ትናንት ቅዳሜ ምሽት በወልዲያ ዩኒቨርሲቲ በተማሪዎች መካከል በተፈጠረ ግጭት ቢያንስ ሁለት ተማሪዎች መሞታቸው ተነገረ።
ያነጋገርናቸው የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች እና መምህር የብሄር መልክ በያዘው ግጭት የሁለት ተማሪዎች ህይወት ማለፉን እና በርካቶች መቁሰላቸውን አረጋግጠዋል።
በዩኒቨርሲቲው መምህር የሆኑት ምንጫችን ትናንት ምሽት በተፈጠረው ግጭት ሁለት ተማሪዎች መሞታቸውን ወደ ዩኒቨርሲቲው ደውለው መስማታቸውን ነግረውናል።
የሆስፒታል ምንጮች እንደጠቆሙት ደግሞ ወደ ወልዲያ ጄኔራል ሆስፒታል 14 ተማሪዎች ተጎድተው መጥተዋል።
ስማቸወን መግለጽ ያልፈለጉ የወልዲያ ጀነራል ሆስፒታል ባልደረባ ለቢቢሲ “እኔ የገባሁት ዛሬ [እሁድ] ጠዋት 2፡30 ላይ ነው። ተማሪዎቹ ጉዳት ደርሶባቸው ሲመጡ አልተመለከትኩም። ግን አሁን ከ14-15 የሚሆኑ ጉዳት የደረሰባቸው ተማሪዎች በሆስፒታሉ የህክምና ክትትል እየተደረገላቸው ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
እኚሁ የሆስፒታል ባልደረባ በተማሪዎች ላይ የደረሰው ጉዳት ከቀላል እስከ ከባድ መሆኑን የጠቀሱ ሲሆን፤ ጉዳቱ ያጋጠመው በድብደባ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ከዚህ በተጫማሪ ትናንት ምሽት የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ በተፈጠረባቸው የደህንነት ስጋት ከዩኒቨርሲቲው ቅጥር ግቢ ለመውጣት የሞከሩ ተማሪዎች ከግቢው እንዳይወጡ መከልከላቸውን ያነጋገርናቸው ተማሪዎች ተናግረዋል።
ግጭቱን ተከትሎ የደህንነት ስጋት የገባቸው ተማሪዎች ከዩኒቨርሲቲው ቅጥር ግቢ ለመውጣት ሲሞክሩ መከልከላቸውን ተናግረዋል።
ስሙ እንዳይጠቀስ የጠየቀ አንድ ተማሪ ለቢቢሲ “ትናንት የተፈጸመውን አይተን እንዴት ነው ዶርም ውስጥ የምንተኛው?” ሲል ተናግሯል። ጨምሮም “ትናንት የተፈጸመው ዳግም ላለመከሰቱ ምንም ማረጋገጫ የለንም” በማለት ከዩኒቨርሲቲው ቅጥር ግቢ እንዳይወጡ መደረጉ አግባብ አለመሆኑን ጠቁሟል።
በጉዳዩ ላይ የሚመለከታቸው የዩኒቨርሲቲው ባለስልጣናትን ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም። የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ዲን ፕሬዝደንት መረጃ እያጠናቀርን ነው በማለት ዝርዝር መረጃ ሊሰጡን አልቻሉም። የዩኒቨርሲቲው ሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ ስልክ ደግሞ ሊሠራልን አልቻለም።
የወልዲያ ዩኒቨርሲቲ የጥበቃ እና ደህንነት ሺፍት ኃላፊ የሆኑት ሻምበል መንግሥቱ ትናንት ምሽት በዩኒቨርሲቲው ቅጥር ግቢ ስለተፈጸመው መረጃ እንዲሰጡን ጠይቀናቸው “ምንም መረጃ የለኝም” በማለት መረጃ ከመስጠት ተቆጠበዋል።
የአማራ መገናኛ ብዙሃን በበኩሉ የሰሜን ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ወልደትንኤ መኮንን በመጥቀስ ትናንት ምሽት ተማሪዎች በጋራ እግር ኳስ በቴሌቪዝን ተመልክተው ሲመለሱ በተፈጠረ ግጭት ሁለት ተማሪዎች መገደላቸውን እና ስምንት ተማሪዎች ላይ ደግሞ ጉዳት መድረሱን ዘግቧል።
ምንጭ፦ ቢቢሲ
Average Rating