በንጉሥ ተክለ ሃይማኖት ቤተ መንግሥት ውስጥ የተለያዩ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ሲገለገሉ መቆየታቸውን ተከትሎ ቅርሱ የተለያየ ጉዳት ስለደረሰበት የመፍትሄ እርምጃዎች መወሰድ ተጀመሩ። ከኹለት ዓመታት በፊት የምሥራቅ ጎጃም ዞን አስተዳዳሪዎች በቤተ መንግሥቱ ውስጥ ሲኖሩ የነበሩ ሲሆን ለዕድሳት በሚል እንዲወጡ የተደረገ ቢሆንም፣ በቅርሱ ውስጥ ሌሎች የመንግሥት ቢሮዎች እስካሁን እየተገለገሉበት ይገኛል።
ንጉሱ ባሠሩት የግብር አዳራሽ ውስጥ አገልግሎት ሲሰጡ የነበሩት የስብሰባ አዳራሽ፣ የጎጃም የባሕል ቡድን መለማማጃ፣ የምሥራቅ ጎጃም ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት፣ ፖሊስ መምሪያ፣ ዐቃቤ ሕግና ሌሎች ቢሮዎች በመገልገል ላይ ናቸው። የምሥራቅ ጎጃም ዞን አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ኀላፊ የኔነው ኹነኛው ለአዲስ ማለዳ እንዳስታወቁት ከሆነ፣ እነዚህ መገልገያ ቢሮዎች እንዲለቀቁ የታዘዘ ሲሆን፣ ከኹለት ዓመታት ጀምሮ ይደረጋል የተባለው ዕድሳት በተለያዩ ምክንቶች ሳይደረግ ቆይቷል።
“ከሩቅ አገር የንጉሥ ተክለ ሃይማኖትን ቤተ መንግሥት ለመጎብኘት የሚመጡ ሰዎች ቢሮ እንጂ የተከበረ ቤተ መንግሥት ሳያገኙ አዝነው ይመለሳሉ” ሲሉ የሄነው ተናግረዋል። የዞኑ ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮም እንግዶች ሲሔዱ የነበረውን ታሪክ በቃል ከማስረዳት በዘለለ ቤተ መንግሥቱን ለማሳደስ የሔደበት ርቀት ደካማ እንደሆነ የዞኑ ባሕል እና ቱሪዝም የመዳረሻ ልማት ባለሙያ መስከረም ፈንታ ይናገራሉ። “የቤተ መንግሥቱ ቅጥር ግቢ ለክብሩ እና ለታሪኩ የሚመጥን ሥራ አልተሰራለትም” ሲሉም አክለዋል።
የንጉሥ ተክለ ሃይማኖት የልጅ ልጆች በቤተ መንግሥቱ ቅጥር ግቢ ውስጥ ከመኖር በዘለለ ታሪኩን መጠበቅ እንዳልቻሉ የሚያወሱት መስከረም፣ ቤተ መንግሥቱን የዞኑ አስተዳደር እድሳት እንደሚደረግለት ቃል ገብቶ እንደነበርም ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። ረጅም ዕድሜ ያስቆጠረውን ቤተ መንግሥት ታሪካዊ መልኩን እና ይዘቱን ሳይለቅ ለማሳደስ ሥራዎች እንደተጀመሩ ያስታወቁት የኔነህ በበኩላቸው፥ ቤተ መንግሥቱን ለማደስ በተደረገው የመጀመሪያ ዙር ጥናት 22 ሚሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ ለክልሉ ምክር ቤት ማሳወቃቸውን ገልጸዋል።
የኔነው ፍርድ ቤት፣ ፖሊስ ጣቢያ እና ዐቃቢ ሕግ በቀጣይ ዓመት ቤተ መንግሥቱን ለቅቀው አዲስ ወደ ተሠራላቸው ቢሮ እንደሚሔዱ ሲናገሩ ሌሎች ቢሮዎች ግን መቼ እንደሚለቁ የታወቀ ነገር እንደሌለ ተናግረዋል።
ቤተ መንግሥቱን አድሶ የጎጃምን ባሕል እና ወግ የሚገልፁ ቅርሶችን እና በቤተ መንግሥቱ የነበሩ የቀደሙ ገዢዎች
ያስቀመጧቸውን ታሪካዊ ቅርሶች በአንድ ላይ አድርጎ ሙዚዬም ለማድረግ እንደታሰበ የኔነው ተናግረዋል። የደብረ
ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ጊዜያዊ እድሳት ለማድረግ ከባለሙያዎች ጋር ለመምከር ቀጠሮ መያዙንም አክለው ገልጸዋል።
Average Rating