ሰሞኑን በጣም በብዛት ሲደርሱኝ ከነበሩ መልእክቶች አንዱ የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን ሰራተኞች ቅሬታ ይገኝበታል። ቅሬታዎቹ የመጡት መስሪያ ቤቱ የመዋቅር ስራውን አጠናቆ ያለፈው አርብ ውጤቱን ይፋ ካደረገ በሁዋላ ነበር።
ቅሬታዎቹን ሰብሰብ ሳደርጋቸው ይህንን ይመስላሉ:
– መስሪያ ቤቱ ካሉት 3 ሺህ ገደማ ሰራተኞች ውስጥ 1,080ዎቹ ምደባ አልተሰጠንም፣ በተለይ በብዛት በሲኒየርና ከዛ በላይ ባሉ መደቦች ሲሰሩ የነበሩ አልተመደብንም
– አዲስ የመጡት ሃላፊዎች ነባሮች እንዲቀጥሉ አይፈለጉም፣ ምደባው በውድድር ነው ቢባልም ሀላፊዎች ለማይፈልጉት ዝቅተኛ ነጥብ በመስጠት ለሚፈልጉት ደግሞ ከፍተኛ በመስጠት አንዱን መድቦ ሌላውን አንሳፈዋል
– አሁን በዚህ የኮሮና ቫይረስ አለምን በሚያስጨንቅበት ወቅት ይፋ መደረጉ አግባብ አይደለም
– የእኛ የሰራተኛ የወደፊት እጣ ፈንታ ምንድን ነው የሚለው አሳስቦናል የሚሉ ይገኙበታል።
በጉዳዩ ላይ ማምሻውን የቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ ሀላፊ የሆኑትን ኢ/ር ሰናይት ዳምጠውን አናግሬ ነበር። መልሳቸው ይህንን ይመስላል:
“ከዚህ በፊት በተሰራ የቢፒአር ስራ ተቋማት ሁሉ እንደ አዲስ ተደራጅተዋል። የኛ ተቋም ወደ ድልድሉ ወይም ምደባው ያልገባው ተቋሙ በጣም ግዙፍ ስለሆነ እና ሌሎችም የሚሰሩ ስራዎች ስለነበሩ በሽግግር ላይ ስለቆየ ነው። አሁን ላይ ላለፉት ወራት የተደረገው ውድድር ሂደቱ ተጠናቆ ነው ይፋ የተደረገው። ይህ ማለት አዳዲስ መደቦች አሉ፣ የታጠፉም አሉ። እዛ ላይ ካሉት 3,000 በላይ ሰራተኞች እንዲወዳደሩ ነው የተደረገው። ስለዚህ አሁን ዋናው ጉዳይ በተወዳደረበት ቦታ ማን ውጤት አገኘ ነው እንጂ ሁሉም በተቋማችን ውስጥ መስራት ይቀጥላሉ። በሚመጥናቸው ቦታ ይመደባሉ፣ ግን በፈለጉበት የስራ ቦታ እንዳይመደቡ በሌሎች ሰራተኞች ተበልጠዋል ማለት ነው። ከዚህ በሁዋላ ቅሬታ ያለው እንዲያቀርብ ይደረጋል። እዚህ እኛ ጋር 1,080 ሰው የሚፈልገውን ቦታው አላገኘም፣ ግን ደግሞ ራሳቸውን የሚጠብቅ ከ1,200 በላይ ክፍት መደብ አለ። እውነታው ይሄ ነው እንጂ ሰራተኛ የሚያሰናብት ተቋም በዚህ ወቅት የለም፣ ደሞዛቸው እና ጥቅማ-ጥቅማቸውም እንደተጠበቀ ይሆናል።”
Average Rating