“በመንግስት የቀረቡ አማራጮች ህገ-መንግስታዊ መሰረት የላቸውም” (አብሮነት)
የሽግግር መንግስት የማቋቋም ሃሳብን የሚያቀነቅነው “አብሮነት ለኢትዮጵያ ፌደራላዊ አንድነት” የተሰኘው የሶስት ፓርቲዎች ስብስብ፤ ሀገሪቱ ለገጠማት ህገ መንግስታዊ ቀውስ መፍትሔው ብሔራዊ የምክክር መድረክ መጥራት ነው ብሏል፡፡ ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በበኩላቸው፤ የሽግግር መንግስት በኢትዮጵያ መቼውንም ቢሆን የማይታሰብ መሆኑን አስረግጠው ተናግረዋል፡፡
ኢዴፓ፣ ኢሃን እና ህብር ኢትዮጵያ በጋራ የመሠረቱት አብሮነት የተሰኘው የፖለቲካ ሃይል ሰሞኑን ለፓርቲዎች የቀረበውን ባለ አራት አማራጭ የወደፊት አቅጣጫዎች አስመልክቶ ባወጣው የአቋም መግለጫ፤ በመንግስት የቀረቡት አማራጮች ህገ መንግስታዊ መሠረት የላቸውም ሲል አጣጥሏል፡፡
“መንግሥት እነዚህን ህገ መንግስታዊ መሠረት የሌላቸው አማራጮች በማቅረብም በህገ መንግስት ከተሰጠው ስልጣንና መብት ውጪ ስልጣኑን ለማራዘም እየሞከረ ነው” ሲልም አብሮነት ወንጅሏል፡፡
በመንግስት የቀረቡ አማራጮችን ከህገ መንግስቱ የተለያዩ ድንጋጌዎች አንፃር መመልከቱንና ህገ መንግስቱም በርካታ ክፍተቶች እንዳሉበት መረዳቱን የጠቆመው አብሮነት፤ህገ መንግስቱ ለተለያየ ትርጉም የተጋለጠ መሆኑን አስረድቷል፡፡
በመንግስት የቀረቡ አማራጮች ህገ መንግሥታዊ መሠረት የሌላቸው በመሆናቸው መንግስት ስልጣንን በህገ ወጥ መንገድ ለማራዘም የሚያደርገውን ሙከራ አቁሞ፣ አሁን ሀገሪቷ ያጋጠማት “ህገ መንግስታዊ ቀውስ” መሆኑን አምኖና ተቀብሎ ጉዳዩን ከመደበኛ የህግ አሠራር ውጭ፣ የተፈጠረውን “ህገ መንግስታዊ ቀውስ እንዴት እንፍታው?” ብሎ ቁጭ ብሎ የሚመካከርና አቅጣጫ የሚያስቀምጥ ሁሉን አቀፍ አገራዊ የምክክር መድረክ መጥራት አለበት ብሏል፡፡
በአሁኑ ወቅት ዋናው ትኩረት ኮሮናን መከላከል ሊሆን እንደሚገባ ያስገነዘበው ፓርቲው፤ ቢያንስ እስከ ነሐሴ 2012 ዓ.ም የብልጽግና ፓርቲ በጉዳዩ ላይ አጀንዳ ይዞ እንዳይነጋገር፣ የትግራይ ክልልም በተናጠል ምርጫ አካሂዳለሁ ከሚለው አካሄዱ እንዲቆጠብ አሳስቧል፡፡
አሁን በስልጣን ላይ ያለው ገዥ ፓርቲ ከመስከረም 30 ቀን 2013 ዓ.ም በኋላ ለአንድም ቀን በስልጣን ላይ የሚያቆየው ህጋዊ መሠረት እንደሌለ በመግለጽም፤ ብቸኛ መፍትሔው ብሔራዊ ምክክር ማድረግ መሆኑን ይጠቁማል – አብሮነት፡፡
ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ባለፈው ረቡዕ ከፓርቲዎች ጋር በምርጫ ማራዘምና አገራዊ መንግስቱ በማስቀጠል ዙሪያ ባደረጉት ውይይት ላይ እንደገለፁት፤ ህገ መንግስቱን መነሻ አድርገው ከሚቀርቡ መፍትሔዎች በስተቀር ሌሎች አማራጮች ፈጽሞ ተቀባይነት እንደማይኖራቸው አስታውቀዋል፡፡ በተለይ የሽግግር መንግስት ፈጽሞ የማይታሰብ መሆኑን አስረግጠው ተናግረዋል፡፡
“የሽግግር መንግስት የሚባለውን ነገር እኔ የሽግግር ሳይሆን የብጥብጥ መንግስት ነው የምለው፤ እንኳን በጋራ መንግስት ለመሆን በጋራ ምክር ቤት ተወያይቶ አጀንዳ መወሰን ያልቻለ ስብስብ ነው ያለው፡፡ በዚህ ወሳኝ ወቅት እንደዚህ አይነት ቀልድ መቀለድ አያስፈልግም” ብለዋል፡፡
“ከዚህ ከወጣችሁ ከ1 ሰዓት በኋላ በኢትዮጵያ ሉአላዊነት ላይ ምን እንደሚያጋጥም ማንም አያውቅም፤ ዝም ብሎ ዘሎ ስልጣን መያዝ የሚቻልበትን መንገድ ከምንከተል በተቻለ መጠን ምርጫውን ዲሞክራሲያዊ ማድረግ ነው የሚያዋጣው” ብለዋል – ጠ/ሚኒስትሩ፡፡
የአገር ሉአላዊነትን አደጋ ላይ በሚጥል ጉዳይ ግን መንግስታቸው እንደማይታገስ ጠ/ሚኒስትሩ አስረግጠው ተናግረዋል፡፡ መንግስታቸው ለሀገሪቱ ሉአላዊነት፣ ለህዝቦች ደህንነትና ለሀገሪቱ ብሔራዊ ጥቅም ከምንም በላይ ቅድሚያ እንደሚሰጥና በዚህ በኩል የሚመጡ ችግሮችን በትዕግስት እንደማይመለከትም ጠንካራ አቋማቸውን ገልፀዋል፡፡
Average Rating