ዛሬ የሚጠናቀቅ የነበረው የአማራ ባንክ አክሲዮን ማኅበር የአክሲዮን ሽያጭ ለአምስት ሳምንታት መራዘሙን አደራጅ ኮሚቴው አስታውቋል፡፡
ትውልደ ኢትዮጵያውያኑ በ”ፋይናንስ ሴክተሩ”እንዲሳተፉ የተመለከተውን አዋጅ መሠረት አድርጎ መመሪያ የወጣው የካቲት 20/2012 ዓ.ም ላይ እንደሆነ አደራጅ ኮሚቴው ዛሬ በሰጠው መግለጫ አመላክቷል። ይህም ማለት የባንኩ የአክሲዮን ሽያጭ ማጠናቀቂያ እንደሆነ ተገልጾ ከነበረው የካቲት 30/2012 ዓ.ም በ10 ቀናት ብቻ የቀደመ ነው። ይህም በቂ ጊዜ ኖሯቸው በታሰበው ልክ እንዲሳተፉ አያደርግም።
የአክሲዮን ሽያጩ የተራዘመውም በተለያዩ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የአክሲዮን ሽያጩ ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ተጨማሪ ዕድል ለመስጠት መሆኑን የአደራጅ ኮሚቴው ዋና ሰብሳቢ አቶ መላኩ ፈንታ ገልጸዋል።
የአክሲዮን ሽያጩ ሲጀመር ሙስሊሙን ማኅበረሰብ ያሳተፈ እንደነበር የተናገሩት አቶ መላኩ በቂ መረጃ እንዲኖራቸው ለማድረግ በማሰብ ተጨማሪ ቀናት ማስፈለጉንም አስታውቀዋል።
የአክሲዮን ሽያጭ ቀኑ መራዘሙ የካፒታል መጠኑን ስለሚያሳድገው ቀደም ብሎ አክሲዮን ለገዙትም ተጠቃሚነታቸውን ከፍ እንደሚያደርገው ነው አቶ መላኩ ያስገነዘቡት።
በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ወገኖች አክሲዮን መግዛት የሚችሉት በውጭ ምንዛሬ እንደሆነም ገልጸዋል። ይህም የባንኩን የካፒታል አቅም ለማሳደግ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ታምኖበታል። እነዚህ ወገኖች አክሲዮን ግዥ የፈጸሙበትን “ስዊፍት ኮድ” በባንኩ ድረ ገጽ ማግኘት እንደሚችሉም አቶ መላኩ አስረድተዋል።
የአማራ ባንክ አክሲዮን ማኅበር የአክሲዮን ሽያጭ ከተጀመረ ስድስት ወራት ከ15 ቀናት ሆኖታል። በእነዚህ ጊዜያትም 145 ሺህ አክሲዮን ተሽጧል፤ የ5 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር አክሲዮን ተፈርሟል፤ 4 ቢሊዮን ብር ደግሞ የተከፈለ ካፒታል እንደሆነ አቶ መላኩ ገልጸዋል።
ዘጋቢ፡- ጽዮን አበበ -ከአዲስ አበባ
Average Rating