HAMESA LOMI·FRIDAY, OCTOBER 11, 2019·ግልጽ ደብዳቤ ለኢትዮጵያ መንግስት በሊባኖስ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን አስከሬኖችን ወደ አገር ቤት መላክ ደከመን በሊባኖስ ለምንገኝ ኢትዮጵያውያን ሰራተኞች ሞትና ስቃያችን እንዲቆም አፋጣኝ የሆነ እርምጃ እንዲወሰድልን እንፈልጋለን። ለኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስቴር ጥቅምት 2012 ይህንን ደብዳቤ የምንጽፍልዎ በአገረ ሊባኖስ ከቀን ወደቀን እየተቀጠፈ ያለው የኢትዮጵያውያኖች ውድ ሕይወት እና እየደረሰባቸው ያለው ግፍ እና መከራ ባስችኳይ ይቆም ዘንድ የበኩሎትን ጥረት እንዲያደርጉ ጥሪ ለማስተላለፍ ነው።
እስካሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ በኢትዮጵያውያኖች ላይ እየደረሰ ባለውን ግፍ እና ሰቆቃ በይገባኛል ስሜት አገርን ወክሎ በመንቀሳቀስ ረገድ በሊባኖስ ያለው የኢትዮጵያ ቆንስላ ሙሉ ሃላፊነትም ሆነ ግዴታ ቢኖረውም፤ እውነታው ግን ፍጹም ከዚህ የራቀ ነው። በመሆኑም ክቡርነትዎ በሊባኖስ ያለው የኢትዮጵያውያኖች ህይወት ምን እንደሚመስል እና ምን መደረግ እንዳለበት በገባን እና በተረዳነው መሰረት ከዚህ እንደሚከተለው አቅርበነዋል።የኢትዮጵያኖች ኑሮ በሊባኖስ ባለፈው የፈረንጆች አመት ከሊባኖስ የሰራተኞች ሚኒስቴር ባወጣው ዳታ መሰረት 269,643 የውጭ ሃገር ዜጎች በሊባኖስ እንደሚኖሩ ተገልጧል። ከላይ ከተጠቀሰው አሐዝ ውስጥ 161,311 ደግሞ ኢትዮጵያውያኖች ናቸው።
ይህ ከላይ የተጠቀሰው የኢትዮጵያውያኖች አሐዝ በሊባኖስ በህጋዊ መንገድ ለመስራት በመንግስት ተመዝግበው ያሉ ሲሆኑ በእኛ እምነት ቢያንስ ከአንድ መቶ ሺህ(100000) የሚበልጡ ኢትዮጵያውያኖች በተለያዩ ምክንያት በህጋዊ መንገድ ተመዝግበው መንቀሳቀስ የማይችሉ እንዳሉ እንገምታለን።እንደሚታወቀው ማንኛውም በሊባኖስ ሃገር ውስጥ ተቀጥሮ የሚሰራ የውጭ ሃገር ዜጋ የሚተዳደረው ከፋላ ተብሎ በሚታወቀው ስርዐት ነው። ይህንን ከፋላ የሚባለውን ስርዐት ደግሞ በተቀዳሚነት የሚቆጣጠረው የሊባኖስ መንግስት ሲሆን የሰራተኛ አስቀጣሪ ደላሎች ተጽእኖም በጣም ከፍ ያለ ድርሻ አለው። በዚህ የሰራተኛ አስቀጣሪነት ድለላ መስክ ተሰማርተው የሚሰሩ ደላሎች የተውጣጡት ከተለያዩ ሃገራት ሲሆን ኢትዮጵያም አንዷ ነች።
