******************
በደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ የነበሩና ወደ ቤተሰቦቻቸው በመጓዝ ላይ የነበሩ “ተማሪዎችን አግተዋል” በሚል ወንጀል የተጠረጠሩ 17 ግለሰቦች በዛሬው ዕለት በሽብር ወንጀል ክስ ተመሰረተባቸው ፡፡
በእነ ከሊፋ አብዱረሂማን በሚጠራው የክስ መዝገብ ውስጥ 17 ግለሰቦች በጠቅላይ ዓቃቤ ህግ 3 ክስ ተመስርቶባቸዋል፡፡
የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በዛሬው ዕለት ክሱን አድምጧል፡፡
ህዳር 24 እና 25 ፣2012 በደምቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ የነበረውን ግጭት ተከትሎ በፍራቻ ወደ ቤተሰባቸው ሊሄዱ የነበሩ የአማራ ክልል ተማሪዎች በአንድ ዶልፍን መኪና ተሳፍረው ሲሄዱ በቄሌም ወለጋ ዞን ደምቢዶሎ ከተማ ሰዬ እና አንሰሎ ወረዳዎች በሚገኙ ሚንኮና ሱዲ ቀበሌዎች መኪና በማስቆም ተማሪዎችን እየደበደቡ ጫካ በመውሰድ ለኦነግ ሸኔ አመራሮች ማስረከባቸው በክስ መዝገቡ ላይ ተገልጿል፡፡
በዛሬው የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተረኛ ችሎት ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ባቀረበው ክስ 7 ተከሳች የቀረቡ ሲሆን ሁለቱ ምንም እንኳ በቁጥጥር ስር ቢውሉም በኮሮና ቫይረስ በመጠርጠራቸው በችሎቱ አልቀረቡም፡፡
ቀሪ ተከሳሾችን ፖሊስ አፈላልጎ መጥሪያ እንዲሰጣቸው ፍርድ ቤቱ ትእዛዝ ሰጥቷል፡፡
በእነ ከሊፋ አብዱረሂማን በሚጠራው የክስ መዝገብ ውስጥ 17 ግለሰቦች በጠቅላይ ዓቃቤ ህግ 3 ክስ የተመሰረተባቸው ሲሆን ፣ሁለቱ ክሶች በፀረ ሽብር አዋጅ 652/2001 አንቀጽ 3 ንዑስ ቁጥር ሶስት መሰረት የተፈፀመን የእገታና ጠለፋ የሽብር ወንጀልን የሚመለከቱ ናቸው፡፡
ሶስተኛው ክስ ደግሞ ተከሳሽ ተፈራ ሂካ ህዳር 26፣2012 ተማሪዎቹ በሚፈለገው ጫካ ውስጥ እየተጓዙ ሳለ መሽቶባቸው ታጋቾች መሆናቸውን እያወቀ ቤቱ በማሳደሩ እና ለየትኛውም የመንግስት አካል ባላማሳወቁ የሽብር ወንጀልን ባለማሰወቅ ወንጀል በሚል ክሶቹ መቅረባቸው ተመልክቷል፡፡
ዛሬ በአካል የቀረቡ ተከሳሾች “ጠበቃ እናቆማለን” ማለታቸውን ተከትሎ ከጠበቃቸው ጋር ተመካክረው እንዲቀርቡና ክሳቸው እንዲሰማ ችሎቱ ለሐምሌ 30፣20 12 ተለዋጭ ቀጠሮ ይዟል፡፡
Average Rating