ፍርድ ቤቱ ተጣርቶ እንዲቀርብ ትዕዛዝ ለማረሚያ ቤቱ ሰጠ
የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ ቀድሞ ማዕከላዊ ተብሎ ይጠራ በነበረው ተቋም ውስጥ ይሠሩ የነበሩት የሽብር ወንጀሎች የቀድሞ ዳይሬክተርና በክስ ላይ የሚገኙት ኮማንደር ዓለማየሁ ኃይሉ፣ በሰኔ 16 ቀን 2019 ዓ.ም. የቦምብ ፍንዳታ ተጠርጣሪ ተከሳሾች የድብደባ ጥቃት እንደደረሰባቸው ለፍርድ ቤት አመለከቱ፡፡
ኮማንደሩ እንዴት የድብደባ ጥቃቱ ሊደርስባቸው እንደቻለ ለፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 12ኛ ወንጀል ችሎት እንዳስረዱት፣ እሳቸውን ጨምሮ ሌሎች አሥር የፌዴራል ፖሊስ አባላት በተመሠረተባቸው በዋና ወንጀል ተካፋይ በመሆንና በማይገባ የአሠራር ዘዴ መጠቀም ወንጀል ክስ፣ የዓቃቤ ሕግ ምስክሮች የሚደመጡበት ቀን በመሆኑ ግንቦት 15 ቀን 2011 ዓ.ም. ጠዋት ወደ ልደታ ፍርድ ቤት ለመምጣት ከነበሩበት ቃሊቲ ማረሚያ ቤት እንዲወጡ ይጠራሉ፡፡ ከነበሩበት እስር ቤት ሲወጡ በተዘጋጀ ማድረሻ መኪና ላይ የተሳፈሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድን (ዶ/ር) ለመደገፍ ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም. ሰላማዊ ሠልፍ በወጣው ሕዝብ ላይ፣ ቦምብ በመወርወርና ጉዳት በማድረስ ክስ ተመሥርቶባቸው በክርክር ላይ ያሉ ተጠርጣሪዎች እንደነበሩ ተናግረዋል፡፡
የወንጀል ድርጊቱ በተፈጸመበት ቀን በሥራ ላይ እንደነበሩ ያስታወሱት ኮማንደሩ፣ ተከሳሾቹ ከተያዙ በኋላ የምርመራ ሒደቱን ካጣሩት ውስጥ እሳቸውም ስለነበሩበት፣ ከእነሱ ጋር ወደ ፍርድ ቤት መሄድ እንደማይችሉ በወቅቱ ለነበሩ ኦፊሰር ማስረዳታቸውን ተናግረዋል፡፡ ምክንያታቸው ደግሞ አሁን እሳቸውም ተከሳሽ በመሆናቸው ሌሎቹ ተከሳሾች፣ እሳቸው የእነሱን የወንጀል ድርጊት በማጣራታቸውና ለእስር መዳረጋቸውን ምክንያት በማድረግ ጥቃት ሊያደርሱባቸው እንደሚችሉ ጭምር ለኦፊሰሩ ቢያስረዷቸውም፣ ‹‹ለአንተ ሌላ መኪና ከየት ሊመጣ ነው?›› በማለትና በማስፈራራት እንዲሳፈሩ እንዳደረጉም አስረድተዋል፡፡
በወቅቱ በአቃቂ ማረሚያ ቤት ውስጥ የተፈጠረውን አለመግባባት የማረሚያ ቤቱ አስተዳዳሪ ጭምር መጥተውና ከቂሊንጦ የመጡትን ተከሳሾች ጭምር ካነጋገሩ በኋላ፣ ኮማንደር ዓለማየሁ አብረው እንዲመጡ መደረጉን ተናግረዋል፡፡
በሥጋት ውስጥ ሆነው ወደ ልደታ ፍርድ ቤት ያመሩት ኮማንደር ዓለማየሁ፣ ፍርድ ቤት ሲደርሱ ፖሊሶች በአግባቡ እስረኞቹን አስወርደው መውረድ ሲገባቸው፣ እነሱ ቀድመው በመውረድ እንዲወርዱ ሲያደርጉ ከቂሊንጦ የመጡት የሰኔ 16 ቀን ቦምብ ፍንዳታ ተከሳሾች በመሀል አስገብተው በካቴና በታሰረ እጃቸው ማጅራታቸውን እንደመቷቸው ገልጸዋል፡፡ እሳቸውም በታሰረ እጃቸው ለመከላከል ሲሞክሩ በካቴናው አንገታቸውን ሊያንቋቸው ሙከራ በማድረግ ጉዳት እንዳደረሱባቸውና በፖሊሶች ኃይል ሊድኑ እንደቻሉ ገልጸዋል፡፡
በተጠረጠሩበት ወንጀል ምርመራ ሲደረግባቸው ቆይቶ ክስ ሲመሠረትባቸው የቆይታቸውን ሁኔታ በሚመለከት ለፍርድ ቤት ባመለከቱበት ወቅት እነሱ ፖሊስ በመሆናቸውና በምርመራ ሥራ ላይ የቆዩ መሆናቸውን በማስገንዘብ፣ ጥቃት ሊደርስባቸው ስለሚችል በፖሊስ ማቆያ ቤት እንዲቆዩ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ጥያቄ አቅርበው እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ ነገር ግን ሥራ የሚከናወነው በሕግ በመሆኑና እነሱ በተለየ ሁኔታ በፖሊስ ማረፊያ ቤት እንዲቆዩ የሚያደርግ (የሚያዝ) የሕግ መሠረት እንደሌለ በመግለጽ ጥያቄያቸውን ፍርድ ቤቱ ውድቅ በማድረግ፣ ምንም እንኳን ተመላላሽ ተከሳሽ የሚቆየው ቂሊንጦ ተከሳሽ ማቆያ እስር ቤት ቢሆንም፣ ለደኅንነታቸው ሥጋት ስላላቸው በቃሊቲ ማረሚያ ቤት እንዲቆዩ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ መስጠቱንም ኮማንደር ዓለማየሁ አስረድተዋል፡፡ የፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ እያለና በዕለቱም እሳቸው ሥጋት እንዳላቸው እየተናገሩ አንድ ላይ እንዲሳፈሩ በማድረግ ጉዳቱ እንዲደርስባቸው የተደረገው ‹‹ሆን ተብሎ ነው፤›› ብለዋል፡፡
ፍርድ ቤቱ ተከሳሹ ያቀረቡት ‹‹የድብደባ ጥቃት ተፈጽሞብኛል›› አቤቱታን የማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ቃሊቲ ማረሚያ ቤት ለግንቦት 16 ቀን 2011 ዓ.ም. እንዲያቀርብ ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር፡፡ ግንቦት 16 ቀን 2011 ዓ.ም. ምላሽ ለመስጠት የቀረቡ የቂሊንጦ እስረኛ ማቆያ ተወካይ ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዱት፣ ድርጊቱ መፈጸሙን የሰሙት በምሽት ስለነበር ዝርዝር ሁኔታውን ማጣራት አልቻሉም፡፡ ድርጊቱ ሊፈጸም የቻለው የመኪና እጥረት በመፈጠሩና ሌላም ጊዜ የቂሊንጦንና የቃሊቲን እስረኞችን ቀላቅለው የማምጣት ልምድ በመኖሩ በዚያ ምክንያት መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ይኼ አሠራርም ሁለተኛ እንደማይደገም ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን ኮማንደሩ ጥቃቱ የደረሰባቸው እሳቸው እንዳሉት ሆን ተብሎ አለመሆኑንና ማረሚያ ቤቱም ያንን የሚያደርግበት ምንም ምክንያት እንደሌለው አስረድተዋል፡፡
‹‹እኔ ከእስረኞች ጋር አልሄድም ያልኩት ሌላ እንክብካቤ ለመፈለግ ሳይሆን የደኅንነት ሥጋት ስላለብኝ ነው፤›› ያሉት ኮማንደር ዓለማየሁ፣ እነሱ የሌሎችን ሰብዓዊ መብት አሳጥታችኋል ተብለው ተከሰው፣ እነሱም የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሊፈጸምባቸው እንደማይገባ ተናግረዋል፡፡
‹‹እኔ ፖሊስ ነኝ፣ ፖለቲከኛ አይደለሁም፤›› በማለት ወንጀል ፈጽመዋል ተብለው ከታሰሩ በኋላ፣ እንደ ማንኛውም እስረኛ ፈጽመዋል የተባለው ወንጀል በማስረጃ ከተረጋገጠባቸው በሕግ ይቀጣሉ እንጂ፣ ያላግባብ ድብደባና የአካል ጉዳት ሊደርስባቸው እንደማይገባም አክለዋል፡፡ እሳቸው ድርጊቱ የተፈጸመባቸው ሆን ተብሎ ነው ያስባላቸው፣ በሕግ ማስከበር ሥራ ላይ ረዥም ጊዜ ከመሥራታቸው አኳያ አንድ የፖሊስ አካል እንዴት መሥራት እንደሚችል ስለሚያውቁ፣ ጥቃቱ በደረሰባቸው ቀን የነበሩ ፖሊሶችም ሆኑ የማረሚያ ቤት ኃላፊዎች አሠራሩን እያወቁና እሳቸውም ምልክቶች በማየታቸው እያመለከቱ በዝምታ ታልፎ ጥቃቱ ስለደረሰባቸው መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ጠበቃቸውም ትዕዛዝ የተሰጠው የቃሊቲ ማረሚያ ቤት ኃላፊዎች ቀርበው እንዲያስረዱ ሆኖ ሳለ፣ የቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ተወካይ የተላኩት አግባብ ባለመሆኑ፣ ቀደም ብሎ ተከሳሾቹ ለብቻቸው እንዲጠበቁ የተሰጠውን ትዕዛዝ ለምን እንዳላከበሩ ጭምር ተጠርተው እንዲጠየቁላቸው ለፍርድ ቤቱ አመልክተዋል፡፡
ፍርድ ቤቱ አቤቱታውንና ምላሹን ግራና ቀኝ ካዳመጠ በኋላ ቀደም ብሎ በተሰጠ ትዕዛዝ፣ ተከሳሾቹ ችግር በማይደርስባቸው ማረሚያ ቤት ማለትም ቃሊቲ እንዲቆዩ መደረጉን አስታውሶ፣ ይህ በሆነበት ሁኔታ ለምን ችግሩ እንዲፈጠር እንደተደረገ ተጣርቶ እንዲቀርብ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ በተጨማሪም ኮማንደር ዓለማየሁን ጨምሮ ለሌሎችም ተከሳሾች ተገቢ ጥበቃ እንዲደረግላቸው፣ ጉዳት የደረሰባቸው ተከሳሽ ተገቢ ሕክምና እንዲያገኙ እንዲደረግና ድርጊቱን በፈጸመው ሌላው ተከሳሽ ላይ ተገቢ ማጣራት ተደርጎ፣ የቃሊቲ ማረሚያ ቤት ኃላፊ ቀርበው እንዲያስረዱ ትዕዛዝ ተሰጥቷል፡፡
ኮማንደር ዓለማየሁን ጨምሮ ሰባት የፌዴራል መርማሪ ፖሊሶችና ሦስት የአዲስ አበባ ፖሊስ አባላት፣ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32 (1) (ሀ እና ለ) እና 424 (1) ድንጋጌን በመተላለፍ በዋና ወንጀል ተካፋይ በመሆን በፈጸሙት በማይገባ የአሠራር ዘዴ መጠቀም ወንጀል 77 ክሶች ተመሥርቶባቸው ክደው በመከራከራቸው፣ ከግንቦት 12 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ ዓቃቤ ሕግ ምስክሮቹን እያሰማባቸው ሲሆን፣ 93 ምስክሮችም ተቆጥረውባቸዋል፡፡
Average Rating