www.maledatimes.com የኢትዮጵያ የካናቢስ ገበያ የ9.8 ቢሊዮን ዶላር አቅም እንዳለው አንድ ጥናት አመለከተ - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

የኢትዮጵያ የካናቢስ ገበያ የ9.8 ቢሊዮን ዶላር አቅም እንዳለው አንድ ጥናት አመለከተ

By   /   May 26, 2019  /   Comments Off on የኢትዮጵያ የካናቢስ ገበያ የ9.8 ቢሊዮን ዶላር አቅም እንዳለው አንድ ጥናት አመለከተ

    Print       Email
0 0
Read Time:1 Minute, 45 Second

መቀመጫውን በአሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ ያደረገው ኒው ፍሮንቲየር ዴታ የተባለ ተቋም ባለፈው ሳምንት ይፋ ባደረገው የአፍሪካ እ.ኤ.አ. የ2019 ቀጣናዊ የካናቢስና የሄምፕ (አነስተኛ የሆነ አነቃቂነት ያለው ካናቢስ) ሪፖርት፣ ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አገሮች ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ ለካናቢስ ገበያ የ9.8 ቢሊዮን ዶላር አቅም እንዳላት አስታወቀ፡፡ ኢትዮጵያን በመቅደም በአንደኝነት የተቀመጠችው ናይጄሪያ የ15.3 ቢሊዮን ዶላር የገበያ አቅም እንዳላት በሪፖርቱ ተመላክቷል፡፡

ዓለም አቀፉ የካናቢስና የሄምፕ ጠቅላላ ገበያ 344.4 ቢሊዮን ዶላር መሆኑን የገለጸው ሪፖርቱ፣ አፍሪካ የዓለምን ገበያ 11 በመቶ እንደምትሸፍንና የ37.7 ቢሊዮን ዶላር የገበያ አቅም እንዳላትም ገልጿል፡፡

በዓለም 263 ሚሊዮን የካናቢስ ተጠቃሚዎች እንዳሉና 83 ሚሊዮን ተጠቃሚዎች በአፍሪካ እንደሚገኙ ያመላከተው ጥናቱ፣ በአፍሪካ ያለው የካናቢስ ዕፅ ተጠቃሚነት ምጣኔ 11.4 በመቶ መሆኑንም ጠቁሟል፡፡ ይኼም አኃዝ ከዓለም የተጠቃሚነት ምጣኔ ስድስት በመቶ አንፃር ሲታይም በግማሽ ያህል እንደሚበልጥ አትቷል፡፡

ሃምሳ አራት የአፍሪካ አገሮችን በመሸፈን የተሠራው ጥናት በሁሉም አገሮች ሰዎችን በአካል በማግኘትና በመጠየቅ መከናወኑን በማመላከትም፣ በአፍሪካ ከሚገኙ 83 ሚሊዮን የካናቢስ ተጠቃሚዎች መካከል 20.8 ሚሊዮኑ በናይጄሪያ ሲገኙ፣ 7.1 ሚሊዮን የሚሆኑ ተጠቃሚዎች ደግሞ በኢትዮጵያ ይገኛሉ ብሏል፡፡

እነዚህ ተጠቃሚዎችም በዓመት 9.8 ሚሊዮን ዶላር አውጥተው ካናቢስ እንደሚጠቀሙ፣ ምንም እንኳን በአገሪቱ ካናቢስን መትከል የተከለከለ ቢሆንም በርካታ አካባቢዎች ዕፁን እንደሚያበቅሉ ጥናቱ ያስረዳል፡፡ በተለይም በራስ ተፈሪያን መኖሪያነት የሚታወቀው የሻሸመኔ አካባቢን በቀዳሚነት ያስቀምጣል፡፡

ኢትዮጵያ ለጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ትኩረት ሰጥታ የጥጥ ምርት ስትራቴጂ ብታዘጋጅም፣ የጥጥ ምርት በተለያዩ ምክንያቶች ውጤታማ ላይሆን ይችላል ይላል ጥናቱ፡፡ ከእነዚህም ምክንያቶች አንዱ ጥጥ ከፍተኛ ውኃ እንደሚፈልግ ያትታል፡፡ ነገር ግን የካናቢስ ውጤት የሆኑት ጨርቆችን ለፋብሪካዎች ማቅረብ አዋጭ ሊሆን እንደሚችልና ከጥጥ ሲነፃፀርም ሩብ ያህሉን ውኃ ብቻ እንደሚፈልግ፣ ብሎም በትንሽ ቦታ ላይ ተጠጋግቶ መትከል ስለሚቻል ከፍተኛ ምርት ማግኘት እንደሚቻል በጥናቱ ተመልክቷል፡፡

በኢትዮጵያ ካናቢስ ማምረትም ሆነ መጠቀም በሕግ ያልተፈቀደና ድርጊቱም ሕገወጥ ሲሆን፣ ካሁን ቀደም በበርካታ አካባቢዎች የተለያየ መጠን ያላቸው ምርቶች ሲንቀሳቀሱ ተይዘው ያውቃሉ፡፡ ተጠቃሚዎችም በሕግ ይቀጣሉ፡፡

ከወራት በፊትም በአማራ ክልል የካናቢስ ምርት ለማምረት የሚፈልግ በኢትዮጵያውያንና በካናዳውያን የተመሠረተ ‹አፍሪካና ካናቢስ ሆልዲንግ› የተባለ ኩባንያ ፈቃድ በመጠየቅ ላይ ሳለ በቀረበበት ተቃውሞ ሲያፈገፍግ፣ የክልሉ መንግሥት ለኢንቨስትመንት ፈቃድ ለመስጠት እንዳላሰበ ማስታወቁ ይታወሳል፡፡ የጤና ሚኒስትሩ ዶ/ር አሚር አማን፣ ‹‹በኢትዮጵያ ይኼንን ዓይነት ኢንቨስትመንት ለመፍቀድ የሕክምናም ሆነ ሌላ ምክንያቶች የሉንም፤›› ሲሉ በትዊተር ገጻቸው ላይ ጽፈው ነበር፡፡

የዓለም ጤና ድርጅት በቅርቡ ይፋ ያደረገው ጥናት እንደሚያመለክተው ካናቢስ ለሕክምና የሚሆን ጥቅም እንዳለው በመጥቀስ፣ በተለይ የሚጥል በሽታን ለማከም ጥቅም ላይ ሊውል ይችላል ሲል አመላክቷል፡፡

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 6 years ago on May 26, 2019
  • By:
  • Last Modified: May 26, 2019 @ 10:00 am
  • Filed Under: Ethiopia

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar