www.maledatimes.com ቅዱስ ነአኵቶ ለአብ ጻድቅ (ንጉሠ ኢትዮጵያ) - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

ቅዱስ ነአኵቶ ለአብ ጻድቅ (ንጉሠ ኢትዮጵያ)

By   /   November 12, 2023  /   Comments Off on ቅዱስ ነአኵቶ ለአብ ጻድቅ (ንጉሠ ኢትዮጵያ)

    Print       Email
0 0
Read Time:4 Minute, 54 Second


𝐍𝐚’𝐚𝐤𝐮𝐞𝐭𝐨 𝐋𝐚’𝐚𝐛 – 𝐚 𝐊𝐢𝐧𝐠, 𝐚 𝐒𝐚𝐢𝐧𝐭, 𝐚 𝐏𝐫𝐢𝐞𝐬𝐭 𝐚𝐧𝐝 𝐚 𝐦𝐞𝐦𝐛𝐞𝐫 𝐨𝐟 𝐭𝐡𝐞 𝐙𝐚𝐠𝐰𝐞 𝐝𝐲𝐧𝐚𝐬𝐭𝐲

እንኳን ለካህኑ፣ ለጻድቁና ለንጉሡ ቅዱስ ነአኲቶ ለአብ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን።

የዘር ሐረጋቸው ከሰሎሞን ዘር ሲያያዝ የመጣ ከ10ኛው እስከ 13ኛው መቶ ክፍለ ዘመን (920 -1253 ዓ.ም ገደማ) በላስታ ቡግና ምድር የነገሡ የላስታ ቡግና ተወላጅ የሆኑ የኢትዮጵያ ቅዱሳን ነገሥታት የንግሥናቸው መጠሪያ ‹‹የዛጉዌ ሥርወ መንግሥት›› ወይም ‹‹የላስታ መንግሥት›› በመባል ይታወቃል፡፡

ከዛጉዌ ነገሥታት ውስጥ የመጀመሪያው ንጉሥ መራ ተክለሃይማኖት የዐፄ ድልነአድን ልጅ መሶበ ወርቅን አግብቶ ዐራት ልጆችን ወልዷል፤ ሦስቱ ወንዶች ጠንጠውድም፣ ግርማ ስዩምና ዣን ስዩም ይባላሉ። ጠንጠውድም ገብረ መስቀልን ወለደ፣ ግርማ ስዩም ቅዱስ ይምርሃነ ክርስቶስን ወለደ፣ ዣን ስዩም ደግሞ ቅዱስ ገብረ ማርያምንና ቅዱስ ላሊበላን ወለደ፡፡ ገብረ መስቀልም ጣራው ክፍት ሆኖ ዝናብ የማያስገባውን ገዳም የመሠረቱትን የመቄቱን ታላቁን አባት አቡነ አሮንን ወለደ፡፡ ቅዱስ ገብረ ማርያም ደግሞ ቅዱስ ነአኵቶ ለአብን ወለደ፤ ይኸውም ቅዱስ ነአኵቶ ለአብ በዛሬዋ ዕለት ሞትን ሳያይ እንደነ ሄኖክና ኤልያስ የተሰወረ ነው፡፡

ቅዱስ ነአኵቶ ለአብ በዛግዌ ሥርወ መንግሥት ከነገሡ አሥራ አንድ ነገሥታት አንዱ ሲሆን ከመጨረሻውም ኹለተኛ ነው። እርሱን በአሥራ ኹለተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የወለዱት ቅዱሱ ንጉሥ ሐርቤ (ገብረ ማርያም) እና መርኬዛ ናቸው። ዘመኑ ቅድስና በላስታ ዙሪያ የመላበት በመሆኑ ቅዱስ ሐርቤ ከመመነኑ በፊት ነበር ነአኩቶ ለአብን የወለደው።

ንጉሥ ነአኵቶ ለአብ የቅዱስ ላሊበላ የወንድም ልጅ ነው። አባቱ ሐርበይ እናቱ መርኬዛ ይባሉ ነበር። ይህ ጻድቅ፤ ቅዱስ ነአኵቶ ለአብ ክህነትን ከንግሥና ይዘው ኢትዮጰያን ከመሩ ዐራቱ የዛግዌ ነገሥታት አንዱ ነው። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ለእነዚህ ዐራት ነገሥታት ጽላት ቀርጻ እና ቤተክርስቲያን አሳንጻ እንዲሁም የቅድስና ስም ሰጥታቸው ታከብራቸዋለች። እነሱም ይምርሃነ ክርስቶስ፤ ላሊበላ፣ ነአኵቶ ለአብ እና ገብረ ማርያም ናቸው።

የነአኲቶ ለአብ እናት መርኬዛ እርሱን ልትወልድ ምጥ ተይዛ ሳለ ጆሮዋ ቅዳሴን ይሰማ ነበር። ቅዳሴው ሲጀመር የጀመራት ምጥ ድርገት ሲወርዱ (ሥጋ ወደሙ ሲሰጥ) ተፈታላትና ልጇን ተገላገለች። ሕፃኑን አንስታ ስትታቀፈው ዲያቆኑ ማቁረቡን ፈጽሞ “ነአኵቶ” እያለ ሲዞር ሰማችው።

እዚያው ላይም “ነአኵቶ ለአብ” (አብን እናመስግነው) ስትል ስም አወጣችለት። ወዲያው ግን አባቱ ቅዱስ ሐርቤ መንግሥቱን ለቅዱስ ላሊበላ ሰጥቶ በርሃ በመግባቱ ቅዱሱ ሕፃን ወደ አጐቱ ላሊበላ ቤተ መንግሥት ውስጥ ገባ።

የቅዱስ ላሊበላ ቤት ደግሞ በቅድስና ያጌጠ ነውና ከእርሱና ከሚስቱ (ቅድስት መስቀል ክብራ) ሕፃኑ ነአኵቶ ለአብ ምናኔና ፍቅረ ክርስቶስን ተማረ። በዘመኑ ብዙ ሊቃውንት ስለ ነበሩ ቅዱሳት መጻሕፍትን በደንብ አጠና። ክህነት ተቀብሎ ቤተ ክርስቲያንን ሲያገለግልም እድሜው ሠላሳ ደረሰ።

በወቅቱ ቅዱስ ላሊበላና ባለቤቱ መስቀል ክብራ ልጃቸው ይትባረክ እያለ ንግሥናቸውን ለቅዱስ ነአኩቶ ለአብ አወረሱ። ቅዱሱ ነአኵቶ ለአብም ምን እንደሚሠራ ሲያስብ አንድ ነገር ተገለጠለት። ቤተ መንግሥቱን እንደሚገባ ካደራጀ በኋላ በቤት ውስጥ አንድ ጉድጓድን በቁመቱ ልክ አስቆፈረ።

በውስጡም በአራት አቅጣጫ ጦሮችን ተከለባቸው። ድንግል ካህን ነበረና ቀን ቀን ሃገር ሲያስተዳድር፣ ቅዳሴ ሲቀድስ በጾም ይውላል። ሌሊት ደግሞ ወዳስቆፈረው ቦታ ገብቶ ያለማቋረጥ እየጸለየ ይሰግዳል።

ወደ ምድር ሲሰግድ በፊቱ ያለው ጦር ይወጋዋል። ቀና ሲል ደግሞ የጀርባው ይቀበለዋል። እንዲህ እያለ የፈጣሪውን ሕማማት ይካፈላል። በተለይ ዓርብ ዓርብ ሲሆን ደሙ፣ እንባውና ላበቱ ተቀላቅሎ ይፈስ ነበር። እርሱ መስቀሉን ተሸክሞ ጌታውን ይከተል ዘንድ መርጧልና።

ከተጋድሎው ጐን ለጐን ቅዱስ ነአኵቶ ለአብ አብያተ ክርስቲያናትንም ያንጽ ነበር። በተለይ በ፲፪፻፲፩ ዓ.ም አካባቢ ያነጻት አሸተን ማርያም ልዩ ናት። እርሷን ካነጸ በኋላ ከቤተ መንግሥቱ በደመና ሠረገላ ተጭኖ እየሔደ ያጥናት፣ ይቀድስባትም ነበር።

