ቤተ ከርስቲያናችን ለዘመናት ዓርማ አድርጋ ስትጠቀምበት የኖረችውን እና አሁንም የምትጠቀምበትን ባንዲራ ለበዓል ይዛችሁ ወጥታችኋል፤ በቤተ ክርስቲያን ጣሪያ እና ጉልላት ላይ ቀብታችኋል በማለት ምእመናንን የሚያዋክቡ፣ወጣት ክርስቲያኖችን የሚያስሩ አካላት ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ ተጠየቀ።
በተጨማሪም የቤተ ክርስቲያንን ተቀማጭ ገንዘብ ከንግድ ባንክ አውጥታችሁ እኛ በምንፈልገው ባንክ አስቀምጡ በማለት የሚያስገድዱ በአንዳንድ አህጉረ ስብከት የሚገኙ አካላት ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ ያስጠነቀቀው 38ኛው የመንበረ ፓትርያርክ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ቅዳሜ ጥቅምት 8 ቀን 2012 ዓ.ም በተጠናቀቀበት ዕለት ነው።
ቤተ ክርስቲያንን ለማጥቃት ርዕዮተ ዓለም ቀርጸው፣ የሐሰት ታሪክ ፈጥረው በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን የሚነዙ አቀጣጣዮችን (አክቲቪስት ነን ባዮች) እና ፖለቲከኞችን እኩይ ድርጊት መቃወም እንደሚገባ ጉባኤው በመግለጫ አሳውቋል።
ሕዝብን ከሕዝብ ለማጋጨት የሚሞክሩ ጽንፈኞች ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ፣ በቤተ ክርስቲያን እና በምእመናን ላይ እየተፈጸመ ያለው ግፍ እንዲቆም የሚያግዝ እና ጥፋት ከመፈጸሙ በፊት ሙያዊ ትንተና የሚያቀርብ ኮሚቴ እንዲቋቋም ጉባኤው ጠይቋል።
የሕግ ባለሙያዎች የተካተቱበት ከመንበረ ፓትርያርክ እስከ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን የሚደርስ ኮሚቴ በቅዱስ ሲኖዶስ እንዲቋቋም ጉባኤው አሳስቦ አገራዊ ለውጡ ተስፋ የሰጠ ቢሆንም በቤተ ክርስቲያን እና በምእመናን ላይ እየደረሰ ያለው እኩይ ተግባር ቤተ ክርስቲያንን እያሳዘናት እና እያሳሰባት መሆኑንም አስገንዝቧል።
በቤተ ክርስቲያን ላይ የሚፈጸመውን ጥፋት በሰላማዊ መንገድ በሽምግልና እና በውይይት ለመፍታት ጥረት ማድረግ የሚገባ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ በብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የሚመራ ዓለም አቀፍ ሰላማዊ ሰልፍ መደረግ እንደሚኖርበትም አሳስቧል።
የጥምቀት እና የመስቀል በዓላት ማክበሪያ ቦታዎችን ሙሉ በሙሉ ነጥቀው፣ አንዳንድ ጊዜም ቆርሰው ለሌሎች የሚሰጡ አካላትን እኩይ ድርጊት አጥብቆ የተቃወመው መግለጫው በአገር ውስጥም በውጭም የቤተ ክርስቲያንን አንድነት ለመፈታተን የሚሞክሩ ግለሰቦችን እና ቡድኖችን እኩይ ድርጊት ቅዱስ ሲኖዶስ በጥበብ እና በትዕግሥት ማሳለፉ የሚያስደንቅ መሆኑን ገልጧል።
ምንጭ:-ማህበረ ቅዱሳን
Average Rating