www.maledatimes.com በሃይማኖት ካባ ሥር – ጸያፍ ፖለቲካ! በሰሎሞን ተሰማ ጂ. - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

በሃይማኖት ካባ ሥር – ጸያፍ ፖለቲካ! በሰሎሞን ተሰማ ጂ.

By   /   December 8, 2012  /   Comments Off on በሃይማኖት ካባ ሥር – ጸያፍ ፖለቲካ! በሰሎሞን ተሰማ ጂ.

    Print       Email
0 0
Read Time:39 Minute, 0 Second

                        (semnaworeq)

ባለቅኔው ክፍለ ዮሃንስ ከዘመናት በፊት፣ “ወከመ ለሰማይ ኢንርአይ ሥነ ግዘፉ፤  ትንንያ ካልአን በክንፉ!” እንዳለው ነው፡፡ እውነትነት አለው፡፡ ስለ”እውነትም” ነው የተቀኘው፡፡ (ትርጓሜውም እንዲህ ነው፤ እውነትን እንኳንና ከምድር በላይ ሊያስርዋት፣ ከምድር ከርስም ውስጥ ቢቀብሯት፣ በድንጋይ መዝጊያ ተዘግቶባት፣ በጠንካራ የብረት መዝጊያም ጭምር እንደገንዘብ ቢከዝኗትና በትጉኋን ዘበኞችም ቢያስጠብቋት፣ “እውነት” መቼውንም የሚሰማ ድምጽ አላት፡፡ ከትልቁ የተራራ ሕንፃና ዋሻ ውስጥ ቢያሽጉባትም ሆነ፣ ከጥልቁ ውቅያኖስ ውስጥ ቢቀብሯት፣ በድንጋይ መዝጊያም ቢከረችሟት፣ ከድቅድቁ ዋሻ ውስጥም አዕላፍ ሀሰተኞች ቀርበው ሊይዟት ስለማይችሉ፣ በሦስተኛው ቀንም ተነስታ ሁሉንም ከንቱ አድርጋ እስከዛሬዋ ቀን ድረስ በእውነትነቷ እየፎከረችና እየሸለለች፣ “አዋቂዎች ነን!” ባዮችን፣ “ዋሾዎች ሆይ!” እያለች ስታሳፍራቸው ትኖራለች፡፡ ልክ በማቴዎስ ወንጌል 27፣ 57-66 እና በ1ኛ ቆሮ 1፣ 18-22 እንደተመሰከረው ነው፡፡)

የመንፈሳዊ ሥልጣንም ሆነ የፖለቲካ ሥልጣኑ ያላቸውን ሰዎች እንዴት የትንኝ ክንፍ የምታክል ሀሰት፣ ተራራ የሚያክለውን እውነት ልትከልላቸው/ልትጋርድባቸው እንደምትችል ለማወቅ ብንጥርም መረዳት አልቻልንም፡፡ በተለይም ብፁዐን አባቶቻችን እንዴት የቤተ-ክርስቲያንን ቀኖና ሊጥሱት እንደደፈሩ ለማመንም ተቸግረናል፡፡ ምናልባትም፣ በሃይማኖት ካባ ሥር – ጸያፍ ፖለቲካን የሚያቀነቅኑ “አማካሪ” ተብዬዎች ገፋፍተዋቸው ይሆናል የሚል ቀና ጥርጣሬ ያድርብናል እንጂ፣ በፍፁም ብፁዐን አባቶቻችንን፣ እኛ ከትንኟም ክንፍ የምናንሰው ምዕመናን ከመውቀስ ተቆጥበን ቆይተናል፡፡ መቼም፣ ውኃና ተግጻጽ ቁልቁል ሲተም እንጂ፣ ሽቅብ ሲጋልብ አላየንምና፣ ሃሳባችንንም በኢትዮጵያዊ ይሉኝታና ትሕትና አፍነን ይዘነው ቆይተን ነበር፡፡ ሆኖም፣ በኅዳር 30/2005á‹“.ም ይደረጋል የተባለውን የፓትረያርክ ምርጫ ዝግጅት ስንሰማ፣ ድምፃችንን ልናሰማ ወደድን፡፡ ሃሳባችንንም፣ የትንኝ ክንፍ የምታክል ሕጸጽ እንዳትጋርድብን፣ አምላካችን ቅዱስ እግዚአብሔርም ይረዳን ዘንድ፣ እውነቱንና እውነቱንም ብቻ እንዲያናግረን ከመንበሩ ሥር ተደፍተን እንማፀነዋለን፡፡… ለዘላለሙ አሜን!!!

የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ በ1968ዓ.ም፣  የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሪዎስ በ1984ዓ.ም ከፓትረያርክነታቸው የተሰናበቱበትና የብፁዕ ዳግማዊ አቡነ ዮሳብ ከግብፅ ቤተ-ክርስቲያን መንበራቸው በ1947ዓ.ም የተሰናበቱበት ሁናቴ በብዙ መልኩ ተመሳሳይ ነው፡፡ ሦስቱም ፓትረያርኮች፣ በኢትዮጵያና በግብፅ የነበሩትን መንግሥታት በኃይል ተገርስሰው፣ ከነርሱ ለጥቀው የመጡት የደርግና የኢሕአዴግ-በኢትዮጵያ በኮሎኔል ጋማል አብደል ናስር ይመራ የነበረው ወታደራዊ ቡድንን በግብፅ ጡጫ አቅምሷቸዋል፡፡ ሁለቱ ፓትረያርኮች መንበራቸውን ለቀው ወደገዳም ሕይወታቸው ገብተው ነበር፡፡ ብፁዕ አቡነ መርቆሪዎስ፣ በጥር 1984 ዓ.ም ማለቂያ ላይ ነው ሲሰናበቱ ወደምስካዬ ህዙናን ገዳም ላጭር ጊዜ ገብተው ነበር፡፡  በተመሳሳይ ሁኔታም፣ ብፁዕ ዳግማዊ አቡነ ዮሳብም ከካይሮ ወጣ ብላ ወደምትገኘው ቁስቋም ገዳም ገብተው ለአንድ ዓመት ያህል ቆይተዋል፡፡ በአንጻሩ፣ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስን ወታደራዊው ደርግ ገዳም እንዲገቡ ሳይፈልግ ቀርቶ፣ ለእስርና ለግፍ ግድያ ተዳረጉ፡፡

በሕገ ወጥ ሁናቴም በሰኔ 30/1968ዓ.ም አባ መላኩ የተባሉትን የገዳም መነኩሴ ከሁለት ጳጳሳትና ከሁለት መነኮሳት ጋር አወዳድሮ ሾማቸው፡፡ እኚህ አባትም ብፁዕ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ከተባሉም በኋላ፣ እንደምንኩስናቸው ዘመን በባዶ እግራቸው ነበር የሚሄዱት፡፡ ደርግ በሃይማኖት ካባ ሥር በሠራው ጸያፍ ፖለቲካም፣ ሁለተኛው ፓትረያርክ ከዚህ አለም በሞት እስኪለዩም አላስችል ብሎት፣ የቤተ-ክርስቲያኗን የፓትረያርክ ምርጫ ደንብ እንደሚፈልገው አሻሽሎ፣ ለምዕመናኑ “ይኼውላችሁ የመረጥኩላችሁ ፓትረያርክ!” አለ፡፡ ከፍ ብሎ የተሰማ የተቃውሞ ድምጽ ስለመኖሩ መዛግብት አያሳዩም፡፡ በመሆኑም፣ የደርግ ፀረ-ቀኖናና ፀረ-ሕገ ቤተክርስቲያን አጀንዳ ተተገበረ፡፡ በሐምሌ 7/1971ዓ.ምህረትም አቡነ ቴዎፍሎስን አንቆ ገድሎ የአቡነ ተክለ ሃይማኖትን ሹመት እንዳያከራክር አድርጎ ከረቸመው፡፡

1948/9 ዓ.ም፣ የኢትዮጵያ ቤተ-ክርስቲያን ተወካዮች 115ኛው ፓትረያርክ አቡነ ዮሳብ ወደመንበራቸው እንደሚመለሱ ክፍተኛ ጥረት አድርገው ነበር፡፡ ሁለተኛው ፓትረያርክ አቡነ ቴዎፍሎስና አራተኛው ፓትረያርክ አቡነ መርቆሪዎስ ወደመንበራቸው እንዲመለሱ  የተደረገ እዚህ ግባ የሚባል ጥረት ግን አልነበረም፡፡ “ቄሱም ዝም፣ መጽሐፉም ዝም!” የሆነ መሰለ፡፡ ይህም የብፁዐን አባቶች ተግባር፣ በ35 ዓመታት ውስጥ (ከ1948-1984ዓ.ም) ምን ያህል ቁልቁል እንደሄድን አመላካች ነው፡፡ ብፁዐን አባቶችና የቤተ ክርስቲያኗም ለመርህ የመቆም አቅም ሙልጭ ብሎ ጠፍቶ ወደአዘቅት ለመውረዱ ዋናው ማሳያ ነው፡፡ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስና አቡነ መርቆሪዎስ ያለአጥጋቢ ምክንያት ከመንበራቸው ሲነሱ አብዛኞቹ የቤተ ክርስቲያኗ ሊቃነ ጳጳሳት የአቋም መግለጫ እንኳን ሳያወጡ መቅረታቸው በሰፊው አጠያይቋል፡፡ ዝምታው ፍርሀት የወለደው ነበር፡፡ “ፍርሃቱ ከዬት መጣ?” ካሉ ደግሞ፣ በሃይማኖት ካባ ስር ስውር የዘር ፖለቲካ የሚከተሉ አባቶች ስለነበሩ ነው፡፡ ለራሳቸው ፈርተው፣ ሌሎችንም አስፈራሩ!

ይህ ባይሆን ኖሮ፣ ከ35ዓመታት በፊት የግብፅ  ቤተ-ክርስቲያን ብፁዐን አባቶች ያደረጉት ሕግና ሥርዓትን የማክበር ተግባር እነርሱም ይፈፅሙት ነበር፡፡ የእስክንድርያ ፓትረያርክ ብፁዕ ዳግማዊ አቡነ ዮሳብ  በኅዳር 4 ቀን 1949 ዓ.ም ካረፉ በኋላ ነበር ቀጣዩ ፓትረያርክ ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ ስድስተኛ፣ በግንቦት 2 ቀን 1951 ዓ.ም (ልክ የዳግም ትንሳኤ ዕለት) የተቀቡት፡፡ አቡነ ቄርሎስም በቁጥር 116ኛው ፓትረያርክ ሆኑና ሥራቸውን ጀመሩ፡፡ በአንፃሩ ደግሞ በኢትዮጵያ የፓትረያርክነት መንበር ሲቀመጡ ሁለተኛና አራተኛ የሆኑት ብፁዐን፣ ከዚህ ዓለም በሞት እስኪለዩ ድረስ ሳይጠበቁ፣ በሰኔ 30/1968 እና በሐምሌ 5 ቀን 1984 ዓ.ም፣ ተተኪዎቹ ፓትረያርኮች በአናት ተቀቡ፡፡ ብፁዕ አቡነ ትክለ ሃይማኖት ከገዳም መጥተው የተሾሙ የመጀመሪያው ፓትረያርክ ሲሆኑ፣ ብፁዕ አቡነ ጳውሎስ ደግሞ ከስደት መልስ የተሾሙም የመጀመሪያው ፓትረያርክ ሆኑ፡፡

ይህ ያቡነ ተክለ ሃይማኖትም ሆነ የአቡነ ጳውሎስ ሹመት፣ ከፍተኛ የሆነ የቀኖና፣ የሕገ ቤተ ክርስቲያን ጥሰቶች የተስተዋሉበት ነው፡፡ የዚህ ጽሑፍም መነሻ ነጥብም በዋናነት ስለሦስተኛውና ስለአምስተኛው የኢትዮጵያ ብፁዕ ወቅዱሳን ፓትረያርኮች ጉዳይ ይመለከታል፡፡ በእርግጥ ሁለተኛውና አራተኛው የተሻሩበት አግባብና ሦስተኛውና አምስተኛው ፓትረያርኮች የተሾሙበት ሥርዓት በኒቅያው ቀኖና አንቀጽ 50፣ እንዲሁም በዚሁ በኒቂያው ቀኖና ስለፓትረያርክ በሚናገረው፣ በ4ኛው አንቀጽ በ5ኛው ክፍል የተደነገጉትን ሕጎች የሚተላለፍ ከመሆኑም በላይ፤ “ስለኢትዮጵያ ፓትረያርክ አመራረጥ የወጣውን የ1963 ዓ/ም የምርጫ ደንብና የ1968ቱን የምርጫ ማሻሻያ ደንብ” ሥነ ሥርዓቶች መሠረት ባለመካሄዱ ትክክለኛ አልነበረም፡፡

ይህንን ትክክለኛ ያልሆነ የቤተ-ክርስቲያን ቀኖናና ደንብ ጥሰት ለማለባበስ ከሰሞኑ የሚታዩትም ሩጫዎች የሚስተዛዝቡ ሆነዋል፡፡ የማኅበረ-ቅዱሳን ሁለቱ ልሳኖች፣ ማለትም “ስምዓ ጽድቅ” ጋዜጣና “ሐመር” መጽሔት፣ ችግሩ የእርቅና የምሕረት እንደሆነ አድርገው በኅዳር ወር እትማቸው “ከፓትረያርክ ምርጫ በፊት እርቀ ሰላም ይቅደም” የሚል አጀንዳ ያራግባሉ፡፡ በርግጥ ቤተ-ክርስቲያን የዕርቅና የምሕረት አደባባይ መሆኗ ባይካድም፣ የተያዘው አቋም ግን ትክክል አይደለም፡፡ በሌላም በኩል፣ ባለፈው ጥቅምት ወር ተሰብስቦ የነበረው የሲኖዶስ ጉባኤ አንድ አስገራሚና ከብፁዓን አባቶች የማይጠበቅ ውሳኔ ማስተላለፉ ተገልጧል፡፡ “እንዴት አምስተኛው ፓትረያርክ ስንል ሃያ አመታት ያህል ኖረን፣ እንደገና ወደ አራተኛው ፓትረያርክ እንመለሳለን? ሰውስ ምን ይለናል?” የሚል ስጋት እንዳላቸውም ተሰምቷል፡፡ ይህም ቢሆን ዓለምን ንቀው፣ በእግዚአብሔር መንገድ ለሚመላለሱ ብፁዐን አባቶች ያልተገባ አቋም ነው፡፡ ከበቁ የሃይማኖት መሪዎችና አባቶች አእምሮ እንዲህ ያለ የይሉኝታና የፖለቲከኛነት አስተያየት እንሰማለን ብለንም ለማንጠብቀው ለኛ ለምዕመናኑም ቢሆን አሸማቃቂ ነው፡፡

ዛሬም ከ55ዓመታት በኋላ የኢትዮጵያ ቤተ-ክርስቲያን አባቶች፣ የዛሬ ሃያ ዓመት የፈፀሙትን ስህተት ለማረም ወኔ ማጣታቸው ያስደንቃል፡፡ ታሪክ ጠቅሰን፣ የዛሬ 55ዓመት የኢትዮጵያ ቤተ-ክርስቲያን መሪዎች እንዴት በዜግነት ባዕድ ለሆኑት፤ ነገር ግን በሃይማኖት መሪነታቸው ለሚያከብሯቸው ለብፁዕ ዳግማዊ አቡነ ዮሳብ እንደተከራከሩና ታሪክም እንደሰሩ እናስታውሳችሁ፡፡ (እርግጥ ነው፣ ነገራችን ሁሉ “ለቀባሪው አረዱት” ዓይነት ነው፡፡) የመግለጫው መግቢያ ቃል እንዲህ ይነበባል፡፡ “የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስቲያን፤ የእስክንድሪያ ፓትረያርክ ብፁዕ ዳግማዊ አቡነ ዮሳብ ከሥልጣናቸው መወገዳቸውን እንደሰማች፤ ይህ ከሲኖዶስ የወጣ አደራረግ፤ አንደኛ) ከአባቶቻችን ከሐዋርያት ሲያያዝ የመጣውን መንፈሳዊ ሥርዓት የሚቃወም በመሆኑ፤ ሁለተኛ) ኢትዮጵያ ከ1600 ዘመን ጀምሮ ከመንበረ-ማርቆስ ጋር ባላት መንፈሳዊ ግንኙነት መሠረት፣ የእስክንድሪያን ፓትረያርክ መንፈሳዊ መብት የሚነካ ነገር በተነሣ ጊዜ ሁሉ ጉዳዩ በቀጥታ የሚያገባት መሆኑን በማመልከት ለግብፅ መንግሥትና ለመጅሊስ ሚሊ አባሎችም” መልዕክት ተልኳል፡፡

ብፁዕ ዳግማዊ አቡነ ዮሳብን ወደመንበራቸው ለመመለስ በነበረው ክርክር ዋና ዋናዎቹ የመከራከሪያ ነጥቦች የሚከተሉት ነበሩ፡፡ አንደኛ) የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስቲያን በነሐሴ 30/1947ዓ.ም የፓትረያርኩን ከመንፈሳዊ ሥልጣናቸው መነሣት ተቃውማ፣ በመስከረም 16/1948ዓ.ም “ቀኖና ተጥሷል” ብላ በሊቀ ጳጳሷ በኩል ቴሌግራም ማስተላለፏን ያወሳል፡፡ ሁለተኛም) ኢትዮጵያ በትልቁ የዓለም ፓትረያርኮች ጉባኤ ላይ በስምንተኛው መንበር ላይ የምትቀመጥ ሀገርና ተሰሚነቷም ቢሆን ከፍተኛ እንደሆነና ይህም በኒቂያው ቀኖና በ42ኛው አንቀጽ መሠረት የፀና መሆኑን ይገልፃል፡፡ ሦስተኛ) በዚሁ በኒቂያው ቀኖና በአንቀጽ 50 መሠረት፣ አንድ ፓትረያርክ ላይ ክስ ሲቀርብ ነገሩን ለመስማት በሚደረገው ጉባኤ፣ በሃይማኖት መካከል ቢያንስ አንድ ፓትረያርክ፣ ቢበዛ ደግሞ ሁለትና ከዚያም በላይ ፓትረያርኮች መገኘት የሚገባቸው ሲሆን፣ “በፓትረያርኩ ብፁዕ ዳግማዊ አቡነ ዮሳብ ላይ ውሳኔ ሲደረግ በስብሰባው ላይ አንድም ፓትረያርክ ያልተገኘበት በመሆኑ ስብሰባውም ሆነ ውሳኔው ሕጋዊ አይደለም፤” ይላል፡፡ አራተኛ) በኒቂያው ቀኖና ስለፓትረያርክ በሚናገረው 4ተኛው አንቀጽ፣ በ5ተኛው ክፍል እንደሚደነግገው ከሆነና፣ በቤተ-ክርስቲያንም ቀኖና መሠረት፤ “አንድ ፓትረያርክ ከመንፈሳዊ ሥልጣኑ የሚነሳው አእምሮው ከተናወጸ ብቻ ነው፤” ይላል፡፡ ስለዚህም ውሳኔው ሕግን የተመረኮዘ አለመሆኑን በስፋት የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ጋዜጣ፣ ዓርብ ጥር 4/1948ዓ.ም፣ ገጽ-1 ላይ ይገልፃል፡፡

እነዚህ ከላይ የጠቀስናቸው ሁለት የመከራከሪያ ጭብጦች መሠረት፣ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሪዎስ፣ ከፓትረያርክነታቸው የተሰናበቱበት አግባብ ሕጋዊ አልነበረም፡፡ በመጀመሪያ፣ አንድም የተገኘ ፓትረያርክ ሳይኖር በመሰናበታቸውና፤ ምንም የጤንነት ችግር ሳይኖርባቸው ከመንበራቸው በመነሳቸው ነው፡፡ የጤናቸውን ጉዳይ ላለፉት 21ዓመታት በሙሉሰውነት መኖራቸው ያረጋግጣል፡፡ በስደትም ላይ ሆነው ቤተ-ክርስቲያንን እየመሩ ናቸው፡፡ በተጨማሪም፣ ፓትረያርኩ የተሰናበቱት በሽግግር መንግሥቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ትዕዛዝ ለመሆኑ የwikileaksም ማረጋገጫ ከአዲስ አበባው የአሜሪካን ኤምባሲ ተገኝቷል፡፡ ይኼ ሕገ-ወጥ አካሄድ፣ እ.አ.አ በ1929 በዓለም አብያተ-ክርስቲያናት ጉባኤ የተወሰነውንና ኢትዮጵያም ያፀደቀችውን የጳጳሳት ምልዐተ-ጉባኤ ደንብ ያላከበረ ነው፡፡ ስምምነቱ እንደሚለው ከሆነ፣ የሲኖዶስ ውሳኔዎች ሲወሰኑ ቢያንስ ሁለት-ሦስተኛው የጳጳሳት ምልዐተ-ጉባኤ መሟላት ነበረበት፡፡ በ1984ዓ.ም ግን ይህ አልሆነም፡፡ አቶ ታምራት ላይኔ፣ በልዩ ትዕዛዝ ፓትረያርኩን አሰናብቶ ሲያበቃ፣ በሐምሌ 5/1984ዓ.ም በተወካዩ በአቶ መረባ አለማየሁ አማካይነት እንዲህ አለ፤ “ያለፉት የጭለማ ዓመታት አልፈው ሰላም፣ ዲሞክራሲ የሕግ የበላይነት እየተስፋፉ ነው” (አዲስ ዘመን ጋዜጣ፣ ሐምሌ 7/1984ዓ.ም፣ ገጽ-1)፡፡ (እውነት ነው፤ ሰላም ተስፋፍቷል፡፡ ነገር ግን፣ የዲሞክራሲውንና የሕግ የበላይነቱን መስፋፋት አቶ ታምራት አንዴ ይደግሙልን ይሆን? እንጃ! አይመስለንም፡፡)

**********************

ይህንን ጽሑፍ ከማጠናቀቃችን በፊት ለሰፊው የዚህ መጣጥፍ አንባቢዎች አንዳንድ ታሪካዊ ማስታወሻዎችን ልናካፍላቸው እንወዳለን፡፡ በተለይም እስከዛሬዋ ዕለት ድረስ፣ አራተኛው ፓትረያርክ ይመለሱ ይሆን ወይስ ስድስተኛውን ፓትረያርክ ይመርጡና በኢ-መርሕ፣ በኢ-ቀኖናና በ1963ዓ.ም የፀደቀውን፣ “ስለኢትዮጵያ ፓትረያርክ አመራረጥ የወጣውን የምርጫ ደንብና”፤ በ1968ዓ.ም የወጣውን ማሻሻያ ወደጎን ትተው ይቀጥሉበት ይሆን?” ለምንለው ምዕመናን በቂ መልስ ይሰጠናል፡፡ ከላይ እንደገለጽነው አራተኛውን ፓትረያርክ መልሶ በመንበራቸው ማስቀመጥ ከፍተኛ የሆነ ክርስቲያናዊ ተግባርና ለቀኖናም ተገዢነት ነው፡፡ “የለም፣ አምስተኛው ስንል ኖረን እንዴት ወደአራተኛው ፓትረያርክ እንመለሳለን!” ማለቱ ደግሞ ቤተ-ክርስቲያኗን ከፍተኛ ዋጋ ሊያስከፍላት እንደሚችል እናምናለን፡፡ (መቼስ፣ “ሃይማኖት ማለት ማመን ነውና፣ “እንዴት ልታምኑ ቻላችሁ?” ብላችሁ እንደማትጠይቁን፣ አሁንም እናምናለን!!!)

ስድስተኛው ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ መጡም-አልመጡም፣ ከአንደኛው እስከ አምስተኛው ብፁዕ ወቅዱስ ፓትረያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሆነው ሲመረጡ ምን ዓይነት የቤተ-ክርስቲያን አገልግሎት አበርክተው እንደሆነ ተራ በተራ እናወሳለን፡፡ በመጀመሪያም ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ እንጀምራለን፡፡ በ1884ዓ.ም በሚዳ አውራጃ፣ በአሞደል ጊዮርጊስ ተወለዱ፡፡ ሥመ-ጥምቀታቸውም ገብረ ጊዮርጊስ ነበር፡፡ በ1905ዓ.ምህረትም አመክሯቸውን ጨርሰው በደብረ ሊባኖስ መነኮሱ፡፡ በ1911ዓ.ም ጀምሮም የመናገሻ ማርያም መምህር ሆነው ተሾሙ፡፡ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስም የቁምስና ማዕረግ ጨመሩላቸው፡፡ ከ13ዓመታትም በኋላ፣ በ1924ዓ.ም በአዲስ አበባ የመንበረ መንግሥት ቅዱስ ገብኤል (ግቢ ገብርኤል) አስተዳዳሪ ሆነው ተሾሙ፡፡ በ1925ዓ.ም ደግሞ፣ በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ገዳማት ራይስ(ጠቅላይ አስተዳዳሪ) ሆነው ለሁለት ዓመታት ሠሩ፡፡ በ1927ዓ.ም ከኢየሩሳሌም ተጠርተው መጥተው የደብረ ሊባኖስ 59ኛው እጨጌ ሆነው ተሾሙ፡፡ በ1940ዓ.ም በእጨጌነቱ ላይ የጵጵስና ማእረግ ተሰጣቸው፡፡ እስከ1951ዓ.ምህረትም አርባ ሁለት አብያተ-ክርስቲያነትን አሠርተዋል፡፡ አስራ ሁለት ትምህርት ቤቶችንም አልምተዋል፡፡ በተለይም፣ በደብረ ጽጌ ያለውን የእብነት ትምህርት ቤት በግል ገንዘባቸው ነበር የሚያስተዳድሩት (አዲስ ዘመን፣ ጥቅምት 3/1963ዓ.ም)፡፡

ጥር 6/1943ዓ.ም፣ “ሊቀ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ” ተብለው እስከ 1951ዓ.ም ድረስ ቆዩ፡፡ በሰኔ 21 ቀን 1951ዓ.ም፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ለመጀመሪያ ጊዜ የራሷን “ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ወፓትረያርክ” ስታገኝ፤ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ የኢትዮጵያ ፓትረያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሆነው ካይሮ በሚገኘው የቅዱስ ማርቆስ ቤተ-ክርስቲያን፣ ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቄርሎስ ሳድሳዊ እጅ ተሾሙ፡፡ በተወለዱ በ79ዓመታቸው ጥቅምት 2/1963ዓ.ም፣ ከቀኑ በአስር ሰዓት ዐረፉ፡፡ ጥቅምት 4/1963ዓ.ም በደብረ ሊባኖስ ተቀበሩ፡፡

ሁለተኛው ፓትረያርክም በዓለ ሲመት መጋቢት 29 ቀን 1963 ዓ.ም በመንበረ ፓትረያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ቤተ ክርስቲያን ተከናወነ፡፡ “ሕዝባዊ መንግሥት እንጂ፣ ወታደራዊ ጁንታ አያዋጣንም!” ስላሉ፣ ወታደራዊ ደርግ የካቲት 9/1968ዓ.ም ከመኖሪያ ቤታቸው ወስዶ፣ መጀመሪያ በእዮቤልዩ ቤተ-መንግሥት፣ ከዚያም በልዑል ራስ አስራተ ካሣ ቤት አስሮ ካቆያቸው በኋላ፣ በሐምሌ 7/1971ዓ.ም በዚያው በታሰሩበት ቤት በገመድ ታንቀው እንዲገደሉ ተደረጉና እዚያው እንዲቀበሩ መደረጋቸውን፣ አዲስ ዘመን ጋዜጣ በሐምሌ 3/1984ዓ.ም ዕትሙ ይገልፃል፡፡ ከልዑል ራስ አስራተ ካሣ ግቢም አፅማቸው ወጥቶ፣ በሐምሌ 4/1984ዓ.ም፣ በቅድስተ ቅዱሳን ሥላሴ ካቴድራል ተቀበሩ፡፡ ፓትረያርክ ከመሆናቸውም በፊት የሐረርጌ ሊቀ ጳጳስ ሆነው ከ1943ዓ.ም ጀምሮ ከሠላሳ ሁለት አብያተ-ክርስቲያናትን አሠርተዋል፡፡ አቡነ ጳውሎስን ጨምሮ፣ በርካታም ጳጳሳትን ሾመዋል፡፡

ሦስተኛው ፓትረያርክም ሆነው የተመረጡት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ናቸው፡፡ ፓትረያርክ ከመሆናቸውም በፊት በወላይታ አውራጃ፣ በደብረ መንክራት ተክለ ሃይማኖት ገዳም መነኩሴ ነበሩ፡፡ ሆኖም፣ በሰኔ 30/1968á‹“.ም ከ619 ድምጽ ውስጥ 317ቱን አግኝተው ፓትረያርክ ሆኑ፡፡ በነበሩበትም በወላይታ አውራጃ ከሦስት መቶ ሺህ በላይ ምእመናንን ከማጥመቃቸውና የቤተ ክርስቲያኗም ተከታዮች ከማድረጋቸው በላይ፣ 35 አብያተ-ክርስቲያናትን አሠርተዋል፡፡ አስራ ስድስት የሕፃናት ማሳደጊያዎችን አቋቁመው፣ ከሃያ ሺህ በላይ ችግረኛ ሕፃናትን አሳድገዋል፡፡…. ግንቦት 28/1980á‹“.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩና ስርዓተ-ቀብራቸውም በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ሰኔ 1 ቀን 1980á‹“.ም ተፈፀመ፡፡

አራተኛው ፓትረያርክም ሆነው የተመረጡት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሪዎስ ናቸው፡፡ ከላይ በመግቢያችን በሰፊው ስለርሳቸው ያተትን በመሆኑ አንደግመውም፡፡ ነሐሴ 22/1980ዓ.ም ፓትረያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሆነው እስኪመረጡ ድረስ፣ የጎንደር ክፍለ-ሀገር ሊቀ ጳጳስ ነበሩ፡፡ በክፍለ-ሀገሩም ሠላሳ አብያተ ክርስቲያናትን ከማሠራታቸውም ባሻገር፣ የተለያዩ የአረጋዊያን መጦሪያ ተቋማትን፤ ከሃያ በላይ ወፍጮ ቤቶችን፣ 32 ዳቦ ቤቶችንና የተለያዩ የልማት ተቋማትን አሠርተው እንደነበር፣ አዲስ ዘመን ጋዜጣ በነሐሴ 24/1980ዓ.ም ዕትሙ ገልጧል፡፡ እኚህ ፓትረያርክ ከሀገር ከወጡም በኋላ የዴንቨር የቅዱስ ገብርኤል ቤተ-ክርስቲያን ብዙ ጳጳሳትን ሾመው ሲኖዶሳቸውን አጠናክረዋል፡፡

ወደማጠቃለያችን እየሄድን ነው፡፡ አምስተኛው ፓትረያርክም ሆነው የተመረጡት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ናቸው፡፡ በሐምሌ 5/1984ዓ.ም ፓትረያርክ ከመሆናቸው በፊት፣ በደርግ መንግሥት ለሰባት ዓመታት ያህል ታስረዋል፡፡ ከዚያም በስደት ግብፅ-አሌክሳንደሪያና አሜሪካን ኖረዋል፡፡ በስደት ላይም ሳሉ፣ በሥነ-መለኮት የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ተቀብለዋል፡፡ በ1983ዓ.ም ማብቂያም ላይ በወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው፣ አምስተኛው ፓትረያርክ ለመሆን በቅተዋል፡፡ እስከሚሾሙም ድረስ ያሠሯቸውን አብያተ-ክርስቲያናት ቁጥር አዲስ ዘመን ጋዜጣ አልገለፀም፡፡ በታኅሣሥ 1968ዓ.ም ጵጵስና የሾሟቸውን የሁለተኛውን ፓትረያርክ የብፁዕ አቡነ ቴዎፍሎስን አጽም ከበዐለ ሢመታቸው አንድ ቀን ቀደም ብለው፣ በሐምሌ 4/1984ዓ.ም በክብር እንዲያርፍ በዋናነት የተጉት፣ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ናቸው፡፡ በነሐሴ 11/2005ዓ.ምህረትም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተው፣ በነሐሴ 18/2005ዓ.ም በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተቀብረዋል፡፡ (ቸር እንሰንብት!) 

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 12 years ago on December 8, 2012
  • By:
  • Last Modified: December 8, 2012 @ 12:10 pm
  • Filed Under: Ethiopia
  • Tagged With:

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar