www.maledatimes.com ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ፅጌ - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ፅጌ

By   /   July 1, 2019  /   Comments Off on ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ፅጌ

    Print       Email
0 0
Read Time:1 Minute, 47 Second

ባሳለፍነው ረቡዕ፣ ሰኔ 19፣ 2011 በላሊበላ ከተማ በላሊበላ ቤተ ክርስቲያን በቤተ ማሪያም እና በቤተ ሚካኤል ደማቅ ስርዓተ ቀብር የተደረገላቸው የአማራ ክልል የሰላም እና የፀጥታ ቢሮ ኀላፊ ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ፅጌ ስለ ለውጡ ደጋፊነታቸውን የሚገልጹ ንግግሮች በሕይወት እያሉ የተለያዩ አስተያየቶችን ይሰጡ ነበር።

በተደረገ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ተጠርጥረው ለዘጠኝ ዓመታት በአገር ክህደት ወንጀል የዕድሜ ልክ ፅኑ እስራት የተፈረደባቸው ብርጋዴር ጄነራል አሳምነው የለውጡን መምጣት ተከትሎ ከእስር ተፈትተው እና ማዕረጋቸውም በክብር ከጠቅላይ ሚኒስቴሩ ተመልሶላቸው ወደ ክልሉ ከፍተኛ የአስተዳደር እርከን በአማራ ክልል የሰላም እና ፀጥታ ቢሮ ኀላፊነት ተሹመው ሲያገለግሉ ቆይተዋል። ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው የዛሬ ዓመት ገደማ የተደረገው የለውጡ የድጋፍ ሰልፍ ላይ ባደረጉት ንግግር ላይ “ሙሴ እስራኤልን ነፃ ያወጣው በአርባ አመቱ ነው፤ ዐቢይ ኢትዮጵያን ነጻ ያወጣው በ40 ዓመቱ ነው” ብለው ንግግር አድርገዋል።

አክለውም “የእስራኤልን ነጻነት የመራው ሙሴ ነው፤ የኢትዮጵያን ነጻነት የመራው ዐቢይና ወንድሞቹ ናቸው” ብለውም ነበር። እንደ ቢቢሲ አማርኛ ዘገባ ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ፅጌ ተወልደው ያደጉት ወሎ ላስታ ውስጥ ሲሆን የትጥቅ ትግሉን ከመቀላቀላቸው በፊት በደሴ ከተማ በሚገኘው የመምህራን ኮሌጅ ውስጥ መምህር ሆነው አገልግለዋል። ወታደራዊውን አገዛዝ በመቃወም የወቅቱን ኢህዴን በኋላ ብአዴን የተባለውን የአማራ ድርጅትን የተቀላቀሉት አሳምነው ደርግ ከሥልጣን ከተባረረ በኋላ በትውልድ አካባቢያቸው አስተዳዳሪ ሆነው ተሹመው ነበር።

በማስከተልም ወደ መከላከያ ሠራዊቱ ገብተው በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የድንበር ጦርነት ውስጥ ተሳታፊ ሆነው የነበሩት አሳምነው በአንድ ወቅትም ከጀርመኑ ሬዲዮ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስም “የውትድርናው ዓለም የተደራጀ እና የሠለጠነ ነው። ምንም እንኳን መስዋትነት የሚያስከፍል ቢሆንም ግን አያስቸግርም። ይንን ዓይነት ተቋም በታሪክ አጋጣሚ የሚገኝ ነው፤ እኔም ከሲቪል ዓለም ወጥቼ በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት የመምራት ዕድል አገኝቼ ነበር” ሲሉ መናገራቸው ይታወሳል።

በመቀጠልም ወደ አሜሪካ በመሔድ ወታደራዊ ትምህርታቸውን የተከታተሉ ሲሆን ከጦርነቱ በኋላ የጄኔራልነት ማዕረግ አግኝተው በመከላከያ ሠራዊት ውስጥ በኃላፊነት ሲያገለግሉ ቆይተዋል።

ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው የመከላከያ ሠራዊቱን ኮሌጅ በበላይነት በመምራትና በማስተማር እንዳገለገሉ ያተተው ቢቢሲ በ2001 በቀረበባቸው ክስ ጥፋተኛ ስለተባሉ ማዕረጋቸው ተገፎ የዕድሜ ልክ እስራት ተፈርዶባቸው ለዘጠኝ ዓመታት በእስር ላይ ከቆዩ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ከእስር ተፈትተው ለአገራቸው የከፈሉትን መስዋዕትነት ዕውቅና በመስጠት ማዕረጋቸው እንዲመለስና የሚያገኙት ጥቅም እንዲከበርላቸው አድርገዋል።

የአማራ ክልልም ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ፅጌን ተጠሪነታቸው ለክልሉ ፕሬዝዳንት ሆኖ ለአጭር ጊዜ በቆዩበት የአማራ ክልል የፀጥታ ቢሮ ኃላፊ ሆነው እንዲያገለግሉ ሹመት ሰጥቷቸው ነበር። ብሔራዊው ቴሌቪዥን እንደገለጸው ብርጋዴር ጄነራል አሳምነው ፅጌ መንግሥት ‘መፈንቅለ መንግሥት’ በሚል በጠራው የግድያ ተግባር ተጠርጥረው ሲሳደዱ ከቆዩ በኋላ ባሕር ዳር ዙሪያ በሚገኝ ዘንዘልማ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ በፀጥታ ኃይሎች መገደላቸውን ታውቋል።

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 6 years ago on July 1, 2019
  • By:
  • Last Modified: July 1, 2019 @ 8:21 am
  • Filed Under: Ethiopia

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar