“ኮቪድ19 ምርጫን ማራዘም እና የህግ አማራጮች” በሚል ርዕስ ውይይት እየተካሄደ ነው
አዲስ አበባ ፣ ሚያዚያ 21 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በኮቪድ19 ምክንያት ቀጣዩን ምርጫ ለማካሄድ አስቸጋሪ በመሆኑ መንግስት አራት የመፍትሄ አማራጮችን አቀረበ።
“ኮቪድ19 ምርጫን ማራዘም እና የህግ አማራጮች” በሚል ርዕስ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተገኙበት መንግስት ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ሲቪክ ማህበራት ጋር ውይይት እያካሄደ ነው።
ኢትዮጵያ በህገ መንግስቱ መሰረት እስከ ነሃሴ ወር ማለቂያ ድረስ አጠቃላይ ምርጫ የማካሄድ ግዴታ ቢኖርባትም የኮቪድ19 ወረርሽኝ ምርጫን ማከናወን የማያስችል ደረጃ ላይ በማድረሱ ምክንያት ህግና እውነታውን አጣጥሞ መሄድ አስፈላጊ መሆኑ ተነስቷል።
የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ምክትል አቃቤ ህግ ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ እንዳሉት ችግሩን ህገ መንግስታዊ ስርአቱን በማያፋልስ መልኩ ለመቅረፍ አራት የመፍትሄ አማራጮች ተቀምጠዋል።
1. የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን መበተን
2. የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅ
3. ህገ መንግስት ማሻሻል
4. የህገ መንግስት ትርጓሜ መጠየቅ ናቸው ብለዋል።
አማራጭ 1 የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን መበተን፦ በህገ መንግስቱ አንቀጽ 60/1 መሰረት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የስልጣን ዘመኑ ከማለቁ በፊት አዲስ ምርጫ ለማካሄድ በምክር ቤቱ ፈቃድ ምክር ቤቱ እንዲበተን ማድረግ ይችላል።
በዚህ አንቀጽ እንደሰፈረው ምክር ቤቱ የተበተነ እንደሆነ ከስድስት ወር ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ምርጫ መደረግ አለበት። ይህም እስከ የካቲት ወር ድረስ ምርጫ ሳይካሄድ ለመቆየት ያስችላል።
የመፍትሄ ሃሳቡ ጠንካራ ጎን – ሂደቱ የሚጠይቀው አብላጫ ድምጽ ቀላል ነው።
ይህ አካሄድ በፓርላሜንታዊ ስርአት የተለመደ ቢሆንም የራሱ ውስንነቶች አሉበት። በአንቀጽ 60/5 መሰረት ምክር ቤቱ ከተበተነ በኋላ ሃገሪቱን የሚመራው የፖለቲካ ድርጅት የመንግስትን የዕለት ተዕለት ስራ ከማከናወን እና ምርጫን ከማካሄድ በስተቀር አዲስ አዋጆችን፣ ደንቦችን እና ድንጋጌዎችን ማውጣት ወይም ነባር ህጎችን መሻርና ማሻሻል አይችልም።
ይህም ለተለያዩ ፈተናዎች በቂ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል ሙሉ መንግስት እንዳይኖር ያደርጋል። በየክልሉ ህገ መንግስት መሰረት ተመሳሳይ አማራጭ አለመኖሩም ድክመቱ ነው።
አማራጭ 2 የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፦ ጠንካራ ጎኑ አስፈላጊውን ስልጣን እና ሃላፊነት ያለው መንግስት እንዲኖር ያስችላል። በሃገር አቀፍ ደረጃም ተፈጻሚ ይሆናል።
በህገ መንግስቱ አንቀጽ 93/1 መሰረት የውጭ ወረራ ሲያጋጥም ወይም ህገ መንግስታዊ ስርአቱን አደጋ ላይ የሚጥል ሁኔታ ሲከሰትና በተለመደ የህግ ማስከበር ስርአት መቋቋም የማይቻል ሲሆን፤ ማናቸውም የተፈጥሮ አደጋ ሲያጋጥም ወይም የህዝብን ጤንነት አደጋ ላይ የሚጥል በሽታ ሲከሰት የፌደራሉ መንግስት የሚኒስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የመደንገግ ስልጣን አለው።
በአንቀጽ 93 እንደሰፈረው ከህገ መንግስቱ አንቀጽ 1፣ 18፣ 25 እና 39/1 እና 2 በስተቀር ያሉ መብቶች ላይ ገደብ ይጥላል። በዚህም የምርጫ ጊዜን ማራዘም ይቻላል።
ሆኖም ይህ አማራጭ ብቻውን ተግባራዊ ቢደረግ ምርጫው በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማዕቀፍ ውስጥ ይሆናል፤ ተዓማኒነት እና ነጻነቱንም ጥያቄ ውስጥ ይጥላል።
እንዲሁም ህገ መንግስታዊ ስርአቱን የሚያዳብር አይሆንም።
አማራጭ 3 ህገ መንግስት ማሻሻል፦ በህገ መንግስቱ ግልጽ የሆነ መሰረት ያለው ሲሆን አንቀጽ 104 እና 105 ላይ በግልጽ ተቀምጧል።
የህገ መንግስት ማሻሻያ ሃሳብን ለማመንጨት ሶስት ምዕራፎች አሉ።
የህገ መንግስት ማሻሻያ ሃሳብን ማመንጨት፤ የፌደራል መንግስት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ2/3 ድምጽ ከደገፈው ወይም የፌዴሬሽኑ ምክር ቤት በ2/3 ድምጽ ሲያጸድቀው ነው።
የፌዴሬሽኑ አባል ከሆኑ ክልሎች 1/3 ድምጽ (አሁን ባለው ሁኔታ ከዘጠኙ ሶስቱ ክልሎች በምክር ቤቶቻቸው ከደገፉት የማሻሻያ ሃሳብ መንጭቷል ማለት ይቻላል።
መላውን ህዝብ ያሳተፈ ውይይት ማድረግ።
የማሻሻያ ሃሳቡን ማጸደቅ፤ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት በጋራ ስብሰባ በ2/3 ድምጽ የቀረበውን ማሻሻያ ሲያጸድቁት እና ከፌዴሬሽኑ አባል ክልሎች ምክር ቤቶች የ2/3 ክልሎች ምክር ቤቶች በድምጽ ብልጫ የቀረበውን ማሻሻያ ሲያጸድቁት ነው።
ይህም የራሱ ውስንነቶች አሉት፤ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅት የዜጎችን በሃገራቸው ጉዳይ የመሳተፍ መብት የሚፈታተን ነው። ህዝባዊ ውይይት ለማድረግ ኮቪድ19 እንቅፋት ይሆናል። ሌሎች የህገ መንግስት ማሻሻያ ጥያቄዎችን አብሮ ለማየት ምቹ ሁኔታና ጊዜ አይደለም።
በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅት የሚደረግ የህገ መንግስት ማሻሻያ ቅቡልነቱ ጥያቄ አለበት።
ጥንካሬው አማራጩ ህገ መንግስታዊ ነው።
አማራጭ 4 የህገ መንስት ትርጓሜ መጠየቅ፦ በህገ መንግስቱ አንቀጽ 62/1 እና አንቀጽ 84/1 መሰረት በግልጽ ተቀምጧል።
ጠንካራ ጎኑ የህገ መንግስት ክፍተቶችን ለመሙላት የተለመደ አሰራር ነው፤ በህገ መንግስቱ የተሻለ ተቀባይነት አለው።
በአንቀጽ 38 (የመምረጥና የመመረጥ መብት)፣ 58 (የምክር ቤቱ ስብሰባ እና የስራ ዘመን) እና 93 (ስለ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ) መካከል ያለውን ክፍተት ለማስወገድ ያግዛል።
ውስንነቱ በዚህ ሂደት የሚገኘው ውጤት በእርግጠኝነት ቀደም ብሎ መተንበይ አይቻልም። የአሳታፊነት ጥያቄም ይነሳበታል።
በአላዛር ታደለ
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።
Average Rating