የአሜሪካ ሜሪላንድ ግዛት ገዥ ዊስሊ ዋቴንዴ ሙር የአፍሪካ ጉዳዮች ኮሚሽን አቋቋሙ፡፡ ይህ ኮሚሽን በሜሪላንድ የሚገኙ አፍሪካዊያንን ኢኮኖሚያዊ፣ የስራና የንግድ እንቅስቃሴ በተመለከተ ለገዥው ወይንም ለሌሎች የመንግስት መስሪያ ቤቶች እንደአማካሪ ቦርድ ሆኖ የሚያገለግል መሆኑ ተገልጿል፡፡ ኮሚሽኑን ናይጄሪያዊ በሊቀመንበርነት የሚመሩት ሲሆን አራት ኢትዮጵያዊያን በአባልነት ተካተውበታል፡፡
አንደኛው ፕሮፌሰር አለምሰገድ አባይ ናቸው፡፡ በፎረስትበርግ ስቴት ዩኒቨርስቲ የታሪክ ፕሮፌሰር የሆኑት አለምሰገድ በተለይ በአፍሪካ፣ መካከለኛው ምስራቅና በአፍሪካዊ አሜሪካዊያን ላይ ትኩረት በማድረግ ያጠኑ ናቸው፡፡ በአሁኑ ወቅትም በተለያዩ አለም አቀፍ ኮንፈረንሶች ላይ በመገኘት የጥናት ውጤቶቻቸውን እያቀረቡና እያብራሩ ይገኛሉ፡፡
ሁለተኛዋ የኮሚሽኑ አባል አዲዳና አሸብር ትባላለች፡፡ እስከቅርብ ጊዜ የቪሌጅ ካፒታል አካባቢያዊ ዳይሬክተር ሆና የሰራቸው አዲዳና ድርጅቱ ከሰሀራ በታች የሚያከናውናቸውን የሀይል ልማቶች ስትመራ ቆይታለች፡፡ ቀደም ሲልም የአፍሪካ ሌደርሺፕ ኔትወርክ የአፍሪካ ቢዝነስ ፌሎውሺፕ ኔትወርክ ፕሮግራም ዳይሬክተር ነበረች፡፡
በሶስተኝነት የኮሚሽኑ አባል እንድትሆን የተመረጠችው የፒኤምኤስ ፓርኪንግ ባለቤት አምሳለ ገብሩ ናት፡፡ አምሳለ በዲሲ፣ ሜሪላንድና ቨርጂኒያ አካባቢዎች በአየር ማረፊያና በተለያዩ ቦታዎች ላይ በርካታ የመኪና ማቆሚያዎች ያሏትና በድርጅቷ አማካኝነት የምታስተዳድር መሆኑ ይታወቃል፡፡ እንዲሁም የአሜሪካዊ ኢትዮጵያዊያን ህዝብ ጉዳዮች ኮሚቴ የሜሪላንድ ቻፕተርን ከመሰረቱት አንዷ ናት፡፡
ሌላኛዋ የኮሚሽኑ አባል ዮዲት ነገደ ናት፡፡ ዮዲት በጂኦ ስኮፕ ኢንቫይሮሜንታል አለም አቀፍ የፕሮግራም ማኔጀር ከመሆኗም በላይ የፔምበርተን ኮፊ ባለቤት ናት፡፡ በተለይም በተለያዩ ፕሮጀክቶቿ ኢትዮጵያን የሚመለከቱ ጉዳዮችን በማንሳት ድጋፍ እንዲደረግላቸው ቅስቀሳ በማድረግ ትታወቃለች፡፡
Average Rating