋ ትግራይ”- ምስረታን መርሀ ግብር ለጊዜው ወደ ጎን ቢተዉም ቅሉ በወቅቱ ለተከሰተው ድንገተኛና አስቸጋሪ ነባራዊ ሁኔታ ተጋለጡ። ኢሕአዲጎቹ አባቱ ሻዕቢያን ተከትሎ ኦሮምያን ለማስገንጠል ያሰፈሰፈውን ኦነግ ለማዘናጋት እንዲሁም አዲስ አበባ ድረስ አብሯቸው የመጣውን የጦር አጋራቸውን ሻዕቢያ ላለማስቀየም መላ በመዘየድ የብሔረሰቦች ራስን በራስ ማስተዳደር እስከመገንጠል የሚለውን የማርክሲዝም ሌኒኒዝም ጽንሰሃሳብ አንቀጽ 39 በህገመንግስቱ ውስጥ ለማካተት ተገደዱ። ቀስ በቀስ ግን ኢሕአዲግ የኦነግን
ሠራዊት ከቦ ከማረከና መሪዎቹን ከምክር ቤቱ ሲያስወግድ ” አንቀጽ 39″ ለይስሙላ የተቀመጠች አንቀጽ መሆኗ ገሀድ ወጣ። የሕወሃቶቹ ትግራይዋዎቹ፣ ከተወሰኑ ዓመታት ቆይታ በኋላ፣ ኤርትራውያን ቀድሞ ያካበቱት ሃብት ንብረታቸው ተቀምቶ ባዷቸውን እንዲባረሩ ሲያደርጉ መገንጠል ፋይዳ ቢስ የእልኸኞች ፖለቲካ መሆኑን በማሳየት ከመቶ ሃምሳ ዓመት በፊት ማርክስና ኤንግልስን ውዥንብር ውስጥ ከቶ የነበረውን የብሄረሰቦች እስከመገንጠል ጥያቄን ውጤት አልባነትን በተግባር በማሳየት ለሲሪላንካ ታሚል ተገንጣዮች አዲስ ትምሕርት አስገኙ። ኢሕአዲግ በሌላ በኩል ደግሞ የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻ አውጭ ግንባርን (ኦብነግ) በመፋለም ላይ ሲገኝ የመገንጠሉ ጥያቄ ከስታሊን ጋር አብሮ ለመቀበሩ ገለጻ ለማድረግ ናይሮቢ ውስጥ ስብሰባ ጠርተዋቸዋል።
በመሆኑም ከስታሊናዊው – “የብሔር ራስን በራስ ማስተዳደር እስከመንገንጠል” – ጽንስ የተወለደችዋ ኤርትራ ውርዴ ስትሆን አንቀጽ 39 የእንግዴው ልጅ ነው። በዚህም በዚያም ሰበብ ግን ገናናዋና ጥንታዊዋ ኢትዮጵያ ወደብ አልባ ሀገር እንድትሆን ክፉ ደባ ተሸረበባት።
የመገንጠሉ ሰለባ የሆነው የኤርትራ ሀገር ሕዝብ እንደ ግለሰብ እጅግ መልካሞች ናቸው። ከሚወዷት እናት ሀገራቸው የነጠላቸው ዘመናዊው የፈረንጆቹ ፖለቲካ ነው። ይኸው የትዕቢትና የማናህሎኝነት ማኦኢስት ፖለቲካዊ አስተሳሰብ በተማሪዎች ንቅናቄ ዘመን ከነበሩት ተማሪዎችና የዛሬው መሪዎች አዕምሮ ውስጥ ፈጽሞ እስካልተነቀለ ድረስ ሕዝቡ በራሱ ፈቃድ መኖር አይችልም። ፖለቲካ በማስተዋል ካልታገዘ መከራን ይወልዳል። ፖለቲካ በጥበብ፣ በትዕግስት፣ በሥነምግባርና በጨዋነት ካልተመራ ሕዝብን ያሸብራል። ከንቱ እልህና ጀብደኝነት ደሀውን ያሰቃያል። በምስኪኑ ሕዝብ ስቃይ የሚደሰቱ ደግሞ የኋላ ኋላ የመከራውን ጽዋ ይጨልጡታል። የእቴጌ ጣይቱ ፍርሀት እውን ሆኖ ኢትዮጵያ ራሷ ዘመናዊ ትምህርት ያስጨበጠቻቸው ልጆችዋ ተረከዛቸውን አነሱባት። በእርግጥ እግዚአብሔር ታሪክ ሠሪ ነው።
ኢትዮጵያን እየጠበቀ ዘመን ከዘመን አሻግሯታል። እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ፈጽሞ አይተዋትም። የሻዕቢያው ባለሥልጣናትና በርከት ያሉ ኤርትራውያን ደጋፊዎቻቸው ኤርትራ ከእናት ሀገርዋ ኢትዮጵያ መሬት ጋር ዳግም እንድትዋሀድ አይፈልጉም። ኤርትራን የጀግንነት ምሳሌአቸው፣ የስልጣኔ ምንጫቸውና የቀይ ባህር በራቸው አድርገው ይቆጥሯታል። ማንም እንዲነካባቸው አይፈልጉም። የሕወሀቶቹ ኤርትራውያኖቹም ቢሆን ባለርስቱ ፕሬዚደንት ኢሳይያስን ማስቀየም አይፈልጉም። ከዚህ ቀደም ሥልጣን ላይ በነበሩት የሕወሀቱ ትግራዋዮች የተፈጸመውን ኤርትራን የኢትዮጵያ ኤኮኖምያዊ ድጋፍ ያሳጣውን ርምጃ ለመካስ በሚቻለው ይሞክራሉ። ላንዳንዶቹ ንግዳቸውንና ቤታቸውን እየመለሱላቸው ነው።
አንዳንዶቹም የተጀጋጀውን ቅጽ እየሞሉ ኢትዮጵያው ውስጥ ኢንቨስት እንዲያደርጉ ፈቅደውላቸዋል። “ጠርጥር ከገንፎም አይጠፋ ስንጥር” – ያሉ ደግሞ ነገ ምን እንደሚፈጠር ስለማይታወቅ መጠንቀቁ ይበጃል በሚል አርፈው እተሰደዱበት ሀገር ሆነው አድፍጠዋል። የሻዕቢያውም ሆነ የሕወሀቱ ቀን የሰጣቸው ኤርትራውያኖች በክፉም በደጉም ጊዜ አብረውት የኖሩትን የየዋሁን ኢትዮጵያ ሕዝብ ስነልቦናዊ አመለካከት ጠንቅቀው ስለሚያውቁ ማናከሱን፣ ማከፋፈሉንና ማጠላለፉን እንደ በቀል ዱላ ይጠቀሙበታል። የግፍ ሥራዎችንም የሥልጣን ዘመናቸው ማራዘምያ ምትሀት አድርገው ሊጠቀሙበት ይሞክራሉ። “የቤት ሥራ” – የሚሏቸውን እነዚህኑ የርኩስ መንፈስ
ሕዋሳት በየፖለቲካ ማህበሮች፣ ትምህርት ቤቶች፤ ሕዝባዊ ስብስቦችና በየመዝናኛ ቦታዎቹ ሳይቀር እንደ አንደ አንደ መተት እያሰሩ የዋሁን ኢትዮጵያዊ ያደነዝዛሉ። ታድያ ይህን እያወቁ አንዳንድ ተቃዋሚዎች ከሻዕቢያ ጋር የመሞዳሞዳቸው ጥፋት – “የፖለቲካ ቂልነት” ወይም “የፖለቲካ ንዝህላልነት” – ተብሎ ብቻ ሊታለፍ የሚችል አይደለም። ማን ይሙት ማን ሻዕቢያ የወያኔን መውደቅ ይሻል? ወያኔም ቢሆን ልብን በፕሮፖጋንዳ እያደረቀ እግዚአብሄር በቃ እስከሚለው ቀን ድረስ ያሾፋል እንጂ ከኤርትራ ጫፍ እንኳንስ ጦር ሣር እንደማይመዘዝ ያውቃል።
እግዚአብሄር በቃ ሲል ኤርትራውያን ወንድምና እህቶቻችን በበጎና በንጹህ ፍላጎት ወደ እናት ሀገራቸው ጉያ ይመጣሉ። ተንኮል – ተንኮልን መውለዱን ያቆማል። መሠሪነት፣ ሸርና ደባ ወደ ጥልቁ ይወረወራሉ።ጊዜው ይቅረብም ይራቅም እግዚአብሔር ይህንንም መስራት አይሳነውም። ኢትዮጵያ ስትበደል እግዚአብሔር ዝም አይልም። ሰላምና ብልጽግና – ፍቅርና አንድነት ለመላው ሕዝብ ይሁን።
ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሄር ትዘረጋለች። አሜን
abebehabesha@gmail.com/ከሀበሻ አበበ (ኖርዌ)

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 12 years ago on November 3, 2012
  • By:
  • Last Modified: November 3, 2012 @ 2:13 pm
  • Filed Under: Ethiopia
  • Tagged With:

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar