በከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተጠርጥረው ምርመራ ሲደረግባቸው የከረሙትና ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ የተመሠረተባቸው የቀድሞው የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው አሰፋን ጨምሮ አራት ተከሳሾችን፣ የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ በአድራሻቸው አፈላልጎ መጥሪያ እንዲሰጥ ለሦስተኛ ጊዜ ትዕዛዝ ተሰጠ፡፡
ትዕዛዝ የተሰጠው ዓርብ ግንቦት 16 ቀን 2011 ዓ.ም. በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አንደኛ ወንጀል ችሎት ሲሆን፣ ፍርድ ቤቱ ግንቦት 9 ቀን 2011 ዓ.ም. የሰጠው ትዕዛዝ ዘግይቶ ስለደረሰውና የመጥሪያ ደብዳቤውን የሚያደርሰው የትግራይ ክልል መሆኑን ጠቁሞ ተጨማሪ ጊዜ እንዲሰጠው ፌዴራል ፖሊስ በመጠየቁ ነው፡፡
ከሳሽ ዓቃቤ ሕግም በተሰጠው ትዕዛዝ መሠረት ክትትል ማድረጉን ጭምር በማስገንዘቡ፣ ፍርድ ቤቱ ተጨማሪ ጊዜ ማስፈለጉን ስላመነበት 17 ቀናት ተጨማሪ የማድረሻ ጊዜ ፈቅዷል፡፡
ፍርድ ቤቱ ቀደም ብሎ የቀረበለትን የተከሳሾች አቤቱታ፣ ማለትም ደመወዛቸው በመቋረጡ ቤተሰቦቻቸው እየተቸገሩ ስለመሆናቸው በሚመለከትም ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ ችሎቱ የወንጀል ችሎት በመሆኑና ከፍትሐ ብሔር ጥያቄዎች ጋር በተያያዘ ድጋፍ የሚሰጥ የሕግ ድንጋጌ ባለመኖሩ ጥያቄያቸውን አልተቀበለውም፡፡ በመሆኑም ተከሳሾቹ በሲቪል ሰርቪስ በኩል ወይም በሚመለከተው አካል በኩል ጥያቄያቸውን እንዲያቀርቡ በመንገር፣ ያቀረቡትን አስተዳደራዊ አቤቱታ አልፎታል፡፡
በሌላ በኩል ዓቃቤ ሕግ በክሱ የገለጸውን 18 የሲዲ ማስረጃዎች በሚመለከት ሲሆን፣ ከአንድ ሲዲ በስተቀር 17 አባዝቶ በማቅረቡ ለተከሳሾች እንዲደርስ ከተደረገ በኋላ፣ አንደኛውንና በተራ ቁጥር አራት የተጠቀሰ የሲዲ ማስረጃ፣ በቀጣይ ቀጠሮ አባዝቶ እንዲያቀርብ ትዕዛዝ ተሰጥቷል፡፡ ዓቃቤ ሕግ በ21ኛ ተከሳሽ አቶ ሰይፈ በላይ ለቀረበው የመጀመርያ ክስ መቃወሚያ ምላሽ ሲሰጥ፣ ሌሎች ተከሳሾችም በጠበቆቻቸው አማካይነት ዓቃቤ ሕግ ለ29 ምስክሮቹ በአዋጅ ቁጥር 699/2003 ድንጋጌ መሠረት ጥበቃ እንዲደረግለት ባቀረበው አቤቱታ ላይ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
የተከሳሾቹ ጠበቆች ባቀረቡት መቃወሚ እንደገለጹት፣ ዓቃቤ ሕግ ያቀረበው መቃወሚያ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 9 (4) እና 13 (2) ድንጋጌን የሚቃረን መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ምንም እንኳን በአዋጁ አንቀጽ 4 (1) ድንጋጌ መሠረት ጥበቃ እንደሚደረግ የተደነገገ ቢሆንም፣ በሌላ በኩል ደግሞ የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 20 (4) ድንጋጌ የሚቃረን መሆኑንም አክለዋል፡፡ በአንቀጽ 20 (4) ጉዳዮችን በግልጽ ችሎት የመስማት መብት የሚቃረን በመሆኑ ውድቅ እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል፡፡