የእነዚህ ደላሎች ዋና አላማ በሊባኖስ ሃገር ተሰድደው ለመስራት ከሚፈልጉ እህቶታችንን ላይ የሚሰበስቡትን ገንዘብ ብቻ ማካበት ሲሆን ከዛ ባለፈ ሊፈጠር የሚችለውን የእህቶቻችንን ስቃይ እና እንግልት የማሰብም ሆነ የመመልከት የኢትዮጵያዊነት ሞራሉም ሆነ ግዴታው የላቸውም።በሊባኖስ ሁሉም ስደተኛ ሰራተኞች ባለው የሰራተኞች ህግ ተጠቃሚ ካለመሆናቸው የተነሳ ምንም አይነት ህጋዊ መብታቸውን ለምሳሌ በሃገሪቱ ያለውን ዝቅተኛ ደሞዝ መጠን የመጠየቅ ፣ በሃገሪቱ ያለውን መደበኛ የስራ ሰአት መጠን የመጠየቅ ወይንም የእረፍት ቀናቶችን የመጠየቅ ምንም አይነት መብቱ የላቸውም። እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ መንግስት እና የሊባኖስ መንግስት በሚስጥር የሁለትዮሽ ስምምነት ለማድረግ በመወያየት ላይ ናቸው።
የዚህም የውይይት አጀንዳ እና ይዘት እስካሁን በሊባኖስ ለምንገኝ ኢትዮጵያውያኖች ግልጥ ባለመደረጉ እና የእኛንም ግብኣት ያላካተተ በመሆኑ በአሁኑ ሰአት በኢትዮጵያውያን ዜጎች ላይ እየደረሰ ያለውን ግፍ እና በደል ያሻሽለዋል ወይንም ይቀርፈዋል ብለን አንገምትም።በፈረንጆቹ 2016 በአለም አቀፍ ሰራተኞች ድርጅት( ILO) ከሊባኖስ አሰሪዎች ዘንድ በተሰበሰበው መረጃ መሰረት 94.3% የሚሆኑት ሰራተኞቹን የመጓጓዣ ወረቀት ወይንም ፓስፖርት አሰሪዎቹ እንደያዙት ወይንም ሰራተኞቹ ሊያገኙት በማይችሉበት ስፍራ ያስቀመጡት ሲሆን ከዚህም ውስጥ 73.8% የሚሆኑት ሰራተኞች ለስራ የተዋዋሉበት ውል እንደሌላቸው (እንዳልተሰጣቸው) እና ቢሰጣቸውም አብዛኛውን ግዜ ውሉ ተዘጋጅቶ የሚቀርበው በቋንቋቸው እንዳልሆነ ተጠቅሷል። ጥናቱም የደሞዝ ክፍያን በተመለከተ ባወጣው መረጃ መሰረት 40% የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በአማካኝ በወር ሁለት መቶ የአሜሪካን ዶላር በታች የሚከፋላቸው ሲሆን፣ በአንጻሩ የፊሊፒንስ፣ ሲሪላንካ እና ኔፓል የሚመጡ ሰራተኞች ከላይ ከተጠቀሰው የወር ክፍያ በላይ እንደሚከፈላቸው አሳይቷል።
የስራ ሰአትንም በተመለከተ ጥናቱ እንዳሳየው 57.3% የሚጠጉት ሰራተኞች በሳምንት ሰባት ቀን የሚሰሩ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 36% የሚጠጉ ኢትዮጵያውያኖች በቤት ወስጥ ተዘግቶባቸው እንደሚያገለግሉ አሳይቷል። በነገራችን ላይ ይህ ጥናት ምንጩ አሰሪዎች ሆነው እንጂ ጥናቱ ሰራተኞችን ያካተተ ቢሆን የጥናቱ ውጤት ምን ሊሆን እንደሚችል መገመት አያዳግትም። ምክንያቱም ከራሳችን ልምድ ብቻ ተነስተን ብናትት አካላዊ ጥቃትን ጨምሮ መደፈር መራብ እና ደሞዝ መከልከል አልያም ክፍያ ማዘግየት የኢትዮጵያውያን ሰራተኞች የቀን ተቀን ህይወታቸው እንደሆነ እናውቃለን።ይህ በእንዲህ እንዳለ በሊባኖስ የምንኖር ኢትዮጵያውያን ሰራተኞች በሃገራችን ኢኮኖሚ ላይ ቀላል የማይባል አስተዋጽኦ እያደረግን እንገኛለን።
ለምሳሌ ያክለ ለመጥቀስ ቢያስፈልግ ለታላቁ ግድብ ማስገንቢያ የኢትዮጵያ መንግስት ለመላው ኢትዮጵያውያኖች ያስተላለፈውን ጥሪ ተከትሎ በሊባኖስ የምንኖር ኢትዮጵያውያኖች ከ7.3 የአሜሪካን ዶላር በላይ ማዋጣታችን ይታወቃል. ከዚህም በዘለለ በአግሪቱ የወጪ ምንዛሬ ላይም ይህ ነው የማይባል አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ እንገኛለን። እንደሚታወቀው ከላይ የተጠቀሰውን ገንዘብ ለማፍራት በሊባኖስ የምንኖር ኢትዮጵያውያኖች እጅግ ታላቅ መስዋዕትነትን እየከፈልን መሆኑ ሊዘነጋ አይገባም።
እንደ IRIN የ2017ቱ ሪፖርት ከሆነ በሊባኖስ በሚሰሩ የውጭ ሃገር ዜጎች ላይ ከሚደርሰው አካላዊ እና መንፋሳዊ ጥቃት ባለፈ በየሳምንቱ ሁለት ሰራተኞች ህይወታቸውን ያጣሉ። ህይወታቸውን ከሚያጡት ሰራተኞች መካከልም አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያኖች እንደሆኑ ያሳያል። የሕይወት ማጣታቸውም መንስኤ በአብዛኛው በአሰሪዎቻቸው በሚደርስባቸው አሰቃቂ ተግባር ምክንያት አራሳቸውን በማጥፋት እና ከዚህም አሰቃቂ ህይወት ለማምለጥ በሚደረግ ግብግብ ነው።ከላይ የተጠቀሰው አሐዝ በ2018 የሰውልጆች መብት ተሟጋች ድርጅት ያወጣውን አሐዝ በእጥፍ የሚበልጥ ነው( አንድ ሰው በሳምንት). በነገራችን ላይ ይሄ ጉዳይ በሊባኖስ አልያም በኢትዮጵያ መንግስት ቢመረመር አልያም ቢጠና ቁጥሩ ፍጹም አስፈሪ እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለንም። ለዚህም እንደማረጋገጫ ይጥቅመን ዘንድ በ2019 ብቻ ህይወታቸውን ያጡ ኢትዮጵያኖች ቁጥር መመልከት በቂ ነው። ባሳለፍናቸው ሰባት ወር ከግማሽ ውስጥ ብቻ 34 ኢትዮጵያውያኖች ሕይወታቸውን አጥተዋል።
ስለሆነም ይህ ዘግናኝ ሁኔታ ይቆም ዘንድ በሊባኖስ የኢትዮጵያ ቆንስላ አፋጣኝ ለውጥ እንደሚያስፈልገው ይሰማናል። ላለፉት አስር አመታት በሊባኖስ ያለውን የኢትዮጵያ ቆንስላ ስንመለከተው በትልቁ ጎልቶ የሚታየው የዜጎች ህመም የማይታየው በሚሰጠው መረጃ ፍጹም የማይታመን፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ ዜጎች እንግልት እና ስቃይ በሚደርስባቸው ግዜ የድረሱልን ጥሪ ሲያስተላልፉ ምንም እንዳልሰማ በመምሰል ጆሮ ዳባ ልበስ ብሎ በዜጎች ስቃይ የሚያላግጥ እንደሆነ ነው።በቆንስላውም ውስጥ የሚገኙት ሰራተኞች ያልተማሩ ወይም የዜጎችን መብት በማስከበር ረገድ ምንም እውቀት የሌላቸው እና ሙሰኞች ናቸው።
በተደጋጋሚ አቤቱታ ይዞ የመጣን ዜጋ መፍትሄ ከማፈላለግ ይልቅ ማመናጨቅ እና በሊባኖስ አሰሪዎቻቸው ጎን በመቆም ዜጎችን እያስመረሩ እና ከአሰቃዮች ጎን እየቆሙ የገኛሉ። ይህንንም የምንለው እንደው በጭፍን ጥላቻ ተነሳስተን ሳይሆን በመረጃ ላይ ተደግፈን መሆኑን ለመግለጽ እንወዳለን። ለማሳሌ ያክል በቆንስላው ወስጥ የሚሰራ ኢትዮጵያዊ ከሊባኖስ አሰሪ ጋር በመመሳጥረ የሰራችበትን ደሞዝ ሳትቀበል ያለ እውቀቷ ወደ አገር እንድትባረር የተደረገች ኢትዮጵያዊት አለች። ከዚህም ባለፈ ቆንስላው ወጥና ግልጽ የሆነ የህግ ጠለላን የማረጋገጥ ሂደት የሌለው ከመሆኑም ባሻገር ይህንንም ሁኔታ ለማሻሻል ምንም አይነት ተነሳሽነት የለውም።በቆንጽላው ቅጥር ግቢ ስላለው መጠለያ የኢትዮጵያ መንግስት እንደሚያውቀው በሊባኖስ የኢትዮጵያውያኖች ማህበረሰብ ማህበር የሚያስተዳድረው አንድ መጠለያ በቆንስላው ጽፈት ቤቱ ስር አለ።
ይህም መጠለያ በቆንስላው ምንም አይነት የበጀት ድጋፍ የማይደረግለት በመሆኑ ከመጠለያው ጋር የተያያዘን ማንኛውንም ወጪ የሚሸፍነው በሊባኖስ የኢትዮጵያኖች ማህበረሰብ ማህበር ነው። የመጠለያውም ጠቅላላ ይዞታ እጅግ ለጤና አስጊ የሆነ ደረጃ ላይ የደረሰበት ሁኔታ ነው ያለው። የክፍሎቹ ስፋት ሶስት ሜትር በሶስት ሜትር ተኩል ሲሆን ባሉት ሁለት ክፍሎች ውስጥ ከሃምሳ አስከ አንድ መቶ ሰላሳ ዜጎችን አጉሮ ለመያዝ የተገደደበት ሁኔታ ነው ያለው። ለመኝታ የሚያገለግሉ ፍራሾችም ከተለያዩ ግብረሰናይ ድርጅቶችና ግሩፖች በስጦታ መልክ የተበረከቱ ናቸው። ለምሳሌ ከመስዋዕት ፣ ሃምሳ ሎሚ ፣ ፍካት ፣ እኛ ለእኛ ወዘተ። በዚህም መጠለያ ውስጥ አንድ የገላ መታጥቢያ ብቻ የሚገኝ ሲሆን ፣ ምንም አይነት የህግ እና የምክር አገልግሎት የሌለበት ስፍራ ነው። መጠለያውም ከመቆለፉ የተነሳ ማንም በመጠለያው ውስጥ ያለ ዜጋ የመንቀሳቀስ መብቱ የታገደበት ሁኔታ ነው ያለው። ስለ መጠለያው ጥበት ከላይ የጠቀስነው እንደተጠበቀ ቢሆንም በአማካኝ ከሁለት እስከ አምስት ዜጋ ወደ መጠለያው ይመጣል። ከሚመጡትም ወስጥ በአማካኝ 15% የሚሆኑት የአእምሮ ህመም ችግር ያለባቸው ናቸው።
በመጠለያው ውስጥ የሚኖሩት ሁሉም እህቶች በአንድም በሌላም በአሰሪዎቻቸው በደል የተፈጸመባቸው ሲሆኑ ግማሾቹ በደረሰባቸው በደል ፍትህን የሚጠባበቁ ሲሆኑ ቀሪዎቹ ደግሞ ወደ ሃገራቸው መመለስን የሚጠባበቁ ናቸው። ከዚህም ባለፈ አብዛኛዎቹ የሰሩበት ደሞዛቸው ያልተከፈላቸው እና እንዲከፈላቸው የሚጠባበቁ ሲሆን ይህም ሂደት ከአምስት እስከ አስራ ሁለት ወራቶች የሚፈጅ በመሆኑ እና ቆንስላውም ጉዳያቸውን በአግባቡ ስለማይከታተልላቸው አብዛኞቹ ተስፋ በመቁረጥ ለጭንቀት የሚጋለጡበት ሁኔታ ነው ያለው። በቆንጽላው ጽፈት ቤት የሚሰሩ ሰራተኞች በመጠለያ ውስጥ ያሉትን እህቶች ለመጎብኘት እንኳን ፍቃደኛ ካለመሆናቸውም በላይ በመጠለያው ውስጥ እየተስተዋለ ያለውን እራስን የማጥፋት ሙከራ እንደ ቀላል ጉዳይ ነው መመልከት የያዙት። በመጠለያው ውስጥ ካሉት እህቶቻቸን ለሚቀርበውም አቤቱታ ማለትም ጉዳያቸው የሚስተናግድበት ወይንም የሚፈጸምበት ወቅት መራዘምን አስመልክቶ ከቆንጽላ ጽፈት ቤት የሚሰጠው መልስ አጥጋቢ ያልሆነና በደፈናው የሊባኖስ የጸጥታ ክፍልን እንደ ምክንያት ማቅረብ
ነው። እንደሚታወቀው የሊባኖስ ጠቅላላ የጸጥታ ተቋም በአገሪቱ ላለው የፍትህ መጓደል ዋንኛ ምክንያት ነው። ይሁን እንጂ በዚህ ተቋም ያለፍትህ ወደ እስር ቤት የሚወሰዱ አልያም ከአገር ለሚባረሩ ዜጎች ቆንስላው ጠበቃ ሆኖ ትክክለኛውን ፍርድ እንዲበየንላቸው የማድረግ ሃላፊነትም ሆነ ግዴታ ቢኖረውም አብዛኛውን ግዜ የሚስተዋለው ግን ከዳር ሆኖ መመልከት ነው። በመሆኑም ቆንስላው በራሱ በሊባኖስ የመኖሩን ምክንያት ጠንቅቆ ያወቀው አልያም የዘነጋው ይመስላል። ከዚህም ባለፈ ቆንስላው ሆን ብሎ በመጠለያ ውስጥ ያሉትን የእህቶቻችንን ያኗኗር ሁኔታ በህዝብ ዘንድ እንዳይታወቅ ከማከላከሉም በላይ ለኢትዮጵያም መንግስት ትክክለኛውን ሁኔታ እንዳላሳወቀ ይታወቃል። ባለፈው አስር አመታት ውስጥ ተከስቶ በሚድያ ለመላው አለም ከተሰራጩ ክስተቶች አንድ ሁለቱን እንመልከት። በፈረንጆቹ 2012 አለም ደቻሳ የምትባል የሁለት ልጆች እናት የነበረች ኢትዮጵያዊት ከቆንስላው ፊት ለፊት ወደ ሊባኖስ ባስመጧት ግለሰቦች ተደብድባ በግድ በመኪና ታፍና ስትወሰድ ቆንስላው ምንም አይነት መከላከል ባለማድረጉ እና ከደረሰባት ጥቃት የተነሳ ለአእምሮ ህመም ተዳርጋ ለህክምና የስነ-አእምሮ ሆስፒታል ትገባለች በገባችም በሶስተኛው ቀን ህይወቷን ማጥፋቷ ይታወሳል። ይህንንም ጥቃት የሚያሳይ በተንቀሳቃሽ ምስል በሊባኖስ መንግስት እና በተለያዩ የአለም የመገናኛ ብዙሃኖች የተሰራጨ መሆኑ ይታወሳል።
ባሳልፍነውም የፈረንጆች አመት ማለትም ግንቦት 2018 እ.አ.አ እንዲሁ ለምቢቦ የምትባል የሃያ ስድስት አመት ኢትዮጵያዊት በአሰሪዎቿ ቅጥር ግቢ ባለ የመዋኛ ገንዳ ውስጥ ሰጥማ ህይወቷ እንዳለፈ የሚታወስ ነው። በርግጥም ትክክለኛው የለምቢቦ አሟሟት የተረጋገጠ ባይሆንም አንዳን አክቲቪስቶች ግን በአሰሪዋ አባት ከተደፈረች በኋላ እንዳረገዘችም ያምናሉ። እንዲሁም ልጇም ህይወቱ ከማለፉ በፊት ተወልዶ እንደነበርና ልጇን የማየት እድል እንደተነፈገች የሚያሳይ ምስል ተለቆ እንደነበር የሚታወስ ነው። ይሁን እና እንደ ህኪሞች ዘገባ ከሆነ ብዙም ሳይቆይ ህይወቱ እንዳለፈ መገለጹ የሚታወቅ ነው። አሟሟቷንም በተመለከተ ከበርካታ ሊባኖሳውያን እና ኢትዮጵያውያን ሁኔታው በአግባቡ እንዲጣራ ቢጠየቅም ቆንስላው ጉዳዩን በአግባቡ ለመከታተልም ሆነ ለመደገፍ ፍቃደኛ ባለመሆኑ ጉዳዩ ከዳር ሳደርስ ቀርቷል። ከላይ እንደ ምሳሌ የጠቀስናቸው እና ሌሎችም እጅግ ብዙ በደሎች በዜጎቻችን ላይ እየደረሰ ቢሆንም እስካሁን በቆንስላው እንቅስቃሴ ድክመት ምክንያት ምንም አይነት የተሻሻለ ነገር የለም። በመሆኑም እህቶቻችን ይህ ነው የማይባል መከራን እየተጋፈጡ ይገኛሉ። ይህንንም ተከትሎ በሊባኖስ የምንኖር የኢትዮጵያውያኖች ህብረት ከዚህ ቀጥሎ የተዘረዘሩት ነጥቦች የኢትዮጵያ መንግስት አጽንኦት ሰጥቶ እንዲመለከታቸው ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፦
አሁን ያለውን ቆንስላ ወደ ኤምባሲ ማሳደግ የሚቻልበት ነገር እንዲመቻች። ● በቆንስላው ተመድበው የሚመጡ ጉዳይ ፈጻሚ ሰራተኞች እምነት የሚጣልባቸው ፣ እውቀቱ ያላቸው እና ቦታውን የሚመጥኑ ቢሆኑ እና በሚደርሱ የግድያዎች ፣ ራስን ማጥፋት ፣ የጉልበት ብዝበዛ ፣ ጥቃቶች ፣ ወንጀሎች እና ወደ አገር መሳፈር የሚፈልጉ ሰዎችን ጉዳይ በተመለከተ ትክክለኛው ምርመራ እና ማጣራት እንዲደረግ። ● በሊባኖስ ግዴታውን እና ሃላፊነቱን ለይቶ የሚያውቅ ቆንስላ እንዲከፈትልን ወይንም ቆንስላው በቀደምትነት የመኖሩ ምክንያት የኢትዮጵያኖች መብት መከበርን ማረጋገጥ እንደሆነ እንዲያውቅ እና ባወቀውም ተግቶ የሚሰራ መሆኑን እንዲረጋገጥለን ። ● ቢያንስ እነዚህን ጉዳዮች የሚከታተል የሙሉ ግዜ ጠበቃ በቆስላው ስር እንዲቀጠርልን። ● እየታየ ያለውን የመጠለያ ቀውስ ያቃልል ዘንድ መንግስት ለመጠለያው በጀት እንዲመደብልን። ● በሊባኖስ ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች የኢትዮጵያ መንግስት መሰረታዊ በሆኑ ሰብአዊ መብቶች መከበርና ዜጎች ለሚደርሱባቸው ጥቃቶች ፍትህን በእኩልነት እንዲያገኙ ጠንካራ የቅስቀሳ ስራ ከታች የተገለጹትን ጨምሮ በሊባኖስ መንግስት ላይ መስራት አለበት\ ○ ከሊባኖስ መንግስት ጋር የሰራተኞችን ሁኔታ ከግምት በማስገባት ጠንካራና ግልጽ የሆነ የሁለትዮሽ ስምምነት ተግባራዊ እንዲደረግ፣ ቢያንስ ዝቅተኛ የደሞዝ እርከን ፣ ውስን የስራ ሰዓት ፣ የሳምንት እረፍት እና ሌሎች መሰረታዊ የሰራተኛ መብቶች በስምምነቱ ላይ እንዲካተቱ። ○ በደልን ፣ በዜጎቻችን በሚደርስ ሁከት ፣ ሞት እና ራስን የመግደል ሪፖርቶች የተሟላና ግልፅ ምርመራ እንዲደረግ። ○ በረጅም ግዜ እቅድ የከፊል ስርዓቱ እንዲያቆም ● በህገወጥ መንገድ ሰራተኞች የሚመጡበትን መንገድ ለማስቀረት መንግስት የበኩሉን ጥረት እንዲያደርግ እንጠይቃለን።የተፈረመ – በ እኛ ለእኛ – በ 50 ሎሚ – በ መስዋዕት – በ ፍካት ለኢትዮጵያ ደጋፊ ድርጅቶች – ARM ( Anti-racism moment ) – The Knowledge Workshop – A Project
Average Rating