- መንግሥት የጥፋት መልዕክተኞችን በሕግ እንዲጠይቅ ቅዱስ ሲኖዶስ አሳሰበ
የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮችን በአፍ መፍቻ ቋንቋ ለማሠልጠን ማዕከል እንዲከፈት ወሰነ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በተለይ በክርስቲያኖችና በአብያተ ክርስቲያናት ላይ እየደረሰ ያለው ስደትና መከራ እንዲያበቃ፣ መንግሥት የጥፋት መልዕክተኞችን በሕግ እንዲጠይቅ አሳሰበ፡፡
ቅዱስ ሲኖዶስ በፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ 5(164) ድንጋጌ መሠረት ከጥቅምት 12 እስከ 24 ቀን 2012 ዓ.ም. (በመሀል ጥቅምት 12 ቀን 2012 ዓ.ም. በተለይ በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ተፈጥሮ በነበረው ጥፋት ለቀናት መቋረጡ ይታወሳል)፣ ያደረገውን ጉባዔ ሲያጠናቅቅ በ14 ጉዳዮች ላይ ውሳኔ አስተላልፏል፡፡
ምልዓተ ጉባዔው ባስተላለፈው ውሳኔ እንደገለጸው፣ ኢትዮጵያውያን ሁሉ በተለይ በአሁኑ ጊዜ ለአገራዊ አንድነትና ሰላም ቅድሚያ መስጠት አለባቸው፡፡ በአንድነትና በሰላም ተባብሮ በጋራ ለመኖር፣ ለመሥራትም ሆነ ሠርቶ ለመበልፀግ የአገር አንድነት መጠንከር እንዳለበት አጽንኦት ሰጥቷል፡፡
ክቡር የሆነው የሰው ልጅ ሕይወት በማንኛውም ሁኔታ በከንቱ መጥፋት እንደሌለበት የቅዱስ ሲኖዶስ ሰብሳቢ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ ቀዳማዊ ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም መንግሥት የአገርን ሰላም፣ የዜጎችን ደኅንነት የመጠበቅና ዜጎች በአገራቸው በእኩልነት ተሳስበው የሚኖሩበትን መንገድ በመቀየስ ኃላፊነቱን እንዲወጣም አሳስበዋል፡፡
በሁለትና ሦስት ቀናት ውስጥ ከ80 በላይ ኢትዮጵያውያን ሕይወት አላግባብ በማለፉ ቅዱስ ሲኖዶስን እጅግ እንዳሳዘነው ፓትርያርኩ ጠቁመው፣ መንግሥት ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ መሥራትና አጥፊዎች እንዲጠየቁ ማድረግ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
የተፈናቀሉት ወደ ቀዬአቸው እንዲመለሱና ለጠፋው ንብረታቸው ማቋቋሚያ እንዲሰጣቸውም አክለዋል፡፡
በቤተ ክርስቲያኗ ሌላው አንገብጋቢ ጉዳይ ሆኖ የነበረው አብነት ትምህርት የሚሰጥበት የቋንቋ ችግር መሆኑን የተመለከተው ቅዱስ ሲኖዶስ፣ የእምነቱ ተከታዮች በቋንቋቸው እንዲማሩና እንዲያገለግሉ፣ በየሀገረ ስብከቱ የሚገኙ የአብነት ትምህርት ቤቶች እንዲጠናከሩ ተጨማሪ በጀት እንዲመደብና በቀጣይ በሁሉም በአፍ መፍቻ ቋንቋዎች ለማሠልጠን ማዕከል እንዲቋቋም መወሰኑን ፓትርያርኩ አሳውቀዋል፡፡
በኦሮሚያ ክልል ለሚገኙ ተጎጂ ወገኖች በጊዜያዊነት የሚደርስ ምግብና አልባሳት እንዲደርስ፣ ችግሩን እየተከታተለ ዘለቄታዊ ዕርዳታ የሚያሰባስብ ኮሚቴ እንዲቋቋም ቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ማስተላለፉንም ፓትርያርኩ ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንና በሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን መካከል ሊኖር ስለሚገባው ግንኙነት፣ ወደፊትም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ማሳለፉን ፓትርያርኩ አስረድተዋል፡፡FacebookTwitterLinkedInShare
Average Rating