Read Time:1 Minute, 15 Second
በአዲስ አበባ ከተማ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ በተለያዩ ተቋማት ውስጥ የተከማቹ 19 ቦንቦችና እና ሌሎች በርካታ የጦር መሳሪያዎች መያዙን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።
የጦር መሳሪያ አከማችተው በሚገኙ ተቋማት ላይ የሚደረጉ ፍተሻዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ኮሚሽኑ ገልጿል።
የጥፋት ሃይሎች ለመዲናዋ የደገሱላትን ሽብርና እልቂት ለመቀልበስ የሚከናወነው ጠንካራ ህግን የማስከበር ተግባር በህብረተሰቡ የዕለት ተዕለት መረጃ ሰጪነት እየታገዘ ተጠናክሮ መቀጠሉን ነው የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የገለፀው፡፡
ህዳር 9 ቀን 2013 ዓ.ም በአዲስ አበባ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ በተለያዩ ወረዳዎች በሚገኙ የተለያዩ ተቋማት ውስጥ የተከማቹ 19 ቦንብ፣ 55 ክላሽንኮቭ ጠመንጃ፣ 21 ሽጉጦች፣ 2 ኤስ ኬ ኤስ ጠመንጃ፣ 3 ቺኮዝ፣ 1 ብሬን ፣ 6 ቺቺ ጠመንጃ፣ እና ሌሎች ጠመንጃዎች በአጠቃላይ 113 የተለያዩ የጦር መሳሪያዎች ተይዘዋል።
በተጨማሪም 309 የሽጉጥ እና 4 ሺህ 829 ዓይነታቸው የተለያየ ጥይቶች ፖሊስ ይዟል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ በዚሁ ክፍለ ከተማ ወረዳ 1 ትራኮን ሪልስቴት አካባቢ በአንድ ግለሰብ መኖሪያ ቤት ውስጥ በተደረገ ብርበራ 64 ሺህ 200 የአሜሪካ ዶላር መያዙን እና ጉዳዩ በምርመራ ላይ እንደሚገኝ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል።
በሰሜን ዕዝ የመከላከያ ሰራዊት ላይ ከሃዲው የህወሓት ቡድን የፈፀመውን ጥቃት ተከትሎ በአዲስ አበባ የጁንታው ቡድን ተላላኪዎች ሽብር እና ሁከት ለመፍጠር ሲንቀሳቀሱ ተደርሶባቸው ከበርካታ የጦር መሳሪያዎች ጋር በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ማስታወቁ ይታወሳል።
በሀገሩ ጉዳይ ድርድር የማያውቀው ህዝብ አንድ መሆኑ ያሥጨነቃቸው የጥፋት ሃይሎች በየጥጋ-ጥጉ እየጣሉት ከሚገኘው የጦር መሳሪያ ባሻገር በጥርጣሬ ውስጥ ከገቡ ተቋማትና ግለሰቦች በፍተሻና በብርበራ በርካታ የጦር መሳሪያዎችና የጦር ሜዳ ቁሳቁሶች እየተያዙ መሆኑንም የገለፀው።
ኮሚሽኑ የህብረተሰቡን ድጋፍና ጥቆማ በመጠቀም የጦር መሳሪያ ያከማቻሉ ተብለው በሚጠረጠሩ ተቋማት ላይ የሚያደርገውን ክትትል እና ፍተሻ አጠናክሮ እንደሚቀጥል መግለጹን ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
Average Rating