የህወሓት ማእከላዊ ኮሚቴ ከመስከረም 26 እስከ ጥቅምት 2/ 2012 ዓ/ም ድረስ ለተከታታይ 7 ቀናት ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ በ2011 ዓ/ም ተይዘው የነበሩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ዕቅዶች፤ ድርጅታዊና ፖለቲካዊ ስራዎች በተለይ ደግሞ በአዲሱ የፖለቲካ መድረክ የትግራይ ህዝብ ህልውና፣ ደህንነትና ዋስትና ለማስጠበቅ የተካሄደ ሁለንተናዊ የመመከት ትግል እና ይህንን መሰረት በማድረግ የተሰሩ ስራዎች በዝርዝር ገምግሟል፡፡ በዚህ ልዩ የትግል ምዕራፍ የታዩ ጥንካሬዎችንና ጉድለቶችን በመገምገም ሊወሰድ የሚችል ትምህርት በመለየት በዚህ ዓመት ሊሰሩ የሚገባቸው ልማታዊና ፖለቲካዊ ዕቅዶችንም አጽድቋል፡፡
በተጨማሪም አሁን ያለው ተጨባጭ አገራዊ ሁኔታዎችንና ዕድገቶችን በመገምገም በቀጣይ ለሚኖረው ትግል መሰረት ያደረገ የመመከትና ደህንነትን የማረጋገጥ አቅጣጫዎችንና ዕቅዶችን በዝርዝር ተወያይቶ በዚህ ዓመት ሊኖር የሚችለውን ሁለንተናዊ ትግል ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የሚያስችሉ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ስብሰባውን አጠናቋል፡፡
ባለፈው ዓመት ተይዘው የነበሩ የልማት፣ የመልካም አስተዳደርና የሰላም ዕቅዶችን በቀጣይነት ለማስፋትና ለማጎልበት የሚያስችል ዘርፈብዙ ጥረት እየተካሄደ ቆይቷል፡፡ ከጀመርነው የፀረ- ድህነት ትግል ለአፍታም ሳንዘናጋ፣ በዋነኛው አጀንዳችን ላይ ለመረባረብ የሚያስችል አቅጣጫ ይዘን ሰፊ ርብርብ ስናደርግ ቆይተናል፡፡ በህዝባችን የተደራጀ ትግልና እንቅስቃሴ ከትክክለኛ መንገዳችን ሳንወጣ በልማት እቅዶቻችን ላይ ከፍተኛ ትኩረት በማድረግ ስንሰራ ቆይተናል፡፡
የሁሉም ዘመቻዎቻችንና ርብርቦቻችን ትኩረት የህዝባችን ደህንነትና ህልውና ከማስጠበቅ አንፃር እየቃኘንና ቅድሚያ ሰጥተን፣ የሁሉም ነገር ማጠንጠኛ ልማትና የህዝባችን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ መሆኑን በማመን ሁሉም ነገር ትተው ከነ አካቴው ወደ ጥፋት በገቡና ይባስ ብለው እኛንም ጎትተው ከመንገዳችን ሊያስወጡን በሚጥሩ ሀይሎች ሳንደናገር ስራችንን ማእከል አድርገን ከፍተኛ ርብርብ ስናደርግ ቆይተናል፡፡
ልማታዊ ዲሞክራሲያዊው መስመራችንን ጨብጠን የህዝባችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በተለይ ደግሞ የወጣቶችንና የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማስፋት የሚያግዙ ተግባሮች በትግራይ እንዲከናወኑ ስናደርግ ቆይተናል።
ህዝባችን በየጊዜው የሚያነሳቸውን የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመፍታት ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ በመልካም አስተዳደር መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት የቆዩ ችግሮች ፈትተን የህዝባችን ፍላጎቶች ለመመለስ የቀበሌን መዋቅር ለማስተካከል የተጀመረው የሪፎርም ስራ ተስፋ በሚሰጥ ደረጃ ወደ ተግባር ገብቷል፡፡ ስፋትና ጥልቀት ባለው ሁኔታ ሲደረግ የነበረው የወረዳ ሪፎርም ጥናትም ህዝባችን ልማትና ውጤታማ አገልግሎት እንዲያገኝ በሚያስችል መልኩ በዚህ ዓመት በከፍተኛ ትኩረት ለመፈፀም እንስቃሴ እየተደረገ ቆይቷል፡፡ ይህ በቀጣይ ለሚኖሩን ስራዎች እንደ አንድ ትልቅ መነሻ ሆኖ ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት ያግዛል፡፡
ይሁን እንጂ በልማት ስራዎቻችን በሚፈለገው መጠንና ስፋት በሚጠበቀው መጠን ውጤት ያላስመዘገብንባቸው ሁኔታዎች አሉ፡፡ በዋናነት በመልካም አስተዳደር ጉዳይ አሁንም ችግሮቻችን ሰፋፊ መሆናቸውን አይተናል፡፡ እየተጠራቀሙ በመጡ ችግሮች ሳቢያና በማስፈፀም አቅማችን ጉድለት ምክንያት ያልፈታናቸው የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዳሉ እንገነዘባለን፡፡ በተለይም በወጣቶችና ሴቶች ተጠቃሚነት ላይ አሁንም ሰፊ ችግር እንዳለ፣ በገጠርም በከተማም እየታየ ያለው የመሬት አስተዳደር ችግር፣ አገልግሎት በመስጠት ዙርያ ያለው ችግርና መንገላታት፣ ለልማት ምቹ ሁኔታ በመፍጠር ዙርያ ያሉ መዘግየቶችና እንቅፋቶች እንዲሁም ሌሎች ተዛማጅ ችግሮች የህወሓት ማእከላዊ ኮሚቴ በዝርዝር የተመለከታቸው ጉዳዮች ናቸው፡፡
በመሆኑም እነዚህ ችግሮች በዚሁ ዓመት “በጊዜ የለም” መንፈስ እንዲፈቱ ከፍተኛ ጥረትና ርብርብ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ተመለክተናል፡፡ የልማት ስራችን የሁሉም ቋጠሮ መሆኑን በመገንዘብ፣ ለዘላቂ ህልውናችንና ደሕንነታችን መረጋገጥ ባለው ትርጉም ተገንዝበን በላቀ ቁርጠኝነትና ወኔ ልንዘምትና ልንገሰግስ ይገባል፡፡ ከዚህ የልማት እንቅስቃሴ የወጣቶችንና የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የላቀ ርብርብ ይደረጋል ብቻ ሳይሆን የእንቅስቃሴው አስኳል ይሆናል፡፡
ከዚህም አልፎ በእያንዳንዱ አከባቢ ያለው ፀጋ ግምት ውስጥ ያስገባ የልማት አደረጃጀትና ስምሪት እንዲደረግ እና በዚሁ ላይ የሚመሰረት በገጠርም ይሁን በከተማ ወደ አዲስ የልማት እንቅስቃሴ የሚያስገቡ አቅጣጫዎችንም የህወሓት ማእከላዊ ኮሚቴ ለይቷል፡፡ የተጀመረው የቀበሌና የወረዳ ሪፎርም ስራ ተጠናክሮ ወደ ተግባር እንዲገባና በመልካም አስተዳደር መሰረታዊ ለውጥ እንዲያመጣ እንቅስቃሴ እንዲደረግ የህወሓት ማእከላዊ ኮሚቴ አቅጣጫዎችን ለይቶ አስቀምጧል።
የተከበርክ የትግራይ ህዝብ፤
ባለፈው ዓመት በአንድ በኩል ፀረ ድህነት ትግል በማካሄድ፣ በሌላ በኩል ደግሞ የትምክህት ኃይሎችን በመመከት ላይ ቆይተናል። የትግራይ ህዝብንና ህወሓትን ለማንበርከክ ከሁሉም አቅጣጫዎች ሲያጋጥመን የቆየው ፈተና ቀላል አልነበረም። እንደፈለግነው እንዳንሆን ማለፊያ የከለከሉን እና የጎን ውጋት እየሆኑብን ያሉት “የትግራይ ህዝብና ህወሓት ናቸው” ብለው ማለቂያ የሌለው ሴራና በደል ለመፈፀም ያልሞከሩት ፀረ-ህዝብ ተግባር አልነበረም።
ይሁን እንጂ ምኞታቸውና ዓላማቸው ስለተገነዘብን በትክክለኛ መንገድ ያደረግነው ፍትሃዊ ትግልና የመመከት ተግባር የጠላቶቻችን ምኞትና ህልም አምክነን ወደፊት እየተራመድን እንገኛለን። በህዝባችን ፅኑ አንድነትና ስምረት፣ በበሳል ንቃትና ምክንያታዊ ትግል፣ በማይነጥፍ ወኔ የተሳካ የመመከት ተግባር ስናከናውን ቆይተናል። ይህ ከትግራይ ህዝብ ጥረትና ትግስት ውጭ እንደማይሳካ እሙን ነበር። ያለፈው የሩቅና የቅርብ ታሪክህ እንደሚያሳየው ከትግልህና ከጥረትህ ውጭ መብትህንና ጥቅምህን ለማስከበር ፍቃድ የሚሰጥህ አካል አልነበረም፤ አሁንም አይኖርም።
ሁሉ ጊዜ ለፍትህና ለእኩልነት እንደቆምክ፣ ትክክለኛ መስመርህንና ዓላማህን ይዘህ በፅናት እየታገልክ፣ በሁሉም የትግል ምዕራፎች ያጋጠሙህ መሰናክሎችንና እንቅፋቶችን እየጠራረግክ በመጓዝ ላይ ትገኛለህ። ወደፊትም ብቸኛው መንገድህ ይህና ይህ ብቻ ነው። በዚህ እልህ አስጨራሽ የትግል ምዕራፍ ያካሄድከው ወደር የለሽ የመመከት ተግባር በአጠቃላይ የትግራይ ህዝብ፤ በተለይም ደግሞ የትግራይ ወጣቶች፣ ምሁራንና ሴቶች ለፈፀማችሁትና እየፈፀማችሁ ላላችሁት ገድል የህወሓት ማእከላዊ ኮሚቴ የተሰማውን ክብርና ኩራት በዚህ አጋጣሚ ሊገልጽላችሁ ይወዳል።
የተከበርክ የትግራይ ህዝብ
አሁንም ቢሆን ሁኔታዎች እየከበዱና እየባሱ በመምጣታቸው ደህንነትህንና ህልውናህን ለማስጠበቅ የምታደርገው ትግል ይበልጥ አጠናክረህ ልትቀጥልበት ይገባል፡፡ ሁሉም ህዝብ ሊገነዘበው የሚገባ ሃቅ ሊገጥመን የሚችለው ፈተና እና ፈተናውን ለመሻገር የሚጠይቀን ትግልና ጥረት እጅግ እየከበደ ሊመጣ ይችላል። ወደፊት መራመድ ሲያቅታቸው፣ በራሳቸው ድክመትና ፀረ-ህዝብ ተግባራቸው ፈተና ሲበዛባቸው ወደ ሌላ ወገን እየለጠፉ እያደናገሩ ዕድሚያቸውን ለማራዘም ጥረት ማድረጋቸው አይቀርም፡፡ አንድነትህንና ፅናትህን ለማደፍረስ በውስጣችን የሚታዩ ችግሮችን እንደ ዕድል ለመጠቀም እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ አልፎ አልፎ የሚታየውን ከባቢያዊነትም ይሁን በሃይማኖት ስም በመካከልህ ልዩነት ለመፍጠር ያላሳለሰ ተግባር እየፈጸሙ ይገኛሉ፡፡ ይህን ለማ
ስጽፈፀም ታስቦ የሚላከው ባንዳ ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም፡፡ ይህ እንደሚሆን ተገንዝበህ እንደወትሮህ አንድነትህን አጠናክረህ፣ በአንድ ላይ ሆነህ ለላቀ ትግል ተዘጋጅ፡፡ የምንጊዜም ዋስትናህና የድል አድራጊነት ምስጢር አንድነትህ፣ መስመርህና ፅናትህ ነው፡፡ የትግራይ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ ባለሃብቶችና ምሁራን አሁንም እንደቀድሞ በአንድነት ፀንታችሁ ሊኖረን ለሚችለው ትግል በላቀ ደረጃ ልትዘጋጁ ይገባል፡፡
መላው የድርጅቱ ኣባላትና አመራሮችም የላቀ ፅናትና ተነሳሽነት የሚጠይቀውን ትግል ህዝባችንን ይዘን ወደ ዘላቂ ድል ለመገስገስ መሪ ሚናችሁን ልትፈፅሙ ይገባል፡፡ ከዚህ ባለፈ የትግራይ ህዝብ ህልውናና ደህንነት ለማረጋገጥ በሚደረገው ትግል የነበረውን የትግል አቅሞች ሁሉ ለማንቀሳቀስ ይሰራል፡፡ በትግራይ ውስጥ ካሉ ፖለቲካዊ ድርጅቶችና ሲቪክ ማህበራትም በጋራ ለመስራት ህወሓት የተለየ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ ሊያረጋግጥላችሁ ይወዳል፡፡
የተከበርክ የትግራይ ህዝብ፤
የህወሓት ማእላዊ ኮሚቴ በስፋት ካያቸው መሰረታዊ ጉዳዮች አንዱ በሀገራችን እየታየ ያለው ፈጣን አደጋና ወዲፊትም ሊኖረው የሚችል አጠቃላይ ሁኔታ የሚመለከት ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በአገራችን ከጊዜ ወደ ጊዜ ችግሮች እየተበራከቱ፣ ጥፋት በጥፋት ላይ እየተደራረበ፣ የጥፋቱ ስፋትና መጠን በየቀኑ እየጨመረ ወደ ከፋ አገር የመበተን ደረጀ እየደረሰ ነው፡፡ አደጋው ወደ ከፋ ደረጃ እንዲሄድ እያደረገ ያለው አንዱ ምክንያት የፓርቲ ውህደት ለመፈፀም እየተደረገ ያለው የችኮላ እንቅስቃሴ ነው፡፡ የፓርቲ ውህደት ጥያቄ በኢህአዴግ ውስጥ በተለያየ ጊዚያት እየተነሳ የቆየና ይህንን ለማድረግ ደግሞ ሊሟሉ የሚገባቸው መሰረታዊ ጉዳዮች እንዲታዩና በጥናት ላይ በመመስረት እንዲመለሱ መግባባት ላይ የተደረሰበት ጉዳይ ነው፡፡ ህወሓትም ቢሆን በመሰረተ ሃሳብ ደረጃ የተለየ እምነት አልነበረውም፡፡ ሆኖም ግን ይህን ለማድረግ በሁሉም መሰረታዊ የመስመር ጥያቄዎች፣ ፕሮግራም፣ ስትራቴጂ ወደ አንድ የሚያስተሳስር አመለካካተና እምነት በሁሉም እህት ድርጅቶች ሲፈጠር ብቻ ነው መተግበር የሚችለው፡፡ አንድ ሊያደርግ የሚችል የጋራ የአመለካከትና የተግባር አንድነት በሌለበት ወቅት አንድ ድርጅት እንደ ድርጅት መጠን ህልውና ሊኖረው አይችልም፡፡ ከውህደት በፊት የሚያዋሃህድ አመለካከትና እምነት መለየት አለብን፡፡ ኢህአዴግንና አገርን እየበተኑ ካሉት የተገዙ ደባል አመለካከቶች የሚለይ መስመር እና አጥር በጠራ መልኩ ሳይለይና ሳይቀመጥ ውህደትን ማሰብ አይቻልም፡፡ በደፈረሰ አመለካከትና በአንድነት ሊሰምሩ በማይችሉ እሳትንና ጭድ አስተሳሰቦችን በተሸከመ ኢህአዴግ አይደለም ውህደት ቀርቶ በግምባርነት ለመቀጠል የማይችል የተበተነ ድርጅት ነው አሁን ያለው፡፡ እንደዚህ ያለ የተበተነ ድርጅት ወደ አንድ ፓርቲ ውህደት ይመጣል ብሎ ማሰብ በራሱ ድርጅቱን ከመበተን አልፎ አገርን የሚበትን ተግባር ነው ሊሆን የሚችለው፡፡
ከዚህም አልፎ በቅርቡ ከግንባሩ እምነትና መተዳደሪያ ደንብ ውጭ የፓርቲ ውህደት ለመፈፀም እየተደረገ ያለው ሩጫ ችግሩ እንዲባባስ የሚያደርግ ፀረ-ዲሞክራሲያዊ አካሄድ እየሰፋ መምጣቱን የሚያሳይ ነው፡፡ የቅርፅ ውህደት ብቻ ሳይሆን በይዘትና በያዘው ፕሮግራሙ በመሰረቱ የተለወጠ አዲስ ፓርቲ ለመመስረት ነው ጥረት እየተደረገ ያለው፡፡ ይህ ሲሆን የኢትዮጵያ ህዝቦች ኢህአዴግ ለያዘው ፕሮግራም መሰረት አድርገው የሰጡት አገርን የመምራት ስልጣን ያከትማል ማለት ነው፡፡ አገርን ለመምራት ሓላፊነት ያልተሰጠው አዲስ ፓርቲ እንዲመሰረት ነው እየተደረገ ያለው፡፡ እንዲህ ያለ አዲስ ፓርቲ በሃገራችን ፖለቲካዊ ድርጅቶች የምዝገባ ህግ ያላለፈ፣ በህዝቦች ፈቃደኝነት በስልጣን ላይ ለመቆየትም ሆነ ስልጣን ለመያዝ ለመወዳደር የማይችል ህገ-ወጥ ድርጅት ነው የሚሆነው፡፡
በመሆኑም በውህደት ስም በፍፁም ፀረ-ዴሞክራሲያዊ መንገድ አዲስ አሃዳዊ ድርጅት ሊመሰረት አይገባም፡፡ በሁሉም መለኪያዎች አንድ ፓርቲ ለመሆን የሚያስችል መነሻና ምክንያት በሌለበት ኢህአዴግን አፍርሶ ሌላ ፓርቲ ለማቋቋም ማሰብ አገርን የሚበትን ተግባር ነው፡፡ ስለዚህ ኢህአዴግ እንደ ግንባር ተደራጅቶ ችግሮችን በትግል እየፈታ አገር ሊመራ ይገባል፡፡ ከጊዜ አንፃርም ይህ ሊቆይ የሚገባው ጉዳይ ነው፡፡ አጋር ድርጅቶችም በውህደት ስም እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ ህልውናችሁን የሚያጠፋ መሆኑን ልትገነዘቡ ይገባል፡፡ ይሁን እንጂ አጋር ድርጅቶች ወደ ኢህአዴግ በሙሉ አባልነት ገብታችሁ በጋራ ትግልና ጥረት አገርን የሚያድን ተግባር ሊትፈፅሙ እንደሚገባ ህወሓት በፅናት ያምናል፡፡ ከዚህ ውጭ ህወሓት በእንደዚህ ያለ አገርን የሚበትን ተግባር ውስጥ ገብቶ ሊንቦጫረቅ እንደማይፈልግ ሊታወቅ ይገባል፡፡ መላው የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በውህደት ስም ኢህአዴግን ለማፍረስ የሚደረገው እንቅስቃሴ ሓላፊነት በተሞላበት ተገቢውን ትግል እንድታደርጉ ህወሓት ጥሪውን ያቀርብላችኋል፡፡
የተከበራችሁ የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች
ህገ መንግስታችንና ህብረ ብሄራዊ ፌደራላዊ ስርዓታችን የሚሸረሽሩና የሚጥሱ ተግባራት በየቀኑ ማየት የተለመደ ተግባር ሆኗል። በዚሁ ወቅት የትምክህት ሐይሎች በአመለካከትና በተግባራዊ እንቅስቃሴ ጉልበት ፈጥረው አገር የሚያምሱበት ሁኔታ ተፈጥሯል። በብዙ የአገራችን አከባቢዎች የሰላም እጦት እየተስፋፋ፣ በዚሁም ምክንያት ከጊዜ ወደ ጊዜ መንግስት የማይቆጣጠራቸው አከባቢዎች እየተበራከቱ ይገኛሉ። ለመብቱና ለማንነቱ ለታገለ ህዝብ በርካታ ግፍና በደል የሚፈፀምበት፣ ዜጎች በእርጋታ የማይኖሩበት፣ በማንነታቸው ምክንያት በዜጎች ላይ ግፍ የሚፈፀምበት፣ ለህይወታቸውና ንብረታቸው ዋስትና ያጡበት፣ በዚች አገር ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ህውከትና መፈናቀል የተበራከተበት፣ መንግስት የዜጎች ሰላምና ደህንነት ለመጠበቅ እየተቸገረ የመጣበት፣ ከዚህ አልፎም የአገሪቱ የመከላከያ ከፍተኛ አመራሮች እና የአማራ ክልል አመራሮች እስከመግደል ተግባር የተፈፀመበት፣ ሌላ ቀርቶ የነዚህ ምርጥ ጀነራሎችና መሪዎች ግድያ እንኳን በአግባቡ በማጣራት ለህዝብ ግልፅ ለማድረግ በማይቻልበት፣ የህግ በላይነት እየተጣሰ፣ የዜጎች ህይወት መጥፋትና መፈናቀል ማዳን የማይችል መንግስትና ስርዓት ወደ መሆን ተሸጋግረዋል ማለት ብቻ ሳይሆን ይህንን ለማስቆምና ለመግታትም ዋና ተግባሩ ያላደረገና ቁርጠኝነትም የሌለው ሆኗል።
የህዝብ መሰረታዊ ጥያቄዎችን ወደ ጎን በመተው ሌላ ጉዳይ ላይ በማትኮር የአገሪቱ ኢኮኖሚ እየተዳከመ ወደ ከፍተኛ ድቀትና ማሽቆልቆል እየገባ ነው። የአገሪቱ ልማት የሚመራውና የሚደግፈው አጥቶ፣ ልማታዊ አቅሞች እየመከነ፣ ስራ አጥነት እየተባባሰ፣ የህዝብ ኑሮ ውድነት ከጊዜ ወደ ጊዜ ሰማይ የሚሰቀልበት ሁኔታ ተፈጥሯል። በዚህ ምክንያትም ችግር በችግር ችግር እየተመሰቃቀለና እየተደራረበ በመሄድ ላይ ይገኛል። የህዝባችን ዋስትና የሆነው ህገ መንግስታችንና ህብረ ብሄራዊ ፌዴራል ስርዓታችን በማፍረስ አሃዳዊ ስርዓትን መልሶ ለመትከል እየሰራ ያለውና በዋናነት ይህንን አደጋና ጥፋት እየፈጠረና እየመራ የሚገኘው ትምክህተኛው ሀይልና በዙርያው የተሰባሰበ ፀረ ህዝብ ሐይል ነው።
በውስጣቸው ያለውን ድክመትና ፀረ-ህዝብ ተግባር ከመፍታትና ከማጥራት ይልቅ የሁሉም ችግር “ሶስተኛ ወገን አለው” የሚል የቆየ ዘፈን ሲደጋግሙ እየታየ ነው፡፡ ለአማራ ህዝብ የማይመለከተውና ያልተገባ ምስል እያስያዙና “ትምክህተኛ ተብለሃል!” እያሉ በዚህ ተሸፋፍነው በህዝቦች መካከል የቆየውን ዝምድናና ወንደ
ማማችነት ለማደፍረስ እየጣሩ ይገኛሉ፡፡ የአማራ ህዝብ ትምክህተኞችን ታግሎ በእኩልነት የሚኖርባት አዲሲቷ ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ እንድትመሰረት የማይተካ ሚና የተጫወተ ህዝብ ነው፡፡ የትግራይና የአማራ ህዝቦች በጋራ ትግላቸው ትምክህተኛውን አሸንፈዋል፡፡ ለወደፊትም ቢሆን እነዚህ ህዝብ ለህዝብ አጋጭተው እንዲባላ በማድረግ መኖር የሚፈልጉና ሓላፊነታቸውን ትተው ለጥፋት የተሰማሩ ሓይሎች በተደራጀ መንገድ ሊታገላቸው ይገባል፡፡
መላው የሀገራችን ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦችም ህብረ-ብሄራዊ ፌዴራላዊ ስርዓታችንን ለማዳን በሚደረገው ወሳኝ ትግል ከማንኛውም ጊዜ በላይ አገራችንን ለማዳን ሊረባረብ ይገባል፡፡ሕብረ ብሄራዊ ፌዴራላዊ ሓይሎች የጀመራችሁትን ትግልና ሰፊ ትብብር መድረኮች አማራጭ የሌለው መሆኑን ተገንዝባችሁ ትግላችሁን አጠናክራችሁ ልትቀጥሉበት ይገባል፡፡ ህወሓትም የተጀመረውን ትግል ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የሚቻለውን ሁሉ እንደሚያደርግ ሊያረጋግጥላችሁ ይወዳል፡፡
በዚህ አጋጣሚ ሕገ-መንግስት፣ ሰላምና የህዝቦችና የአገርን ደሕንነት በመጠበቅ የላቀ ሓላፊነት ያለብህ የሀገር መከላከያ ሰራዊት፤ አገራችን እያጋጠማት ያለውን አደጋ በሚገባ ተገንዝበህ ከጥፋት ለማዳን እያደረገው ያለው ርብርብ፣ ለዚች ልዩ ታሪክና ክብር ያላት ሃገር ሉኣላዊነቷንና ሰላሟን በመጠበቅ ረገድ ዛሬም እንደወትሮ በላቀ ደረጃ ህዝባዊ ሓላፊነትህን ተቋማዊ እንድትህን አጠናክረህ በምታደርገው ሁለንተናዊ እንቅስቃሴም የትግራይ ህዝብና ህወሓት ከጎንህ ሆነው አስፈላጊውን ሁሉ እንደሚፈፅሙ ልናረጋግጥ እንወዳለን፡፡
በህገ- መንግስቱ መሰረት ስድስተኛው አገር አቀፍና ክልላዊ ምርጫ በያዝነው ዓመት የግድ መካሄድ ያለበት ነው፡፡ በመሆኑም ህወሓትና የትግራይ ህዝብ ምርጫው በወቅቱ እንዲካሄድ በተደጋጋሚ አቋማቸውን እየገለፁ ቆይተዋል፡፡ ይሁን እንጂ ምርጫው ለማካሄድ የሚያስችል ምንም ዓይነት ዝግጅት እየተደረገ አይደለም፡፡ “በቂ ዝግጅት አላደረግንም” ተብሎ ምርጫውን ለማራዘም የሚደረገው ጥረት ፈፅሞ ተቀባይነት ሊኖሮው አይችልም፡፡ በአገራችን ያሉ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ነፃ የመወዳደር ዕድል አግኝተው ህዝብ በነፃ ፍላጎቱ የሚመርጠውን መንግስት ወደ ስልጣን እንዲመጣ በህዝብ ፍፁም ፈቃድ በስልጣን ላይ እንዲቆይ የሚያደርግ ህገ-መንግስታዊ መብት በጥብቅ መከበር አለበት፡፡ ይህ በማይሆንበት ወቅት መላው የአገራችን ህዝቦች መብታችሁንና ሕገ-መንግስታዊ ስልጣናችሁን አደጋ ላይ እየጣለ መሆኑን አውቃችሁ የላቀ ትግል ልታደርጉ በሚጠይቅ አስገዳጅ ጊዜ ላይ እንገኛለን።
የተከበርክ የኤርትራ ህዝብ
የትግራይና የኤርትራ ህዝብ ለጋራ መብትና ጥቅም በጋራ የታገሉ ወንድማማች ህዝቦች ናቸው፡፡ የነበረውና አሁንም ያለው ዝምድናና መደጋገፍ ወደ ዘላቂ አስተማማኝ ደረጃ ለማድረስ ባለፈው ዓመት የተጀመረው የሰላም ጭላንጭል በዚህ ዓመትም ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል፡፡ በጋራ ለዘላቂ ሰላም ተደጋግፈን ልንሰራ ይገባል፡፡ የጀመርነው አዲስ እፎይታና ሰላም ዋስትና ያለው እንዲሆንም የሁለቱም ህዝቦች ትስስርና ግንኙነት እንዲጠናከር መስራት አለብን፡፡ የትግራይ ህዝብና ህወሓትም ይህንን ለማጠናከር ከነሱ የሚፈለገውን ሁሉ እንደሚፈፅሙ ደጋግመን ልናረጋግጥልህ እንወዳለን፡፡
የማንሻገረው ፈተና አይኖርም
ዘልአለማዊ ክብርና መጎስ ለስማእቶቻችን!
የህወሓት ማእከላይ ኮሚቴ
ጥቅምት 4/ 2012 ዓ/ም
መቐለ
Average Rating