www.maledatimes.com ፖሊስ ላይ ቅጣት የጣሉት ዳኛ ጥቃት ደረሰባቸው - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

ፖሊስ ላይ ቅጣት የጣሉት ዳኛ ጥቃት ደረሰባቸው

By   /   September 26, 2019  /   Comments Off on ፖሊስ ላይ ቅጣት የጣሉት ዳኛ ጥቃት ደረሰባቸው

    Print       Email
0 0
Read Time:3 Minute, 54 Second

ተከታታይ ጊዜ የሰጡትን ትዕዛዝ ባለመፈፀም እና ችሎቱን በመድፈር አንድ የፖሊስ አባል ላይ የሰጡትን ፍርድ ተከትሎ፣ ዳኛውን ለማሰር ሙከራ የተደረገ ሲሆን ዳኛው በተፈጠረባቸው የደኅንነት ስጋት ከተማውን ለቀው እንዲወጡ ተደረገ። በፍትኀ ብሔር ክርክር መዝገብ ተከሳሽ የሆኑትን አስናቀ አባተን ይዘው እንዲያቀርቡ ስምንት ተከታታይ ትዕዛዝ የተሰጣቸው ምክትል መርማሪ ብርሃኑ እንቁ ማርያም፣ ትዕዛዙን ያልፈፀሙ ሲሆን በችሎት ቀርበውም ምክንያታቸውን ለማስረዳት ፈቃደኛ አልነበሩም።

ለመጨረሻ ጊዜ የተሰጠውን ትዕዛዝ ተከትሎ ወደ ችሎት የቀረቡት ብርሃኑ ሳይፈቀድላቸው ወደ ችሎት ገብተዋል የሚሉት ዳኛው አቤሴሎም ‹‹ተከሳሹን ለማቅረብ የተሰጠኝ ግዜ በቂ አይደለም›› በማለት ፖሊሱ ችሎቱን መጠየቃቸውን እና ችሎቱም ጥያቄአቸውን ውድቅ በማድረግ ትዕዛዙን አንዲፈፅሙ ያዝዛል።

የችሎቱን አስተያየት ወደጎን በማለትም ‹‹እንድታውቀው ብዬ እንጂ ትዕዛዙ አይፈፀምም›› በማለት የፍርድ ቤቱን ክብር በመግፋት ከችሎት ወጥው ሄደዋል የተባሉት ፖሊሱ፣ ችሎቱ ፀሐፊ በመላክ እንዲመለሱ ቢጠይቃቸውም ሳይመለሱ ቀርተዋል። ‹‹ምንም እንኳን ያደረጉት ድርጊት በወንጀል ሕጉ እስከ ስድስት ወር ቢያስቀጣም ችሎቱ የአንድ ወር እስር እና ስድስት መቶ ብር ቅጣት ጥሎባቸዋል›› ሲሉ አቤሴሎም ተናግረዋል።

‹‹በእለቱ ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ላይ ተከሳሽን ይዘው እንዲቀርቡ የተሰጣቸውንም ትዕዛዝ ሳይፈፅሙ ቀርተዋል።” ብለዋል። ትዕዛዙን ሌላ የፖሊስ ባልደረባ እንዲፈጽሙ ትዕዛዝ የተሰጣቸው ሲሆን ‹‹በሦስት ሰዓታት ውስጥ አፈፅማለሁ›› ባሉት መሰረት የአፈፃፀም ተከሳሽን አስረው ማቅረብ ችለዋል›› ያሉት አቤሴሎም፤ ‹‹ችሎቱ በብርሃኑ ላይ ያለውን መሰረታዊ ችግር ከተረዳባቸው ምክንያቶችም መካከል እርሳቸው በስምንት ቀጠሮ ያልፈፀሙትን ትዕዛዝ ባልደረባቸው በሦስት ሰዓት መፈፀማቸው ነው፡፡›› ሲሉ አክለዋል።

መርማሪ ፖሊስ የሆኑት ብርሃኑ ተይዘው ከቀረቡ በኋላ ፍርድ ቤቱ ውሳኔውን ያነበበላቸው ሲሆን፣ ከደቂቃዎች በኋላም አንድ አቃቤ ሕግ ወደ ችሎቱ በመግባት ዳኛው ሊታሰሩ እንደሆነ ይገልፁላቸዋል። የወረዳው የፖሊስ ኃላፊ ዋና ኢንስፔክተር ሀሰን እንድሪስ ‹‹ይሄ ዳኛ አስሮ ሊጨርሰን ነው፣ የተፈረደበት ፖሊስም አይታሰርም›› በማለት ለአቃቤ ሕጉ በመግለፅ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ በመፃረር ችሎቱንም ብዙ ቁጥር ባላቸው ፖሊሶች ወዲያውኑ አስከብበዋል።

