Read Time:15 Minute, 56 Second
ለወደፊት የዜና እና የትረካ ዝግጅት በቀላሉ እንዲደርስዎት የማለዳ ሚዲያ ዩቲዩብን ሰብስክራይብ ያድርጉ
https://www.youtube.com/channel/UCqAuXzJD_f5q7zV1ItVKAdA?view_as=subscriber
ታህሳስ ወር 1953 ዓ.ም ኢትዮጵያ ውስጥ ከተደረገው የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ በኋላ መወሰድ ስላለባቸው የፖሊሲ እርምጃዎች በክቡር አቶ ሐዲስ አለማየሁ ለግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ ጥር 23 ቀን 1953 ዓ.ም የተፃፈ ማስታወሻ፡-
ማስታወሻ
በቅርቡ በኢትዮጵያ ተነሥቶ ያለፈው ሁከት፤
ለኢትዮጵያ ደህንነትና ግርማዊነትዎ ለወጠነው ሥራ መልካም ፍጻሜ የሚመኙትን ሰዎች ሁሉ እጅግ ሊያሳስብና የእውነተኛ ስሜታቸውን ሳይደብቁ በቅንነት እንዲገልጹ ሊያደርጋቸው ይገባል ብዬ ስለማምን እኔም ከነዚህ ሰዎች እንዳንዱ የሚጠቅም የመሰለኝ አሳብ ከዚህ ቀጥዬ ለማቅረብ እንዲፈቀድልኝ በፍጹም ትሕትና እለምናለሁ።
ማናቸውም ነገር መነሻ ምክንያት ሳይኖረው… እንዲሁ ከደልዳላ ሜዳ አይፈልቅም፤ ወይም ከጥሩ ሁከት አይነሣም፤ እንዲህ ለምሳሌ – አለመደሰት፤ ወይም ቅርታ – ከሌለ ሁከት አይነሣም፤ እንዲህ ላለውም አለመደሰት፣ ወይም ቅርታ ምክንያት የሆኑትን ነገሮች በጊዜ መርምሮ ካላስወገዷቸው፣ ይዋል ይደር እንጂ ሁከት መነሳቱ አይቀርም። አንዳንድ ጊዜ በሕዝብ መሐከል ቅርታ መኖሩን የሚያውቁ ሰዎች ተቆርቋሪዎች ሆነው በመታየት ለግል ዓላማቸው መሣርያ ያደርጉታል። ምናልባትም በቅርቡ በኢትዮጵያ ሁከት ያስነሡት ጥቂት ሰዎች በዚሁ መንፈስ የተመሩ ናቸው ለማለት ይቻል ይሆናል።
የሆነ ሆኖ አለመደሰት፤ ወይም ቅርታ ካለ ሁከት የሚነሣበት ጊዜ፤ የሚነሣበት መልክ፤ የሚያነሡት ሰዎች ወይም ዓላማው የተለያዩ ይሁኑ እንጂ መነሳቱ ስለማይቀር ከሁሉም የሚሻለው መነሻ የሆኑትን ምክንያቶች በጊዜ ደህና አድርጎ መርምሮ ማስወገድ ነው።
ለማናቸውም ነገር መነሻ የሆነው ሥሩ እንደተደበቀ ተቀምጦ ከላይ የሚታየውን ቅርንጫፉን ብቻ ቢጨፈጭፉትና ለጊዜው እንኳ የጠፋ ቢመስል የተመቸ ጊዜ ሲያገኝ የተደበቀው ሥር ዳብሮ፤ ተስፋፍቶ፤ ለማጥፋትም እንደሚያስቸግር ሆኖ በብዛትና በብርታት ይነሣል። ይህ እንዳይሆን መነሻ የሆነው ምክንያት ደህና ሆኖ ተመርምሮ ከታወቀ በኋላ ሁለተኛ እንዳያቆጠቁጥና እንዳይቀጥል ከሥሩ መቆፈርና ነቅሎ መጣል ነው እንጂ ከላይ ቅርንጫፉን መጨፍጨፍ ምንም ያኽል ጠቃሚ አይሆንም።
ስለዚህ ላለፈውም ይሁን ለወደፊት በሕዝብ መሐከል ለቅርታና ለሁከት መነሻ የመሰሉኝን ምክንያቶችና ዳግመኛ ሁከት የሚያስከትል አለመደሰት ወይም ቅርታ እንዳይነሣ ዓይነተኛ መከላከያ የመሰለኝን ሀሳብ በፍጹም ቅንነትና ግርማዊነትዎን ለመርዳት በማሰብ ብቻ ተመርቼ ከዚህ እንደሚከተለው አቀርባለሁ።
፩ የኢትዮጵያ መንግሥት ስሪት
በጠቅላላው የኢትዮጵያ መንግሥት ስሪት – ምንም እንኳ ከግርማዊነትዎ በፊት በነበሩት ነገሥታት ጊዜ ከነበረው ስሪት ጋር ሲተያይ የማይቀራረብ፤ እጅግ የቀደመ ቢሆን – እንደ ኢትዮጵያ በነፃነት ብዙ ዘመን ከቆዩት አገሮች ስሪት ጋር ሲመዛዘን ተካክሎ የማይገኝ መሆኑንና ለምንኖርበት ዘመን የማይስማማ መሆኑን የውጭ አገር ጸሐፊዎች ስለሚጽፉና በኢትዮጵያም ውስጥ የተማሩ ሰዎች ስለሚገልጹ – እንዲህ ያሉትን ጽሑፎች የሚያነቡና የተማሩ ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ፣ ከነሱ ጋር ግንኙነት ያላቸው ሁሉ እርስ በርሳቸው የመቆርቆርና የቅርታ ስሜታቸውን ከብዙ ጊዜ ጀምሮ እንደሚገልጹ በያካባቢው ይሰማል።
ግርማዊነትዎ እንደ ሌሎች አገር ነገሥታት ሳይገደድና ደም ሳይፈስ በፈቃዱ ለሕዝቡ ሕገ መንግሥት መሥራቱን፤ ሕዝቡ በመረጠው ፓርላማ አማካይነት ለመንግሥቱ ሥራ ተካፋይ እንዲሆን ማድረጉን፤ ኢትዮጵያ በኢኮኖሚክ፤ በሶሻል፤ በአስተዳደርና በትምህርት ረገድ ብዙ ዘመን ከቆየችበት የእስረኛነት ኑሮ ሰብራ እንድትወጣ ማድረጉን፤ በኢትዮጵያ ውስጥም ሆነ በውጭ የሚክድ የለም። ነገር ግን ይህም ሁሉ ሆኖ ሕዝቡ ለመንግሥቱ ሥራ በሙሉ ተካፋይ ለመሆንና ነፃ እንደመሆኑ መጠን ራሱን ለማስተዳደር በሕገ መንግሥቱ የተሰጠው መብት፣ ከሌሎች አገሮች ሕገ መንግሥት ጋር ሲመዛዘን ሙሉ ሆኖ ስለማይገኝ ላለመደሰት ወይም ለቅርታ ምክንያት ሆኗል።
1) ለምሳሌ፡- “የኢትዮጵያ ፓርላማ አባሎች የሚመረጡበት የፖለቲካ፤ የኢኮኖሚክ፤ የአስተዳደርና የሶሻል ዓላማና ለእንደዚህ ያለው ዓላማ ማስፈጸምያ ፕሮግራም የሌላቸው ከመሆናቸውም ሌላ፡- ሕግ ለማውጣት የመጨረሻ ሥልጣን እንዳይኖራቸው በሕገ መንግሥቱ (አንቀጽ 88፣ 89፣ 90፣ 91) የተወሰኑ ስለሆኑ፤ በጠቅላላው የኢትዮጵያ ፓርላማ ሥልጣን ቢበዛ የአማካሪነት ነው እንጂ – እንደ ሌላ አገሮች ፓርላማዎች የመወሰን ሥልጣን አይደለም” የሚል ነቀፋ አለ።
ሁለተኛ፡- “ካንድ ወገን በሕገ መንግሥቱ (አንቀጽ 26፣ 27፣ 29፣ 66፣ 68፣ 69) የኢትዮጵያ መንግሥት መሥርያ ቤቶች ሁሉ አቋቋማቸውም ሆነ የያንዳንዱ መሥርያ ቤት ባለሥልጣኖች የሚሾሙበት፤ የሚያድጉበትና የሚሻሩበት – በሕግ ሳይሆን በንጉሠ ነገሥቱ ፈቃድ መሠረት በመሆኑና ኃላፊነታቸው ለንጉሠ ነገሥቱ በመሆኑ በሥራቸው ጉድለት ቢኖር ኃላፊነቱን ወደ መጨረሻው ባለሥልጣን፤ ወደ ንጉሠ ነገሥቱ ሲመሩ ሲችሉ ከሌላ ወገን በሕገ መንግሥቱ (አንቀጽ 4-26) ንጉሠ ነገሥቱ በማናቸውም የአስተዳደር ጉድለት የማይወቀሱ ስለሆኑ የኢትዮጵያ መንግሥት መሥርያ ቤቶችና ባለሥልጣኖች ክስና ወቀሳ እንደማይደርስባቸው ሆነው መግቢያ በሌለው የሕገ መንግሥት አጥር የተጠበቁ ናቸው” እየተባለ ይታማል።
ሦስተኛ፡- “ዛሬ ከዓለም ውስጥ በሬፑብሊክ መንግሥት የሚተዳደሩት አገሮች ቀርተው በንጉሠ ነገሥት፤ በንጉሥና በፕሪንስ ከሚተዳደሩት አሥራ ሰባት አገሮች መሐከል እንኳ በጣም የሚበዙት አገሮች ሕገ መንግሥቶች የመጨረሻው የመንግሥት ሥልጣን የሚመነጨው ከሕዝብ መሆኑን ሲያውጁ – የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት (አንቀጽ 26) የሥልጣን ምንጭ ንጉሠ ነገሥቱ መሆናቸውን ስለሚያውጅ ይህ ኢትዮጵያ የፖለቲካ መብት በሙሉ ለሕዝብ ባልተሰጠበት፤ በመሐከለኛው ዘመን የምትኖር ለመሆንዋ አንድ ምልክት ነው” የሚል የነቀፋ ድምፅ ይሰማል።
ከዚህ በላይ ስለ ኢትዮጵያ መንግሥት ሥሪት ለምሳሌ ያኽል ያመለከትኋቸውና እነሱን የመሳሰሉት ኢትዮጵያ በተለይ በፖለቲካ ያደረገችው እርምጃ – እንደስዋ ረዥም ዘመን በነፃነት ከኖሩት አገሮች ብቻ ሳይሆን በቅርቡ ከቅኝ ግዛት ነፃ ከወጡት አገሮች ጭምር የማይተካከል መሆኑን ስለሚያመለክቱና ወደፊትም የመንግሥቱ ስሪት ካልተሻሻለ ይህኑ የፖለቲካ እርምጃዋን እንዳታፋጥን እንቅፋት ይሆናል የሚል ስሜት ስላለ በዚህ ምክንያት ቅርታ የተፈጠረ መሆኑ የታወቀ ነው።
፪ የኢትዮጵያ መንግሥት አስተዳደር
ስለ ኢትዮጵያ መንግሥት ስሪትና ስለ ሕገ መንግሥቱ ጉድለት የውጭ አገር ሰዎች የሚጽፉትን የሚያነቡም ሆነ፤ ራሱን ሕገ መንግሥቱን አጥንተው የሚቅፉ ኢትዮጵያውያን፤ ወይም ከነሱ ጋር የኢትዮጵያንና የሌሎችን አገሮች ሕገ መንግሥቶች ለማመዛዘን የሚችሉ ሰዎች በመጠኑ ትምህርት ያላቸውና የዓለምን ሁኔታ መከታተል የሚችሉ መሆን ስላለባቸው – ቁጥራቸው እጅግ ብዙ ነው ለማለት አይቻልም ይሆናል። ነገር ግን የመንግሥቱ አስተዳደር ከያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የዕለት ተግባር ጋር የተያያዘ ስለሆነ የአሠራሩን ውጤት መመልከት እንጂ ትምህርት የሚያስፈልግ ባለመሆኑ እንዲህ ያለው አስተዳደር የሚሰጠው አገልግሎት ቢያምር ለማመስገን፤ ቢከፋ ለመንቀፍ የሚችሉት ቁጥራቸው እጅግ ብዙ ናቸው።
በእውነቱ ስለ ኢትዮጵያ አስተዳደር ጉድለቱ የማን፤ ወይም በምን ምክንያት ለመሆኑ ላይ የአሳብ ልዩነት ይኖራል እንጂ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ በጠቅላላው አስተዳደሩን ከመንቀፍ በቀር የሚያመሰግን ሰው ሰምቼ አላውቅም።
ተራው ሕዝብ ከርሻ፤ ከንግድ፤ ከፍርድ፤ ከአገዛዝ፤ ከትምህርት፤ ከሕክምና፤ ከመገናኛና እነሱን ከመሳሰሉት፤ ለኑሮው አስፈላጊ ከሆኑት አገልግሎቶች ጋር የተያያዙት ጉዳዮች በቅልጥፍናና በሚገባ ስላልተፈጸሙለት በጠቅላላው የመንግሥቱን ሠራተኞችና ባለ ሥልጣኖች ይወቅሳል። በታችኛው ደረጃ ያሉት የመንግሥት ሠራተኞች – “አገልግሎታችንና ችሎታችን የሚመዛዘንበት፤ በዚያውም መጠን ደመወዛችንና ደረጃችን የሚያድግበት ሕግ ስለሌለና ሥራ፤ የደመወዝና የደረጃ ዕድገት የሚገኝ በወገን፤ ወይም በጉቦ ስለሆነ፤ የመንግሥት ሥራም ትተን የግል ሥራችንን እንዳንሠራ ለዚህ ነፃነት ስለሌለን ሕዝብንም ሆነ ራሳችንን ለማገልገል አልቻልንም” እያሉ ያማሉ። ከነሱ ቀጥለው ወደ ላይ በሹመት ደረጃ ያሉት፡- “ችሎታ የሌላቸው፤ በምቀኝነት የተሞሉ ሚኒስትሮች እንዳይሠሩ ችሎታ ስለሚያንሳቸው፤ የበታቾቻቸውን እንዳያሠሩ ይታወቁና ቦታችነን ይወስዱብናል ብለው በመስጋታቸው ሥራው ወደፊት እንዳይራመድ አገዱት” እያሉ ሚኒስትሮችን ያማሉ፤ ሚኒስትሮች ደግሞ – “ሥራችንን ደህና አድርገን እንዳናቋቁምና የሥራ ችሎታ አላቸው የምንላቸውን ሠራተኞች ቀጥረን እንዳናሠራ የዝርዝሩ ሥራ አመራርና የያንዳንዱ ዝቅተኛ ሹም አመራረጥ ሳይቀር የጃንሆይ ፈቃድ የሚያስፈልገው ስለሆነና ትንንሹን ነገር እንኳ ያለጃንሆይ ፈቃድ እንዳንሠራ ስለተከለከልን፤ ይህ የሥልጣን መከልከል ሥራውን ገደለው” እያሉ ያማርራሉ። ግርማዊነትዎ በበኩሉ – “የያንዳንዱ ሥራ ከባድነትና ከፍ ያለ ሥልጣን የሚጠይቀውን ኃላፊነት መሸከም የሚችሉ ሰዎች ቁጥር በማነሱ ችግር መፈጠሩንና ሥራው እንደሚፈለገው ተፋጥኖ ሊራመድ አለመቻሉን እየገለጸ ያዝናል።”
በዚህ አኳኋን ኃላፊነቱ ከታች ወደላይ ሲወረወር፤ ከላይ ተመልሶ ወደታች ሲወረወር ማረፍያው እዚህ ነው ለማለት የአሳብ ልዩነት ይኑር እንጂ፤ የአስተዳደር ጉድለት መኖሩና ሥራው ሰው ሁሉ እንደሚመኘው ተካክሎና ተፋጥኖ ሊራመድ አለመቻሉ በሁሉም ዘንድ የታወቀ ነው ለማለት ይቻላል።
፫ የኢትዮጵያ ልማት
ያንድ አገር ልማት ከመንግሥቱ ሥሪትና ከአስተዳደሩ ጋር የተያያዘ ስለሆነ በመንግሥቱ ሥሪትና በአስተዳደሩ መልካምነት፤ ወይም መጥፎነት መጠን ልማቱ ከፍ፤ ወይም ዝቅ ያለ ይሆናለ።
የኢትዮጵያ የፖለቲካ፤ የኢኮኖሚክ፤ የሶሻል፤ የትምህርትና እነሱን የመሳሰሉት፤ የሕዝብ ኑሮ ደረጃ መለኪያ የሆኑ ነገሮች ልማት ከሁለት ወገን ሊታይ ይችላል።
ካንድ ወገን፡- ዛሬ ኢትዮጵያ በፖለቲካ፤ በኢኮኖሚክ፤ በሶሻልና በሌሎችም እዚህ በተቆጠሩት ነገሮች የደረሰችበት ደረጃ ከግርማዊነትዎ በፊት በነገሡት ነገሥታት ዘመነ መንግሥት ከነበረችበት ደረጃ እጅግ ከፍ ያለ መሆኑ አይጠረጠርም። ነገር ግን ከሌላ ወገን የመንግሥቱ ስሪት ካሁኑ በተሻለ አኳሀን ቢሠራና፣ አስተዳደሩም ካሁኑ በተሻለ አመራር ቢመራ ኖሮ – የኢትዮጵያ ልማት ካሁኑ የበለጠ ከፍ ወዳለ ደረጃ ሊደርስ አይችለም ነበር ወይ? ተብሎ ሲጠየቅ፤ በብዛት የሚሰማው ድምፅ – ካሁኑ ወደበለጠ ደረጃ ለመድረስ ይችል ነበር የሚል ነው።
በፖለቲካ የኢትዮጵያ ሕዝብ የምንለው – ከአማራ፣ ከትግሬ፤ ከጋላና ከሌሎችም ልዩ ልዩ ቋንቋ፤ ልማድ፤ ዘር፤ ወይም ሃይማኖት ካላቸው ክፍሎች አንድ ላይ ሆኖ በኢትዮጵያ ዘውድ ሥር የሚተዳደረው ነው። ነገር ግን እነዚህ ልዩ ልዩ ቋንቋ፤ ልማድ፤ ዘር ወይም ሃይማኖት ያላቸው ክፍሎች ምንም እንኳ ባንድ ላይ “የኢትዮጵያ ሕዝብ” የሚል ስም ቢሰጣቸውና ባንድ ዘውድ ሥር ቢተዳደሩ – በደስታም ይሁን በመከራ፤ በመልካም ይሁን በክፉ ጊዜ አንድ ላይ የሚያስተሳስረውና ሕዝብን አንድ የሚያሰኘው፤ የሕብረት ማሠሪያ ያላቸው ናቸው ለማለት አያስደፍርም።
በኢትዮጵያ ልዩ ልዩ ክፍሎች የሚኖሩ ሕዝቦች – በቋንቋ፤ በልማድ፤ በዘርና በሃይማኖት እንደመለያየታቸው መጠን የሕይወት ዓለማቸውም የተለያየ ነው። ከመሐከላቸው አንዳንዶቹ ከሁሉም የበላይነት ስሜት የሚሰማቸውና ይህ የበላይነት እንዲሁ እንዳለ እንዲኖር የሚመኙ ናቸው። ሌሎቹ – የበላይ ነን ከሚሉት ባንበልጥ አናንስም የማለት ስሜት የሚሰማቸውና ይህኑ ለማረጋገጥ አጋጣሚ ጊዜ ለማግኘት የሚመኙ ናቸው። ሦስተኛ የበታችነት ስሜት የሚሰማቸውና የበላይ ነን የሚሉትን ክፍሎች ኃይል ሰብሮ ነፃ የሚያወጣቸው ክፉ ቀን እንዲመጣ የሚጠብቁና የሚመኙ ናቸው።
በዚህ አኳሆን የሕይወት ዓላማቸው የተለያየ ክፍሎች “የኢትዮጵያ ሕዝብ” ከሚባለው ስምና ከንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት የጦር ኃይል በቀር ሌላ የሚያስተባብሩዋቸውና አንድላይ የሚያስተሳስሩዋቸው የፖለቲካ ድርጅቶች (Political Institutions) ስለሚጐድሉዋቸው – በእውነተኛው የፖለቲካ ትርጉም የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድ ነው ለማለትና ወደ ከፍተኛው የፖለቲካ ደረጃ ደርሷል፤ ወይም በፖለቲካ የበሰለ ነው ለማለት ያስቸግራል።
አንድ ሕዝብ በፖለቲካ ወደ ከፍተኛ ደረጃ ደርሷል ለማለት የሚቻለው – አባሎቹ የሆኑትን ክፍሎች አንድ አድርጎ የሚይዘው፤ የሕብረትና ያንድነት ማሠርያ ያጠበቀ ሲሆንና እነዚህ አባል የሆኑት ክፍሎች መሪ በሌላቸው ጊዜ በመበታተንና የርስ-በርሳቸውን ጉዳት፤ ወይም ክፋት በመፈላለግ ፈንታ የሕብረት ሥራቸውን ለመቀጠልና መሪያቸውንም ያለ ችግር ለመምረጥ የሚችሉ የሆኑ እንደሆነ ነው። ነገር ግን ዛሬ የኢትዮጵያን ልዩ ልዩ ክፍሎች አንድ ላይ አስተሳስሮ የያዘው፤ የንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት የጦር ኃይልና ንጉሠ ነገሥቱ ባይኖሩ የኢትዮጵያ ሕዝብ መሪውን በሰላማዊ መንገድ መርጦ እስኪተካ – አንድነቱ ሳይናወጽ ሊቆይ ይችላል ለማለት ስለማያስደፍር – በፖለቲካ በኩል ብዙ አልተራመደም ለማለት ይቻላል።
ኢትዮጵያ በኢኮኖሚክ፤ በኩል ዛሬ የደረሰችበት ደረጃ ምንም እንኳ ድሮ ከነበረችበት ጋር ሲመዛዘን በጣም ከፍ ያለ መሆኑ የታወቀ ቢሆን – ከሌሎች አገሮች ጋር ሲተያይ ዝቅተኛ ሆኖ ይገኛል።
ለምሳሌ፡- የተባበሩት መንግሥታት ማኅበር የኢኮኖሚክና የሶሻል ምክር ቤት በቅርቡ የአፍሪቃን የኢኮኖሚክ ልማት ሲያመዛዝን – የያንዳንዱ ሰው መሐከለኛ (Average) ያመት ገቢ፤ በግብፅ፣ የአሜሪካን ዶላር 109፤ በሞሮኮ 191፤ በቱኒስያ 176፤ በጋና 194፤ በናይጀሪያ 96፤ በኬኒያ 78፤ በዩጋንዳ 57፤ በታንጋኒካ 48፤ ሲሆን በኢትዮጵያ 30 መሆኑን ገልጿል። ይህን የተባበሩት መንግሥታት ማኅበር የኢኮኖሚክና ሶሻል ምክር ቤት ያወጣውን ሪፖርት በማስተባበል – የኢትዮጵያ መንግሥት ፕላኒንግ ቦርድ፤ የአሜሪካን ፖይንት ፎርና የኢትዮጵያ መንግሥት ባንክ በየበኩላቸው፤ በኢትየጵያ የያንዳንዱ ሰው ያመት ገቢ የአሜሪካን ዶላር 36 ነጥብ 4፤ 45 ነጥብ 6 እና 40 ነጥብ 8 መሆኑን ገልጸዋል። ነገር ግን የተባበሩት መንግሥታት ማኅበር የኢኮኖሚክና ሶሻል ምክር ቤት የጻፈውን ስሕተት ነው ብለን የኢትዮጵያ መንግሥት ፕላኒንግ ቦርድ፤ የአሜሪካን ፖይንት ፎርና የኢትዮጵያ መንግሥት ባንክ በየበኩላቸው የሰጡትን ቁጥር ብንቀበል እንኳ በማናቸውም አኳሆን በኢትየጵያ የያንዳንዱ ሰው መሐከለኛ ያመት ገቢ በአፍሪቃ ውስጥ ከሁሉም ያነሰ ሆኖ ይገኛል።
እንዲሁም የተባበሩት መንግሥታት ማኅበር የትምህርት፤ የሳይንስና የካልቸር ድርጅት – እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ1960 ዓ.ም የአፍሪቃን የትምህርት ልማት ለማመዛዘን ባወጣው ሪፖርት – የሁለተኛ ደረጃንና ከዚያ በላይ ያለውን ትምህርት ትቶ – በያገሩ በትምህርት ዕድሜ ውስጥ ካሉት ሕፃናት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት የሚያገኙት – በኮንጎ በመቶ 58፤ በካሜሩን በመቶ 45፤ በጋና በመቶ 55፤ በላይቤርያ በመቶ 21፤ በናይጀርያ በመሐከለኛው በመቶ 67፤ በሱማሌ በመቶ 6 ሲሆን በኢትዮጵያ በመቶ 4 መሆኑ ገልጾአል። የኢትዮጵያ መንግሥት የትምህርት ሚኒስቴርም የሰጠው ቁጥር በመቶ 4 ነጥብ 85 ስለሆነ፤ በኢትዮጵያ በመጀመርያ ደረጃ የሚማሩት ሕፃናት ከብዙዎቹ በአፍሪቃ ውስጥ ካሉት አገሮች የሚያንሱ ሁነው ይገኛሉ።
ከዚህ በላይ ለምሳሌ ያኽል ያመለከትኋቸው – ኢትዮጵያ በፖለቲካ፤ በኢኮኖሚክ፤ በሶሻል፤ በትምህርትና እነሱንም በመሳሰሉት የደረሰችበት የልማት ደረጃ፣ እንደስዋ በነፃነት ብዙ ዘመን ከኖሩትና ከሚበዙትም በቅርቡ ከቅኝ ግዛት ነፃ ከወጡት አገሮች ጋር ሲመዛዘን ዝቅ ያለ መሆኑን ስለሚያመለክቱና ይህንም ዛሬ የዓለም ክፍሎች ሁሉ የተቀራረቡ በመሆናቸው ብዙ ኢትዮጵያውያን በማንበብም ሆነ ያላነበቡት ካነበቡት በመነጋገር ስለሚያውቁ፣ ኢትዮጵያ ወደኋላ የቀረችው የመንግሥቱ ባሥልጣኖች የግል ጥቅማቸውን እየተከታተሉ በጠቅላላው የሀገሪቱንና የሕዝቡን ጥቅም ችላ በማለታቸው ነው ብለው ቅር ይላቸዋል።
፬ የተጠራቀመ ዕዳ
እላይ በብዙ ቦታ እንዳመለከትሁት ግርማዊነትዎ በማናቸውም በኩል “ለኢትዮጵያ ዕድገት የሠራው እጅግ ብዙ መሆኑን ጤነኛ አእምሮ ያላቸው ኢትዮጵያውያን ሁሉ አይክዱትም” ከግርማዊነትዎ በፊት በኢትዮጵያ የነገሡ ነገሥታት ሁሉ በየዘመነ መንግሥታቸው ከሀገራቸው ልማት ድርሻ ድርሻቸውን ቢሠሩ ኖሮ ግርማዊነትዎ ከሠራው ጋር አንድ ላይ ዛሬ ኢትዮጵያ የምትገኝበትን ደረጃ እጅግ ከፍ ያደርገው ነበር።
ምንም እንኳ በግርማዊነትዎ ዘመነ መንግሥት ለኢትዮጵያ ልማት የተሠራው ብዙ ቢሆን – በጠቅላላው ካልተሠራው ጋር ሲመዛዘን አንሶ ስለሚታይ – ግርማዊነትዎና መንግሥቱ የተጠራቀመ ዕዳ በሙሉ ሊከፍሉ ባመቻላቸው ተወቃሾች ሆኑ።
ግርማዊነትዎ በፖለቲካ በኢኮኖሚ፤ በሶሻል፤ በአስተዳደር፤ በትምህርትና እኒህንም በመሳሰሉት ሁሉ ለኢትዮጵያ ያደረገውን በመመልከት ከኢትዮጵያ ሕዝብ ደስታና ምስጋና እንጂ ቅርታና ሐሜት አይጠብቅም። ከሌላ ወገን ደግሞ የኢትዮጵያ ሕዝብ በፖለቲካ፤ በኢኮኖሚክና እነሱን በመሳሰሉት የደረሰበት ደረጃ በረዥም የነፃነት ዘመኑ ሊደርስበት ከሚገባው በጣም ዝቅ ያለ ነው ብለው የሚያምኑ ሰዎች በበኩላቸው ኢትዮጵያ በነፃነት አብረዋት ከኖሩት አገሮች ተለይታ ወደኋላ መቅረትዋንና በነዚህ በነፃነት ጓደኞችዋ ለመድረስ ገና ወደፊት የሚያስፈልገው ድካምና ሥራ በጣም ብዙ መሆኑን ሊመለከቱ ያልተደረገው የሚያስርባቸውን ያኸል የተደረገው ሳያጠግባቸው እየቀረ ትዕግሥት ወደማጣትና ወደመበሳጨት፤ መንግሥቱንም ወደመውቀስ ይደርሳሉ። ይህም፡- ሰጭ የሰጠውን ቆጥሮ ለሰጠው የሚገባ ምስጋና ባለማግኘቱ ሲያዝን ተቀባይ በበኩሉ ሳገኝ ይገባኛል የሚለውንና ገና ያላገኘውን ቆጥሮ ማዘኑ በጠቅላላው በሰው ባሕርይ ውስጥ ያለና የተለመደ በመሆኑ ነው።
፭. የአሳብ መግለጽ መብት
ማናቸውም ሰው በጽሑፍም ይሁን በቃል አሳቡን የመግለጽ መብት እንዳለው በኢትዮጵያ ሕገ – መንግሥት የታወጀ ሲሆን ይህ መብት በሥራ ባለመፈጸሙ በሰፊው ቅርታ የፈጠረ ከመሆኑም በላይ ጸሐፊዎቹ ወይም ተናጋሪዎቹ የመንግሥት ጠላቶች እንደሆኑ ተቆጥረው ብዙ ችግር ይደርስባቸዋል የሚል ድምፅ ስላለና ይህም ዛሬ በሰፊው ስለታመነ መንግሥቱን ለሚያደርገው መልካም ነገር ከሚያስመሰግነው ይልቅ ላላደረገው ክፉ ነገር በስውር የሚያማውና የሚነቅፈው ሰው እየበዛ ሔደ።
ሰው በተፈጥሮው ለተከለከለ ነገር ረሀቡ የጸና ስለሆነ መንግሥቱን ማመስገን ካልሆነ መንቀፍ ክልክል ነው የሚባለው ወሬ የገነነ በመሆኑ በያካባቢውና በየጓዳ መንቀፉና ማማቱ ላይቀር ይህ አልበቃው ብሎ እንደተጨቆነ ወይም እንደታፈነ ቆጥሮታል. .
ከዚህም ሌላ መንግሥት የአሠራሩ ጉድለት በጋዜጣ፤ ወይም በጉባኤ በገሃድ እንዳይገለጽ መከልከል ብቻ ሳይሆን በስውር የሚያሙትንና የሚወቅሱትንም በሰላይ ይከታተላቸዋል የሚል እምነት ስለተስፋፋ በያካባቢው የጭቆናና የመታፈን ስሜት ብቻ ሳይሆን የማማረር ድምጽ መስማት ከጀመረ ቆይቶአል።
ይህ ሁሉ የጭቆና ወይም የመታፈን ስሜትና የማማረር ድምፅ የተመሠረተበት ወሬ፤ ወይም እምነት እውነት ሳይሆን ይችላል። የመታፈን ስሜትና የማማረር ድምፅ መኖሩ ግን የማይጠረጠር ነው።
ስለዚህ እንዲህ ያለው ክፉ ስሜትና ክፉ ድምፅ የተመሠረተበት ወሬና እምነት አሰት ቢሆንም ስሜቱና ድምፁ መኖሩ ብቻ በመንግሥቱና በሕዝቡ መሐከል ሊኖር ለሚገባው የመተባበር ግንኙነት ብርቱ መሰናከል ስለሆነ የሚወራው ክፉ ወሬና በወሬው መሠረት በሕዝቡ መሐከል የተፈጠረው እምነት አሰት መሆኑን በቃልም፤ በሥራም ማስረዳት የመንግሥቱ ፋንታ ነው።
ይህ እስኪሆን ድረስ ሕዝቡ የሚወራውን ወሬና መንግሥቱም የሚያሳድደው መሆኑን አምኖ፤ አሰቱን ከእውነት ሳይለይ፤ አንዱን በብዙ እያበዛና በጎውን ወደ ክፉ እየለወጠ፤ ሁሉንም ባንድ ላይ ማቡካቱንና ማፍላቱን ይቀጥላል። እንዲሁ ታፍኖ የሚፈላም ካልተነፈሰ ወደ መፈንዳት ይደርሳል።
፮. ሰላምን ለመሥራት የሁከትን መሠረት ማጥፋት ያስፈልጋል
ከዚህ በቀደሙት አርእስቶች እንዳመለከትሁት ላለመደሰት፤ ለቅርታና ለሁከት ምክንያት የሆኑት ነገሮች እንዲሁ እንዳሉ ተቀምጠው ዘላቂ የሆነ ሰላም ይገኛል ብሎ ማን አስቸጋሪ ይሆናል።
ዛሬ ኢትዮጵያ ከሌሎች የዓለም ክፍሎች ፤ ሕዝቧ ከሌሎች የዓለም ሕዝቦች መሐከል የሚኖሩበት ጊዜ ስለሆነ፤ የመንግሥቱ ሥሪት፤ አስተዳደሩ፤ የፖለቲካ፤ የኢኮኖሚክ፤ የሶሻልና እነሱን የመሳሰሉት ሁሉ ልማት፤ የሕዝቡም መብት ከሌሎች አገሮች የመንግሥት ስሪት፤ አስተዳደርና የሕዝብ መብት ጋር በሙሉ አንድ ዓይነት ሊሆን ባይቻል ተመዛዛኝ መሆን እንዳለበት የታወቀ ነው።
ስለዚህ የኢትዮጵያ መንግሥት ስሪት፤ አስተዳደሩና የልማት ፕሮራም ከሌሎች አገሮች ተመዛዛኝ በሚሆንበት መንገድ ዛሬ ባይሆን ነገ፤ ነገ ባይሆን ከነገወዲያ መሻሻሉ ስለማይቀር በነገ፤ ወይም በተነገወዲያ ፋንታ ዛሬ በሌላ ሰው ፈንታ ግርማዊነትዎ እንዲሻሻል ቢያደርግ ለኢትዮጵያ ዕድገት የመሥራችነትን ብቻ ሳይሆን የደምዳሚነትን ዋጋ ጭምር ታሪክ ይከፍለዋል።
አባት – የሚወደውን ልጁን እየበላ፤ እያጠጣ፤ እያለበሰ፤ ለትምህርት ሲደርስ እያስተማረ፤ ባለበጎ ምግባር እንዲሆን እየቀጣ ያሳድገዋል። ልጁም በበኩሉ ካባቱ ሥር ወጥቶ ለመኖር የሚችልበት ሌላ መንገድ አለመኖሩንና በዙሪያው የሚኖሩ የዕድሜ ጓደኞቹ የሚኖሩበት ከሞላ ጎደል እሱ በሚኖርበት ሁኔታ መሆኑን ስለሚያውቅ፣ ያባቱ ተግሳጽም ሆነ ቅጣት ሳይከብደው ተቀብሎ ይኖራል። ካደገና ጎልማሳ ከሆነ በኋላ ግን፣ አባቱ እንደታናሽ ሕፃን ልመልከትህ ያለው እንደሆነ፤ በግል ጉዳዩ ልግባ ያለ እንደሆነ፤ እንደ ጓደኞቹ ውጭ አምሽቶ ሲገባ ልምታህ ያለው እንደሆነ፤ ማዘንና ይወደው የነበረ አባቱን መጥላት ይጀምራል። ይህም ሁኔታ የቀጠለ እንደሆነ አባትና ልጅ ተማርረው ለመለያየትና ክፉ ለመተሳሰብ ይደርሳሉ። ነገር ግን ብልህ አባት የልጁን ማደግና ስሜቱን አስቀድሞ ተመልክቶ በራሱ እምነት የሚያገኝበትንና ያለሞግዚት ሊተዳደር የሚችልበትን መንገድ የመራው እንደሆነ፤ አባትና ልጁ እየተደጋገፉ እንደተፋቀሩ ይኖራሉ። ግርማዊነትዎም ለኢትዮጵያ ሕዝብ ብልህ አባት እንደ መሆኑ መጠን በትምህርት ያሳደጉት ሕዝብዎ የጎልማሳነት ስሜት ሲሰማው በራሱ እምነት አግኝቶ ያለሞግዚት በሚተዳደርበት መንገድ ቢመራው አሳድጎ፤ አስተምሮ፤ ራሱን ያስቻለውን አባት፤ እንኳን በሕይወቱ ሳለ ካለፈም በኋላ መታሰቢያውን ሲወድና ሲያከብር ይኖራል እንጂ ራሱን ስላስቻለው በማናቸውም መንገድ በክፉ አያስታውሰውም።
፯. የአሳብ ማጠቃለያ፡-
የኢትዮጵያ መንግሥት ሥሪት፤ አስተዳደሩና በፖለቲካም ሆነ በኢኮኖሚክና በሶሻል ልማት ሕዝቡ ዛሬ ያለበት ደረጃ በብዙ ኢትዮጵያውያን መሐከል ላለመደሰትና ለቅርታ ዓይነተኛ ምክንያቶች መሆናቸውንና እነዚህም ምክንያቶች በጊዜ ካልተሻሻሉ ይዋል ይደር እንጂ ለሁከት መነሻ መሆናቸው የማይቀር መሆኑን ከዚህ በላይ በየአርእስቱ እንደተቻለኝ ባጭሩ ለማመልከት ሞክሬአለሁ። ከዚህ በኋላ እነዚህ ለቅርታ ምክንያቶች የሆኑትና ለሁከትም መነሻዎች የሚሆኑትን ነገሮች የሚሻሻሉበት የመሰለኝን አሳብ ቀጥዬ ለማመልከት እንዲፈቀድልኝ በፍፁም ትሕትና ግርማዊነትዎን እለምናለሁ።
ሀ/ ከሁሉ አስቀድሞ የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት መሻሻል ያስፈልገዋል። እንዲሁ ያለውም የሚሻሻለው ሕገ መንግሥት ከሁሉም የመጨረሻ፤ ዘመናዊ እንደመሆኑ መጠን በጣም የተሟላና ከብዙዎቹ አገሮች ሕገ መንግሥት የበለጠ የሕዝብን መብት የሚጠብቅ ቢሆን ግርማዊነትዎን በዓለምና በኢትዮጵያ ሕዝብ ፊት የሚያስወድድና የሚያስከብር ከመሆኑም በላይ ለግርማዊነትዎ ከእንግዲህ ወዲያ በተረፈው ዘመኑ ልቡን ያለማቋረጥ የሚያረካ፤ የደስታ ምንጭ ይሆናል። ያለዚያም ከኢትዮጵያ ሕዝብ ኑሮ የሚስማማ መሆኑ ሳይቀር ከሌሎች አገሮች ሕገ መንግሥት የሚመዛዘን እንጂ በማናቸውም በኩል የሚያንስ የሆነ እንደሆነ ዞሮ ዞሮ ቅርታ መተውና ማሳማቱ አይቀርም።
በዚህ አኳሆን የሚሻሻለውን ሕገ መንግሥት የሚያሰናዳ፤ የሕገ መንግሥት ትምህርት ያላቸውና የኢትዮጵያን ልማድና ሕግ የሚያውቁ ሰዎች ያሉበት አንድ ኮሚሲዮን ቢቋቋም ሥራውን እጅግ ቢዘገይ ባንድ ዓመት ውስጥ ጨርሶ ሊያቀርብ ይችላል። ካወቀውና ከተከራከረበት በኋላ የሚሻሻል ነገር ቢኖር እንደገና ተሻሽሎ፤ ግርማዊነትዎና የኢትዮጵያ ፓርላማ፤ ወይም ግርማዊነትዎና ጠቅላላው የኢትዮጵያ ሕዝብ፤ በሪፈራንደም ሲቀበሉት እንዲሠራበት ይደረጋል። ከዛሬ ጀምሮ የሚሻሻለው ሕገ መንግሥት እሥራ ላይ እስኪውል ድረስ ያንድ ዓመት ተኩል ጊዜ ይወሰድ ይሆናል። ከዚህ በላይ ባመለካትሁት ግርማዊነትዎ የሚስማማ የሆነ እንደሆነ እንደዚህ ለማድረግ የወሰነ መሆኑን ለሕዝብ የሚገልጽ አንድ ማስታወቂያ ቢሰጥ መልካም ይመስለኛል።
ለ/ ሁለተኛው መሻሻል የሚያስፈልገው፣ የመንግሥቱ አስተዳደር መሆኑን እላይ አመልክቻለሁ። ለመንግሥቱ አስተዳደር ኃላፊ የሚሆኑ ባለሥልጣኖች፣ ለማንኛውም ጥፋትና ጉድለት ተከሳሾችና ተወቃሾች መሆን ስላለባቸው ለዚህ እንዲመች፣ ኢትዮጵያን ከግርማዊነትዎ በታች የምናስተዳድርበት የፖለቲካ፤ የኢኮኖሚክና የሶሻል፤ የአስተዳደርና የትምህርት፤ እነሱንም የመሳሰሉ የሌሎች አገልግሎቶች ፕሮግራም፤ አለን የሚሉ ሰዎች በየጓዳቸው ፕሮግራማቸውን በተወሰነ ጊዜ አሰናድተው፤ በጋዜጣ አሳትመው ለሕዝብ እንዲያስታውቁ ቢደረግ እንዲህ ያሉት ፕሮግራሞች ባዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን በየጠቅላይ ግዛቱ፤ በየባለቤታቸው አማካይነት ሰፊ ክርክር ከተደረገባቸውና ሕዝብ ደህና አድርጎ ካወቃቸው በኋላ እጅግ ቢዘገይ ካንድ ዓመት ተኩል እስከ ሁለት ዓመት ድረስ፤ ጠቅላላ ምርጫ ተደርጎ የድምጽ ብልጫ ያገኘው ፕሮግራም ባለቤቶች ወደ ግርማዊነትዎ ቀርበው ከግርማዊነትዎ በታች ኢትዮጵያን ለማስተዳደር ይሾማሉ፤ በዚህ አሳብ ግርማዊነትዎ የሚስማማ የሆነ እንደሆነ ይህን ለማድረግ የወሰነ መሆኑን አስቀድሞ ለሕዝብ ማስታወቅ የሚጠበቅም ይመስለኛል።
ሐ/ ከዚህ በላይ በለ/ ፊደል እንዳመለከትሁት ፕሮግራማቸው በሕዝብ ተመርጦ፤ ግርማዊነትዎ የሚሾማቸው ባለሥልጣኖች ለመንግሥቱ አስተዳደር ኃላፊነቱን እስኪቀበሉ ድረስ (ለጊዜው) ግርማዊነትዎ ለአስተዳደሩ ኃላፊ አድርጎ የሚያስቀምጠው ባለሥልጣን ለየክፍሉ ሥራ ይስማማሉ የሚላቸውን ሰዎች መርጦ ለግርማዊነትዎ እያቀረበ እሱም ለሥራውም፤ ለሠራተኞችም ጉድለት እሱ እስከ ሥራ ጓደኞቹ ተከሳሽና ተወቃሽ እንዲሆን ቢደረግና ይህም መደረጉ ለሕዝብ ቢገለጽ መልካም ይመስለኛል።
መ/ ስለ አሳብ መግለጽ መብትና ስለ ሰላማዊ ስብሰባ፤ በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት የታወጀው በሥራ ላይ ባለመዋሉ፤ ቅርታ የፈጠረና ለነቀፋ ምክንያት የሆነ መሆኑን እላይ ገልጫለሁ፤ በሥራ ያልዋበትም ምክንያት ለኔ እንደሚመስለኝ “የአሳብ መግለጽና የሰላማዊ ስብሰባ መብት በሕግ ይወሰናል” የሚል ክፍል ጭምር በሕገ መንግሥቱ ስላለና እንዲህ ያለው ሕግ ሳይወጣ በመቅረቱ ሳይሆን አይቀርም።
አሁን የሚያስፈልግ የሚመስለኝ፡- በጋዜጣም ሆነ በጉባኤ የሚገለጽ አሳብ የሕዝብን ሞራል የሚያበላሽና አላግባብ የሰውን መብት የሚጎዳ የሆነ እንደሆነ በሕግ በተቋቋመ ፍርድ ቤት በኩል ቅጣት የሚያስከትል መሆኑን የሚገልጽ ሕግ እንዲወጣ ተደርጎ ማናቸውም ሰው አሳቡን በጋዜጣም ሆነ በጉባኤ ለመግለጽ፤ ወይም ሰላማዊ ስብሰባ ለማድረግ መብቱ ያልተከለከለ መሆኑን፤ እንዲሁም ዓቅም ያለው ሰው የግል የጋዜጣ ቤት ለማቋቋም ያልተከለከለ መሆኑን ለሕዝብ ማስታወቅ ነው።
በዚህ ማስታወሻ በመጀመርያው ክፍል እንዳመለከትሁት ስለ ኢትዮጵያ መንግሥት ሥሪት፤ ስለ አስተዳደሩና ስለ ጠቅላላው የልማት ፕሮግራም፣ በሕዝብ መሐከል ቅርታ መኖሩን ስላወቁ በቅርቡ ሁከት አስነሥተው የነበሩ ሰዎች ይህን ሁሉ እናሻሽላለን ብለው ሰብከው ነበር። ስለዚህ “አሁን መንግሥቱ የማሻሻል ሥራ የጀመረ እንደሆነ ሁከቱን ባስነሡት ሰዎች ተመርቶ፤ ወይም የእነሱ ስብከት በሕዝብ መሐከል በፈጠረው ስሜት ተገዶ ነው ተብሎ ሊታማ ስለሚችል ለጊዜው የማሻሻል ሥራ አለመጀመር ይሻላል” የሚል አስተያየት ሊኖር ይችላል። ነገር ግን እንዲህ ያለው አስተያየት ላንዳንድ ጥቃቅን ነገር ሊያገለግል የሚችል ቢሆን እንኳ ካንድ ሕዝብና ከመንግሥት ታሪክ፤ በጠቅላላውም ካንድ አገር ሕይወት ጋር ለተያያዘ ታላቅ ጉዳይ ሊያገለግል የሚችልም፤ የሚገባም አይደለም።
በዚህ ማስታወሻ ያቀረብኩትና እሱን የመሳሰለ የማሻሻል አሳብ ሁሉ፤ ሁከት ካስነሱት ሰዎች በፊት በሌሎች አገሮች ሲሰበክ ያልኖረ ወይም ያልተደረገ፣ አዲስ ነገር አይደለም። በኢትዮጵያም ዛሬ ባይሆን ነገ በግርማዊነትዎ ጊዜ ባይሆን በሌሎች መደረጉ አይቀርም። ነገር ግን ሊደረግ የሚገባውን መልካም ነገር አድሮ የማይገኝ ሽሙጥ ያስከተለ ይሆናል በማለት ብቻ ሳያደርጉ መቅረት. . . ግርማዊነትዎ የታሪክ ሽልማት ለሌሎች፤ ላልደከሙት አሳልፎ ወደ መስጠት ስለሚያደርስ፤ ሊያዝ የሚገባው አስተያየት አይመስለኝም። ከዚህ ሁሉ በላይ ሌሎች እናደርገዋለን ብለው ያወሩትን መልካም ነገር አናደርግም በማለት ከሚገኘው ምስጋና በማድረጉ ምክንያት ሀሜት የሚመጣ ቢሆን እንዲህ ያለውን ሀሜት መቀበል ብዙ ጊዜ የሚሻልና የሚጠቅምም መሆኑ የታወቀ ነው።
ግርማዊ ሆይ
በዚህ ማስታወሻ የገለጽኋቸው አንዳንድ ነገሮችና የገለጽሁበት ቋንቋ ትንሽ መረር ያለ መሆናቸው ይሰማኛል። እንዲሁም ሰው ሆኖ ለተፈጠረ ሁሉ ከመራራ እውነት የተቀመመና የለዘበ ከንቱ ውዳሴ እንደሚጣፍጥ አውቃለሁ። ነገር ግን ዞሮ ዞሮ ከንቱ ውዳሴ የሚያራራውን ጣፋጭ ፍሬ የሚለቅሙና በሱም የሚጠቀሙ አሞጋሾቹ ብቻ በመሆናቸው ተሞጋሾቹ ሁልጊዜም ቢሆን ከመራራው እውነት ጋር ቀሪዎች ናቸው። ስለዚህ ግርማዊነትዎን በሚጣፍጥ ከንቱ ውዳሴ ለማታለልና የሚጎዳውን የሚጠቅም አስመስሎ ለማሳየት ከመሞከር መራራም ቢሆን በኔ አስተያየት ለግርማዊነትዎና ለኢትዮጵያ ሕዝብ ለዘለቄታው ጠቃሚ የመሰለኝን አስተያየት መግለጽ ስለመረጥሁ፤ ይህኑ በፍጹም ቅንነትና በፍጹም ትሕትና አቀርባለሁ።
ጥር ፳፫ ቀን ፲፱፻፶፫/ ዓ.ም
የግርማዊነትዎ አገልጋይ፤
ሐዲስ ዓለማየሁ
· ስለ ክቡር ዶ/ር ሐዲስ አለማየሁ፤
ደራሲው ያሳተሟቸው መፅሐፍት፤ የትምህርትና የትምህርት ቤት ትርጉም፣ ተረት ተረት የመሠረት፣ ፍቅር እስከመቃብር፣ ኢትዮጵያ ምን አይነት አስተዳደር ያስፈልጋታል?፣ ወንጀለኛው ዳኛ፣ የልምዣት፣ ትዝታ የተባሉ ሲሆኑ ሌሎች ያልታተሙ በርካታ ሥራዎች እንዳሏቸው የሕይወት ታሪካቸው ያመለክታል።¾ ከማለዳ ታይምስ ሚዲያ ግሩፕ ፍቃድ ውጭ በዌብሳይቶች ላይም ሆነ በጋዜጦች ወይንም በማንኛውም በሬዲዮ ቴሌቪዥንም ሆነ ዩቲዩብ ማቅረብ የተከለከለ ነው ። በህግም ያስቀጣል ።
Average Rating