አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 8፣ 2012 የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አረዳ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት በጋዜጠኛ ጉዩ ዋርዮ ላይ ዛሬ ለፖሊስ ተጨማሪ የ10 ቀን የምርማራ ጊዜ ፈቅዷል። ተጠርጣሪው ጉዩ ዋርዮ አርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳን ቃለ መጠይቅ በማድረግ ፕሮግራሙን ቆርጦ በማቅረብ፣ ሰኔ 22 እና 23 ቀን 2012 ዓ.ም አመጽና ብጥብጥ እንዲነሳ በኦሮሚያ ሚዲያ ኔትዎርክ (ኦ.ኤም.ኤን) በመቀስቀስ ወንጀል ነው የተጠረጠረው።
ተጠርጣሪው ከሶስት ቀን በፊት በነበረው ቀጠሮ መርማሪ ፖሊስ ጋዜጠኛው አመጽ እንዲነሳ በተጠቀሰው ሚዲያ ቅስቀሳ ማድረጉን የሚያስረዳ የሰነድ ማስረጃ ማሰባሰቡን እና ተጨማሪ የምስክር ቃል መቀበሉን፣ በእጁ ላይ የተገኘ የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያ በፎረንሲክ እያስመረመረ መሆኑንም ማለዳ ሚዲያ መዘገባችን ይታወሳል በተጨማሪም በመረጃ ማሰባሰብ ዙሪያ ላይ ፣ ከኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሰልጣን እና ከተለያዩ ተቋማት ማስረጃ ለማሰባሰብና ቀሪ ምርመራ ለመስራት ተጨማሪ 14 ቀን እንዲሰጠው ፍርድ ቤቱን መጠየቁና ተጠርጣሪውም መቃወሚያ ማቅረቡን እንዲሁም የዋስትና ጥያቄ አቅርቦ ፍርድ ቤቱ መዝገቡን መርምሮ ትእዛዝ ለመስጠት ለዛሬ ጠዋት ተለዋጭ ቀጠሮ መስጠቱ ይታወሳል።
በዚህም መሰረት በዛሬ ቀጠሮ የቀረበው ጋዜጠኛ ጉዩ ላይ መርማሪ ፖሊስ የጀመረው ምርመራ ተጨማሪ ምርመራ ለማድረግ ጊዜ እንደሚያስፈልገው ከግምት ውስጥ ያስገባው ፍርድ ቤቱ የ10 ቀን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜን ለፖሊስ ፈቅዷል። በሌላ በኩል የቀድሞ የኦፌኮ አመራር ደጀኔ ጠሃ እና የአቶ ጃዋር መሀመድ የኮምፒዩተር ሲስተም ባለሙያን አቶ ሚሻ አደም እና አቶ ኮርሳ ደቻሳ አመጽና ሁከት በመፍጠር ወንጀል ተጠርጥረው ፍርድ ቤት ቀርበዋል። መርማሪ ፖሊስ ተጠርጣሪዎቹ በተጠረጠሩበት አመጽና ሁከት በማስነሳት ወንጀል ምርመራ እያከናወነ መሆኑን ጠቅሶ ለቀሪ ምርመራ የሰነድ ማስረጃ ለማሰባሰብ የምስክር ቃል ለመቀበል ተጨማሪ ጊዜ እንዲፈቀደለት ፍርድ ቤቱን ጠይቋል።
ተጠርጣሪዎቹ በበኩላቸው በቁጥጥር ስር ከዋልን ጀምሮ ፖሊስ ቃላችንን አልጠቀበልንም፣ ይህ አግባብነት የለውም፣ በፍትሃዊነት ፍርድ ቤቱ ሊያይልን ይገባል ሲሉ ያቀረቡትን አቤቱታ ያዳመጠው ችሎቱ የሁሉንም ጉዳይ በፍትሃዊነት እየተመለከተ መሆኑን አስርድቷል። ምርመራ እያከናወነ አይደለም ለሚለው መቃወሚያቸው ፍርድ ቤቱ በዛሬው እለት ጠዋት መርማሪ ፖሊስ ከመዝገቡ ጋር የሰራውን በተጠረጠሩበት ወንጀል የሰበሰበውን የሰነድ ማስረጃ ከመዝገቡ ጋር ማያያዙን በመጥቀስ ምርመራ በተገቢው እየተከናወነ መሆኑን ገልጿል። ተጨማሪ ምርመራ እንደሚያስፈልግ ከግምት ውስጥ በማስገባትም ለመርማሪ ፖሊስ ምርመራውን አጠናቆ እንዲቀርብ የ10 ቀን ተጨማሪ ጊዜ ፈቅዷል።
Average Rating