=================================
ሰሞኑን የአሀዱ ሬዲዮ ጣብያ ጋዜጠኛ ታምራት አበራ በሰንዳፋ ከተማ የታጠቁ የፖሊስ አባላት አማካኝነት ተይዞ ለእስር መዳረጉ ይታወሳል።ከዚህ ጉዳይ ጋ በተያያዘ ም የጣብያው ስራ አስኪያጅ ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠም ተይዞ ፍ/ቤት እንዲቀርብ መታዘዙን ለማረጋገጥ ችያለሁ።ይህን ተፈጻሚ ለማድረግም በተመሳሳይ የታጠቁ የፖሊስ አባላት ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠን ለመያዝ ወደ አሀዱ የሬድዮ ጣብያ መሄዳቸውንም አረጋግጫለሁ።ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ ለስራ ጉዳይ ወጣ በማለቱ ፖሊሶቹ ሊያገኙት ባይችሉም ወደ አዲስ አበባ ሲመልስ መያዙና መታሰሩ አይቀርም።
ከዚህ ጋ በተያያዘ እንደ ጋዜጠኛ የሚያሳስቡኝ ጉዳዮች አሉ። ጋዜጠኛ ታምራት አበራ በሰንዳፋ ፖሊሶች ከመያዙና ወደ እስር ቤት ከመወሰዱ በፊት በሰራው ፕሮግራም ላይ በአስራር ላይ የፈጸማቸው ስህተቶች ስለመኖራቸው እና እርምት እንዲያደርግ ምንም አይነት ማሳሰቢያ ከየትኛውም የህግ አካል አልተሰጠውም። በአሰራሩ መሰረትም ለኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሳጣንም ሆነ ለአሀዱ ሬዲዮ የቀረበ ቅሬታ የለም። ጋዜጠኛው ፕሮግራሙን የሰራው የሰበታ ከተማ ፍ/ቤት የመጨረሻውን ውሳኔ ከሰጠና አቤቱታ አቅራቢ ፍትህ ተጓድሎብኛል በማለታቸው ነው።
ጋዜጠኛው የእስር ትእዛዝ የወጣበት ግንቦት 15 ቀን 2011 ዓ.ም ሆኖ ሳለ አርብ ምሽትን ጠብቆ መያዝ ለምን አስፈለገ? ይህ በቀደመውና አሁን ተለውጧል ብለን በምንጮህለት የህወሀት አገዛዝ ወቅት ይፈጸም የነበረና ጋዜጠኞች የሚዘጉባቸውን ቀናት በመምረጥና አንድ ተጠርጣሪ ከተያዘ በኋላ በ48 ሰአታት ውስጥ ለፍርድ ቤት መቅረብ አለበት የሚለውን የህግ ክፍል ሆን ብሎ ለመናድ የሚከተሉት አሰራር ለምን እንዲደገም ሆነ?
ጋዜጠኛ ያለውን የመጻፍና ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መሰረታዊ መብቶች ተከብረዋል በተባለበትና የፕሬስ ነጻነት ቀን በተከበረ ማግስት ይህን መሰል እርምጃ መውሰድስ ምን ይሉት ፈሊጥ ይሆን? በኢትዮጵያ አንድም ጋዜጠኛ እስር ቤት አይገኝም ተብሎ በተደሰኮረ ማግስት ያለምንም ህጋዊ አካሄድ ጋዜጠኛ ታስሯል።ነገ ደግሞ ጥበቡ በለጠ ይቀጥላል። ከነገ ወዲያስ?
በኢትዮጵያ የቅርብ አመታት ታሪክ የታጠቀ ሰራዊት ወደ አንድ የሬዲዮ ጣቢያ የሄደው በ1966 አብዮትና 1983ዓ.ም የመንግስት ለውጥ ላይ ህወሓት ኢህአዴግ የኢትዮጵያ ሬዲዮን መቆጣጠሩ የቅርብ ታሪካችን ነው።የሰንዳፋ ከተማ የታጠቀ ሰራዊት በታሪካችን ለሶስተኛ ጊዜ አንድን ጋዜጠኛ ለመያዝ ወደ አሀዱ የሬዲዮ ጣቢያ ልኴል።ይህ የሚነግረኝ የጋዜጠኝነት ሙያ ለአደጋ የተጋለጠና በቂ የህግ ጥበቃ እንደማይደረግለት ነው።ይህ ለኔ መፈንቅለ ሚዲያ ነው። ከዚህ ጋ በተያያዘ ነገስ ማን ይሆን ሀሳቡን በመገለጹ፣በመጻፍና በመናገሩ ለጥቃት የሚጋለጠው የሚል ፍርሀት እንዲያረብብና ማንም እንደፈለገ የማድረግ መብት እንዳለው እንዲሰጠው የልብ ልብ ይሰጣል።
ከዚህ በተያያዘ ይህን መሰሉን የጋዜጠኞች የመብት ጥሰት እንዳይካሄድና ለጋዜጠኝነት ከለላ እንዲደረግ በስማችን የተቌቋማችሁና አመታትን የምትቆጥሩ ማህበራት ተብዬዎች ከወዴት ናችሁ? የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና የሰብአዊ መብት ተሟጋቾስ ምን እየሰራችሁ ነው? ነገሩ ሳይቃጠል በቅጠል ካልተባለ አንድም የታሰረ ጋዜጠኛ የሌለባት አገር ጋዜጠኞችን ማጎር ስትጀምር መጮህ ዋጋ አይኖረውም።
በየትኛውም ማህበራት ውስጥ ባንታቀፍም ሙያው ውስጥ ያለን ጋዜጠኞችም ስለ መብታችን፣ስለ የመንግስት የህግ ከለላ አስፈላጊነት እና ህገ ወጥ የጋዜጠኞች ወከባዎችና እስሮች በጋራ መቃወምና ለሚመለከተው የመንግስት አካል መረጃዎች እንዲደርሱ መስራት ይጠበቅብናል። ነግ በእኔ ነውና!!!
Via Befekadu Abay
Average Rating