ከአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት ላይ በምትገኘው የዱከም ከተማ ውስጥ ጥንቃቄ በጎደለው ሁኔታ በኮሮናቫይረስ በተያዘ ግለሰብ በቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ የተገኙ 44 ሰዎች በኮሮናቫይረሰ መያዛቸው ተነገረ።
ለቫይረሱ ተጋላጭ ከሆኑት ከአርባ በላይ ሰዎች መካከል በሐዘን ላይ ያሉ የሟች የቤተሰብ አባላትን እንደሚጨምር የኦሮሚያ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ደረጄ አብደና ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ለወረርሽኙ መተላለፍ ምክንያት የሆነው ግለሰብ ህይወቱ ያለፈው ባለፈው ሳምንት ባጋጠመው የመኪና አደጋ ሲሆን በአስክሬኑ ላይ በተደረገ ምርመራ ነበር የኮሮናቫይረስ እንደነበረበት የታወቀው።
ቢሆንም ግን በትራፊክ አደጋ የሞተው ወጣት የምርመራ ውጤቱ ከመታወቁ በፊት አስከሬኑ ለቤተሰብ ተሰጥቶ አስፈላጊው ዝግጅትና ሥነ ሥርዓት ተከናውኖ እንዲቀበር ከተደረገ በኋላ ሟች አስከሬን ላይ የኮሮናቫይረስ መገኘቱ ታወቋል።
ይህንንም ተከትሎ የሟች ቤተሰብ አባላት፣ ጎረቤቶች እና በቀብር ሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙና ንክኪ ሊኖራቸው ይችላል የተባሉ ሰዎችን የመለየት እና ምርመራ የማድረግ ሥራዎች ሲከናወኑ እንደቆዩ የክልሉ ጤና ቢሮ አስታውቋል።
በዚህም መሰረት እስከ ሰኞ ድረስ በንክኪ ምክንያት ለቫይረሱ ሊጋለጡ ይችላሉ በተባሉ ሰዎች ላይ በተደረገው ልየታና ምርመራ መሠረት በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጡ ሰዎች ቁጥር 44 መድረሱን አቶ ደረጄ አብደና ተናግረዋል።
የክልሉ ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ፤ በተለያዩ ምክንያቶች ህይወታቸው ላለፉ ሰዎች በሚከናወን የቀብር ሥነ ሥርዓቶች አማካይነት የሚከሰተው የኮሮናቫይረስ መስፋፋት ለበሽታው መዛመት አመቺ አጋጣሚዎች እየሆኑ እንደመጡ አመልክተዋል።
በኢትዮጵያ ተጨማሪ 561 ሰዎች በኮሮናቫይረስ ሲያዙ፣ የ7 ሰዎች ሕይወት አልፏል
ባለፉት 24 ሰዓታት በተደረገ 6 ሺህ 544 የላቦራቶሪ ምርመራ 561 ሰዎች የኮሮናቫይረስ እንደተገኘባቸው እና የ7 ሰዎች ሕይወት ማለፉን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።
በቫይረሱ ከተያዙ ሰዎች በቦታ ሲለዩ፦
ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 409፣
ከጋምቤላ ክልል 52፣
ከኦሮሚያ ክልል 25፣
ከትግራይ ክልል 16፣
ድሬደዋ 12፣
ደቡብ ክልል 11፣
ከሐረሪ ክልል 8
ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል 8
ሲዳማ ክልል 8
ከአማራ ክልል 6፣
ከሶማሌ ክልል 3 እና
ከአፋር ክልል 3 ናቸው።
Average Rating