www.maledatimes.com መንግሥትና ዘመናዊ የሌብነት ስልቶቻቸው - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

መንግሥትና ዘመናዊ የሌብነት ስልቶቻቸው

By   /   November 4, 2012  /   1 Comment

    Print       Email
0 0
Read Time:15 Minute, 1 Second

 

በመንግሥት ውስጥ የመሸጉ የመንግሥት ሌቦች

እስቲ እንደ መንግሥትም፣ እንደ ሕዝብም፣ እንደ ግለሰብም፣ እንደ ዜጋም ራሳችንን እንፈትሽ፡፡ የድርሻችንን እየተወጣን ነን? እስቲ መንግሥትን ከመፈተሻችን በፊት እንደ ሕዝብና እንደ ዜጋ ራሳችንን እንፈትሽ፡፡

ኢትዮጵያችን ከጉቦ፣ ከሙስናና ከአድልዎ ፀድታ ሕገ መንግሥቱን መሠረት አድርጋ የምትንቀሳቀስ አገር እንድትሆን እንመኛለን፡፡ ነገር ግን ራሳችን እነዚህን እኩይ ተግባራት እንታገላለን? ጉቦ ሰጪ ከሌለ ጉቦ ተቀባይ እንደማይኖር አውቀን እምቢ አንሰጥም ብለን በፅናት እንቆማለን? ጉቦ የሚሰጡትንና ጉቦ የሚቀበሉትን እናጋልጣለን? ፈርተን ወይም እኛም ጉዳያችን እንዲፈጸምልን ብለን ተባባሪ እንሆናለን?

እዚህ ላይ ከፍተኛ ጉድለትና ድክመት በዜጎችና በተለይም እንደ ሕዝብ እየታየብን ነው፡፡ ጠንክረን ሙስናን እየታገልን አይደለም፡፡ አገራችን ስትነጠቅ፣ ስትሰረቅና በሙስና ስትጨማለቅ የድርሻችን እየተጫወትን አንገኝም፡፡ ሌላው እንዲሠራው እንጂ እኛ ራሳችን ኃላፊነታችንን አንወጣም፡፡ አገራችን እንድትነጠቅ እየተባበርን ነን፡፡ ይህ ሁሉ የሚሆነው ስለማንታገል፣ ለመብታችን ስለማንቆምና ግዴታችንን ስለማንፈጽም ነው፡፡

ወንጀል እንዲጠፋ እንፈልጋለን፡፡ መንግሥት ይህን ለምን አያደርግም፣ ፖሊሶች ለምን ዝም ይላሉ፣ ወንጀልኮ እየበዛ ነው፣ ሌብነት ተስፋፋ እንላለን፡፡ ሌላው ማድረግ ያለበትን አለማድረጉ ያስጠይቀዋል፡፡ ነገር ግን እኛ ራሳችንስ እንደ ዜጋና እንደ ሕዝብ ወንጀል ሲፈጸም ስናይ ምን ያህል እንታገላለን? ራሳችን ምን ያህል እናጋልጣለን? የመንግሥትና የሕዝብ ንብረት በየመንገዱ ሲዘረፍ ስናይ ፈርተን ዝም እንላለን ወይስ ደፍረን እናጋልጣለን? መኪና መንገድ ላይ ሲሰረቅ እያየን ዝም፣ የአገር የኤሌክትሪክ፣ የስልክ፣ የውኃ ቧንቧዎች፣ ሽቦዎችና የተለያዩ ዕቃዎች ሲሰረቁ ዝም እንላለን፡፡

መንግሥት ለምን ቆሻሻ አያነሳም እንላለን፡፡ ለምን እዚህ ተደፋ ተከመረ እያልን እናማርራለን፡፡ እንዲህ ማለታችን ጥሩ፤ ነገር ግን እኛ ራሳችንስ እንደ ሕዝብና እንደ ዜጋ ቆሻሻ ከመጣልና የትም ከመድፋት ምን ያህል እንጠነቀቃለን? ምን ያህል አካባቢያችንን እናፀዳለን? ምን ያህል ተባብረን አካባቢያችንን ፅዱና ንፁህ እናደርጋለን? በዚህ ዙሪያም የድርሻችንን እየተጫወትን አይደለንም፡፡

