www.maledatimes.com የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት እስከ ሞት ድረስ መሥዋዕት ለመክፈል እንዲዘጋጁ ፓትርያርኩ አሳሰቡ ፡፡ - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት እስከ ሞት ድረስ መሥዋዕት ለመክፈል እንዲዘጋጁ ፓትርያርኩ አሳሰቡ ፡፡

By   /   November 15, 2019  /   Comments Off on የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት እስከ ሞት ድረስ መሥዋዕት ለመክፈል እንዲዘጋጁ ፓትርያርኩ አሳሰቡ ፡፡

    Print       Email
0 0
Read Time:4 Minute, 21 Second

የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ መደበኛ ስብሰባ መጀመሩን አስመልክቶ ቅዱስ ፓትርያርኩ የሰጡት የመክፈቻ ቃለ ምዕዳን

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤ አሜን፡፡

• ብፁዕ አቡነ ያሬድ፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ እና የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ

• ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ፣ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ እና የምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤

• ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት፣

ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን በደሙ የዋጀ ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንኳን ለዓመታዊው የጥቅምቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ አደረሰን አደረሳችኹ፡፡

“ወይእዜኒ ረዐዩ ዘሀለዉ ኀቤክሙ መርዔቶ ለክርስቶስ፤ አሁንም በእናንተ ዘንድ ያለውን የእግዚአብሔርን መንጋ ጠብቁ” (፩ኛጴጥ. ፪፥፮)

እግዚአብሔር አምላካችን የፍጥረታት ሁሉ ፈጣሪ፣ ጠባቂ፣ መጋቢ፣ አስተናባሪ እና አስተዳዳሪ ነው፤ በሰማይ እና በምድር ያለው የሚታየውና የማይታየው ፍጥረታት በአጠቃላይ በእግዚአብሔር ጥበቃ እና አስተዳደር ሥር ነው፤ ፍጡራን ከእርሱ በተገኘ የአእምሮ ነፃነት በሚፈጽሙት ተግባር የራሳቸው ድርሻ እና ሓላፊነት እንዳላቸው ቢታወቅም ያለእርሱ ዕውቅና የሚደረግ እንደሌለ ግን ከቅዱስ መጽሐፍ እንማራለን፡፡

እንግዲህ እርሱ የጠባቂዎች ጠባቂ ኾኖ ሳለ ከፍጡራን ወገን ደግሞ በልዩ ምርጫው እየሾመ መንጋውን ወይም ፍጥረቱን ያስጠብቃል፤ ይህ ከጥንት ጀምሮ የነበረ የእግዚአብሔር አሠራር እንደ ኾነ ቅዱስ ያሬድ ሲገልጽ፣ “ኢኃደጋ ለምድር እምቅድመ ዓለም ወእስከ ለዓለም እንበለ ካህናት ወዲያቆናት፤ ዓለም ከመፈጠሩ በፊት አንሥቶ እስከ ዘለዓለሙ ድረስ ምድርን ያለ ካህናት እና ያለ ዲያቆናት አልተዋትም፤›› በማለት ያደረጋግጣል፡፡

ይህ የሚያመለክተን፣ እግዚአብሔር ዓለምን ያለጠባቂ የተወበት ዘመን ካለመኖሩም ሌላ ጠባቂዎቹ ካህናት እና ዲያቆናት መኾናቸው ነው፤ “ካህናት” የሚለው ስያሜ የወል ስም ኹኖ ከቅዱስ ፓትርያርክ ጀምሮ ያለው ውሉደ ክህነት በሙሉ እንደሚያጠቃልል ይታወቃል፡፡

ከዚህ አኳያ፣ ኰኵሐ ሃይማኖት ቅዱስ ጴጥሮስ ከጌታችን በተሰጠው የጥበቃ ሓላፊነት መሠረት እርሱም በክህነት ለወለዳቸው ልጆቹ በፈንታው “መንጋውን ጠብቁ” እያለ ምእመናንን ሲያስጠብቅ እናያለን፡፡

ትልቁ የእግዚአብሔር ትእዛዝ እና የቤተ ክርስቲያን ተልእኮም፣ ይህ የጥበቃ ተግባር ነው፡፡

እግዚአብሔር እኛ ካህናትን በሓላፊነት የሾመበት ዋና ዓላማ፣ መንጋውን እንድንጠብቅለት ነው፤ ይህ መንጋ ተብሎ የተገለጸው ወገን፣ የተለየ ሕዝብ እና ጎሳ ሳይኾን፣ ለትዝምደ ሰብእ ወይም የሰው ዘርን በሙሉ ነው፡፡

በራሱ እምቢተኝነት ከሚቀርበት በስተቀር፣ የጌታችን ጥሪ ለትዝምደ ሰብእ በሙሉ እንደኾነ፣ “ሑሩ ወስብኩ ወንጌለ ለኵሉ ፍጥረት፤ ሒዱ ወንጌልንም ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ” በማለት አሳውቆናል፡፡

እንዲሁም ከኾነ ጠብቁ ተብለን የታዘዝነው ያመኑት ወይም የተጠመቁትን ብቻ ሳይኾን፣ ያላመኑትንም፣ ያልተጠመቁትንም በአጠቃላይ እንደ ኾነ ለጥያቄ የሚቀርብ አይደለም፡፡

ከዚህ አንጻር መንጋችንን ስንጠብቅ፣ ያመኑትን በነፍሳቸውም በሥጋቸውም ምንም ዓይነት ጉዳት እንዳይደርስባቸው የተሟላ ጥበቃ እና ክብካቤ በማድረግ፣ ያላመኑትንም በፍቅር በማቅረብ እና ዘመድ ዘመድ በማለት፣ ውሳጣዊ እና መንፈሳዊ ስሜታቸውን በመንፈስ ቅዱስ ኀይል በማነቃቃት እና ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በማምጣት እንደ ኾነ ለሁላችን ግልጽ ነው፡፡

ኾኖም፣ ይህን የጥበቃ ሥራ በአግባቡ ለማሳካት ትልቁ ትጥቃችን ቅዱስ ወንጌል እንደ ኾነ ምንጊዜም መዘንጋት የለብንም፡፡ ቃለ ቅዱስ ወንጌልን ለፍጥረት ሁሉ ለማዳረስ የተለያዩ ዘዴዎችንና አቀራረቦችን፣ ሥልጠናዎችንና አስተምህሮዎችን መጠቀምና በዚህ የባዘነውን በግ ወደ መንጋው የምንመልስበት ታሪካዊ እና ወቅታዊ ሥራ ከፊታችን ይጠብቀናል፡፡

በአሁኑ ጊዜ በየቀኑ የሚባክኑና በተኩላ የሚነጠቁ በጎች በእጅግ እየተበራከቱ ነው፤ ዛሬ ሁሉን ነገር መልካም ነው ብለን የምንዘናጋበት ጊዜ ሳይኾን፣ የጎደለውን ለመሙላት ቃል የምንገባበት ያኑንም በተግባር ፈጽመን በጎቻችንን የምንሰበስብበት ጊዜ ነው፡፡

በዚህ አኳኋን በንቃት እና በትጋት፣ በሓላፊነት እና በቁጭት ከሠራን ከባዘኑት በጎች መካከል ብዙዎችን ወደ መንጋው መመለስ እንደምንችል፣ ያሉትንም ባሉበት ጸንተው እንዲቀጥሉ ማድረግ እንደምንችል ምንም ጥርጥር የለውም፡፡

• ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት፤

የጥበቃ ተግባራችን፣ ከውጭ ኀይሎች ጣልቃ ገብነት እና ከውስጥ ጥቅመኞች የተነሣ ተደጋጋሚ እንቅፋት በበዛበት በአሁኑ ጊዜ፣ ‹‹በእንቅርት ላይ …›› እንደሚባለው፣ በሀገራችን በተፈጠረው ያለመረጋጋት ክሥተት፡- አብያተ ክርስቲያናት ተቃጥለዋል፣ ካህናት እና ምእመናን ተገድለዋል፤ አሁንም ስጋቱ እንዳለ፣ ከቀረበልን የአህጉረ ስብከት ሪፖርት ሰምተናል፤ በዓይናችንም አይተናል፤ ነባር የቤተ ክርስቲያናችን ይዞታዎች ሥልጣንን መከታ ባደረጉ ወገኖች እየተነጠቁ ነው፤ ምእመናን በሚደርስባቸው የማያባራ ተጽእኖና አድልዎ ከቀያቸው እየተፈናቀሉ እና እየተሰደዱ ነው፡፡

በመኾኑም እንዲህ ዓይነቱ ኢሰብአዊ ድርጊት እስከ መቼ ነው የሚቀጥለው? ይህ ድርጊት እንዲቆም እስከ ሞት ድረስ መሥዋዕት መኾን ከዚህ ጉባኤ አባላት ይጠበቃል፡፡ ይህ ጉባኤ የኀያሉ የእግዚአብሔር ጉባኤ ነው፤ ይህ ጉባኤ በኢትዮጵያ ብቻ ከሰባ ሚሊዮን ያላነሰ ሠራዊት ያለው ጉባኤ እንጂ ብቻውን አይደለም፤ ይህ ጉባኤ በሙሉ አቅሙ ሥራውን ከሠራ እና ድምፁን ካነሣ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይኾን በዓለም ዙሪያ ሁሉ ሰሚው ብዙ ነው፡፡

ስለዚህ በቤተ ክርስቲያናችን ላይ በታችኛውም የመንግሥት መዋቅር እየደረሰብን ያለውን የማንታገሠው ግፍ መንግሥት እንዲያስተካክልን ደጋግመን መጠየቅ ይኖርብናል፡፡ እኛም በጸሎት አምላካችንን ከመማፀን ጋራ ሁሌም በተጎጂው ሕዝባችን መካከል እየተገኘን በልዩ ልዩ ግፍ ልባችን የተሰበረውን የልጆቻችን ኀዘን መቅረፍ ይኖርብናል፤ ችግራቸውንም ማጋራት ይጠበቅብናል፤ የተቃጠሉ አብያተ ክርስቲያናትን እንደገና መገንባት አለብን፤ መንግሥትም በሕገ መንግሥቱ የተቀመጠውን የሃይማኖት ክብር ነፃነት እና እኩልነትን በሚሸረሽሩ የታችኛው መዋቅር ባለሥልጣናት ላይ የማያዳግም የርምጃ ማስተካከያ እንዲያደርግ ጥብቅ ክትትል ማድረግ አለብን፡፡

• ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የሲኖዶስ አባላት፤

የመንጋ ጥበቃችን ሥራ እየተሰነካከለ የሚገኘው፣ ከውጭ ኾነው በገንዘብ፣ በፖለቲካ እና በኢኮኖሚ እርስ በርሳችን በመከፋፈል በሚተነኩሱን ኀይሎች ብቻ አይደለም፡፡ በውስጣችን ያለው ያልዘመነ አሠራርም የምእመናንን ልቡና እያቆሰለ የሚገኝ ሌላው የጥበቃችን ዕንቅፋት ነው፤ በመሠረቱ ይህን ችግር ከሥር መሠረቱ ነቅለን በማጽዳት ማስተካከል ካልቻልን ችግራችን በወሳኝ መልኩ ሊቀረፍ አይችልም፡፡

በመኾኑም፣ ቀደም ሲል የተጠኑትን የቤተ ክርስቲያን ኹለንተናዊ ችግር መፍትሔ እና የመሪ ዕቅድ ጥናቶች፣ ይህ ዐቢይ ጉባኤ በወሰነው መሠረት፣ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ በአስቸኳይ ይተገብር ዘንድ ጠበቅ ያለ መመሪያ ሊያስተላልፍ ይገባል፡፡ ከእንግዲህ ወዲህ በብልሹ አሠራር አዙሪት የሚታመስ የቤተ ክርስቲያን አሠራር ሊኖር አይገባም፡፡ በዚህ ዓመት አሠራራችንን ሁሉ አስተካክለን ወደ መንጋ ጥበቃ እና ወደ ልማት ሥራችን በፍጥነት መሸጋገር አለብን፡፡

በመጨረሻም፡-

የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በቤተ ክርስቲያናችን ላይ በተደጋጋሚ እየደረሰ ያለውን ዙሪያ መለስ ጥቃት ለመመከት እና ለመከላከል ብሎም ለማስቆም፣ አንድ የጥቃት መከላከል ግብረ ኃይል እንዲሁም በየአካባቢው የሚሰነዘሩት ጥቃቶች፣ ወከባዎች፣ ተጽእኖዎችና አድሎአዊ አሠራሮችን እየተከታተልን ትክክለኛ ኢንፎርሜሽንን የሚያቀርብ የኮሙኒኬሽን ግብረ ኃይል በአሁኑ ጉባኤያችን አቋቁመን ቤተ ክርስቲያናችንንና መንጋችንን ከመከራ እንድንታደግ፤ የሀገራችንን ሰላም እና የሕዝባችንን አንድነት በጽኑ እንድናስጠብቅ አባታዊ መልእክታችንን እያስተላለፍን፣ የጥቅምቱ ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በዛሬው ዕለት መከፈቱን እናበሥራለን፡፡

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ፤ ይቀድስ፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን!

አባ ማትያስ ቀዳማዊ

ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ

ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት

ጥቅምት ፲፪ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም

አዲስ አበባ ኢትዮጵያ

 ምንጭ፡- ሃራ ተዋህዶ

ሌሎች መረጃዎችን ለማግኘት የዩቲዩብ አድራሻችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ

https://www.youtube.com/channel/UCwkzoJkVym9ALksSo97cJrA

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 5 years ago on November 15, 2019
  • By:
  • Last Modified: November 15, 2019 @ 5:58 pm
  • Filed Under: Ethiopia

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar