www.maledatimes.com የመለስ አምልኮ ፪ – (ከተመስገን ደሳለኝ) - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

የመለስ አምልኮ ፪ – (ከተመስገን ደሳለኝ)

By   /   November 21, 2012  /   Comments Off on የመለስ አምልኮ ፪ – (ከተመስገን ደሳለኝ)

    Print       Email
0 0
Read Time:42 Minute, 3 Second

(ከተመስገን ደሳለኝ)
22 አካባቢ በሚገኘው አክሱም ሆቴል ፊት ለፊት ከተሰቀለው ግዙፉ የቀድሞ ጠቅላይ ሚንስትር ምስል ስር ‹‹መለስ ኩለ መንኡ ንህዝቢ ዘወፈየ ጂግና ወዲ ህዝብ ኢዩ›› (መለስ ሁለመናውን ለህዝብ የሰጠ ጀግና የህዝብ ልጅ ነው) የሚል የትግርኛ መፈክር ይታያል፡፡ በመላ ሀገሪቱ ከተሞችና ገጠሮች የመለስ ፎቶ ያልተሰቀለበት ጉራንጉር ማግኘት የማይታሰብ ነው፡፡ የምንዱባኖች ጠላና ጠጅ ቤቶች እንኳ ሳይቀሩ ‹‹የመለስ ራዕይን እናሳካለን›› የሚል መፈክር ሊወድቅ ባንጋደደ በራቸው ላይ እንዲለጥፉ ተገደዋል፡፡
የሰውየው ሞት በይፋ ከተነገረ ወዲህ የኢህአዴግ አመራርና ካድሬዎች ከፖለቲከኛነት ወደ ‹‹ሀዋርያነት›› ተቀይረዋል፡፡ በየደረሱበት ስለ‹‹መለስ ራዕይ›› ሲቃ እየተናነቃቸው ይሰብካሉ፡፡ያነበሩት መንግስት የመቀጠሉን አስፈላጊነት በእርሳቸው ስም ለማሳመን ቀን ከሌት እየባተቱ ነው፡፡ አዳዲስ ምእመናኖችንም እያጠመቁ ደቀ-መዛሙርታትን በማብዛቱ ላይ ተጠምደዋል፡፡ ሰው ዝር በማይልበት ጭው ባለ ምድረ በዳ ሳይቀር ይጮኻሉ ‹‹የመለስን ራዕይ እናሳካለን!››… ከብሔራዊ ቲያትር እስከ ታላቁ ሩጫ ድረስ ያሉ ህዝባዊ መድረኮች የታላቁ መሪ ራዕይ ይዘከርባቸዋል፡፡ በዚሁ መድረክ ስለራዕዩ ቀጣይነት ተተኪዎቻቸው ቃል ይገቡበታል፡፡ ከወረዳ ካድሬ አንስቶ በተለያዩ
ሀገራት አምባሳደርነት እስከ ተሾሙ ዲፕሎማቶች ድረስ ‹‹መለስ በስጋ እንጂ በመንፈስ የማይሞቱ›› ዘላለማዊ ህያው ስለመሆናቸው ይሰብኩ ዘንድ ድርጅታቸው ተልዕኮ ሰጥቷቸዋል፡፡ መለስን በማምለክ አቅላቸውን የሳቱት በተባበሩት መንግስታት ጽ/ቤት የአሜሪካ ‹‹ቋሚ መልዕክተኛ›› ሱዛን ራይስ በስርአተ ቀብራቸው ላይ ‹‹…it’s deeply unfair to lose such a talented and vital leader so soon, when he still had so much more to give. He was an uncommon leader, a rare visionary… world-class mind›› (ብዙ ነገር ሊሰጠን በሚችልበት ወቅት እንዲህ አይነቱ አስፈላጊ መሪ በአጭር መቀጨቱ እጅግ ያስቆጫል፡፡ 
እርሱ ብሩህ አዕምሮ የታደለ የትም የማይገኝ ባለ ራዕይ መሪ ነበር) ካሉ ከአንድ ወር በኋላ እንኳ ከሀዘናቸው መጽናናት እንዳልቻሉ ያስተዋልኩት በኒውዮርክ ከተማ ‹‹አቢሲኒያ ባብቲስት ቤተ-ክርስቲያን›› ለሟቹ በተደረገ የመታሰቢያ ዝግጅት ላይ እንባ እየተናነቀቻው ‹‹…He worked tirelessly, always inclined to assume the bulk of any burden himself…›› (…ሁልጊዜም ግዙፍ ሸክሞችን በራሱ ላይ የሚጭን ታታሪ ሰው…) ማለታቸውን ስሰማ ነው፡፡ እናም ይህ መፅናናትን ያልወደደው የሴቲቱ ሀዘን በአንድ ወቅት አቶ መለስ የዶ/ር ብርሃኑ ነጋን እና የአና ጎሜዝን ወዳጃዊ ግንኙነት በክፋት በመተርጎም የአውሮፓ ህብረት የምርጫ ታዛቢ ተቋም የ1997ቱን ምርጫ አስመልክቶ ያቀረበውን ሪፖርት ለማብጠልጠል በ‹‹ኢትዮጵያን ሄራልድ›› ጋዜጣ ላይ በተከታታይ በፃፉት ፅሁፍ ይሁነኝ ብለው የመረጡትን ‹‹What’s love got to do with it?›› የሚለውን የቲና ተርነርን ዘፈን ያስታውሰኛል፡፡
‹‹ናፖሊዮን አይሞትም››፤ መለስም… ባለፉት ሃያ አንድ አመታት ‹‹ኢህአዴግ የአርሶ አደሩ ወዳጅ ነው››፣ ‹‹ደርግን ታግሎ የጣለ ብሶት የወለደው ነፃ አውጪ ነው››፣ ‹‹ብሄር ብሄረሰቦችን ከታሰሩበት እስር ቤት የፈታ ነው››… ይባል የነበረው ‹‹በመለስ ራዕይ›› ተቀይሮአል፡፡ ከቅያሬውም ጋር ‹‹መለስን ማምለክ›› እንደ አቅጣጫ ተይዟል፡፡ ‹‹ያ ሁሉ ታጋይ ለ17 ዓመታት መስዋዕትነት መክፈሉ ተረስቷል›› ይላሉ የቀድሞ የድርጅቱ የአመራር አባል የነበሩ ታጋይ፡፡ ‹‹የታገልነው ተረስቶ፣ የተሰዉት ተረስተው ኢህአዴግ ወደ ስልጣን የመጣው በመለስ ራዕይ ይመስል፣ መለስ ከሞቱ በኋላ ‹እርሳቸው ባስቀመጡልን ራዕይ እንጓዛለን› ማለትስ ምን ማለት ነው?›› ሲሉ ይጠይቃሉ-እኚሁ የቀድሞ የድርጅቱ አንጋፋ ታጋይ፡፡ በህይወት ሳሉ በሀገሪቱ ዋና ዋና ከተሞች ‹‹እናከብርሃለን፣ እንኮራብሃለን፣ እንከተልሃለን…›› ከሚሉ ውዳሴዎች ጋር ምስላቸው የታተመባቸው ግዙፍ ቢልቦርዶች፣ ህይወታቸው ካለፈ በኋላ ‹‹ባለራዕይ አይሞትም፣ ራዕይህን እናስቀጥላለን፣ ዘላለማዊ ነህ…›› በሚሉ ቃላት ተተክተው በየመንደሩ፣ በየጉራንጉሩ እንዲሰቀሉ ተደርገዋል፡፡ ራሳቸው መለስ ‹‹በትግላችን ብዙ መለሶችን እናፈራለን›› እንዳላሉ ሁሉ፤ በስማቸው ቴምብር መታተሙን ሲሰሙ ‹‹ድርጅትንም ሆነ ግለሰብን መወደድ ይቻላል፤ ማምለክ ግን ኢ-ዲሞክራሲያዊ ነው፡፡ በመርህ ደረጃ እኔም አላምንበትም›› እንዳላሉ ሁሉ ወራሾቻቸው መለስን ‹‹ተተኪ የሌላቸው አልፋና ኦሜጋ›› አስመስለው ቅቡል ለማድረግ ቀን ከሌሊት እየለፈፉ ነው፡፡ በፖለቲካ ተንታኞች አረዳድ የዚህ ሁሉ መነሻ ‹‹በድርጅቱ ውስጥ ያሉ ወሳኝ ባለስልጣናት ሀገሪቷን ያለ መለስ መምራት አንችልም በሚል ጭንቀት
መወጠራቸው ነው››፡፡ እነዚህን ሁኔታዎች ዛሬ ላይ ሆኜ ስመለከታቸው መለስ ከ12 ዓመት በፊት ከአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ መምህራን ጋር ባደረጉት ውይይት ላይ የተናገሩትን ትንቢት መሰል ጥቁምታቸውን ያስታውሰኛል፡፡ ‹‹አንድ ግለሰብ የድርጅት ምልክት (አይዶል) ከሆነ፤ ያን ጊዜ ድርጅቱ ሞቷል ማለት ነው›› (የመለስ አምልኮ መፅሀፍ፣ ገፅ 113)ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝበእርግጥ በሟች መንፈስ ሃገር ለማስተዳደር የሚደረገው ጥረት አንድ እውነታን ግልፅ አድርጓል፡፡
ይህም ቀድሞውንም ኢህአዴግ የሚባል ድርጅት ያለመኖሩን እና ድርጅትም፣ መንግስትም፣ ፖሊሲም መለስ ብቻ የነበሩ መሆኑን ነው፡፡ በቀጣዮቹ ጥቂት ዓመታት በስልጣን ለመቆየት እና ብሶት የሚወልዳቸውን ተግዳሮቶች ለመሻገር ‹‹መለስ አልሞተም፤ አረገ እንጂ›› ብሎ መወትወት የርዕዮተ- ዓለምን ያህል የሚሰበክ ወሳኝ ፕሮፓጋንዳ ሆኗል፡፡ ኢህአዴግ መለስ በስጋ ቢያልፉም በመንፈስ ዘላለማዊ እንደሆኑ አድርጎ መቀበሉ በ19ኛው ክ/ዘመን መጀመሪያ ፈረንሳይን ያስተዳድር የነበረው ናፖሊዮ ቦናፓርቲ ስለመሞቱ ላረዳው ባልደረባው ‹‹ እኔ ከናፖሊዮን ጋር በብዙ የጦር አውድማዎች ተሳትፌያለሁ፡፡ አንተ ናፖሊዮንን አታውቀውም፡፡ ናፖሊዮን አይሞትም›› አለ ከተባለው ወታደር ጋር የሚነፃፀር ሆኖብኛል፡፡ መለስ አይሞትም… ‹‹መለሲዝም›› እየመጣ ነውን?
የኢትዮጵያ የእግር ኳስ ብሔራዊ ቡድን ለአፍሪካ ዋንጫ ማለፉ ማስታወሻነቱ ለመለስ ተበርክቷል፡፡ ከጨዋታው ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ የቡድኑ አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ‹‹ይህንን ጨዋታ አሸንፈን ወደአፍሪካ ዋንጫ
በማለፍ ለጀግናው መሪያችን ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ መታሰቢያነት እናደርገዋለን›› ማለታቸው ከድሉ በኋላ ተደጋግሞ ተጠቅሷል፡፡ እየተካሄደ ያለው የ2005 ዓ.ም ‹‹የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ›› ውድድርም
‹‹የመለስ ዋንጫ›› የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል፡፡ ወደፊት የሚካሄዱ የተለያዩ ዓመታዊ በዓላት እና የተማሪዎች ውድድሮችም በመለስ ስም መሰየማቸው አይቀሬ እንደሆነ እየተተነበየ ነው፡፡ ዘንድሮ በአዳማ ከተማ እየተከበረ ያለው አራተኛው ‹‹የከተሞች ቀን›› የመለስ ራዕይ ‹‹የሚተነተንበት››ና የሚዘከርበት ከመሆኑ በተጨማሪም የበዓሉ መሪ ቃል ‹‹ከተሞች የክቡር ጠቅላይ ሚንስትሩን ራዕይ ያሳካሉ›› የሚል እንዲሆን ተደርጓል፡፡ በዚሁ ወር መጨረሻ በባህርዳር ከተማ ለሰባተኛ ጊዜ የሚከበረው ‹‹የብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ቀን››ም መለስ የሚመለኩበት ይሆን ዘንድ ተወስኗል፡፡ የዘንድሮውን በዓል ለየት