መንግሥት መንገድ፣ ትምህርት ቤት፣ ክሊኒክ፣ ወዘተ እንዲገነባ እንፈልጋለን፡፡ ኤሌክትሪክ፣ ውኃ፣ ስልክ፣ እንዲዘረጋ እንጠይቃለን፤ ጥሩ፡፡ ነገር ግን መንግሥት ይህንን ለመሥራት ገንዘብ ያስፈልገዋል፡፡ ይህ ገንዘብ የሚገኝበት አንደኛው መንገድ ከግብርና  ከቀረጥ ነው፡፡ እኛ ግብር ካልከፈልን፣ ቀረጥ ካጭበረበርን፣ የቫት ክፍያ ካልፈጸምን መንግሥት የማልማት አቅም አይኖረውም ብለን ምን ያህል ግዳጃችንን እንፈጽማለን? ምን ያህል የድርሻችንን እንጫወታለን? በዚህ ዙሪያም ግዳጁን የማይፈጽም፣ ግብር የማይከፍል፣ ቀረጥ የሚያጭበረብር፣ በአቋራጭ ሀብታም ለመሆን የሚፈልግ እየተበራከተ ነው፡፡ ሰጪ ሳይሆን ነጣቂ እየበዛ ነው፡፡

ምነው ልጆቻችን ሲበላሹ እያየ መንግሥት ዝም አለ ብለን እንወቅሳለን፡፡ ጫት በዛ፣ ሴተኛ አዳሪነት በዛ፣ መጠጥ ቤት በዛ፣ ገስት ሃውስ፣ ማሳጅ፣ ወዘተ  እየተባለ የኅብረተሰቡ ሞራል እየዘቀጠ ለምን መንግሥት ዝም ይላል እንላለን፡፡ ግን ነገር ግን! እኛ ራሳችንስ እንደ ሕዝብ፣ እንደ ዜጋ ልጆቻችንና ቤተሰቦቻችን ከዚህ መጥፎ ሥነ ምግባር እንዲቆጠቡ ምን ያህል እያስተማርን፣ እየጠበቅን፣ እየተከላከልን፣ በመልካም ሥነ ምግባር እየገነባን ነን? የድርሻችንን እየተጫወትን አይደለንም፡፡ እንደ ኅብረተሰብም፣ እንደ ግለሰብም፡፡

ብዙ ብዙ መዘርዘር ይቻላል፡፡ ተጠቃሎ ሲቀመጥ ግን መንግሥት ለምን ይህን አይሠራም ብለን እየወቀስን እኛ ራሳችን ልንሠራው የሚገባንን እየሠራን፣ እየፈጸምን፣ እያከናወንን አይደለንም፡፡ ለአገራችን ለኢትዮጵያ በተገቢ ደረጃ እያሰብን፣ ጥበቃ እያደረግን፣ እየተንከባከብን አይደለንም፡፡ ምን አደረገችልኝ እንጂ ምን አደረግኩላት እያልን አይደለንም፡፡ ለኢትዮጵያችን፡፡

መንግሥትስ የድርሻውን በትክክል እየተጫወተ ነውን? መንግሥትም ከፍተኛ ድክመት አለበት፡፡ የግል ሌቦች ብቻ ሳይሆኑ በመንግሥት ውስጥም የመሸጉ የመንግሥት ሌቦች እንዳሉ መንግሥት ራሱ በትክክል አስቀምጦታል፡፡ በተግባር ግን የመንግሥት ሌቦችን እየታገላቸውና እያፀዳቸው አይደለም፡፡ እንዲያውም እየተጠናከሩና ኔትወርካቸው በእጅጉ እየሰፋ ነው፡፡ በኅብረተሰቡ ላይ የሚበረታውን ያህል በራሱ በውስጡ ትግል አካሂዶ የውስጥ ሌቦችን ለማጥፋት በቂ ጥረት አያደርግም፡፡ ለአገራቸው ከሚሰጡ ይልቅ አገራቸውን የሚነጥቁ የመንግሥት ሌቦች በመብዛታቸው መንግሥት ራሱ ተጠያቂ ነው፡፡ የድርሻውን እየተጫወተ አይደለም፡፡

ጋዜጣ ለማሳተም የብቃት ማረጋገጫ ያስፈልጋችኋል፤ ሆቴል ለመሥራት፣ ክሊኒክና ሆስፒታል ለማቋቋም እንደዚሁ የብቃት መለኪያ እያለ  መንግሥት ያወጣል፡፡ ጥሩ ነው ተገቢ ነው፡፡ የራሱን ሥራ ሲሠራ ግን የብቃት ማረጋገጫ አያቀርብም፡፡ የብቃት ማረጋገጫ ያልተሰጠው የፕሬስ ሥራ ሲሠራ ይታያል፡፡ የብቃት ማረጋገጫ የማይሰጠው ‹‹ሲያስነጥስ›› የሚቆፋፈር መንገድ በብዛት ሲሠራ ይገኛል፡፡ መፀዳጃ ቤት የሌለው ሆስፒታል አለው፡፡ ብቃት የሌላቸው በርካታ ሹሞችና ሠራተኞች አሉት፡፡ ኦዲት የማይደረጉና ሪፖርት የማያቀርቡ በርካታ ድርጅቶች ይዟል፡፡ ከኅብረተሰቡ የሚጠብቀውን ራሱ ሲፈጽመው አይታይም፡፡ የድርሻውን አይጫወትም፡፡ ተገቢውን መመዘኛ የማያሟሉ ተቋማት፣ ሕንፃዎች፣ መንገዶች፣ የኤሌክትሪክ መስመሮች፣ የውኃ ቧንቧዎች፣ የቴሌፎን ኔትወርኮች በብዛት አሉት፡፡

በግሉ ዘርፍ ኢንቨስትመንት ላይ በርካታ ሕጎችን ያወጣል፡፡ ቁጥጥር ተገቢ ነው፡፡ የራሱን ኢንቨስትመንት፣ የራሱን የበጀት አጠቃቀም፣ የራሱን የዕቃ ግዥ፣ የራሱን የጨረታ ሒደት፣ የራሱን የአፈጻጸም ሪፖርት ግን የግሉን የሚቆጣጠረውን ያህል አይቆጣጠርም፡፡ የድርሻውን እየተጫወተ አይደለም፡፡

አቶ እከሌ ሕግ አላከበርክም፣ እከሊት መመርያ ጥሰሻል በማለት መንግሥት ይቀጣልም፣ ፈቃድ ይነጥቃልም፣ ያስራልም፡፡ ቁጥጥሩ ተገቢ ነው፡፡ የራሱ ተቋም ሕግ ሲጥስና ሌላውን ሲያደናቅፍ ግን ተገቢ ቁጥጥር አያደርግም፡፡ ሌላውን እየገመገሙና እየወረፉ የሚውሉ ተቋማት ራሳቸው በሕዝብ ቢገመገሙ ምን ሊመስሉ እንደሚችሉ መንግሥት እየታየው አይደለም፡፡ የድርሻውን እየተጫወተ አይደለም፡፡

እነዚህን ለአብነት ጠቃቀስናቸው እንጂ መንግሥት የድርሻውን ያለመጫወት ተግባር እጅግ በርካታ ነው፡፡ ዋናው ቁም ነገር ራሳችንን እየፈተሽንና ድክመታችን እያስወገድን አገራችንን እንገንባ፣ እንጠብቅ፣ እናጠናክር ነው፡፡ ከአገራችን የምንፈልገውና ልናገኘው የሚገባ እንዳለ ሆኖ በቅድሚያ ግን እኛ ለአገራችን ማድረግ የሚገባንን እናድርግ ነው፡፡ እንደ ሕዝብ፣ እንደ ዜጋና እንደ መንግሥት፡፡

‹‹አገሬ ለእኔ ምን አደረገችልኝ ብለህ ከመጠየቅህ በፊት እኔ ለአገሬ ምን አደረግኩላት? ብለህ ጠይቅ›› ፕሬዚዳንት  ኬኔዲ፡፡
እኛም ደግመን ደጋግመን እንለዋለን፡፡ ‹‹ላድርግላት›› የሚል እየጠፋ ‹‹ታድርግልኝ›› የሚል እየበዛ ነውና፡፡ ‹‹የሰጪ›› ቁጥር እያነሰ ‹‹የነጣቂ›› ቁጥር እየበዛ ነውና፡፡

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 12 years ago on November 4, 2012
  • By:
  • Last Modified: November 4, 2012 @ 1:10 pm
  • Filed Under: Ethiopia
  • Tagged With:

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%

One thought on “መንግሥትና ዘመናዊ የሌብነት ስልቶቻቸው

Comments are closed.

<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar