⬆️
በደጀን እና ጎሃ ፅዮን መሥመር ወደ አዲስ አበባ ተጓዦችን አሳፍረው ሲሄዱ የነበሩ ተሽከርካሪዎች ወደ መጡበት እንዲመለሱ መደረጉንም የዓይን እማኞች ለአብመድ በስልክ ተናግረዋል፡፡
ተጓዦቹ ከረፋዱ 3:00 ገደማ ጀምሮ በጎሃ ፅዮንና አካባቢው እንዳያልፉ ተደርገዋል፡፡ ከ60 በላይ ተሽከርካሪዎችም ወደ ደጀን ከተማ እንዲመለሱ መደረጋቸውን ነው ያስረዱት፡፡
ክልከላው ‹‹በመጭው እሑድ አዲስ አበባ ላይ በተጠራው ሰልፍ ልትሳተፉ ነው›› በሚል እንደሆነም ነው ተጓዦች የጠቆሙት፡፡ ለአብመድ አስተያየታቸውን ከሰጡት መካከል በአማራ ክልል የሚገኙ መንፈሳዊ ቦታዎችን ጎብኝተው ወደ አዲስ አበባ በመመለስ ላይ የነበሩም ይገኙበታል፡፡ ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚሔዱ ተማሪዎች እና ለሕክምና ክትትል ቀጠሮ ወደ አዲስ አበባ የሚሂዱ ተጓዦችም እንደንዳሉ ታውቋል፡፡ ጉዳዩ የሚመለከተው የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ከአዲስ አበባ ወደ አማራ ክልል የሚገቡ ተሽከርካሪዎች በሠላም እንዲገቡ እየተደረገ መሆኑን አስታውቋል፡፡
ከአማራ ክልል ወደ አዲስ አበባ እየሄዱ የነበሩ ተጓዦች ግን እንዳያልፉ መደረጉንና ወደ ደጀን እየተመለሱ መሆኑንም ኮሚሽኑ ከተሳፋሪዎች አገኘሁት ባለው መረጃ አረጋግጧል፡፡ የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ኮማንድ ፖስት ይህ ዜና እስከተጠናከረበት ጊዜ ድረስ የተጣራ መረጃ እንዳልደረሰው አስረድቷል፡፡
ከአስተያየት ሰጭዎቹ ያገኘነው መረጃ የሚያሳየው ግን ከረፋዱ 3:00 ጀምሮ ችግሩ እንደተፈጠረ ነው የተናገሩት፡፡ ኮማንድ ፖስቱ ጉዳዩን ለማጣራትም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየሠራ መሆኑን አስረድቷል፡፡
የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ መረጃው እንደደረሰው ገልጾ ዝርዝር ምክንያቱን እያጣራ እንደሆነ አስታውቋል፡፡
Source አብመድ
Average Rating