የገብረ ክርስቶስ ‹‹ጎልጎታ››
የሠዓሊ ገብረ ክርስቶስ ደስታ ምናብ ውጤት የሆነው የሥነ ስቅለት ሥዕል
ኪንና ባህል ኮሮና ቫይረስ
የገብረ ክርስቶስ ‹‹ጎልጎታ››
15 April 2020
ሔኖክ ያሬድ
ከኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ዓበይት በዓላት አንዱ የእግዚእ ኢየሱስ ስቅለት የሚታሰብበት ነው፡፡ ኢትዮጵያና የምሥራቅ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያን ይህንኑ ዓመታዊ በዓል ከነገ በስቲያ ዓርብ ሚያዝያ 9 ቀን 2012 ዓ.ም. ያከብራሉ፡፡
ጎርጎርዮሳዊውን የዘመን አቆጣጠር የሚከተሉ በምዕራቡም ሆነ በምሥራቁ ዓለም የሚገኙ ምዕመናን ባለፈው ሳምንት ሚያዝያ 2 ቀን በዓሉን አክብረውታል፡፡ የሁሉም አከባበር ግን እንደወትሮው በየአገሮቹ በተለይም በኢየሩሳሌም ቅዱስ መካነ መቃብር ቤተ ክርስቲያን አደባባይ በመውጣት ለማክበር፣ ሥርዓተ አምልኮን ለመፈጸም ያልታደሉት በወረርሽኙ የኮሮና ቫይረስ ምክንያት ነው፡፡
እግዚእ ኢየሱስ ክርስቶስ መጋቢት 27 ቀን 34 ዓ.ም. በቀራንዮ ለመሰቀል መሰቀያውን ተሸክሞ የተጓዘበት የጥንታዊቷ ኢየሩሳሌም ጎዳናዎች በየዓመቱ ምዕመናን በዓሉን ሲያከብሩ መስቀሉን እየተሸከሙ እያጨናነቁ ያልፉበት ነበር፡፡
ዘንድሮ ግን የኢትዮጵያው ደብረ ሥልጣን (ዴር ሡልጣን) ገዳም የሚገኝበት የቅዱስ መካነ መቃብር ቤተ ክርስቲያን በመዘጋቱ አካባቢውን ሁሉ ጭርታ ወሮታል፡፡
ምዕመናን በየአገሮቻቸው በየቤቶቻቸው በዓሉን ከየአብያተ ክርስቲያን የቴሌቪዥን ሥርጭትን በመከታተል አክብረውታል፡፡ እያከበሩትም ነው፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሆሣዕና በዓልን ባለፈው እሑድ ካከበረች በኋላ ከሰኞ ጀምሮ ሰሙነ ሕማማትን እያሰበች ነው፡፡ በየአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ካህናትና ጥቂት ምዕመናን የሚሳተፉበት፣ ከታላላቅ ካቴድራሎች ደግሞ በቀጥታ በሚተላለፈው የቴሌቪዥን ሥርጭት ምዕመናን በየቤታቸው የሥርዓተ አምልኮ ተሳታፊ ሆነው ይገኛሉ፡፡
የገብረ ክርስቶስ ‹‹ጎልጎታ››
ዓምና በኢየሩሳሌም የስቅለት በዓል ሲከበር ኢትዮጵያውያን መስቀል ተሸክመው ሲጓዙ
የገብረ ክርስቶስ ‹‹ጎልጎታ››
የእግዚእ ኢየሱስ ክርስቶስ ዕለተ ስቅለትን ታላላቅ የዓለም ሠዓሊያን በሥራዎቻቸው እንደየምናባቸው ገልጸውታል፡፡ ከእነዚህም አንዱ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሽልማት ድርጅት የሥነ ሥዕል ዘርፍ ተሸላሚው ገብረ ክርስቶስ ደስታ ነው፡፡ ገብረ ክርስቶስ ለሥዕሉ የሰጠው ርዕስ ‹‹ጎልጎታ ኤሎሄ ሥነ ስቅለት›› ይሰኛል፡፡
በሥዕሉ ላይ ሠዓሊና መምህር እሸቱ ጥሩነህ ‹‹ገብረ ክርስቶስ ደስታ – አጭር ትውስታና ጨረፍታዊ ዕይታ›› በሚል ርዕስ በጻፈው ሐቲት ውስጥ የሥዕሉን አንድምታ እንዲህ ፈትቶ አቅርቦታል፡፡
ገብረ ክርስቶስ ደስታ በትምህርት ዓለም እያለ በመጀመሪያዎቹ የፈጠራና የፍለጋ ጊዜው እ.ኤ.አ. በ1961 ከሠራቸው ሥዕላት ውስጥ መጠቀስ የሚገባው ሥራ ቢኖር፣ የኢየሱስ ክርስቶስ ሥነ ስቅለት ነው፡፡ ይህንን ሥዕል ለምን እንደሠራው አንዳንድ መሠረታዊ ግምቶች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ገብረ ክርስቶስ ደስታ የአለቃ ነገዎ፣ ያውም በጣም የሚወዱትና የሚሳሱለት ወንድ ልጃቸው ነው፡፡ የኦርቶዶክስ ሃይማኖት እምነት ከቤተ ክርስቲያን ሥርዓተ ትምህርት ጋር በወጉ እንዲያውቅ አስተምረው አሳድገውታል፡፡ ገብረ ክርስቶስ ብለውም ስም ሲያወጡለት ምክንያት ሳይኖራቸው አይቀርም፡፡
‹‹ገብረ ክርስቶስ ደስታ የኢየሱስ ክርስቶስን ስቅለት ሥዕል ሲሥል፣ እንደማንኛውም አማኝ ክርስቲያን ብቻ አይደለም ብለን መከራከር እንችላለን፡፡ ወደኋላ በወጣትነት ዕድሜው ከደረሰበት አካላዊ ሕመም አኳያ፣ አንድም ለእምነትና ለፈውስ፣ አንድም ለጥበብና ለፈጠራ ኃይል መነሻ እንዲሆነው፣ ምክንያት አግኝቶ ሥሎታል የሚል አጠቃላይ ግምት በደምሳሳው ይኖረናል፡፡ ይህ የገብረ ክርስቶስ ደስታ የሥነ ስቅለት ድርሰት፣ ቅርፅና ይዘት በሁለት አንጻራዊ ሁኔታ ላይ የተቃኘ ነው፡፡ በቅርፁ ዘመናዊ አቀራረብ ሲኖረው፣ በይዘቱ ከሞላ ጎደል በመጽሐፍ ቅዱስ ሁነታ ላይ (Events) የተመሠረተ ሃይማኖታዊና ጥንታዊ ርዕስ ነው፡፡
‹‹በቅርፃዊ አቀራረቡ ሲታይ በወርቃማና ብርማ የብርሃን ድባብ ውስጥ፣ በጥቁር ቀለማት፣ ዓምዳዊና አግድማዊ ወይም መስቀልያ በተሰመሩ ወፍራምና ቀጭን መስመሮች የተሞላ ነው፡፡ በመሆኑም የተመልካችን ዓይን በሰሌዳው ሙሉ ያለዕረፍት እንዲሮጥ ያደርጉታል፡፡ መስመሮቹ በደጀንነት ተደጋግመው በመኖራቸውም ጥልቀትን በሰሌዳው ላይ ከመፍጠራቸውም በላይ፣ መስኮታዊ ትዕይንት አላቸው፡፡ ተመልካች ዕረፍት የሚያገኘው አብዛኛውን የሰሌዳ ክፍል በተቆጣጠረው፣ ግን ትንሽ ቀይ ኅብረ ቀለም ነው፡፡ ይህ ብቸኛ የቀይ ኅብረ ቀለም መስቀልያ አቀባብና አቀማመጥ፣ ሥዕላዊ ድርሰቱን አትኩረን እንድናይ ይጋብዘናል፡፡
‹‹በይዘታዊ አቀራረቡ ፍጹም ንዑዳዊ እውነታዎችንና ተምሳሌትን፣ በክርስቶስ የሥነ ስቅለት ሥዕል፣ ገብረ ክርስቶስ ሲሥል የመስዋዕትነትን፣ የቤዛነትን፣ የህያውነትንና የዘላለማዊነትን፣ እንዲሁም የነፃነትንና የሰላምን ምንነት ባጭሩ በኅብረ ቀለማት የቃኘበትና የተቀኘበት ነው፡፡
‹‹መስቀሉ እውነታዊ ነው፡፡ የተሰቀለው ክርስቶስ ግን ተምሳሌታዊ ነው፡፡ ሥዕሉ እስከ ተሠራበት እስከዚያን ጊዜ ድረስ ብዙ ሠዓሊዎች አካሉን ወይም ሥጋውን አልፎም እውነታዊ ምስሉን ከነስቃዩ ይሥላሉ እንጂ፣ እንደ ገብረ ክርስቶስ ክቡር ደሙን በቀይ ኅብረ ቀለም ብቻ ተምሳሌት አድርገውና ወስነው የሠሩ የሉም፡፡ ይህን በሚመለከት የጀርመን አገር ጓደኛው እጓለ ገብረ ዮሐንስ እንዲህ ጽፏል፡፡
ሠዓሊ ተብሎ የጎልጎታን ተራራ ያልወጣ ትልቁን ትራጀዲ ያላየ የለም፣ ግን የገብረ ክርስቶስ ሥነ ስቅለት ለብቻው ነው፣ ቀለም ተናጋሪ ነው፣ የሚታየው ንጹሑ ብቻ ነው ግራና ቀኝ የነበሩት ፈያት ቦታ የላቸውም ተዘንግተዋል፡፡ ወይም ሠዓሊው ሊያያቸው አልፈለገም ይገርማል፣ ጥበብ ከንጹሕነት ከጽርየት ከርቀት ብቻ እንጂ ከሌላ ጋር ግንኙነት የሌላት መሆኑን ለመረዳት ይቻላል፡፡ ይህ በጋራ የምካፈለው ሐሳብ ነው፡፡››
የገብረ ክርስቶስ ‹‹ጎልጎታ››
ዘንድሮ የኢየሩሳሌም ወደ ጎልጎታ የሚያመራው መንገድ በኮሮና ምክንያት ጭር ብሏል
Average Rating