የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ዙር ውሃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቅ በዲፕሎማሲው ዘርፍ ኢትዮጵያ እያደረገች ያለው እንቅስቃሴ በስኬት የታጀበ መሆኑን በግልፅ እንደሚያሳይ የውሃ ጂኦ ፖለቲካ እና የህግ ጉዳይ ምሁራን ተናገሩ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌት በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቁን አብስረዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካ ጉዳዮች እና የኦሬንታል ጥናት ማዕከል መምህር እና ተመራማሪ ፕሮፌሰር ተስፋዬ ታፈሰ የውሃ ሙሌቱ መጠናቀቅ ከፍተኛ ደስታ እንደፈጠረባቸው ተናግረዋል።
የህዳሴው ግድብ የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌት የተከናወነውም ትልቅ የዲፕሎማሲ ስራ ተከናውኖ መሆኑን ይናገራሉ።
በወሎ ዩኒቨርሲቲ የህግ ትምህርት ቤት መምህሩ እና አሁን ላይ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሶስተኛ ዲግሪ የህግ ተማሪ ደጀን የማነ የውሃ ሙሌቱን ደማቅ ታሪክ ይሉታል።
አቶ ደጀን የህዳሴው ግድብ የውሃ ሙሌት ከዲፕሎማሲ በተጨማሪ በህዝብ እና በመንግስት መካከል ያለውን መተማመን ወደ አዲስ ምዕራፍ የሚቀይር መሆኑንም ያስረዳሉ።
ፕሮፌሰር ተስፋዬ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከህዝቡ ጋር ሆነው እንዲሁም ተደራዳሪዎቻቸው ታላቅ ታሪክ ሰርተዋል ነው የሚሉት።
ከዚህ ጋር ተያይዞም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተለይ ድርድሩን ወደ አፍሪካ ህብረት እንዲመለስ በማድረግ በዲፕሎማሲው ጥረት ከፍተኛውን ድርሻ እንደሚይዙም ጠቅሰዋል።
የህግ ጉዳይ አጥኝው አቶ ደጀን የማነ ኢትዮጵያ በህዳሴው ግድብ ያሳየችው የዲፕሎማሲ ብቃት ዓለም አቀፍ ህግን በጠበቀ እና ድህነትን ለመቅረፍ የተቀመጡ ግቦችን የማሳኪያ አዲስ ምዕራፍ መሆኑን ያሳየችበት ነው ይላሉ።
እንደ ፕሮፌሰር ተስፋዬ ታፈሰ የውሃ ሙሌት ሂደቱ በራሱ ታላቅ ጥበብ የተሞላበት ነው።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያውያን የአንድነት እና የትብብር ማሳያ ታላቅ አርማ መሆኑንም ምሁራኑ ገልጸዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም የውሃ ሙሌቱ ኢትዮጵያ ከድህነት ለመውጣት በምታደርገው ትግል የተስፋ ማብሰሪያ ፕሮጀክት መሆኑን ያረጋገጠ ስኬት ነው ብለዋል።
ዐባይ ወንዝ ነበር ተገርቶ ወንዝም ሀይቅም ሆነ – አቶ ገዱ አንዳርጋቸው
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 15፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የታላቁ ህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌት በመጠናቀቁ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዐባይ ወንዝ ነበር ተገርቶ ወንዝም ሀይቅም ሆነ፤ ከእንግዲህ በወንዝነቱ ይፈሳል፤ በሀይቅነቱ ኢትዮጵያ ለፈለገችው ልማት ሁሉ ለመዋል እጅ ሰጥቷል ብለዋል።
የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ሀይለማሪያም ደሳለኝ በበኩላቸው የግድቡ የመጀመሪያ ዙር ሙሌት በመጠናቀቁ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ግድቡ በአጭር ጊዜ እንዲሞላ ተፈጥሮም ከእኛ ጋር ሆናለች ነው ያሉት።
ለዚህ ስኬታማነት ትልቅ ተሳትፎ የነበራቸውን አካላት አመስግነዋል።
አቶ ሀይለማሪያም ለአፍሪካ ህብረት እና ለሶስቱ ሀገራት መሪዎች ስኬታማ ውይይት በማድረጋቸው ምስጋና አቅርበዋል።
Average Rating