ታዲያ አንድ ቀን አጥኖ ከቤተ መቅደስ ሲወጣ ብዙ ሥውራን ቅዱሳን መቅደሱን ከበው ተመለከተ። እርሱም “ወገኖቼ! ከወዴት መጣችሁ?” ቢላቸው “መዓዛ እጣንህን አሽተን መጣን።” ሲሉ መለሱለት። በዚህ ምክንያትም እስከ ዛሬ ድረስ “አሽተን (አሸተን) ማርያም” ስትባል ትኖራለች።

ዛሬ ታቦቱ ያለበት ገዳሙም በእርሱ የታነጸ ሲሆን እጅግ ተአምረኛ ቦታ ነው። ቅዱስ ነአኵቶ ለአብ የነገሠው በሠላሳ ዓመቱ ነው። ለዐርባ ዓመታት በእንዲህ ባለ ቅድስና ኑሮ ሰባ ዓመት ሞላው። በዚህ ጊዜም ለስም አጠራሩ ጌትነት ይሁንና መድኃኒታችን ክርስቶስ ወደ እርሱ ዘንድ መጣ፤ ሰላምታንም ሰጠው።

“ወዳጄ ነአኵቶ ለአብ! አንተ ስለ እኔ ፍቅር ለዐርባ ዓመታት መከራን ተቀብለሃልና ሞት አያገኝህም። ክፍልህ ከነ ኤልያስ ጋር ነውና። የሚያከብርህን አከብረዋለሁ። ደጅህን የሳመውን፣ ይህ ቢያቅተው በሩቁ ሆኖ በአድናቆት የተመኘህን፣ መታሰቢያህን ያደረገውን ሁሉ እምርልሃለሁ።” አለው።

ቀጥሎም “ይህች ቤት አንተ ስትደማ እንደኖርክባት እርሷም እስከ ምጽዓት ድረስ ለመታሰቢያህ ስትደማ ትኑር።” አለው። እነሆ ዛሬም ድረስ ከመቅደሱ ጠበል ይንጠበጠባል። ለዚህም ደግሞ እኛ ኃጥአን ምስክሮች ነን። ሳይገባን የቅዱሱን ደጅ ተመልክተናልና።

ቅዱስ ነአኵቶ ለአብም የዚህን ዓለም ተጋድሎውን ፈጽሞ ወደ ብሔረ ሕያዋን መላእክት ወስደውታል። የተሰወረበትን ዕለት መጽሐፈ ስንክሳር ኅዳር ፩ ሲያደርገው አንዳንድ መዛግብት ደግሞ በሦስት ነው ይላሉ። በዙፋኑም ላይ የአጐቱ የላሊበላ ልጅ አፄ ይትባረክ ተተክቷል።

ቅዱስ ነአኵቶ ለአብ እንደ ዮሐንስ ፍቁረ እግዚእ የጌታን ሕማምና ሞት በማሰብ በፊቱ ሳቅ ቀርቶ ፈገግታ እንደማያውቅ ቅዱስ ገድል ያስረዳል። በዕለተ ዐርብ የችሎቱን ዙፋኑን አይዘረጋም ከ6 እስከ 9ሰዓት እጁን ዘርግቶ በ9 ሰዓት መራራ ነገር ይቀምስ ነበር። በሥግደትም ጊዜ በፊት በኋላ በቀኝ በግራ የሚዋጉ ጦሮችን በማድረግ የጌታ መወጋትን ያስታውስ ነበር።

ከዚህ በኋላ ቅዱስ ንጉሥ በሰላምና በበረከትና በፍቅር 40 ዘመን፡፡ ከነገሠ በኋላ የቅዱስ ላሊበላ ልጅ ዐፄ ይትባረክ ትምህርት ቤት ሆዶ ስለ ነበር ከአለበት አስፈልጎ አስመጥቶ አነገሠው እርሱም የቀኖና የቱሩፍት ስራውን በበለጠ አጠጋክሮ በጽሞና በጸሎት ተወስኖ ሳለ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከአእላፍ መላእክት ጋር መጥቶ “ከአይነ ሞት የምትሰወርበት ጊዜ ስለደረሰ ቃል ኪዳን ልስጥህ ዘንድ የምትፈልገው ለምነኝ” አለው። እርሱም ለቅዱሳን የሰጠው ምክንያተ ድኅነት የሆነው ልመና ስራቀረበ የሚከተለው ቃል ኪዳን ተቀብላል።

“ዝክረ ስዋሬህን በማሰቡ በየወሩና በየዓመቱ ያከበረ ስምህ የጠራ ዝክርህን የዘከረ ቤተ መቅደስህ የሠራ ያሠራ መጽሐፈ ገድልህን ያጻፈንና የተረጐመውን የሰማውንና ያሰማውን እስከ 7 ትውልድ ምሕረትን እሰጠዋለሁ።

ስለ እኔ ፍቅር መከራ መስቀሌን በማሰብ ስለፈፀምከው መከራ አንድ ክረምት የበቀለውን ቡቃያ የሚያህል ነፍሳትን ምሬልሃለሁ።

መላ ዘመንህን ሁሉ ከአይንህ እንባ ሳታቋርጥ ያፈሰስከውን ምሳሌ ከቤተ መቅደስህ የሚጠባጠብ ጠበልን እሰጠዋለሁ። ይህም የእምባህ ምሳሌ ነው። ጠበልህ ብዙ ድውያንን እስከ ዕለተ ምጽዓት ሲፈውስ ይኑር።

በቃል ኪዳንህ የተማፀኑ ሁሉ የአንተን ልጆችና ወዳጆች መሆናቸው እንዲታወቅ በቅዱስ ገብርኤል እጅ ቀኝ ግራ እጃቸው ታትሞ መንግሥተ ሰማያት ይግብልህ። እድል ፈንታቸው ፅዋ ተርታቸው ከአንተ ጋር ይሁንልህ” በማለት ቃልኪዳኑን አደረገለት (ከሰጠው በኋላ) ከአይነ ሞት የምትሰወረው ኅዳር 3 ቀን ነው ብሎ ወደ ሰማይ ዐረገ።

ዛሬም ድረስ የነአኵቶ ለአብ ቤተክርስቲያኑ ባለበት ከጣራው ስር ፀበሉ እየቆየ ጠብ ጠብ ይላል። ክረምት ከበጋ እይለይም እንዲያውም በበጋ መጠኑ ይጨምራል። እንደገድሉ ታሪክ፣ ቅዱስ ነአኵቶ ለአብ አሸተን ማርያምን አንጾ ከጨረሰ በኃላ ማዕጠንት ይዞ ቤተክርስቲያኑን ሲያጥን ብዙ ቅዱሳን እጣኑን አሽትተው ቤተክርስቲያን ውስጥ ጥቅጥቅ ብለው ቆሙ፤ እናንተ ደግሞ እንዴት መጣችሁ አላቸው እነርሱም እጣኑን አሽትተን መጣን አሉት በዚህም የተነሳ “አሸተን ማርያም ” ተብላለች።

እንደተባለውም በሰባ ዓመቱ ኅዳር 3 ቀን ማዕጠንት በማጠን ላይ እያለ በ7 ሰዓት ገብረ ክርስቶስ የተባለው ዲያቆን በመስቀሉ ባርኮት ኤልሳዕ ኤልያስን እያየ ወደ ሰማይ እንደወጣ እርሱ እያየው ከአይነ ሞት ተሰውሯል።

ከጻድቁ ንጉሥ ከቅዱስ ነአኵቶ ለአብ እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።
አምላከ ቅዱስ ነአኩቶ ለአብ በቃል ኪዳኑ ይማረን።
ከበረከቱም አትረፍርፎ ይስጠን።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር ለዘበቅዱሳኒሁ ይሴባሕ ይእዜኒ ወዘልፈኒ ወለዓለም ዓለም አሜን ወአሜን ለይኩን ለይኩን፡፡

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 1 year ago on November 12, 2023
  • By:
  • Last Modified: November 12, 2023 @ 6:07 pm
  • Filed Under: Ethiopia

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar