በፍቃዱ ገ/ስላሴ
አዎን ይኸው እወቁልኝ፣ ምስክር ሁኑኝ ሰማዕታት ለሷ ነው እንባ እሚያስፈልጋት ከጠላቶቼ ጭብጥ ውስጥ፣ ትንፋሼን በእጄ ሰነጥቃት ሞቴን ከመንጋጋቸው ውስጥ፣ መንጭቄ እኔው ስሞታት ለሀገሬ ብድር ልከፍላት የነፈገችኝን ፍቅር፣ በራሴው ሞት ልለግሳት ዳግሞ ከሞቴ ባንኜ፣ በመንፈስ ጣር ስሞግታት ያኔ ነው እንባዋ የሚያጥራት…….››:: ይህንን ግጥም ያገኘሁት ከባለቅኔው ሎሬት ፀጋዬ ገብረ መድህን ‹‹እሳት ወይም አበባ›› ከሚለው የግጥም መድብል ‹‹ የቴዎድሮስ ስንብት ከመቅደላ›› በተሰኘው የግጥሙ መሀከለኛው ክፍል ነው:: ይህ ግጥም እራሳቸውን ለሀገራቸው መስዋዕት ላደረጉ ድንቅ ኢትዮጵያዊ ጀግኖች የሚመጥን አይነተኛ ክተባ በመሆኑ ለዚህ ግጥም ልዩ ስሜት አለኝ:: ይህ ታላቅ የቅኔ ሰው በስራው ሀገሩ ኢትዮጵያን ለአለም በማስተዋወቅ ሀገራዊ ግዴታውን የተወጣ አንጋፋ የሀገር ባለውለታ ነው:: የዚህን የሀገር ባለ ውለታ የህይወት ዘመን ስራዎቹን ዘመን ተሻጋሪ በመሆናቸው ኢትዮጵያ ሀገራችን እንደነዚህ አይነት ድንቅ ኢትዮጵያዊያን ባለቤት እንደሆነች ማስታወስ ተገቢ ነው ብዬ ስላሰብኩ የዛሬ ምናባዊ እንግዳዬ አድርጌያቸዋለሁ:: ሎሬት ጸጋዬ ገብረመድህን እ.ኤ.አ በ1928 ዓ.ም ቦዳ ተብላ በምትጠራው የአምቦ ከተማ ባለች ትንሽ መንደር እንደተወለዱ ግለ ታሪካቸው ያስረዳል:: ሎሬት ፀጋዬ ለዚህች የትውልድ ስፍራቸው ልዩ ፍቅር ስለነበራቸው እንዲህ በማለት ተቀኝተዋል::
ምነው አምቦ – – – የደማም አምባዎች ቁንጮ፣ አንዳልነበርሽ የደም ገንቦ እንዳልነበርሽ ንጥረ ዘቦ ዙሪያሽ በምንጭሽ ታጅቦ በተራሮችሽ ተከቦ ከጠበልሽ ሲሳይ ታልቦ ከአዝርትሽ ፍሬ ዘንቦ – – – – ››› በማለት ስለትውልድ ከተማቸው የሚሰማቸውን ከትበዋል:: በአንቦ ትምህርት ቤቶች፣ በአዲስ አበባው ጄኔራል ዊንጌት እንዲሁም በአዲስ አበባ የኒቨርስቲ የንግድ ስራ ት/ቤቶች ውስጥ የሀገር ውስጥ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል:: ሎሬት ወደ አሜርካ በማቅናት የህግ ትምህርትም ተምረዋል:: በመቀጠልም፣ በለንደን የቴአትር እንዲሁም በፈረንሳይ የስነ-ጥበብ ትምህርት ከተከታተሉ በኋላ ወደ ሀገራቸው በመመለስ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቴአትር ትምህርት ቤት ያቋቋሙ ባለውለታ ናቸው:: ሎሬት በአማራ እና በኦሮሚያ ባህልና ሀይማኖት ውህድ ናቸው:: በእናታቸው በኩል የሸዋ አማራ በመሆናቸው የእርስትና ሀይማኖት ባህልን ይዘዋል:: በአባታቸው በኩል ደግሞ የኦሮሞን ባህላዊ እምነት የሆነውን ዋቄ ፈታን የማወቅ ሰፊ እድል ነበራቸው:: በአካባቢያቸው የሚነገሩ የኦሮምኛ እና የአማርኛ ቋንቋዎችን ጠንቅቀው የማወቃቸውን ያህል የግዕዝ ቋንቋን እና እንግሊዘኛን መግባቢያቸው ጭምር ነው:: ሎሬት በግጥማቸው የተለያዩ የኦሮሚኛ፣ የግዕዝና የአማርኛ ጠንካራ ቃላትን በመጠቀም ይታወቃሉ:: ሎሬት በእንግሊዘኛ ቋንቋም ቢሆን የተዋጣላቸው ከመሆናቸው የተነሳ እንደ ሼክስፒር ጥርት ያለ እንግሊዘኛ ይናገራሉ የሚሏቸውም ነበሩ:: ሎሬት የፈረንሳይኛ ቋንቋ ችሎታቸውም ለክፉ እንደማይሰጣቸው ግልፅ ነበር:: የእርሳቸው ቴያትሮችና ስነ-ግጥሞች ከትውልድ ትውልድ እንዲሸጋገሩ ያስቻላቸው ተፈጥሮን እና እምነትን መሰረት በማድረግ በይዘታቸው ጥብቅ፣ በቋንቋቸው ምጡቅ፣ በአስተውሎታቸው ጥልቅ በመሆናቸው እንደሆነ ብዙሃኑ ይስማሙበታል:: የዚህ ታላቅ የጥበብ ሰው ተውኔት ከባህልና ከማንነት ጋር ጥብቅ ቁርኝነት ያለው በመሆናቸው ዘመናት ተሻግረው ተወዳጅነታቸውን ይዘው እንዲቆዩ አድርጓቸዋል:: ተውኔቶቹ በአፃፃፋቸውና በግዜያቸው ልዩ ይምሰሉ እንጂ ተመሳሳይ አይነት ይዘቶች እንዳላቸው ባለሙያዎች ያስረዳሉ:: ፀሀፊ ተውኔቱ በህይወት ዘመናቸው ሊያስተላልፉ የሚፈልጉትን መልዕክቶች ከባህልና ታሪክ ጋር አዋህደው ያንፀባረቁባቸው ገፀ-ባህሪያት በየተውኔቶቹ ላይ እንደሚገኙ እና እድሜ ዘመኑን ሀገራዊ እሴቶችን ሲያቀነቅንባቸው የኖሩ የጥበብ ውጤቶች ናቸው:: ሎሬት ኢትዮጵያዊነትን በተላበሰ መልኩ የቀለም፣ የዘር፣ የፆታ፣ የመደብ የመልካም ምድር ልዩነት ባለበት ሀገር ውስጥ ልዩነትን ወደ አንድነት እና ውበት በመቀየር ኢትየጵያዊነትን ድንቅ የተፈጥሮ ስጦታ አድርገን እንድንመለከት ከፍተኛ ጥረት አድርገው አልፈዋል::
Average Rating