አቃቤ ሕጉም ለሀሰን ይግባኝ ማለት እንደሚችሉ ቢገልፁላቸውም፣ በእንቢተኝነት ሊያስሩኝ ኃይል አሰማርተዋል ሲሉ አቤሴሎም ይናገራሉ። በእለቱ ዳኛው ከችሎት ሳይወጡ እንዲቆዩ የተደረገ ሲሆን የወረዳው የፍትህ ቢሮ ኃላፊ አታላይ ይዘልቃል እና የወረዳው ተወካይ ዓለም ታደሰ እንዲሁም የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፖርቲ አመራሮች ወደ ችሎት በመግባት ዳኛውን ማነጋገርም ይጀምራሉ።

በውሳኔው ላይ ቅሬታ እንደሌላቸው በመግለፅ ነገር ግን የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት ከፍተኛ ጥረት ማድረጋቸውን እና ዳኛውም ይህንን በመረዳት ሀሰን ለምን ሊያስሯቸው ትዕዛዝ እንደሰጡ እና የተፈረደባቸውም ፖሊስ እንዳይታሰሩ እንዳደረጉ በችሎት ቀርበው ካስረዱ ችግሩን መፍታት እንደሚሞክሩ ይናገራሉ። ‹‹በሕግ ፊት ሁሉም ሰው እኩል ነው፣ ፖሊስ አይቀጣም የምትሉ ከሆነ ግን ይህ አግባብ አይደለም ብዬ አስረድቻቸው እነሱም ሀሰንን ለማነጋገር ስብሰባ ተቀመጡ፣ እኔም ደኅንነቴ አስጊ ሁኔታ ውስጥ እንደገባ ከሰብሳቢ ዳኛው ፍጹም የኔዓለም ተነግሮኝ እዛው ችሎት ውስጥ እንድቆይ ተደረኩ›› ሲሉ አቤሴሎም ይናገራሉ።

‹‹ልዩ ኃይል ወደ ፍርድ ቤቱ ተልኮ ጉዳዩን እንዲያረጋጉ ትዕዛዝ ቢሰጣቸውም የልዩ ኀይል ኀላፊው ግን ምንም እርምጃ ሳይወስዱ ቀሩ።›› ጉዳዩ በበላይ ኀላፊዎች ተሰምቶ በድጋሚ ትዕዛዝ ስለተሰጠ በልዩ ኀይል ታጅበው ወደ መኖሪያ ቤታቸው ከሰዓት ሰባት ሰዓት አካባቢ እንዲገቡ ተደረገ። ዳኛው በማህበራዊ ገፆቻቸው የደረሰባቸውን ጥቃት ካጋሩ በኋላ ጉዳዩ ወደ ክልል የሥራ ኀላፊዎች በመድረሱ ከ 24 ሰዓታት ቆይታ በኋላ ከመኖሪያ ግቢአቸው እንዲሁም ከከተማው እንዲወጡ መደረጉን ይናገራሉ።

በዚህ ሃሳብ የማይስማሙት ሀሰንም ወደ ችሎት ቀርበው መልስ ያልሰጡበት ምክንያት የስድስት ወር እስር ቅጣት እንደተጣለባቸው እና ዳኛውም እንዲቀርቡ ያዘዙበት ምክንያት ፍርዱን ለማንበብ በመሆኑ እንደሆነ ይናገራሉ። ‹‹የአንድ ሰው መታሰር ማለት ምንም ማለት አይደለም፣ ነገር ግን እኔ ብታሰር ከኔ ስር ያሉት አባላትን ወደ ቁጣ ይከታል ብዬ በማሰብ ወደ ችሎት ሳልቀርብ ቀርቻለሁ›› ሲሉ ተናግረዋል።

‹‹በስልክ እንድንነጋገር ለዳኛው ጥያቄ ባቀርብላቸውም እሳቸው ግን ፈቃደኛ አልነበሩም።›› ብለዋል። የተፈረደባቸው ፖሊስ ብርሃኑም የእስር ጊዜአቸውን ከመፈፀም ይልቅ በካቢኔ ስብሰባዎች ላይ እየተሳተፉ እንደሆነ እና የእስር ጊዜአቸውን እየፈጸሙ እንዳልሆነም በአካባቢው ያሉ ሰዎች ይናገራሉ። በብርሃኑ ላይ የተላለፈው የቅጣት ትዕዛዝ ባለመውጣቱ በተመሳሳይም በታች አርማጨሆ ጣቁሳ ወይም ደልጊ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የወረዳ ፍርድ ቤት ዳኛ የሆኑት ደሳለኝ የኔአካል ነሐሴ 2011 ተመሳሳይ ድርጊት ተፈፅሞ እንደነበር ይናገራሉ።

አምሳሉ ተገኝ የተባሉ አቃቤ ህግ በኹለት እስረኞች ላይ በፖሊስ ድብደባ መፈፀሙን ተከትሎ ምርመራ እንዲጀመር ባቀረቡት ጥያቄ ምክንያት የተለያዩ ምክንያቶች እየተፈለጉ እንዲታሰሩ ለማድረግ ሲሞከር እንደነበር ይናገራሉ። ‹‹መከላከለያ፣ ልዩ ኀይል እንዲሁም ፖሊስ ሰው አስሮ ያቆያል፣ ከዛም ምርመራውም ሳይጀመር ሰዎቹም ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ረጅም ጊዜ ታስረው ሲቆዩ እንዲፈቱ ትዕዛዝ በመስጠታቸው ፖሊስ ሊያስራቸው ቢሞክርም በኀላፊዎች ትዕዛዝ ግን ሳይታሰሩ ቀርተዋል›› ሲሉ ይናገራሉ።

በህዳር 2011 ሔኖስ ላቀ የተባሉ የወረዳው ዳኛ የዳልጊ መዘጋጃ ቤት 18 ሺሕ ብር ካሳ እንዲከፍል ትዕዛዝ ቢሰጡም ኀላፊው ለ6 ተከታታይ ቀጠሮ ሳይቀርቡ ይቀራሉ። ዳኛው ኀላፊው ታስረው እንዲቀርቡ ትዕዛዝ የሰጡ ሲሆን ትዕዛዙን በተደጋጋሚ ባለመፈፀማቸውም የአንድ ወር የእስር ቅጣት ይጣልባቸዋል። በዚህ የተበሳጩት የማዘጋጃ ቤቱ ኀላፊም ወጣቶችን በማደራጀት ወደ ችሎት እንደላኩ አዲስ ማለዳ በፍርድ ቤቱ ካሉ ምንጮቿ ተረድታለች። በአጋጣሚም ዳኛው ከችሎት ወጥተው ስልክ እያወሩ ከወጣቶቹ ጋር ባይገናኙም በችሎት የነበሩ አቃቤአነ ሕግ እና የፍርድ ቤቱ ሠራተኞች ጉዳዩን ለወጣቶቹ በማስረዳት እና በማረጋጋት ጉዳት እንዳይደርስ ለማድረግ ችለዋል።

ዳኛውም መኪና ተልኮላቸው ከፍርድ ቤቱ የወጡ ሲሆን ለደኅንነታቸው አስጊ በመሆኑም ወደ ቋራ ተቀይረው እንደሔዱ ለማረጋገጥ ተችሏል። በተመሳሳይም በደቡብ ጎንደር ደራ ወረዳ በሚገኙ አካባቢዎች ተመሳሳይ ጥቃቶች በዳኞች ላይ ደርሰው እንደነበረም አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ዳኞች ይናገራሉ። በሻሁራ ወረዳ በወንጀል የተከሰሰ የፖሊስ አባል በእስር እንዲቀጣ የወሰኑ ዳኛ በሁለት ፖሊሶች መኖሪያ ቤታቸው በጥይት መደብደቡን ከአካባቢው ያገኘነው መረጃ ያሳያል።

‹‹ከ2009 ጀምሮ በየእለቱ ጠዋት ከቤቴ ስወጣ ልታስር እንደምችል በማሰብ አለባበሴን አስተካክዬ ነው የምወጠው›› የሚሉት ደሳለኝ የኔአካል፣ የሕግ አስፈፃሚው ጫና ከመሻሻል ይልቅ እንደበረታ ይናገራሉ። የደሳለኝን አስተያየት የሚጋሩት አቤሴሎም ‹‹በፍትህ አካላት ላይ እየደረሰ ያለው ጫና ተስፋ የሚያስቆርጥ ቢሆንም የአብዛኛው ግፍ ቀማሽ የሆነው ማህበረሰቡ ግን ይበልጥ ያሳዝነናል›› ሲሉም ይናገራሉ።

ምንጭ ከአዲስ አበባ ሚዲያዎች

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 5 years ago on September 26, 2019
  • By:
  • Last Modified: September 26, 2019 @ 8:36 am
  • Filed Under: Ethiopia

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar