ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ በትግራይ ክልል የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚያስፈጽመውና የሚያስተገብረው ግብረሃይል፣ ፖሊስ ወይንም ሌላ ማንኛውንም የጸጥታ ኃይል ትጥቅ እንዲፈታ የማዘዝ ስልጣን እንደተሰጠው ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ አስታወቀ። ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ ዛሬ በተወካዮች ምክር ቤት በጸደቀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አተገባበርና የአፈጻጸም ወሰን ላይ ለጋዜጠኞች ማብራሪያ ሰጥተዋል። በማብራሪያቸው አዋጁ የሚጸናበትን ጊዜ፣ የአፈጻጸም ወሰንና አዋጁን በሚያስተገብረውና በሚያስፈጽመው ግብረሃይል ስልጣንና ተግባር ላይ ገለጻ አድርገዋል። አዋጁን የማስፈጸምና የማስተግበር ስልጣን የተሰጠው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ግብረሃይል መሆኑንም ተናግረዋል። የግብረሃይሉ ሰብሳቢ የኢፌዴሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም መሆኑን ጠቁመው “ግብረሃይሉም ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ወይንም ለጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ይሆናል” ብለዋል። የአዋጁ የአፈጻጸም ወሰን በዋናነት በትግራይ ክልል ሲሆን እንደ አስፈላጊነቱ ግብረሃይሉ ሊያሰፋውና ሊያጠበው እንደሚችልም ዶክተር ጌዲዮን አመልክተዋል። “ግብረሃይሉ አዋጁ ተፈጻሚ በሚሆንበት ክልል ውስጥ ፖሊስ ወይንም ሌላ ማንኛውም የጸጥታ ኃይል ትጥቁን እንዲፈታ ትዕዛዝ መስጠት ይችላል” ብለዋል። አካባቢውን ለመቆጣጠርና ሰላምን ለማስፈን አስፈላጊውን እርምጃ የመውሰድ ስልጣንም ተሰጥቶታል ነው ያሉት። ግብረሃይሉ አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው ማንኛውንም የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ወደ ትግራይ ክልል እንዳይገባም ሆነ እንዳይወጣ ትዕዛዝ መስጠት እንደሚችል ዶክተር ጌዲዮን ገልጸዋል። ከእዚህ በተጨማሪ ግብረሃይሉ ሰዓት እላፊ ገደብ ለመጣልና የጦር መሳሪያ ይዞ መንቀሳቀስን መከልክል እንዲችል ስልጣን እንደተሰጠውም ማመልከታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ግብረሃይል ትጥቅ ለማስፈታት ትዕዛዝ የመስጠት ስልጣን አለው
Read Time:53 Second
- Published: 4 years ago on November 5, 2020
- By: Abby
- Last Modified: November 5, 2020 @ 9:55 am
- Filed Under: Addis Admas, AFRICA, EASTAFRICA, ኣማርኛ
Average Rating