የሚያደርገው ‹‹የመለስ ራዕይን ለማስፈፀም ቃል የምንገባበት መሆኑ ነው›› የሚል የዜና ማድመቂያም በቴሌቪዥን ተሰምቷል፡፡ ከመለስ ህልፈት ማግስት ጀምሮ እንደጃንሆይ በትንሽ ትልቁ በየቀኑ ከቴሌቪዥን የማይጠፉት የብአዴን የአመራር አባል እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ካሳ ተክለብርሃን ‹‹የብሄር ብሄረሰቦች እና የህዝቦች ቀን የታላቁ መሪያችን ዋነኛ መለያ ነው›› ሲሉ ነው በዓሉን የገለፁት፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎንም መንግስታዊም ሆኑ የግል ተቋማት ‹‹በመለስ ስም››ለሁለተኛ ጊዜ ቦንድ እንዲገዙ የማድረጉ የቅስቀሳ ስራ ‹‹ውጤት›› እያሳየ ነው፡፡ በአንዳንድ ሰዎች ዘንድም ‹‹መለስን ማምለክ›› እየሰረፀ ይመስላል፡፡ ምክንያቱም መንግስት በአዲስ አበባ አንድ አካባቢ ‹‹ቤታችሁ ህገ-ወጥ ነው›› በማለት ለማፍረስ በዶዘር የታገዘ ኃይል ይዞ ሲመጣ ነዋሪዎቹ የመለስን ምስል ይዘው ጎዳና ላይ በመውጣት ‹‹ከደፈራችሁ ይህን ምስል ረግጣችሁ እለፉና አፍርሱ›› አይነት ተቃውሞ ሲያሰሙ አፍራሽ ግብረ ኃይሉ ወደ መጣበት ተመልሷል፡፡
እንደታቦት በመለስ ፎቶ ሲለመን… የግብርና፣ የጤና፣ የትምህርት… ፖሊሲዎች ሁሉ ‹‹የመለስ ራዕይ›› በመሆናቸው በስማቸው እየተጠሩ ነው፡፡ በዚሁ የባጀት ዓመት የገቢዎች ሚኒስቴር የሚሰበስበው ግብር መለስን ማስታወሻ ነው፡፡
የአንድ የመንግስት መስሪያ ቤት ሰራተኞች የስራ ሰዓት አክብረው ለመስራት በመለስ ስም ቃል መግባታቸውን በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ሰምቻለሁ፡፡ ‹‹እልፍ ሆነናል›› የሚለውን የትግል ዘመኑን ዝነኛ መዝሙር ዛሬ አንድም የሚዘምረው የለም፡፡ እንዲያውም በተቃራኒው ድርጅቱ ‹‹አንድ ሰው ሆኗል›› እየተባለ በመዘመር ላይ ነው፡፡
ከድምፀ-ወያኔ እስከ ፋና ያሉ የድርጅቱ ሬዲዮ ጣቢያዎችም በስህተት እንኳን መዝሙሩን አያስተላልፉትም፡፡ ‹‹ደርግን ታግለን ያሸነፍን ነን›› የሚለው የትጥቅ ትግሉ ትርክት ያለፈበት ጉዳይ ሆኗል፡፡ በዚህ ወቅት መዘመርም ሆነ ማሸብሸብ የተፈቀደው ‹‹ለመለስ አምልኮ›› ብቻ ነው፡፡ መለስ መሲህ ናቸው፣ መለስ ዳግማዊ ቴዎድሮስ ናቸው፣ መለስ መለኮታዊ እንጂ ስጋ ለባሽ ፍጡር አይደሉም… በሚሉ ጭብጦች ዙሪያ ካላጠነጠነ መዝሙሩም መዝሙር አይደለም፣ ወረቡም ወረብ አይሆንም፤ ሽብሸባውም… ሚዲያውም ቢሆን ከዚህ ጭብጥ ውጭ ለተዘጋጁ የኪነጥበብ ስራዎች የአየር ሰአት የለውም፡፡ የቀድሞ ጠቅላይ ሚንስትር አስተዳደር ለፈፀመው የሰብአዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብት ረገጣዎች ይሰጥ የነበረው ሰበብ ‹‹እነዚህ መብቶች ለምንከተለው ልማታዊ መንግስት እንቅፋት ናቸው›› የሚለው፤ በድህረ-መለስ ተቀይሮ ‹‹ከኢህአዴግ መስመር ውጭ ያሉ ሃሳቦች በሙሉ የመለስን ራዕይ ያደናቅፋሉ›› በሚል ተተክቷል፡፡ አስገራሚው ነገር ደግሞ ሰውየው ራሳቸውን ችግር ፈቺ፣ ሀሳብ አመንጪ፣ የአለም አቀፍ ፖለቲካ ተንታኝ፣ አርቆ አሳቢ ምሁር… አድርገው ማቅረባቸው ሳያንስ ህይወታቸው ካለፈ በኋላም ይህን ሁሉ መንፈሳቸው የሚፈፅመው ጉዳይ በማስመሰል መቅረቡ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ አብዮታዊ ዴሞክራሲ፣ ነፃ ገበያ፣ ልማታዊ መንግስት፣ ልማታዊ ሚዲያ… የተባሉት የስርዓቱ ጽንሰ ሃሳቦች ‹‹መለሲዝም›› በተባለ የርዕዮተ አለም ስያሜ እንዲጠቃለሉ ተደርገዋል፡፡
የአቶ መለስ ህይወት ማለፉን ተከትሎ በተለያዩ የመንግስት እና የግል ተቋማት ውስጥ በተደረጉ የመታሰቢያ ፕሮግራሞች ላይ ‹‹መለስ መስቀል አደባባይ፣ መለስ ኤርፖርት፣ መለስ የህዳሴው ግድብ…›› የሚሉ ስያሜዎች በአዋጅ ይደነገጉ ዘንድ ሳግ እያደነቃቀፋቸው የጠየቁ ሰራተኞች በርካቶች ናቸው፡፡ …ሁሉም ነገር በመለስ ስም ይሰየም፡፡ አውራ የድርጅቱ አመራሮችም በየዲስኩሮቻቸው መሀል እንዲህ ይላሉ ‹‹የተዘጉ ደጆች በመለስ ስም ይከፈቱ፣ ተራራና ኮረብቶችም ዝቅ ይበሉ… መለሲዝም ነግሷልና›› አብዛኛው የመንግስት መስሪያ ቤቶች ከተቋቋሙበት የስራ ድርሻ ይልቅ ‹‹በመለስ ስም አብልጬ የሰየምኩ እኔ ነኝ›› የሚል ፉክክር ውስጥ የገቡ እስኪመስል ድረስ በየቀኑ አዳዲስ ስያሜዎችን በመገናኛ ብዙሃን እየሰማን ነው፡፡ በሰራዊቱ ውስጥ ተፈጥረው የነበሩክፍተቶች በ‹‹መለስ ራዕይ›› ስም እንዲደፈኑ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ ለዚህ ተግባር ኤታማዦር ሹሙ ጄነራል ሳሞራ የኑስ ዋነኛ የስራ ሂደት ባለቤት ሆነው ታይተዋል፡፡ ከሀይማኖት ተቋማት ላይ እየተሸራረፈ ያለው ‹‹የአምልኮ ነፃነት››ም በመለስ አምልኮ ላይ እንዲጨመር ተደርጓል፡፡ይህም ሆኖ ግን መለስን ‹‹የመለኮት ኃይል›› አልብሶ የማቅረቡ ጥረት በፈተናዎች የታጀበ ነው፡፡ ምናልባት በፈተናው ‹‹ተሰናካይ›› ቢኖር በሚል ቅድመ-ጥንቃቄም የግንባሩ ቀሳውስት ጥብቅ ትዕዛዛትን አውርደዋል፡፡ ከጥብቅ ትዕዛዛቱ አፈንግጦ የተገኘ ድርጅቱ በመሰረተው ምድራዊ ገሃነም ብርቱ ቅጣት ይጠብቀዋል፡፡ በእርግጥ የኢህአዴግ ታሪክ ‹‹የግለሰብ አምልኮ›› (ፐርሰናሊቲ ከልት ግንባታ) በሞት ቅጣት ይወራረድ እንደነበር ይነግረናል፡፡ ሆኖም ያ ዘመን ከተረሳ አመታት ተቆጥረዋል፡፡ ዘመኑን የሚተርኩ ድርሳናትም በሚዲያም ሆነ
በአደባባይ እንዳይገለጡ ባልተፃፈ ህግ ተከልክሏል፡፡ በልዋጩም በተለያዩ ዝግጅቶች ላይ የሚገኙ ተሳታፊዎች ‹‹የታላቁ መሪን ራዕይ›› እንደሚያስፈፅሙ ቃል ሲገቡ በቴሌቪዥን ይታያሉ፤ በሬዲዮ ይደመጣሉ፡፡
ሌላው ጉዳይ ‹‹መለስን›› ማምለክ ለጓዶቻቸው የስልጣን ዕድሜ ማራዘሚያ የሆነውን ያህል፤ ለኪነጥበብ ባለሙያዎች ‹‹እንጀራ›› መሆኑ ነው፡፡ ነዋይ ደበበና ፍቅረአዲስ ነቃጥበብ ‹‹የሙሴ በትር›› ሲሉ ከኦሪቱ ነብይ ጋር አነፃፅረዋቸዋል፡፡
አቶ በረከት ስምኦን በመጽሐፋቸው ላይ መለስ ‹‹ሰውዬው›› እያሉ ያሞካሿቸው እንደነበረ የገለፁበትን የፍቅር ማሳያ፤ጃሉድ የተባለ አርቲስት አቶ መለስን ምን ያህል ያፈቅራቸው እንደነበር ለማስረዳት ተጠቅሞበታል፡፡ አርቲስቱ ‹‹ሰውዬው!የምነግርህ አለኝ›› እያለ በሬጌ የሙዚቃ ስልት ሲያቀነቅንላቸው ተገርሜ ነበር ያደመጥኩት፡፡ ሠራዊት ፍቅሬ ‹‹ማስታወሻ›› በሚል ርዕስ ባዘጋጀው ትያትር ‹‹የብር ኖት ላይ የመለስ ምስል ይታተም›› ሲል ጠይቋል፡፡ ጌትነት እንየውም በዛ አስገምጋሚ ድምፁ ‹‹ራዕዩን ማስቀጠል አለብን›› የሚል ግጥም አቅርቧል፡፡ አቶ መለስና መንግስታቸው ዋነኛ የ‹‹ፖለቲካ ማሻሻጫ›› ላደረጉት ነባሩ የእርቅ ባህላችን መጠቀሚያ የሆኑት ፕሮፌሰር ኤፍሬም ይስሃቅ ሟቹን ጠቅላይ ሚንስትር ከግሪኩ እስክንድር እና ከሮማው ጁሊየስ ጋር አቻ ሲያደርጓቸው፣ ‹‹አይጋ ፎረም›› የተባለው አፍቃሪ ኢህአዴግ ድረ-ገፅ ደግሞ ከስታሊን እና ማኦ ጋር አመሳስሏቸዋል፡፡
በእርግጥም መለስን ‹‹መልከ ፃዴቅ›› ማድረግ እንደአቅጣጫ መያዙን የሚያመላክተው ፕሮፌሰር ኤፍሬም ከመለስ ባህሪ ጋር ፍፁም የሚቃረን ሰብዕናን አላብሰው ማየታችን ነው፡፡ ፕሮፈሰሩ እንዲህ ነበር ያሉት ‹‹አንድም ቀን ስለተቃዋሚዎች ክፉ ሲናገሩ ሰምቼ አላውቅም››፡፡
ፕ/ር ታረቀኝ አዴቦም እንዲሁ ‹‹በርዕዮተ ዓለም፣ በንድፈ ሀሳብና በራዕይ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስን የሚስተካከል የለም›› ሲሉ አድናቆታቸውን ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ አጋርተዋል፡፡ ተዋናዩ ደበሽ ተመስገን ደግሞ ‹‹በምድራችን ላይ
የመጨረሻ ትልቅ ሀዘን ደርሶብናል›› ሲል ነበር ሁኔታውን ያጎነው፡፡ በእርግጥ የኢህአዴግ አመራር ከመለስ ሞት በኋላ መለስን ‹‹ረቢ››፣ ራሱን ደግሞ የረቢው ‹‹ሐዋርያ›› አድርጎ በማቅረብ የስልጣን እድሜውን ማራዘም እና ውስጣዊ ችግሩን ማዳፈን ቁጥር አንድ የቤት ስራው ቢያደርገው የሚያስገርም አይሆንም፡፡ ምክንያቱም በመለስ ያስተዳደር ዘመን ድርጅቱ ጥርስ የሌለው አንበሳ ብቻ ሳይሆን በህይወት መኖሩንም የሚያረጋግጥ ነገር አልነበረውም፡፡ ለአርሶ አደሩ ምርታማነት፣ ለትምህርት ፖሊሲው ስኬታማነት፣ ለጤና ፖሊሲው አዋጭነት… መለስ ነበር የሚጠሩት፡፡ እናም ዛሬ ህይወታቸው ሲያልፍ ተተኪዎቻቸው መለስን አምላክ፣ ሀገሪቱን ቤተ-አምልኮ፣ ራሳቸውን ቀሳውስት፣ ህዝቡን አማኝ ከማድረግ ውጭ የቀረ አማራጭ አልነበራቸውም፡፡ ስለዚህም ይህንን ተልዕኮ ከግብ ለማድረስ ከምሁራን እስከ ሲራራ ነጋዴ፤ ከአርቲስቶች እስከ አትሌቶች በአደባባይ ምስክርነታቸውን እንዲሰጡ ማድረግ ነበረባቸው፡፡ አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ በሰጠው ቃለ-መጠይቅ ላይም እንዲህ ያለው ለዚህ ነው ‹‹የእርሳቸውን ‹ዋጋ› ማወቅ የጀመርነው አሁን ነው፡፡ በእጅ የያዙት ወርቅ ሆነብን እንጂ፡፡ እርግጠኛ ነኝ ወደፊት አቶ መለስን በጣም የምናደንቅና ክብር የምንሰጥበትን ስራዎች ገና እንገነዘባለን፡፡›› …ሀይሌ እንግዲህ ‹‹የመለስ ራዕይ›› ከተገለጠላቸው ‹‹ነብያቶች›› አንዱ መሆኑ ነው፡፡
በኢትዮጵያ የመሪዎች ታሪክ እንደ አቶ መለስ በውዳሴ የተንበሸበሸ ማንም የለ፡፡ በስማቸው በርካታ መፃሕፍት ወደ ገበያው ገብተዋል፡፡ ጥቂት በማይባሉ ከመብረቅ በፈጠኑ አርቲስቶችም ተዘፍኖላቸዋል፡፡ ስለ‹‹ምሉዕ በኩሉሄ›› መሪነታቸው ብዙ ተነግሯል ፡፡ የቀድሞ የኦነግ መሪ አባቢያ አባጆቢር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለፖለቲካ እስረኞች ምህረት እንደሚሰጡ የገለፁበት መንገድ ደግሞ በእጅጉ አስገርሞኛል፡፡ ‹‹ማረሚያ ቤቱን ባዶ አደርግላችኋለሁ ብለውን ነበር›› ነው ያሉት-በራሱ በመለስ መንግስት ላይ ጠመንጃ አንስተው የነበሩት አባቢያ አባጆቢር፡፡ ረዳት ፕሮፈሰር መድህኔ ታደሰ ለመለስ ያላቸውን አድናቆት የተናገሩት ‹‹He is also unusually gifted thinker›› (ያልተለመደ ተሰጥኦ ያለው አሰላሳይ ነው) በማለት ሲሆን፤ በዚህ ሁሉ ጨጨታ መሀል የተለየ አስተያየት የሰጡት ፕሮፌሰር ዱላ አባዲ የተባሉ ምህር በመለስ አንባቢነት ላይ መስማማታቸውን ተናግረው ሟቹን
አምባገነን ‹‹Evil genius›› (የተረገመው ምሁር) ሲሉ ነበር የገለጿቸው የተረሱት አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትርበባህሪያቸው ‹‹ዝምተኛ›› እና ‹‹ጭምት›› እንደሆኑ የተነገረላቸው አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ቃለ-መሀላ ፈፅመው ስልጣን ቢይዙም በየደረሱበት ሁሉ ራሳቸውን የሚገልጡት እንደ ጠቅላይ ሚኒስትር ሳይሆን እንደ ቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር ታማኝ ደቀመዝሙር አድርገው ነው፡፡ ለሀይማኖት ያላቸው ቅርበትም ይህንን
ተልዕኮ ለመሸከም ሳይረዳቸው አልቀረም፡፡‹‹የመለስ አምልኮ›› ፖለቲካ ዋነኛው ሰለባ አዲሱ ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ መሆናቸው አከራካሪ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ዛሬ በሀገሪቱ ላይ ያለው የአመራር ጥበብና ችሎታ የእርሳቸው ሳይሆን ‹‹የመለስ ራዕይ›› ነው ተብሏልና፡፡ ይህ ደግሞ የሚያስከትለው የራሱ የሆነ አደጋ አለው፡፡ ከአደጋው ዋነኛው ኃይለማርያም በኢህአዴግ አባላትም ሆነ በመላው ኢትዮጵያውያን ዘንድ እንደመሪ ተቀባይነት እንዳይኖራቸው ተፅእኖ መፍጠሩ ነው፡፡ አደጋውን የከፋ ያደረገው ግን ይህ አይነቱ አካሄድ ሰውየውን በተቀናቃኝም ሆነ በወዳጅ ሀገራት ዘንድ የሚያሳጣ መሆን መቻሉ ነው፡፡
ለዚህም ይመስለኛል ሰሞኑን አንድ የግብፅ ጦር ሰራዊት ጄነራል ‹‹ችግራችን መለስ ብቻ ነበር›› ሲሉ የተደመጡት፡፡ ይህ ሁኔታ የሀገርን ክብር ከማሳነሱም በተጨማሪ ውሎ አድሮ ለብሄራዊ ደህንነት ስጋት መሆኑ አይቀርም፡፡
የሆነ ሆኖ አዲሱ ጠቅላይ ሚንስትር ምን ያህል እንደተረሱ በግልፅ የምንረዳው ዛሬም መለስ በቴሌቪዥን መስኮት እየተመላለሱ ለችግሮች መፍትሄ እየሰጡ እንደሆነ ተደርገው መቅረባቸውን ስንመለከት ነው፡፡ ሰውየው በህይወት ሳሉ
በተለያዩ የሀገሪቱ ጉዳዮች ላይ የሰጧቸው አስተያየቶች ለወቅታዊዎቹ ችግሮች እንደመፍትሄ መቅረባቸው የሚያመላክተው የኃይለማርያምን መረሳት ብቻ አይደለም፤ ለኃይለማርያም ችሎታ እውቅና መንፈግንም ብቻ አይደለም፤ ይልቁንም ይህ አይነቱ አካሄድ ኃይለማርያም እንደ መሪ እንዳይታዩ ለሚያደርጉት ከጀርባቸው ላሉ ሰዎች ምናልባትም አንድ ቀን ኃይለማርያምን ከስልጣናቸው ማንሳት ቢፈልጉ ‹‹ብቃት ማነስ›› በሚል ተለጣፊ ሰበብ የስልጣን ጠለፋውን ለማቅለል ምቹ መንገድ መፍጠሩም ነው፡፡ እንዲህ አይነት ያልተለመዱ ማኪያቬሊያዊ አሰራሮች ናቸው በኢህአዴግ የአመራር አባላት መካከል ልዩነት ለመኖሩ የሚጠቁሙት፡፡ …ለሃያ አንድ ዓመታት መመለካቸው ሳያንስ ህይወታቸው ካለፈ በኋላ ከበድናቸው ጋር ሀገር ፍቅር እንድትወድቅ ስለተገደድንባቸው ሰው ከዚህ በላይ ማለት ቢገባም እዚህ ላይ ማቆም ሳይሻል አይቀርም፡፡
(እናም መለስ እየተመለኩ ያሉት በምን አይነት መልኩ እንደሆነ የዚህን ያህል ካየን በሌላ ዕትም ደግሞ ‹‹የመለስአምልኮ›› ኢህአዴግ አምባገነንነቱን ይዞ ለመቀጠል ምን ያህል ይጠቅመዋል? ለፓርቲው የሚሰጣቸው ትርፎች /
ከውስጠ-ፓርቲም ሆነ ከውጭ/) ምንድን ናቸው? በዚህ አምልኮ ስር እየተከናወኑ ያሉ ሀገራዊ አደጋዎችን የሚያፋጥኑ የመለስ ውርሶች የትኞቹ ናቸው? በኃይለማርያም ስልጣን ላይ ምን አይነት ተፅእኖ ይፈጥራል? የተለያዩ የህብረተሰብክፍሎች በዚህ አምልኮ ስር መጠመዳቸውን የፓርቲው መሪዎች ለረዥም ግዜ በስልጣን ላይ ለመቆየት እንዴት ሊያውሉት ይችላሉ? የሚሉትን ጥያቄዎች አንስቼ ለመፈተሽ እሞክራለሁ)

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 12 years ago on November 21, 2012
  • By:
  • Last Modified: November 21, 2012 @ 5:44 pm
  • Filed Under: Ethiopia
  • Tagged With:

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar