ከሰላም ሚኒስትር ዲኤታነታቸው ትናንት ሰኞ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተነሱት አቶ ታዬ ደንደአ “መንግሥትን ለመጣል በማሴር” ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገለጸ።
አቶ ታዬ በተደረገባቸውም ክትትል መንግሥት ሸኔ እያለ ከሚጠራው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት አመራሮች ጋር ግንኙነት በመፍጠር መንግሥትን ለመጣል ሲያሴሩ ነበረ ሲል የፀጥታ እና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን በላከው መግለጫ አስታውቋል።
“ከኦነግ ሸኔ አመራሮች እና በሽብር ወንጀል ከተጠረጠሩ ጽንፈኛ ኃይሎች ጋር ትስስር በመፍጠር መንግሥትን በአመጽ፣ በሽብር እና በትጥቅ ትግል ለመጣል ሲያሴር ተደርሶበታል” ሲልም መግለጫው አስፍሯል።
አቶ ታዬ ባለፈው ሳምንት ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ሰፊ ቃለ ምልልስ ላይ በመንግሥት እና በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት መካከል ሲደረግ ለነበረው ድርድር መደናቀፍ መንግሥታቸውን ተጠያቂ ማድረጋቸው ይታወሳል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ትዕዛዝ ከኃላፊነታቸው የተነሱት የቀድሞው ባለሥልጣን “ኢትዮጵያን ለማፍረስ ከሚንቀሳቀሱ ፀረ ሰላም ኃይሎች ጋር በመተሳሰር ለጥፋት ተልዕኮ በህቡዕ ሲሰራ ተደርሶበታል” ሲል የግብረ ኃይሉ መግለጫ ከሷል።
በሰላም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ከፍተኛ ኃላፊ የነበሩት አቶ ታዬ በተለያዩ አካባቢዎች በተፈጸሙ እገታዎች ውስጥም እጃቸው አለበት ተብሏል።
“በአገራችን በተለያዩ አካባቢዎች በንፁሃን ዜጎች ላይ ሲፈፀሙ በነበሩ የሽብር ተግባራት በተለይም ደግሞ ከእገታ ጋር በተያያዘ እጃቸው እንዳለበት የተደረሰበት መሆኑንም” መግለጫው አስፍሯል።
የጋራ ግብረ ኃይሉ ባወጣው መግለጫ አቶ ታዬ በሥልጣን ላይ በነበሩበት ወቅት መንግሥትን እና ፓርቲያቸውን ለመናድ እየሞከሩ ነበር ሲልም ወንጅሏቸዋል።
“መንግሥታዊ ኃላፊነቱን ተቀብሎ እየሠራ በነበረበት ወቅት መንግሥታዊ እና የፓርቲ መዋቅሩን በሴራ ለመናድ በህቡዕ እንቅስቃሴ ሲያደርግ መቆየቱን በመረዳት ያላሰለሰ ጥናት እና ክትትል ሲደረግበት ነበር” ብሏል መግለጫው።
በቁጥጥር ስር በዋሉበት ወቅትም በመኖሪያ ቤታቸው በተደረገ ፍተሻ “በህቡዕ ለሚያደርገው ፀረ ሰላም እንቅስቃሴ ሲገለገልባቸው የነበሩ” የተባሉ ዘጠኝ ሞባይሎች፣ አራት ላፕቶፖች፣ 3 አይፓዶች፣ በርካታ ፍላሾች አራት የተለያዩ ተሽካርካሪ ሰሌዳዎች መገኘታቸውንም አመልክቷል።
በተጨማሪም ልዩ ልዩ የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎች፣ ክላሽንኮቭ ጠመንጃ እና ሽጉጦች፣ ጥይቶች እንዲሁም የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት አርማዎች እና በተለያዩ ግለሰቦች ስም የተዘጋጁ የሠራዊቱ መታወቂያዎች፣ ሰነዶች እና ማስታወሻዎች መገኘታቸውንም ግብረ ኃይሉ ገልጿል ነገር ኝ ተገኙ የተባሉትን ኤግዚቢቶች ለመገናኛ ብዙሃንም ለማሳየት ፍቃደና አልነበሩም ፡፡ ስለዚህ መንግስት በፈለገው አቅጣጫ ይረዳው ዘንድ መረጃዎቹን ከእራሱ ግምጃ ቤት አውጥቶ ሊከሳቸው እንደተዘጋጀም ነው የተሰማው፡፡
በመንግሥት ቁጥጥር ሊውሉ እንደሚችሉ ሲገምቱም “ታጋይ ለመምሰል በራሱ እና በተለያዩ የማኅበራዊ ሚዲያ የትስስር ገጾች አፍራሽ እና ፀረ ሰላም ጽሁፎችን፣ ንግግሮችን እና መግለጫዎችን በማን አለብኝነት ሲያስተላልፍ ቆይቷል” ሲልም የጋራ ግብረ ኃይሉ መግለጫ አስፍሯል።
በጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሥልጣን መሰናበታቸውን ተከትሎ በሕግ ሊያስጠይቃቸው የሚችል ነገር ይኖር እንደሆነ በቢቢሲ ተጠይቀው የነበሩት አቶ ታዬ “ይህ [በሕግ መጠየቅ] ምን ችግር አለው ታዲያ። ነገር ግን ሕግ የታለና በሕግ ይጠይቁኛል። ከጠየቁኝ ደግሞ ዝግጁ ነኝ” ሰኞ ምሽት ገልጸው ነበር።
አቶ ታዬ በግል የማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ በመንግሥት ውስጥ ያሉ አመራሮችን በግልጽ በመተቸት እና ለመገናኛ ብዙኃን በሚሰጧቸው ቃለ ምልልሶች ከሌሎች የመንግሥት ባለሥልጣናት በተለየ ይታወቃሉ።
አቶ ታዬ ስንብታቸውን ተከትሎ በፌስቡክ ገጻቸው ላይ በመጸጸት እንዳሰፈሩት “እውነት መስሎኝ በአገር ህልውና ስም ሲያካሄዱ የነበረውን እና ኢትዮጵያውያንን ከማገዳደል አልፎ አገሪቷን ያደቀቃትን ከንቱ ጦርነት ሳዳምቅልዎ በነበረበት ወቅት ሲያወድሱኝ ነበር” ብለዋል።
የጋራ ግብረ ኃይሉ በበኩሉ አቶ ታዬ “በተደጋጋሚ መንግሥትን ገዳይ እና ጨፍጫፊ እያለ ሲወቅስ የሚደመጥ ቢሆንም፤ በተግባር ግን ከሽብርተኞች፣ ከጽንፈኛች እና ነፍሰ ገዳዮች ጋር የጥፋት ትስስር የነበረው ራሱ መሆኑ በተደረገ ክትትል ተረጋግጧል” ብሏል።
በመንግሥት እና በፓርቲ መዋቅር ሆነው በተመሳሳይ “እኩይ” ሲል በጠራው ዓላማ በተሰማሩ አካላትም ላይ ክትትል እየተደረገ እንደሚገኝም ግብረ ኃይሉ ገልጿል።
Average Rating