ከኢትዮጵያ አየር መንገድ የማስታወቂያና የሕዝብ ግንኙነት የሥራ ክፍሎች ዕውቅና ውጪ፣ በቅጥር ግቢው ውስጥ የፎቶና የቪዲዮ ቀረፃዎች እንዲካሄዱ ፈቃድ ሰጥተዋል የተባሉ የአዲስ አበባ ሽያጭ ክፍል ሠራተኞች ላይ አስተዳደራዊ ዕርምጃዎች መወሰዱ ተገለጸ።
ይህ የተገለጸው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው፣ እንዲሁም የአየር መንገዱ የንግድ ዘርፍ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ለማ ያደቻ ወቅታዊ ጉዳዮችን አስመልክቶ ዛሬ የካቲት 5 ቀን 2017 ዓ.ም. በአየር መንገዱ ዋና መሥሪያ ቤት ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሰጡ ነው።
ኢትዮጵያ እያስተናገደችው ስለምትገኘው የአፍሪካ ኅብረት ጉባዔን ጨምሮ በተለያዩ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ የሰጡት ዋና ሥራ አስፈጻሚው አቶ መስፍን፣ በቅርቡ ለተዋናይትና ሞዴል ምሕረት ታደሰ (ፒፒሎ) የልደት በዓል አየር መንገዱ ፈቃድ ሰጥቶ ተቀርጿል በሚል ስለተሠራጩት የግለሰቧ ቪድዮዎችና ምሥሎች፣ እንዲሁም የአየር መንገዱ ከፍተኛ አመራሮች ስለጉዳዩ መረጃ አልነበራቸውም በሚል ስለተሰጠው ምላሽ ጉዳዩን በዝርዝር እንዲያብራሩ ከጋዜጠኞች ጥያቄዎች ቀርቦላቸዋል።
አቶ መስፍን፣ ‹‹ቪድዮው መቀረፁ ትክክል ነው። ለግለሰቧ ሕጋዊ ፈቃድ ተሰጥቶ የፀጥታ መምርያ ሒደቱን ተከትሎ ጥገና ወደሚደረግበት የአየር መንገዱ ቅጥር ግቢ ገብታ የተከናወነ ነው፤›› ብለው፣ ‹‹የፀጥታ ፕሮሲጀሩን አሟልታ ነው ቪድዮው የተቀረፀው። ለአዲስ አበባ ሽያጭ ቢሯችን ታኅሳስ 27 ጥያቄ ያቀረበችበት ቀን ሲሆን፣ ከሁለት ቀን በኋላ ፈቃድ ተሰጥቶ ቀረፃው ተካሂዷል፤›› ሲሉ ገልጸዋል።
ይሁንና አጠቃላይ ሒደቱ የአየር መንገዱን ተቋማዊ አሠራር በመጣስ መከናወኑን ተናግረው፣ ‹‹በአየር መንገዱ አሠራር መሠረት የማስታወቂያ ሥራዎች ሲሠሩ በሁለት መንገዶች ወይም የሥራ ክፍሎች በኩል ነው። አንደኛው በሕዝብ ግንኙነት ሥራ ክፍል ሲሆን፣ ሁለተኛው ፕሮሞሽንና ማስታወቂያ የሚባለው የሥራ ክፍል ደግሞ አየር መንገዱንና ሥራዎቹን በተመለከተ ለሕዝብ የሚተላለፉ ማስታወቂያዎችን የሚመለከተው ነው። የአርቲስቷ ሥራ ግን ከእነዚህ ሁለት ክፍሎች ውጪ ነው የተሠራው። ጥያቄው ለአየር መንገዱ የአዲስ አበባ ሽያጭ ቢሮ ሲቀርብ ለእነዚህ ሁለት የሥራ ክፍሎች መተላለፍ ነበረበት፤›› ሲሉ አስረድተዋል።
የአየር መንገዱ ከፍተኛ አመራሮች ከአሠራር ጥሰት ባለፈ ስለጉዳዩ ከፍተኛ አመራሮቹ ዕውቅና አልነበራቸውም በሚል ያሠራጨውን መረጃ በተመለከተ ማብራሪያ የሰጡት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ ‹‹የአዲስ አበባ ሽያጭ ቢሮ ለአዲስ አበባ የጥበቃ መምርያ በቀጥታ ነው ፈቃድ እንደተሰጣት የሚገልጽ ደብዳቤ የጻፈው፡፡ ከፍተኛ አመራሩ ስለጉዳዩ መረጃ ሊኖረው የሚችለው የማስታወቂያው ጥያቄ ቀደም ሲል በጠቀስኳቸው ሁለት የሥራ ክፍሎች በኩል ሲመጣ ብቻ ነው፣ ይህ አልሆነም። በኋላ የተፈጠረውን ነገር ስንሰማም የአየር መንገዱ ከፍተኛ አመራሮች በቀጥታ ለኦዲት ክፍሉ መመርያ ሰጥተን፣ ስለጉዳዩ ሙሉ ሪፖርትና ምክረ ሐሳብ ካቀረበልን በኋላ ነው የተንቀሳቀስነው፡፡ የማስታወቂያ ሥራዎችን ለመሥራት ፈቅደን ቢሆንና በትክክለኛዎቹ የሥራ ክፍሎች በኩል አልፎ ቢሆን ኖሮ ውል ይኖረን ነበር፣ ግን ያለ ውል ነው ሥራው የተሠራው፤›› ብለዋል።
በአየር መንገዱ የአውሮፕላኖች ጥገና በሚካሄድበት ቅጥር ግቢ ቪዲዮውን የቀረፀችውና ምሥሉ ከተቀረፀ ከአንድ ወር በላይ ቆይታ ካሠራጨችው ግለሰብ ለአዲስ አበባ ሽያጭ ክፍል ፈቃድ ለመጠየቅ ገቢ የተደረገው ደብዳቤ፣ ‹‹የአየር መንገዱን ክብር በሚጠብቅ መልኩ አየር መንገዱን መሠረት በማድረግ አገሪቱን ለቱሪዝም ሥራዎች ለማስተዋወቅ›› የሚሉ ምክንያቶች የቀረቡ ሲሆን፣ ‹‹ማናቸውንም ምሥሎችና ቪዲዮዎችን ለአየር መንገዱ ገቢ እናደርጋለን፤›› በማለት የተጠቀሰ መሆኑን ሪፖርተር የተመለከተው ደብዳቤ ያሳያል፡፡
ይሁን እንጂ ማናቸውም ፎቶዎችም ይሁኑ ተንቀሳቃሽ ምሥሎች ለኢትዮጵያ አየር መንገድ የትኛውም የሥራ ክፍል ከግለሰቧ አስቀድመው እንዳልተሰጡ የሪፖርተር ምንጮች አረጋግጠዋል፡፡
ከዚህ አኳያ በሕግ ሊኖር የሚችል ተጠያቂነትን በተመለከተ ምላሽ የሰጡት የአየር መንገዱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ፣ ‹‹ከሕግ ክፍላችን ጋር ተነጋግረን በሕግ አግባብ የምትጠየቅበት ሆኖ ካገኘነው እንጠይቃለን፤›› ብለዋል።
‹‹ችግሩ የተፈጠረው በውስጣችን በተፈጠረ የአሠራር ክፍተት ነው። አስተዳደራዊ ዕርምጃዎችን ወስደናል፣ እየወሰድንም ነው። የአየር መንገዱ ከፍተኛ አመራር ጉዳዩን ትኩረት ሰጥቶ ነው የሚያየው። አንደኛ በዚህ ጉዳይ የተሳተፉት ላይ ጠበቅ ያለ ዕርምጃ እንወስዳለን። ሁለተኛ ጥፋቱ እንዳይደገም የሚያስችል አሠራር እየዘረጋን ነው፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡
Average Rating