ተከሳሾቹ የተከሰሱበትን ጉዳይና የሚቀርቡባቸውን ምስክሮች የማወቅ መብት እንዳላቸው፣ የመመርመር ሒደቱም ፍትሐዊ በሆነ መንገድና በግልጽ ችሎት እንዲካሄድና ራሳቸውን የመከላከል መብታቸው እንዲከበር፣ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 9 (4) እና አንቀጽ 13 (2) ኢትዮጵያ ፈራሚ ሆና ያፀ ደቀቻቸውን ሕጎች እንደሚጥስም ጠበቆቹ ገልጸዋል፡፡ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎች የአገሪቱ ሕግ አካል መሆናቸውንም አክሏል፡፡ ዓለም አቀፍ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ስምምነት (አይሲሲፒአር) እና የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ (ዩዲኤችአር) አንቀጽ 14 (3) እና 11ንም የሚጥስ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ አዋጁም ከዓለም አቀፍ ስምምነቶች ጋር የሚጣረስ በመሆኑ ውድቅ እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል፡፡
ምስክሮችና ጠቋሚዎችን ለመጠበቅ የወጣው አዋጅ ቁጥር 699/03 ዝም ብሎ በዘፈቀደ የሚከለክል ሳይሆን፣ ሦስት መሥፈርቶችን እንዳስቀመጠም የተከሳሾች ጠበቆች በምላሻቸው ጠቁመዋል፡፡ ተከሳሽ ከአሥር ዓመት በላይና በሞት በሚያስቀጣ ወንጀል ሲከሰስ፣ የወንጀል ድርጊቱ ያለ ምስክሩ ሊረጋገጥ የማይችል ሲሆንና በምስክሩና በቤተሰቡ፣ እንዲሁም በንብረቱ ላይ ከባድ አደጋ የሚደርስ መሆኑ ሲረጋገጥ ቢሆንም፣ የዓቃቤ ሕግ ክስ ግን ይኼንን እንደማያስረዳ ጠቁመዋል፡፡
በሌላ በኩል ምስክር ጥበቃ የሚደረግለት በአዋጁ አንቀጽ 6፣ 7 እና 8 ድንጋጌ መሠረት ‹‹ጥበቃ ሊደረግልኝ ይገባል›› ብሎ ሲያመለክት መሆኑን ቢደነግግም፣ ዓቃቤ ሕግ በምስክሩ ማመልከቻ ስለመቅረቡ ለፍርድ ቤቱ አለማቅረቡንም ገልጸዋል፡፡ በአዋጁ አንቀጽ 23 (2) መሠረትም ከላይ የጠቀሷቸው ሁኔታዎች መሟላት እንዳለባቸው የተከሳሽ ጠበቆች በመግለጽ፣ የዓቃቤ ሕግ ‹‹ለምስክሮቼ ጥበቃ ይደረግልኝ›› ጥያቄ አዋጁን እንኳን ያላሟላ በመሆኑ ውድቅ እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል፡፡
የዓቃቤ ሕግ ጥያቄ በሌላ በኩል የወንጀል ፍትሕ አመራርና ትክክለኛ ፍትሕ አሰጣጥ ሒደትን የሚያስተጓጉል መሆኑን ጠቁመው፣ የወንጀል ክስ በግል የሚቀርብ በመሆኑ የወንጀል ድርጊቱ በምስክር የሚረጋገጥ ከሆነ የምስክሮቹ ተዓማኒነትና ማንነት ታውቆ ተገቢ መስቀለኛ ጥያቄ መቅረብ እንዳለበትም ጠበቆቹ አስረድተዋል፡፡ እያንዳንዱ ተጠርጣሪ ፈጸመ ለተባለው ወንጀል በድርጊቱ ልክ ኃላፊነት እንዲወስድና በጅምላ የቀረበውን ክስ ከጅምላ ፍርድ ለመጠበቅ፣ እንዲሁም ተከሳሾቹ በሕግ ፊት እኩል ሆነው የመታየት በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 25 የተሰጠው ድንጋጌን ለማክበር፣ የዓቃቤ ሕግ አቤቱታ ውድቅ እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል፡፡
ፍርድ ቤቱም ዓቃቤ ሕግና ጠበቆች በሰጧቸው የአቤቱታ መልሶች ላይ ውሳኔ ለመስጠትና መጥሪያ እንዲደርሳቸው የተሰጠውን ትዕዛዝ ለመጠባበቅ ለሰኔ 3 ቀን 2011 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
Average Rating