www.maledatimes.com ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች በአረብ ሀገር መንግስት ያመቻቸው የሞት መንገድ ዳዊት ሰለሞን - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች በአረብ ሀገር መንግስት ያመቻቸው የሞት መንገድ ዳዊት ሰለሞን

By   /   November 29, 2012  /   Comments Off on ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች በአረብ ሀገር መንግስት ያመቻቸው የሞት መንገድ ዳዊት ሰለሞን

    Print       Email
0 0
Read Time:28 Minute, 16 Second

ፍትህ ለኢትዮጵያ የሚባል ብሎግ ላይ ነው ያገኘሁት ታሪኩ እኔ ከተከታታይ ከማቀርባቸው ጽሁፎች ጋር የተዛመደ ስለሆን ፀሀፊው ዳዊት ሰለሞንን አመስግኜ ሳልጨምር ሳልቀንስ አቅርቤዋለሁ አንብቡት፡፡ ጽሁፉ የእኔ ስላልሆነ ነው ስሜን ያላሳፈርኩት አመሰግናልሁ፡፡
“መዲና መሐመድ ትባላለች በ15 ዓመቷ ወደ ዱባይ ለስራ ሄዳ አሰሪዋ እግሯ ላይ አሲድ ደፍታባት ከፎቅ ላይ ወርውራ ጥላታለች፡፡ አሁን ዱባይ ሆስፒታል ህክምና ላይ ናት፤ ህክምና በአስቸኳይ ያስፈልጋታል፤ የኢትዮጵያውያንን እርዳታ እየጠየቀች ነው፤ የምትችሉ በዚህ ስልክ 00971557255198

እየደወላችሁ እርዷት፡፡” ይህ ተማፅኖ በቅርቡ በማህበራዊ ድረገፆች በሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን የተሰራጨ ነበር፡፡ መዲና መሐመድ አሁን በምን አይነት ሁኔታ ውስጥ እንዳለች ባይታወቅም እንደርሷ ከ18 አመት በታች ሆነው ወደ አረብ ሀገራት የሚጓዙ ህፃናት ሴቶች በየቀኑ ኢትዮጵያን ለቀው ይወጣሉ፡፡ ህፃናት ሴቶቹ ለስራ ሀገር ለቀው ሲሰደዱ የድርሻውን ገንዘብ የሚያስከፍለው የኢህአዴግ መንግስትን
በአፍላ እድሜያቸው ራሳቸውን ለአደጋ አጋልጠው ወደ አረብ ሀገራት የሚጎርፉት ሴት ህፃናት ጉዳይ ያሳሰበው አይመስልም፡፡
ባለፈው አመት የካቲት ወር መላውን አለም ያስደነገጠ ዘግናኝ ዜና ከወደ ሊባኖስ ተደምጦ ነበር፡፡ አለም ደቻሳ የተባለች ኢትዮጵያዊት የነገ ህይወቷን ለማሳመር በማሰብ እንደ ብዙዎቹ የአገሯ ልጆች የአረቡን አለም ተቀላቅላለች፡፡ ሊባኖሳዊው የአለም ደቻሳ ቀጣሪ ግን ያደረሰባት ግፍ ሳያንስ ከለላ ለማግኘት ከሄደችበት የኢትዮጵያ ኤምባሲ በራፍ ላይ በመኪናው እየጎተተ ኢ-ሰብአዊ ድርጊት ፈጽሞባልታ፡፡ ጥቃቱ የተፈፀመባት ምስኪኗ አለም የሚደርስላት ወገንና ጥብቅና የሚቆምላት መንግስት አጥታ ተስፋ ቆረጠች፤ እናም ህክምና በምትከታተልበት ሆስፒታል በተነጠፈላት አንሶላ ራሷን አንቃ
አስከፊውን ህይወቷን በአስከፊ ሁኔታ ለቀሪው አለም ዜናው የሚሰቀጥጥ ይሁን እንጂ በአረቡ ሀገራት ለስራ ፍለጋ የሚያመሩ እህቶቻችን የሚደርስባቸው መራር ጥቃት ለኛ ለአበሾቹ አዲስና እንግዳ ነገር አይደለም፡፡ አስገራሚው ነገር እህቶቻችን ሞት አለበት የተባለውን መካከለኛው ምስራቅ ለመቀላቀል የሚያደርጉት ጉዞ ከፊት ይልቅ በየዕለቱ እየጨመረ መምጣቱ ነው፡፡
ምናልባትም ለኢትዮጵያዊያኑ በአረብ ሀገራት ያለው ሰቆቃ ማባሪያ ስለማጣቱ በዚህ ገጽ ልብ ሰባሪን ታሪኮችን ማስፈር ተገቢ ነው፡፡ ረሂማ ሐሰን ትባላለች፤ ዕድሜዋ 19 የትውልድ ስፍራዋ ደግሞ ሰሜን ወሎ ነው፡፡ ለብዙ ጊዜያት እንዴት ወደ አገሯ ለመመለስ እንደበቃች የምታውቀውና የምትመልሰው ነገር አልነበራትም፡፡ አጋር የተባለ አገር በቀል የበጎ አድራጎት ድርጅት ከኤርፖርት አስተዳደር ጋር በፈጠረው የስራ ግንኙነት ተረክቧት ህክምና እንድታገኝ ከረዳት በኋላ በዙሪያዋ ምን የተፈጠረ እንደሆነ በመጠኑ መለየት ጀምራለች ፡፡ ረሂማ ለስራ ካቀናችባት ባህሬን እንዴት ወደ አዲስ አበባ እንደተመለሰች አሁን የቤተሰብ ያህል እየተንከባከቧት የሚገኙትን የአጋር በጎ አድራጎት ድርጅት ሠራተኞች ተገቢውን እንክብካቤ ማድረጋቸው አሁን ለሚታይባት ለውጥ ትልቁን አስተዋፅኦ አበርክቷል፡፡
ከድርጅቱ የተሰበሰቡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት የረሂማ ዘግናኙ የህይወት ታሪክ የሚጀምረው ከተወለደችበት ቀዬ ነው፡፡ ወላጅ አባቷን በህፃንነቷ በሞት በማጣቷ ከእናቷ ጋር የሦስት ታናናሽ ወንድሞቿን ህይወት የማቆየት ፈተና ወደቀባት፡፡ ዕድሜዋ ለትምህርት ቢደርስም እናት የማጀቱን ስራ እንድትጋራቸው በማሰብ ወደ ትምህርት ቤት ሊሰዷት አልፈቀዱም፡፡ ወንድሞቿ ያገኙትን የቀለም እድል በቤተሰቧ ላይ ያጠላው ድህነት ከእናቷ አለመማር ጋር ተደማምሮ የቀለም ለዛ ነፈጋት፡፡ ረሂማ ተፈጥሮ የደቀነችባት የመጀመሪያው መሰናክል ሴት ሆና መፈጠሯ እንደሆነ ታስባለች፡፡ ይህንን
ደግሞ ማምለጥ አልቻለችምና ተሸነፈች፡፡ ሁለተኛው ፈተናም ይህንኑ ሴትነቷን በመከተል የተደቀነ ነበር፡፡ የ12 ዓመት እንቦቃቅላ ህፃን ሳለች በመኖሪያ ጎጆዋ ከተለመደው ወጣ ያለ ግርግር መለየት ጀመረ፡፡ የመንደሩ ሽማግሌዎች በዚያች ደሳሳ ጎጆ መለስ ቀለስ ማለት አበዙ፡፡ እናትም አባትም አድርጋ የምትመለከታቸውን ወላጅ እናቷን ስትፈራ ስትቸር ምን የተከናወነ እንደሆነ ጠየቀቻቸው “ነገ ሰርግሽ ነው” አሏት፡፡ የሰማቸውን ለማመን ብትቸገርም አማራጭ ስለሌላት አስከፊውን የህይወት ምዕራፍ ከመጀመር ያለፈ አማራጭ አልነበራትም፡፡
የልጅነት ወግ ያላየችው ረሂማ ለሌላ መከራ እናቷ አሳልፈው እንደሰጧት ተረዳች፡፡ ባለቤቷ ከእርሷ በዕድሜ ሦስት እጥፍ የሚበልጥ ጎልማሳ ነው፡፡ በማጀትና በምግብ እጦት የተደቆሰው እንጭጭ ሰውነቷ ቀንበር በመጎተትና በሬ በመጥመድ የደረጃውን የባለቤቷን ሰውነት መቋቋም አልተቻለውም፡
፡ የምትመራው ህይወት ከሲኦል ወደ ገሃነም እሳት ተሸጋገረ፡፡ በተለይ አዳሯን አምርራ ተጠየፈችው፡፡ ከሦስት የስቃይ አመታት በኋላ የተጎራበተቻት አንዲት የአገሯ ልጅ ወደ አረብ አገር ለመሄድ ወደ አዲስ አበባ ለማምራት መዘጋጀቷን ሹክ አለቻት፡፡ ከገሃነም እሳቱ ማምለጫ መንገድ አጥታ የቆየችው ረሂማ በሰማችው አዲስ ነገር ሁለቱ ጆሮዎቿ እንደ ቀስት ተገተሩ፡፡ ስለ አዲስ አበባ በአለፍ ገደም ከመስማት ውጪ በከተማይቱ የምታውቀው ዘመድ
የሌላት ረሂማ ከእናቷ ተማክራ ጥቂት ጥሪት ተቋጥሮላት ለባለቤቷ የጉዞዋን ታሪክ ሳትነግረው ከመንደሯ ልጅ ጋር አዲስ አበባ ገባች፡፡
ምንም እንኳን ዕድሜዋ 15 አመት ቢሆንም ለእርሷ ግልጽ ባልሆነላት መንገድ ዕድሜዋ 18 ዓመት እንደሞላ ተደርጎ በጎረቤቷ በኩል በተዋወቀችው ደላላ አማካኝነት ፓስፖርት ለማውጣት በቃች፡፡ ወደ አረብ አገር ከሚወስዳት ኤጀንሲ ጋር ያገናኛት ይኸው ደላላ በአዲስ አበባ መጠጊያ ዘመድ እንደሌላት በመረዳቱ ጉዞዋን እንደሚያፋጥንላት ቃል በመግባትና በተለያየ መንገድ በመደለል የወሲብ አምሮቱን ሲወጣባት ከረመ፡፡ የደላላው መጫወቻ የነበረችበት ጊዜ ተገባዶ ወደ ባህሬን አቀናች፡፡ በባህሬን አየር መንገድ ኢትዮጵያዊያን ከተቀበሏት በኋላ ቀጣሪዋ እስኪወስዷት ድረስ ፆሟን ኤጀንሲ ቢሮ ውስጥ ለሦስት ቀናት ለማደር ተገደደች ፡ ፡ ከሦሰት ቀናት በኋላ የመጣው የረሂማ ቀጣሪ ገና እንደተመለከታት እንዳልወደዳት ባሳያት ብትረዳም አብራው ከመሄድ ውጪ አማራጭ አልነበራትም፡፡
ከኢትዮጵያ ሳትወጣ የተነገራት ልጅ የሌላቸው ባለትዳሮች ቤት እንደምትገባ ቢሆንም የመጀመሪያውን ቀን ያሳለፈችው ስድስት የቤተሰብ አባላት ባሉበት ቤት ውስጥ ነበር፡፡ ቀጣሪዋ በእጇ የሚገኘውን ፓስፖርት በመረከብ በአንድ ሳጥን ውስጥ ሲቆልፍባት ተመልክታለች፡፡ የቀጣሪዋ አባት፣ ወንድምና እህት በየተራ እየተቀባበሉ እየወሰዷት የመኖሪያ ቪላቸውን እንድታፀዳ፣ ምግብ እንድታበስልና ልብሶቻቸውን እያጠበች እንድትተኩስ ያደርጓት ጀመር፡፡ እነዚህ ስራዎች ለእርሷ እንግዳ በመሆናቸው የተነሳ የምትፈጽማቸው ስህተቶች ድብደባ፣ ስድብ፣ የደሞዝ ቅጣት እንዲደርስባት
ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡ በአንድ ማለዳ ያጋጠማት ለየት ያለ ነገር ግን በአዲስ አበባ ለመገኘቷ ምክንያት ሆኗል፡፡ ከመጀመሪያው ዕለት አንስቶ የተፈታፊት ሊያሳያት ያልፈቀደው ቀጣሪዋ ለጊዜው ትዝ በማይላት ጥፋት የተነሳ ሦስተኛ ፎቅ ላይ ከሚገኘው መኖሪያ ቤቱ ወደ ውጪ ገፍትሮ ይጥላታል፡፡በአደጋውም ጥርሷ እረግፏል፤ እጆቿ እና አንድ እግሯ ተሰብረዋል፡፡ ከሁሉም በላይ ህሊናዋን ለበርካታ ቀናት ስታ ቆይታለች፡፡ ወደ አገሯ የተሸኘችውም በዚህ ሁኔታ ውስጥ እንዳለች ነው፡፡ አሁን ረሂማ በህክምና ጥበብ የተሰሩ ጥርሶች ተገጥመውላታል፡፡ የተሰበሩት እጆቿ እና እግሯ መንቀሳቀስ ጀምረዋል፡፡ የወላጅ እናቷንና የትውልድ መንደሯን ስም ደጋግማ ታነሳለች፡፡ ነገር ግን በፍፁም ወደ ሰሜን ወሎ የመመለስ ፍላጎት የላትም፡፡
ይህ አይነቱ ታሪክ የረሂማ ብቻ አይደለም፤ ሆኖም አዳዲሶቹ የአረብ አገራት ተጓዥ ኢትዮጵያውያን እንዲህ አይነት አጋጣሚዎች ሊያጋጥሟቸው እንደሚችል ቢያውቁም የሞቱን መንገድ ወደ ጎን ለመተው አልፈቀዱም፡፡ እናም ባገኙት አማራጭ ሁሉ ወደ አረብ ሀገራት ይተማሉ፡፡ የኢትዮጵያ ኢሚግሬሽን መሥሪያ ቤት በሦስት ቀናት ዕድሜ ፓስፖርት ለሚጠይቀኝ አቀርባለሁ በማለት እንዳልፎከረ በአሁኑ ሰዓት ጠያቂዎቹን ከሦስት ወራት በላይ መቅጠር ግድ ብሎታል፡፡ የዚህ መንስኤው ደግሞ የአረብ አገራት ተጓዦች ቁጥር አስደንጋጭ በሆነ መልኩ በብዙ እጥፍ መጨመሩ ስለመሆኑ ብዙዎች ይስማማሉ፡፡
ዘመናዊ የኮንትራንት ባርነት
ኢትዮጵያውያን እንደ አገር የምንኮራበት በቅኝ ያለመገዛት ታሪካችን በዘመናዊ የኮንትራት ባርነት ከተደረፈ ረዘም ያሉ አመታት ተቆጥረዋል፡፡ ባለፉት አስርት አመታት በመካከለኛው ምስራቅ የተገኘው የነዳጅ ዘይት ሀብት አገራቱን በኢኮኖሚ እንዲመነደጉ አብቅቷቸዋል፡፡ በአረብ አገራት የሚገኙ ዜጎች ከነዳጅ ሀብቱ ተካፋይ መሆናቸውም ዝቅተኛ ተብለው በሚወሰዱ ስራዎች ላይ ለመሰማራት ያላቸውን ተነሳሽነት ገድሎታል፡፡ የስራ ዕድል በስፋት ባልተፈጠረባቸው እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ደሃ አገራት የሚኖሩ ሴቶች በአረቦቹ የተናቁ ስራዎችን ለመስራት አጋጣሚውን እንደ መልካም ዕድል በመቁጠር መትመም ጀመሩ፡፡ የተለያዩ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ከሆነም በአረብ ሀገራት ከ200,000(ከሁለት መቶ ሺህ) በላይ ኢትዮጵያዊያን ሴቶች ይገኛሉ፡፡
ከነዚህ ውስጥ ከ95% በላይ የሚሆኑት የተሰማሩ በቤት ሠራተኝነት ነው፡፡ምንም እንኳን ኢትዮጵያዊያኑ የቤት ሰራተኞች በዋናነት ወደ ኩዌት፣ ጆርዳን፣ ሳውዲ አረቢያና ሊባኖስ የሚያቀኑት በህጋዊ መንገድ ቢሆንም በቀጣሪዎቻቸው መብቱ ሊከበርለት እንደሚገባ ሠራተኛ ሳይሆን እንደ ባሪያ መታየታቸው አልቀረም፡፡ ገና የቀጣሪዎቻቸውን ቤት እንደረገጡ ፓስፖርታቸው ይወሰዳል፣ ከወሰዳቸው ኤጀንሲ ወይም ከቤተሰቦቻቸው እንዳይገናኙ ስልኮች ይቆለፉባቸዋል፡፡ ቴሌቪዥኖችን መመልከት እንደማይችሉ ይነገራቸዋል፡፡ ደሞዛቸውን በየወሩ አያገኙም፡፡ የረሂማን ገጠመኝ ማንሳት ለዚህ ማሳያ ይሆናል፡፡ ረሂማ በሀዘንና በቁጭት ተሞልታ “ለአንድ አመት ያህል የሰራሁበትን ደሞዝ አልሰጡኝም” በማለት የደረሰባትን በደል ትተርካለች፡፡ መንግስት ለወጉ ያክል የኮንትራት ውል እንዲሞላ የሚያደርግበት አሰራር ቢኖረውም፣ በተለይ በቀጣሪዎቹ ዘንድ ኮንትራቱ ለመከበሩ የሚከታተልበት መንገድና አቅም የለውም፡፡ ለዚህም በዋንኛው ምክንያት በሚበዙት የአረብ አገራት የኢትዮጵያ መንግስት ኤምባሲዎችን አለመክፈቱ እንደሆነ ታዛቢዎች ያስረዳሉ፡፡ በቆንሲላ ደረጃ የተከፈቱ ቢሮዎችም ለሚፈጠሩ ችግሮች ያላቸው ተደራሽነት ከቁጥር የሚገባ አይደለም፡፡
ወገኛው ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ
በአረቡ አለም በሴት እህቶቻችን ላይ የሚደርሰውን ሰቆቃ ለመቀነስ ይረዳል በማለት ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር የተለያዩ መመሪያዎችን
በማውጣት በኤጀንሲዎች ላይ ከፍተኛ ቁጥጥር ለማድረግ ሞክሯል፡፡ የኤጀንሲ ፈቃድ በመውሰድ ሴቶቹን ወደ አረብ አገራት የሚወሰዱት ደላሎች እውቅና ማግኘት እንደሚገባቸው መመሪያው ከመጥቀሱም ባሻገር ሴቶቹ ኢትዮጵያን ከመልቀቃቸው አስቀድሞ ካዛንቺስ አካባቢ በሚገኘውየሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ቅጥር ግቢ በመገኘት ጠቃሚ ያላቸውን ትምህርት እንዲወስዱ ያስገድዳል፡፡
መስሪያ ቤቱ ትምህርቱን ለአንድ ሳምንት፣ ለአራት ቀን በመጨረሻም ለሦስት ቀናት ሲሰጥ ከቆየ በኋላ በአሁኑ ሰዓት የትምህርቱን ጊዜ በአንድ ቀን ብቻ
እንዲወሰን አድርጓል፡፡ “በአረብ አገር ጉዟቸው ከሚያጋጥማቸው አዲስ ነገር ጋር በፍጥነት እንዲላመዱ ይረዳል” የተባለው ትምህርት በራሱ ብዙ ችግሮችን ያዘለ መሆኑ አስገራሚ ያደርገዋል፡፡ብዙዎችም ትምህርቱ በዘመቻና በስሜት የተጀመረ እንጂ በቂ ጥናት ያልተደረገበት ስለመሆኑ ይናገራሉ፡፡ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሴቶች በአንድ ጠበብ ያለ አዳራሽ ውስጥ እንዲታጨቁ ተደርገዋል፡፡ በሰው ብዛት የተጨናነቀው አዳራሽ በቂ አየር ማስገባት የሚችል ባለመሆኑ በታመቀ አየር ተሞልቷል፡፡ አዲስ ሰው ወደ ውስጥ ሲገባ በቤቱ የታመቀው መጥፎ ጠረን አቀባበል ያደርግለታል፡፡ ሙቀቱና ምቾት የማይሰጠው አጠቃላይ ሁኔታ ሴቶቹ የሚሰጠውን ትምህርት እንዲከታተሉ የሚያስችል አይደለም፡፡ አስተማሪዎቹ ወደ አረብ አገር የሚጓዙ ሴቶች ሊጠቀሟቸው የሚገቡ የንፅህና መጠባበቂያ ቁሳቁሶችንና ሞዴስ እንዴት መጠቀም እንደሚገባቸው ያስተምራሉ፡፡ ነገር ግን እነዚህን ቁሳቁሶች ሠራተኛና
ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ባለማዘጋጀቱ አሰልጣኖቹ ከመንገደኞቹ የጥርስ ቡርሾችንና ሳሙናዎችን፣ ሞዴሶችንና ዲዩድራንቶችን “እባካችሁ አንድ ጊዜ
ስጡን” በማለት ይለምናሉ፡፡ የትምህርቱ የመጨረሻ ማሳረጊያ በአረብ አገር እንግልት የደረሰባቸውን፣ በአሳሪዎቻቸው በመደፈርና ከፎቆች ላይ ተወርውረው ጉዳት የደረሰባቸውን እንስቶችን ታሪክ የሚያሳይ ነው ዶክመንተሪ ፊልም ነው፡፡
ከገጠሪቱ የአገራችን ክፍሎች የመጡት አብዛኞቹ በአዳራሹ ውስጥ የተገኙት ሰልጣኞች በዚህ ወቅት በመሪር ለቅሶ ይሞላሉ፡፡ ነገር ግን ፊልሙን መመልከታቸው ከጉዟቸው የማስቀረት ጉልበት ያለው አይመስልም፡፡ በዕለቱ ያነጋገርናቸው በዛ ያሉ ሴቶች ጉዟቸው አይቀሬ ስለመሆኑ ነግረውናል፡፡የሚበዙት ሴቶች ዘመናዊ የመፀዳጃ ቤቶችን አጠቃቀም አያውቁም፣ አልጋ እንዴት መነጠፍ እንዳለበትም ምንም አይነት ልምድ የላቸውም፤ ልብስ ተኩሰውም አያውቁም፡፡ እንዲህ አይነት ሴቶች ከአገር ወጥተው ቋንቋውን ከማያውቁት ቀጣሪ ጋር እንዴት ሊግባቡ እንደሚችሉ ማሰብ በራሱ አዕምሮን ይፈትናል፡፡ ወገኛው ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ግን “እያስተማርኩ ነው” ይለናል
Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 12 years ago on November 29, 2012
  • By:
  • Last Modified: November 29, 2012 @ 3:01 am
  • Filed Under: Ethiopia
  • Tagged With:

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar