www.maledatimes.com የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ዝግጅቱን ዛሬ ይጀምራል - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ዝግጅቱን ዛሬ ይጀምራል

By   /   December 8, 2012  /   Comments Off on የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ዝግጅቱን ዛሬ ይጀምራል

    Print       Email
0 0
Read Time:23 Minute, 18 Second

በ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን 26 ተጨዋቾችን በመጥራት ዛሬ ዝግጅቱን ሊጀምር ነው፡፡ የብሄራዊ ቡድኑ የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ የተሳካ ለማድረግ የሚካሄዱ ልዩ ልዩ ዝግጅቶች በተመለከተ ጋዜጣዊ መግለጫ በሳምንቱ አጋማሽ ላይ በኢንተርኮንትኔታል ሆቴል በጉዞና ገንዘብ አሰባሳቢ አብይ ኮሚቴ ተሰጥቷል፡፡ ኮሚቴው ለብሄራዊ ቡድኑ የሚሆን እስከ 80 ሚሊዮን ብር ለማግኘት ማቀዱን ገልጿል፡፡ በጉዞና ገንዘብ አሰባሳቢ አብይ ኮሚቴው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ተ/ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ተካ አስፋው ፤ልዑል በእደማሪያም መኮንን፤ አምባሳደር ተወልደ ገብሩ፤ ኮ/ሃምሳሉ ገ/እግዚ፤አትሌት ኃይል ገ/ስላሴ፤ ኢንጂነር ተክለብርሃን አምባዬ፤ አቶ ሰለሞን አለምሰገድ፤አቶ አማረ ማሞ፤አቶ ሸዊት ወ/ሚካኤል፤አቶ አዋድ መሃመድ በመስራት ላይ ናቸው፡፡

ለብሄራዊ ቡድኑ በመጀመርያ ዙር የተጠሩ 26 ተጨዋቾች ታውቀዋል፡፡ እነዚህ ተጨዋቾች ትናንት እና ከትናንት በስቲያ አስፈላጊውን የህክምና ምርመራ በማድረግ ዛሬ ወደ ልምምድ እንደሚገቡ ይጠበቃል፡፡ ለብሄራዊ ቡድኑ ዝግጅት ሲባል የዘንድሮው የፕሪሚዬር ሊግ ውድድር ለሁለት ወራት ተቋርጧል፡፡ በ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ለሚሳተፈው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የተጠሩ 26 ተጨዋቾች ዝርዝር ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ደደቢት የአንበሳውን ድርሻ ይዘዋል፡፡ ከቅዱስ ጊዮርጊስ 10 ተጨዋቾች ደጉ ደበበ፣ቢያድግልኝ ኤልያስ፣ አበባው ቡጣቆ፣ ሽመለስ በቀለ፣ አዳነ ግርማ፣ ኡመድ ኡክሪ፣ ፈፁም ገብረማርያም፣ አሉላ ግረማ፣ ያሬድ ዝናቡና ዘሪሁን ታደለ፤ ከደደቢት 9 ተጨዋቾች ሲሳይ ባንጫ፣ ጌታነህ ከበደ፣ ብረሃኑ ቦጋለ፣ አይናለም ሃይሉ፣ስዩም ተስፋዬ፣አክሊሉ አየነው፣ አዲስ ህንፃ፣ ምንያህል ተሾመ እና በሃይሉ አሰፋ ተመርጠዋል፡፡ ከኢትዮጵያ ቡና ጀማል ጣሰው እና ዳዊት እስቲፋኖስ፤ ከኤልፓ አስራት መገርሳ፤ ከንግድ ባንክ ፍቅሩ ተፈሪ፤ ከሰበታ ከነማ ደረጀ አለሙ፤ ከመከላከያ መድሃኔ ታደሰ እንዲሁም ከአርባምንጭ ሙሉዓለም መስፍን በመጀመርያው ምርጫ ለብሄራዊ ቡድኑ የተጠሩ ሌሎች ተጨዋቾች ናቸው፡፡
ለብሔራዊ ቡድኑ ዝግጅት የሚሆኑ 3 ወዳጅነት ጨዋታዎች መመቻቸታቸውን የገለፀው አብይ ኮሚቴው ከሜዳ ውጭ ከታንዛኒያ እና ከካሜሮን ጋር እንዲሁም የአፍሪካ ዋንጫው ከመጀመሩ አንድ ሳምንት ቀደም ብሎ እዚያው በደቡብ አፍሪካ ከሞሮኮ ጋር ለመጫወት ስምምነት መደረጉንም አሳውቋል፡፡በብሔራዊ ቡድኑ ዝግጅት አሰልጣኞች እቅድ ማውጣታቸውን ገልፃ፣ የስነልቦና አማካሪዎች፣ የህክምና ኮሚቴው የየራሳቸውን እቅድ አውጥተው ስራ መጀመራቸውንም ገልፀዋል፡፡
በሆላንዱ አያክስ አምስተርዳም ጋር እየሠራ የሚገኝ ተቋምደግሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በአፍሪካ ዋንጫ ላይ የሚኖረውን ተሳትፎ እና የምድብ ተቀናቃኞችን አቋም ለመለካት በሚያስችል የጨዋታ ዳሰሳና ስሌት ለመስራትም ከፌዴሬሽኑ ጋር ስምምነት አድርጓል፡፡
ለ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ከቀረቡ 500ሺ ትኬቶች ውድድሩ ሊጀመር ከ6 ሳምንታት ያነሰ እድሜ ሲቀረው 30ሺ ብቻ መሆኑ አዘጋጆቹን አሳስቧቸዋል፡፡ በተለያዩ ዘገባዎች የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን 15ሺ ትኬቶችን ለመግዛት መጠየቁን ቢገልፁም የፌደሬሽኑ ሃላፊዎች ይህን መረጃ ከእወነት የራቀ ብለውታል፡፡የትኬት ዋጋ ከ6-600 ዶላር ነው፡፡
80 ሚሊዮን ብር ለማግኘት
8100 የኤስኤምኤስ ውድድር እና የኤምቲኤን ‹ሴሌብሬት 31 ኦን 831› የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬኽን ለብሄራዊ ቡድኑ ያቆመው የገቢ አሰባሳቢ እና የጉዞ አመቻች ኮሚቴ ባለፈው ረቡእ ከሰዓት በኤስኤምኤስ መልዕክት ሽልማት የሚያስገኝ ውድድር ጀምሯል፡፡ ለዚሁ የኤስኤምኤስ ውድድር በርካታ ሽልማቶች መቅረባቸውን ያመለከተው ኮሚቴው ከቤት ሽልማት በቀር ሌሎቹ ሽልማቶችን በስፖንሰርሺፕ ድጋፍ አግኝቷል፡፡ በለንደን ኦሎምፒክ ወቅት ለኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ቡድን የተዘጋጀው የኤስኤምኤስ ውድድር ስኬታማነት በመከተል በ8100 በ2 ብር ክፍያ ኢትዮጵያውያን እንዲሳተፉ ጥሪ ሲቀርብ ሽልማቶቹ 1.2 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ ቤት፤ 2 የቤት መኪናዎች፤ ሁለት ባጃጆች፤ 7 ቴሌቭዥኖች፤ 10 ላፕቶፖች፤6 ፍሪጆች፤ 150 ሳምሰንግ የሞባይል ቀፎዎች፤ የደቡብ አፍሪካ ጉዞ የደርሶ መልስ ትኬቶች፤ የብሄራዊ ቡድን ትጥቆች እና በአምስቱ የስታድዬም መግቢያዎች ለእያንዳንዳቸው አምስት አምስት የ1ዓመት መግቢያ ትኬት እንደየደረጃው እንደሚሰጡ ተገልጿል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘም ኤምቲኤን ኢትዮጵያ ከ31 ዓመታት በኃላ ማለፋን ለማድነቅ ‹ሴሌብሬት 31 ኦን 831› በሚል የኤስኤሜስ የጥያቄ እና መልስ ውድድር አዘጋጅቷል፡፡ የውድድሩ አሸናፊዎች የሚሆኑ አምስት ተሳታፊዎች 29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ወደምታስተናግደው ደቡብ አፍሪካ የደርሶ መልስ ቲኬት ፤ ኢትዮጵያ በምድቧ የመክፈቻ ጨዋታ ከዛምቢያ ጋር የምታደርገው ግጥሚያ መግቢያ ትኬት እና የ3 ቀናት የሆቴልና የምግብ መስተንግዶ ወጪን የሚሸፍኑ ሽልማቶች እንደሚያገኙ ተነግሯል፡፡ ኤምቲኤን በሞባይል ኮምኒኬሽንና በአይሲቲ የሚሰራ ኩባንያ እና በ23 አገራት 180 ሚሊዮን ደንበኞች ያፈራ የደቡብ አፍሪካ ኩባንያ ነው፡፡
ሌሎች የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅቶች
በብሄራዊ ቡድኑ ዙርያ 5 የገቢ ማግኛ እና ማሰባሰቢያ ዝግጅቶችን ባዋቀረው ኮሚቴ የነደፈው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ከ8100 የኤስኤምኤስ ውድድሩ ባሻገር ያቀዳቸው አሉ፡፡ የመጀመርያው በገና በዓል ሰሞን እኛ በሙያችን ለብሄራዊ ቡድናችን በሚል የአገሪቱ ታዋቂ አርቲስቶች ያለአንዳች ክፍያ በበጎ ፈቃደኝነት እንሰራዋለን ብለው ቃል የገቡት የሙዚቃ ኮንሰርት ነው፡፡ በአዲስ አበባ ስታድዮም ሊደገስ የታቀደውን ይህን የሙዚቃ ኮንሰርት አዲካ እንደሚያዘጋጀው ሲታወቅ በዝግጅቱ ከትኬት ሽያጭ ባሻገር በስፖንሰሮች ገቢ ለማግኘት መታቀዱን ለማወቅ ተችሏል፡፡ በሌላ በኩል ከብሄራዊ ቡድኑ ጋር የተያያዙ የልዩ ልዩ ቁሳቁሶች ሽያጭ በፌደሬሽኑ በኩል የሚደረግ ሲሆን ለብሄራዊ ቡድኑ መሸኛ ተብሎ የተዘጋጀ ልዩ የእራት ግብዣም ይኖራል፡፡ በሚሊኒዬም አደራሽ ከ2500 በላይ እንግዶችን በማሳተፍ የሚከናወነው የእራት ግብዣ ቀደም ሲል የተከበሩ ሼህ መሃመድ ሁሴን አላሙዲ ለዋልያዎቹ እና ለሉሲዎች ቃል የገቡት 10 ሚሊዮን ብር የሚሰጥ ሲሆን በወቅቱ ለብሄራዊ ቡድኑ የሚሆን እስከ 20 ሚሊዮን ብር ገቢ ለማሰባሰብ በተያዘ እቅድ ከእራት ግብዣው ጋር ጎን ለጎን እንቅስቃሴዎች ይደረጋሉ፡፡
የሄኒከን ስፖንሰርሺፕ
ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አብይ ስፖንሰር የሆነው ሄኒከን ነው፡፡አብይ ኮሚቴው በአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ ትልቅ ትኩረት ያገኘውና በዓለምአቀፍ ዜናዎች የገባውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ስፖንሰርሺፕ ለሄኒከን የተሰጠው በ3 ምክንየቶች መሆኑን ገልጿል፡፡ የመጀመሪያው ኩባንያው በስፖንሰርሺፕ ለመክፈል ቃል የገባው የገንዘብ መጠን ከፍተኛ መሆኑ ነው፡፡ በ2ኛ ደረጃ ደግሞ ኩባንያው በስፖርት ስፖንሰርሺፕ ከፍተኛ ልምድ አለው፡፡ በ3ኛ ደረጃ ዋልያዎችን ብራንድ ለማድረግ ያቀረበው ሃሳብ ዓለምአቀፍ ገጽታን ለመገንባት ያግዛል ተብሎ ስለታመነበት ነው፡፡
ሄኒከን በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ስፖንሰርሺፕ ከከፈለው ገንዘብ ባሻገር በተለያዩ ሸቀጣሸቀጦችና ቁሳቁሶች በማስተዋወቅ ለመስራት መወሰኑም ተመራጭ አድርጐታል፡፡ ኮሚቴው ከሄኒከን ጋር ባደረገው ስምምነት የብሄራዊ ቡድኑ መለያ በሆነው የዋልያ ብራንድ የሚዘጋጁ ቲሽርት፤ኮፍያ ጨምሮ የተለያዩ ቁሳቁሶች ለገበያ እንደሚቀርቡ አስታውቀዋል፡፡ ለዋልያዎቹ ከሄኒከን ጋር የተደረገው ስምምነት እና የገንዘቡ መጠን ታህሳስ 4 ኩባንያው በሚያዘጋጀው ስነስርዓት ይፋ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡ አብይ ኮሚቴው እንደገለፀው ለብሔራዊ ቡድኑ ከዋናው ስፖንሰር ውጭ በሁለተኛ ደረጃ ስፖንሰር የሚያደርጉ ኩባንያዎችን በመፈላለግ ላይ ናቸው፡፡ ሄኒከን ከዓመት በፊት ታዋቂዎቹን የሃረር እና በደሌ ቢራ ጠማቂ ኩባንያዎች በ163 ሚሊዮን ዶላር በመግዛት ኢንቨስት ያደረገ የሆላንድ ቢራ ጠማቂ ኩባንያ ነው፡፡ በአፍሪካ 20 አገራት በአጠቃላይ በዓለም 170 አገራት በመንቀሳቀስ በ57 አገራት ደግሞ 116 የቢራ ማምረቻ ፋብሪካዎች በማቆም የሚሰራው ሄኒከን በአውሮፓ ትልቁ የቢራ ብራንድም ነው፡፡ የአውሮፓ ሻምፒዮንስሊግ ኦፊሺያል ስፖንሰር በመሆን በአመት እስከ 70 ሚሊዮን ዶላር ሲከፍል የቆየው ሄኒከን በደቡብ አፍሪካ፤ በአሜሪካ እና በካሬቢያን በተደረጉ የራግቢ ዓለም ዋንፃ፤ የሜዳ ቴኒስ እና የጎልፍ ውድድሮች ስፖንሰርነት ድጋፍ የሰጠ ኩባንያ ነው፡፡ በ2011 እኤአ በመላው ዓለም በሚገኙ የሄኒከን ቢራ ማምረቻ ኩባንያዎች በተለያዩ ብራንዶች 16.46 ቢሊዮን ሊትር ቢራ የጠመቀው ኩባንያው ከ64ሺ በላይ ሰራተኞች ሲኖረው በዓለም ከሚገኙ 3 ግዙፍ ቢራ ጠማቂዎች አንዱ ነው፡፡
ዋልያዎቹ ወይስ ጥቁር አናብስቱ
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ቅፅል ስም ዋልያዎቹ ወይንስ ጥቁር አናብስቱ የሚለው ሁኔታም ባለፈው ረቡእ አብይ ኮሚቴው በሰጠው መግለጫ እልባት ያገኘ መስሏል፡፡ በወቅቱ የሚወጋ እና አጥቂነትን ያሳያል የተባለ አዲስ የብሔራዊ ቡድን ሎጐም ተዋውቋል፡፡ሎጎውን የብሄራዊ ቡድኑ መለያ ብራንድ ለማድረግ እንደተፈጠረ አብይ ኮሚቴው አብራርቷል፡፡ አንዳንድ አስተያየት ሰጭዎች የብዙዎቹ የአፍሪካ ብሄራዊ ቡድኖች በጣም ሃይለኛ እና ግርማ ሞገስ ባላቸው አራዊቶች ቅፅል ስም ሲወጣላቸው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በፍየል ዝርያ መመሰሉ አልተመቻቸውም፡፡ የፌደሬሽኑ ሃላፊዎች በበኩላቸው በኢትዮጵያ ብቻ በሚገኝ ብርቅዬ እንስሳ ብሄራዊ ቡድኑ በመሰየሙ ልዩ ገፅታ ያላብሰዋል በሚል ይከራከራሉ፡፡ ከአፍሪካ ዋንጫ ጋር ተያይዞ በሚሰሩ ዘገባዎች ግን ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ዋልያዎቹ ሆነ ጥቁር አናብስቱ በእኩል ደረጃ በመጠቀስ ቀጥለዋል፡፡ በሌላ በኩል ይሄው ሎጎ የታተመበት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ትጥቅ በመዘጋጀትም ላይ ነው፡፡ አቶ ተክለብርሃን አምባዬ የብሔራዊ ቡድኑን ማልያ በልዩ ጥራት ለማሠራት ውጭ አገር እንደሚገኙ የገለፀው አብይ ኮሚቴው እያንዳንዱ ተጨዋች ከየማሊያው 5 እንዲኖረው ይደረጋል ብሏል፡፡ በዚህም ማንኛውም ተጨዋች ማልያ ለመቀየር ወይም ለመወርወር የሚችልበት ደረጃ ላይ ተደርሷል፡፡
ወደ ደቡብ አፍሪካ ጉዞን በተመለከተ
አብይ ኮሚቴው ከ2 ዓመት በፊት በደቡብ አፍሪካ በተዘጋጀው የዓለም ዋንጫ ላይ የነበረው መጥፎ ተሞክሮ በአፍሪካ ዋንጫው መደገም የለበትም ይላል፡፡ አብይ ኮሚቴው የ26 ጋዜጠኞችን ሙሉ ወጪ ሸፍኖ ወደ ደቡብ አፍሪካ ለመውሰድ መዘጋጀቱን አስታውቋል፡፡ ወጪውን በስፖንሰር ለመሽፈን ባደረገው ጥረት አዲካ፤አሰር ኮንስትራክሽን የሶስት የሶስት፤ኢንተር ኮንትኔታል ሆቴል ስድስት ጋዜጠኞች ወጪ ለመሸፈን ቃልየገቡ ሲሆን፤የቀሪዎቹን ወጪ ሼህ መሀመድ ሁሴን አል-አሙዲ እንደሚሸፍኑ ተገልጿል፡፡
ከእያንዳንዱ ክለብ 5 ደጋፊዎችን፣ በስፖርት ማህበራትን ወደ ስፍራው ለመውሰድ ተወስኗል፡፡ የደቡብ አፍሪካ ኤምባሲ ወደ ስፍራው ለሚጓዙ የኢትዮጵያ ደጋፊዎች እና ሌሎች ልዑካኖች ያወጣው መስፈርት ግን የሚያስጨንቅ ነው፡፡ በተለይ ለ26 የሚዲያ አባላት እና ለደጋፊዎች ኤምባሲው ለቪዛ አገልግሎት የጠየቀው ዋስትና ለፌደሬሽኑ እና እድሉን ማግኘት ለሚፈልጉት ኢትዮጵያውያን የሚያሳስብ ሆኗል፡፡ በደቡብ አፍሪካ ኤምባሲ መስፈርት መሰረት ቪዛ ለማግኘት አመልካቾች የመኪና ወይም የባንክ አካውንት፤ የሆቴል ሪዘርቬሽን፣ የአውሮፕላን ትኬትና የድጋፍ ደብዳቤ ጠይቋል፡፡ አብይ ኮሚቴው ይህን ሁኔታ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና ከደቡብ አፍሪካ ኤምባሲ ጋር በመነጋገር አፋጣኝ መፍትሄ እያፈላለገ ነው፡፡
Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 12 years ago on December 8, 2012
  • By:
  • Last Modified: December 8, 2012 @ 1:35 pm
  • Filed Under: Ethiopia

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar