www.maledatimes.com የጠቅላይ ሚኒስትሩ የፓርላማ ውሎ - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የፓርላማ ውሎ

By   /   July 3, 2019  /   Comments Off on የጠቅላይ ሚኒስትሩ የፓርላማ ውሎ

    Print       Email
0 0
Read Time:7 Minute, 7 Second

ዶ/ር አብይን እንደ መልስ ሳጥን ቆጥሮ ሁሉን በአንድ ቀን ፍታ የሚል ጤነኛ ኢትዮጵያዊም የለም፡፡

መስከረም አበራ

ጠንካራ ነኝ ማለቱ ለበጎ ያልሆነው ህወሃት የማዕከላዊ መንግስቱን መዘወሩን ካቆመ ወዲህ የመጣው የዶክተር አብይ መንግስት የተረከባት ኢትዮጵያ በጉያ በጀርባዋ፣ በእጅ በእግሯ፣በአፍ በሆዷ ውስብስብ ችግር አዝላ የምትጎተት ነች፡፡ይህ ችግር በድንገት በመጣው የዶ/ር አብይ መንግስት ቀርቶ በማኛውም እኔ ነኝ ባይ የምድር ጠቢብብ በአንድ አመት ውስጥ ሊፈታ አይችልም፡፡ ዶ/ር አብይን እንደ መልስ ሳጥን ቆጥሮ ሁሉን በአንድ ቀን ፍታ የሚል ጤነኛ ኢትዮጵያዊም የለም፡፡

ሆኖም ከችግሩ ውስብስብነት እና ውዝፍነት የተነሳም ሆነ ከእርሳቸው ሰዋዊ ድክመት የተነሳ ችግር መፍታት ቢያቅታቸው እንኳን እሳቸው የሚያመጡት ተጨማሪ ችግር እንዳይኖር ለሚሰሩት ስራ ሁሉ ተጠያቂነት ሊኖራቸው ግድ ነው፡፡በመንግስታቸው አሰራር ላይ ጥያቄ የሚያነሳው ኢትዮጵያዊ ሁሉ አላማው እሳቸውን ማጣጣል፣ የጀመሩትን ጉዞ ማጨናገፍ፣ ይበጃል ብለው እየሰሩ ያለውን ነገር ዋጋ ለማሳጣት ሊሆን አይችልም፡፡

ይልቅስ ሃገራችን በጣም አሳሳቢ ችግር ውስጥ እንደመሆኗ መንግስታቸው በችግሩ አሳሳቢነት መጠን ያልተራመደ የሚመስለው ዜጋ ሊተቻቸው ይችላል፡፡ ይህ አይነቱ ትችት የእሳቸውን ልፋት ገደል ለመክተት የተደረገ ክፉ ነገር አይደለም፡፡ እሳቸው ግን የሚቀርብባቸውን ትችት በበጎ ጎኑ የሚረዱት አልመሰለኝም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በትናንቱ የፓርላማ ውሏቸው ካሳዩት ሁኔታ የተረዳሁት የሃሳብ ልዩነትን እና የመንግስት ተጠያቂነትን እምብዛም እንደማይፈልጉ ብቻ ሳይሆን ስሜታዊ ብስጭት ውስጥ ሊከታቸው እንደሚፈትናቸው ነው፡፡

የእርሳቸው ስሜታዊ መሆን ደግሞ የሚያጠፋው ብዙ ነው፡፡ ወጣት መሪ መሆናቸው፣ ሃገሪቱ ራስ አዟሪ ውስብስብ ችግር ውስጥ በተዘፈቀችበት ጊዜ ወደስልጣን መምጣታቸው ተደማምሮ ብስጭታቸውን ሊያብሰው ይችላል፡፡ ሆኖም መንግስትነት ሆደ-ሰፊነት መሆኑን ማሰቡ ለእራሳቸውም ለሃገራችንም በጎ ውጤት ይኖረዋል፡፡በግሌ ዶ/ር አብይ ውስብስብ ችግር ያዘለችውን ሃገር ሊመሩ መንበር ከጨበጡ ወዲህ ኢህአዴግ ውስጥም ኢትዮጵያ ትታየኛለች፡፡ ህወሃት መራሹን ኢህአዴግ በምጠረጥርበት ሃገር የማፍረስ ሴራ የዶ/ር አብይን ኢህአዴግ አልጠራጠውም፡፡

ዶ/ር አብይ “በኢትዮጵያ ህልውና ላይ አንደራደርም” ሲሉ እኔም ስለምሳሳላት ኢትዮጵያ እኔ በሚሰማኝ መጠን እየተሰማቸው እንደሚያወሩ አምናለሁ፡፡ ህወሃት ኢትዮጵያ እንዳትፈርስ ሲል ግን ስልጣኑን አጥብቆ እያሰረ እንደሆነ ብቻ እረዳ ነበር! ስለዚህ እኔን ጨምሮ እያንዳንዱ ኢትዮጵያን የሚወድ ዜጋ ከዶ/ር አብይ ጋር የሚያስማማው አንድ ጉዳይ አለ-የኢትዮጵያ ህልውና! በዚህ መሰረታዊ ነገር የተስማማን ሁሉ ግን ዶ/ር አብይ ኢትዮጵያን ለማዳን እርሳቸው ትክክል ነው ብለው አምነውበት በሚሄዱበት አካሄድ ሁሉ እንስማማለን ማለት አይደለም፡፡

ይህ መሰረታዊ አንድነት ሳይረሳ ጥፋት የጠፋ ሲመስለው የተቸ ቢያንስ ኢትዮጵያን በማለቱ ላይ ያለው ተመሳሳይ ምኞት ተረስቶ ለጥፋት የቆመ፣ መተቸት ብቻ የሚያስደስተው፣ የአሉባታ ሱስ ብቻ የሚያናገረው ተደርጎ በመንግስት ዘንድ የሚታሰብ ከሆነ ቀጣዩ ትዕይንት ጋዜጠኛን እና ተችን እያሳደዱ ማሰር ነው የሚሆነው፡፡ጠ/ሚ አብይ በሰሞኑ የፓርላማ ውሏቸው ከተነሱ ጥያቄዎች ውስጥ ገሚሶቹ ስሜታዊ አድርገዋቸው ተችዎችን “እኛ የያዝነው እውነት ነውና ማሸነፋችን አይቀርም፤ እናንተ ግን እግዚአብሄር ይፍረድባችሁ” እስከማለት አድርሷቸዋል፡፡

ይህን ንግግራቸውን ስሰማ ዶ/ር አብይ ለትችት ያላቸውን ስስ ስሜት በደንብ ተረድቻለሁ፤ ብዙ ነገርም ወደ ህሊናየ መጥቷል-ጭንቀት ጭምር! ዶ/ር አብይ የእግዚአብሄር ፍርድ እንዲያገኛቸው ለፈጣሪ አሳልፈው የሰጧቸው ሚዲያዎች በውጭ ሃገር የሚገኙ፣ በዩቱብ የሚሰራጩ እንደሆኑ አብረው ገልፀዋል፡፡ “ባህር ማዶ ስላላችሁ እኔ ምንም ላደርጋችሁ አልችልም” ሲሉም አክለዋል፡፡ አብይ በተችዎቻቸው ላይ የመለኮት ፍርድ እንድትመጣ የፈለጉት እነዚህ ሚዲያዎች ከእርሳቸው ግዛት ውጭ ስለሆኑም ጭምር ነው፡፡ይህ ንግግራቸው እና ብስጭታቸው ሚዲያዎቹ በአብይ ግዛት ቢሆኑስ ኖሮ ማስባሉ አይቀርም፡፡ ከዚህ መረዳት የሚቻለው ነገር በዶ/ር አብይ ግዛት ሆኖ መንግስታቸውን መተቸት እምብዛም እድሜ ያለው ፈለግ ላይሆን እንደሚችል ነው፡፡ጠ/ሚው እያደር ስሜታዊነት እየታየባቸው መምጣቱ ሁለት አደጋ አዝሎ ይታየኛል፡፡ አንደኛው የአምባገነንነት ዋዜማ ሁለተኛው በዶ/ር አብይ ዘንድ እየተተከለ የመጣ የተጠልቻለሁ ስጋት፡፡ ሁለቱም አሳሳቢ ናቸው፡፡

አብይ ወደ አምባገነንነት እያዘነበሉ ከሄዱ የኢትዮጵያ ህዝብ ደግሞ አምባገነንነትን የመሸከም ትዕግስቱ ስለተመናመነ ሃገርን ክፉ ችግር ውስጥ የሚከት፣ የመንን እና ሶሪያን የሚመስል የመንግስት እና የህዝብ አምባጓሮ ሊመጣ ይችላል፡፡ አብይ የተቻቸው ሁሉ የጠላቸው አድርገው የማሰባቸው ሁለተኛው ችግር ሰውየው የስነልቦና መረጋጋት እንዳይኖራቸውና የሃገሪቱን ችግር ሰከን ባለ ልቦና እንዳይፈቱ ያደርጋል፣ ለህዝብ የመስራት ተነሳሽነታቸውንም ይቀንሳል፣ በስነልቦና አለመረጋጋት እና ግራ መጋባት ውስጥም ሊከታቸው ይችላል፡፡ ይህም ሃገሪቱን ወደ ቀውስ ሊመራ የሚችል ነገር ነው፡፡ ይህ ደግሞ አሳሳቢ ነው፡፡በበኩሌ በብዙ ችግር ተቀስፋ የተያዘቸው ሃገሬ በከፍተኛ ጥንቃቄ መያዝ ያለባት ተሰባሪ እቃ እየመሰለችኝ ከመጣች ዋል አደር ብያለሁ፡፡አሁን የቀድሞዋ የምትባለው ይጎዝላቪያ ከመፈራረሷ አንድ አመት በፊት የመፍረስ ምልክት ያልነበረባት መሆኗን የሰማሁ ነኝና “እንዴትም አድርገን ብንይዛት ኢትዮጵያ አትፈራርስም” ከሚሉት ወገን አይደለሁም፡፡

ይልቅስ “ከአያያዝ ይቀደዳል” ባይ ነኝ! በተለይ የዘር ፖለቲካ የበላት ሃገር አትፈርስም ብሎ ከመተማመን ይልቅ ተቃራኒውን አስቦ አያያዙ ላይ ጠንክሮ መስራቱ የበለጠ ትርጉም ይሰጠኛል፡፡ አያያዙን ማሳመሩ የሁላችንም ሃላፊነት ቢሆንም መንግስትን የሚዘውሩት ዶ/ር አብይ ፖለቲካዊ እና ስነልቦናዊ አቋቋም ደግሞ ይበልጥ አስፈላጊ ይመስለኛል፡፡ አብይ በቋፍ ያለችውን ሃገሬን በመሃል እጃቸው ይዘው የቆሙ ሰው ይመስሉኛል፤ ሃገርን ያህክል ውድ ነገር እጃቸው ላይ ያስቀመጥንባቸውን ሰው በከንቱ ሊያስመርር ትችት ይዞ የሚመጣ አለመኖሩን ቢረዱ መልካም ነው፡፡ እንዲህ ያለ ሰው አይጠፋም ከተባለም ነገሩን ንቆ የተሻለ ነገር ወደመስራቱ ማዘንበሉ ይመረጣል፡፡

የጠሚው ስነ-ልቦናዊ ብርታት፣ የአስተሳሰብ ከፍታ፣ እንደሚያወሩት የይቅርታ ሰውነት፣ በሌላው ጫማ ገብቶ የማሰብ ነገር፣ ፖለቲካዊ ግንዛቤ እና ቁርጠኝነት፣ አለማዳላት፣ የሚናገሩትን ሆኖ መገኘት በሃገሬ ፖለቲካዊ እጣ ፋንታ ላይ የማይተካ ሚና ያለው እንደሆነ አስባለሁ፡፡ የተሳሳቱ ሲመስለኝ አካሄዳቸውን ብተችም ያሉበትን አስቸጋሪ ሁኔታም እረዳለሁ፡፡ በአንፃሩ ያሉበት አስቸጋሪ ሁኔታ የማይከለክላቸው ሊያደርጉ ሲገባ ያላደረጉት፣ አለማድረግ ሲገባቸው ያደረጉት ነገር እንዳለም ይሰማኛል፡፡ ባፈው አንድ አመት የኦሮሞ ብሄርተኞች በሚዲያቸውም ሆነ በጠመንጃቸው ያጠፉትን ጥፋት ሃይ አለማለታቸው ሊያደርጉ ሲገባ ያላደረጉት ነገር ነው ብየ አስባለሁ፡፡

የሚመሩት ፓርቲ ኦዴፓ ካድሬዎች የምስኪኖችን ቤት ያውም በክረምት እያፈረሱ ማባረራቸው እና እሳቸውም አልሰማሁም ማለታቸው ባያደርጉት ምንም የማይጎዳቸው ግን ወገባቸውን ታጥቀው የሰሩት ጥፋት ይመስለኛል፡፡ ይህን ከባድ ጥፋት በሪፖርታቸው በአብዛኛው ሳይነኩት ከነኩትም አድበስብሰውት አልፈዋል፡፡በሰፊው እያነጋጋረ ያለው የኦሮሞ ባለስልጣናት በርከት ብሎ መሾምን በተመለከተ ሳይጠየቁ ራሳቸው አንስተውት “ኦሮሞ ያለአግባብ፣ በማይገባው ሁኔታ ስልጣን ይዞ ከሆነ ከእኔ ጀምሮ ተጠያቂ እንደረግ” ብለዋል፡፡ መልሳቸው ሁለት ትርጉም አለው፡፡ አንደኛው ኦሮሞ በዛ ብሎ ተሹሞ ከሆነም የሚገባውን ቦታ ነው የያዘው አይነት ሲሆን ሁለተኛው ኦሮሞ በዝቷል እየተባለ የሚባለው ነገር ከነአካቴው ውሸት ነው የሚል አንድምታ አለው፡፡

አባባላቸው ኦሮሞ ብዙ ሆኖ መሾሙ ያለ አግባብ አይደለም ሲለሚገባው ነው የሚል ከሆነ የህወሃትን መጨረሻ እንዲያስቡ ከመምከር ውጭ ምንም የሚባል ነገር የለም፡፡ ኦሮሞ ስልጣን ላይ በርከት ብሎ ተሹሟል የሚለው ነገር እውነት አይደለም የሚሉ ከሆነም በንግድ ባንክ የተሰገሰጉት፣ በኢትዮጵያ ጉምሩክ ባለስልጣን ላይ የበዙት፣ በውትድርናው መስክም ቢሆን በስመ ምክትል ኢታማጆር ሹምነት ይዝ መምሪያዎችን ሁሉ ለጠቅልሎ መያዙን አየር ሃይሉን፣ የመከላከያ ሚኒስትርነቱን፣ የሃገር ውስጥ ደህንነቱን፣ የጠቅላይ አቃቤህግነቱን ኦሮሞ የያዘ መሆኑ እየታወቀ ይህ ምንም ችግር የለውም ብየ ስናገር መታመንን አገኛለሁ ብለው ከሆነ ይህ ከህዝብ የሚያርቅ እንጅ የሚያቀርብ ነገር አይደለም፡፡

ከሁሉም በላይ የአዲስ አበባ ከንቲባ የሆኑትን አቶ ታከለ ዑማን የሾሙበት መንገድ ኦሮሞን ያለ አግባብ የመሾሙ ምልክት አይደለም ተብሎ ከሆነ የነገውን መፍራት ሊኖርብን ነው፡፡ በመንግስታዊ መዋቅሩ ላይ የኦሮሞ ባለስልጣናት በርከት ብለው ከመታየታቸው ባሻገር በመደበኛው የመንግስት መዋቅር ላይ ምንም ስልጣን የሌላቸው እንደ ጃዋር ያሉ ኦሮሞዎች ሁሉን ማድረግ እንደሚችሉ የሚናገሩት፣ የባሰባቸው ደግሞ በቪዲዮ ምስላቸውን እያሳዩ የሰው ህይወት እንሚያጠፉ የሚዝቱት እና ደግሞ ምንም የማይደረጉት፣ወደ ሃያ የሚጠጉ በንኮችን የዘረፈው የኦሮሞ ድርጅት ምንም አለመባሉ ኦሮሞ ያለ አግባብ መብት እያገኘ ስላልሆነ ከሆነ ትርጉሙ ምን ሊሆን ይችላል?

የህገ-መንግስት መሻሻልን በተመለከተ የተነሳውን ጥያቄ የመለሱበት መንገድ አንድም ቅንነት በጎደለው ሁለትም የችግሩን አንገብጋቢነት በማይመጥን መልኩ የተመለሰ ሆኖ አግኝቸዋለሁ፡፡ ጠ/ሚ አብይ መልሳቸውን የጀመሩት “ህገ-መንግስቱ አይወክለንም የሚሉ ሰዎች ህገ-መንግስቱ ከሚሰጣቸው መብት መጠቀማቸውን አልተውም” በሚል ንግግር ነው፡፡ በመጀመሪያ ህገ-መንግስትም ሆነ ሌላ ህግ እንዲቀየርለት የሚጠይቅ አካል ጥያቄው ተሰምቶ ህጉ እስኪቀየር ድረስ ባለው ህግ የመገዛት ግዴታ አለበት፡፡ የማይፈልጉትን ህገ-መንግስት አክብረው መብቱንም የሚጠቀሙ ግዴታውንም የሚያደርጉ ሰዎች ሊመሰገኑ እንጅ ሊወቀሱ አይገባም፡፡ አብይም መብትን ይጠቀማሉ ብለው ከሰሷቸው እንጅ ጠያቂዎቹ ህገመንግስቱ የጣለባቸውን ግዴታም እየተወጡ ነው፡፡

ሁለተኛው እና ዋናው ነገር ህገመንግስቱ እንዲቀየር የሚጠይቁ ሰዎች ህገ-መንግሰቱ ሲረቀቅ አብረው ያላረቀቁ፣ ባልተስማሙበት ህግ እንዲገዙ የተፈረደባቸው የዘር ፖለቲካው ባይትዋሮች ናቸው፡፡ እነዚህ አካላት አብይ እንደሚያስቡት የአማራ ክልል ነዋሪዎች ብቻ አይደሉም፡፡ ይልቅስ ከአማራ ክልል ህዝብ በተጨማሪ ህገ-መንግስቱ የማያውቃቸው የኢትዮጵያ የከተማ ነዋሪዎች በአብዛኛው፣ ከሁለት እና በላይ ብሄሮች የሚወለዱ ሰዎች በአጠቃላይ ናቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች ባልተስማሙበት ህግ ይገዙ ዘንድ የሚጣልባቸው ዕዳ ከየት እንደመጣ ህገ-‘መንግስቱ ጫፉ አይነካ’ የሚሉ አካላት እንዲያስረዷቸው ሁኔታዎችን ማመቻቸት የአብይ መንግስት ሃላፊነት ነው፡፡

በተረፈ ‘ህገ-መንግስቱ እኔን እና ቤቴን ስለሚያረካ አናንተ እና ቤታችሁ እኛ ባወጣነው ህገ-መንግስት ትገዙ ዘንድ የተገባ ነው’ የሚሉ አካላትን እና ከህገ-መንግስቱ አንቀፆች ውስጥ በአንዱ ንዑስ አንቀፅ ውስጥ እንኳን ፍላጎታቸውን እንዳያካትቱ የተፈረደባቸውን ዜጎች እኩል “ዋልታ ረገጥ” ብሎ መሰየም ቅንነት አይደለም፤ሚዛንንም ሰባራ ያደርጋል፡፡ ከሰሞኑ የሞት አጀብ አስከትሎ የመጣውን ፖለቲካዊ ቀውስ አስመልክቶ የተነሳውን ጥያቄ ሲመልሱ ጠ/ሚው ስሜታዊነታቸው በርትቶ፣ እርግማናቸው በዝቶ አንድ ወገንን መልኣክ ሌላውን ሰይጣን የማድረግ መዛመም ታይቶባቸዋል፡፡ \

ወደ መልዓክት ወገን ሊያስጠጓቸው የከጀላቸውን፣ በስም የጠሯቸውን ሟቾች (ዶ/ር አምባቸው እና ጀነራል ሰዓረን) የገደለውን አካል እስከመግደል ያደረሰውን ምክንያት ሁሉ በፓርላማ ውሏቸው እንዲነግሩን አይጠበቅባቸውም፡፡ ሆኖም ቢያንስ ገዳዮቹን ለዚህ እርምጃ ያበቃቸው አብይ የሚሉት ክፋት፣ እርኩስነት፣ ፍልቅልቅ ሰው ላይ የመጨከን እርኩሰት፣ ያጎረሰ እጅን የመንከስ ውለታ ቢስነት ብቻ እንደማይሆን አውቆ ላልተኛ ሁሉ የሚሰወር ነገር አይደለም፡፡ በአዴፓ መሪዎች መሃል ለተከሰተው መጋደል የፌደራል መንግስቱ እጅ የለበትም ማለትም የኢህአዴግን የፓርቲ ባህል አለማወቅ ነው፡፡

በተለይ አሁን አዴፓ ሆኛለሁ ያለው ብአዴን ለንጉስ የማጎንበስን የረዥም ዘመን ታሪክን ለሚያውቅ የገዳይ እውነት አብይ ከሚሉት እጅግ የተለየ ሌላ ሊሆን እንሚችል፤ ፅድቃቸው በፌደራል መንግስት በጣም የተወራላቸው ሟቾችም መታዘዛቸው ፅድቅ ሆኖ የተቆጠረላቸው ሊሆኑ እንደሚችሉ መጠርጠር አይከፋም፡፡ በተረፈ ገዳይ ተብሎ የተብጠለጠለው ቡድንም የራሱ ቤተሰብ፣ደጋፊ ያለው ለሃገርም ይበጃል ያለውን ሊሰራ የሞከረ በመሆኑ ቢያንስ ቀብሩ መዘገብ እንደነበረበት ለፍቅር እና ይቅርታ ሰባኪው ጠ/ሚ አብይ ማሳሰብ እወዳለሁ፡፡

በአንፃሩ በዓብይ መንግስት ድርጎ የሚሰፈርላቸው የሃገር ውስጥ ሚዲያዎችም ሆኑ የአብይ መንግስት ፍቅር ያነሆለላቸው ወዶ ገባ የባሕር ማዶ ሚዲያዎች አስር ሰኮንድ ወስደው አብይ አምርረው የጠሏቸውን የብርጋዴር ጀነራል አሳምነው ፅጌን ቀብር መዘገብ አልፈለጉም፡፡ ይህ የመረረ ጥላቻ አብይንም ሆነ ለአብይ መንግስት የሚያሸበሽቡ ሚዲያዎችን ትዝብት ላይ የሚጥል ብቻ ሳይሆን በፖለቲካዊ ድራማው ላይ ግድያውን የጀመረው ማን ነው? በዚህ ውስጥ የፌደራሉ መንግስት እጅስ የለበትም ወይ? የሚለውን ጥያቄ ያጠናክራል፡፡

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 6 years ago on July 3, 2019
  • By:
  • Last Modified: July 3, 2019 @ 11:44 am
  • Filed Under: Ethiopia

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar