www.maledatimes.com ይህም አለ ክፍል 5 በፀሐይ በየነ … - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

ይህም አለ ክፍል 5 በፀሐይ በየነ …

By   /   December 17, 2012  /   Comments Off on ይህም አለ ክፍል 5 በፀሐይ በየነ …

    Print       Email
0 0
Read Time:24 Minute, 43 Second
ይህንን ስሎት ብዙም እንዳይገርምዎት አመት ሙሉ ነጭ ሩዝ በጨው ቀቅሎ ሲበላ የከረመ ሰው ሁላ ለረመዳን ሲሆን ከየት እንደሚያመጣው አያውቁም፡፡ አይነት ደርድሮ ሲበላ የሚያዩት፡፡ ፆሙ ገብቶ እየተገባደደ ሲሄድ ደግሞ የልብስ፣ የእቃ የጫማና የጌጣጌጥ መግዣ ጊዜ ነው፡፡ ሁሉም የገበያ ቦታ በልጅ፣ በአዋቂ በወንድ በሴት ተጨናቆ ያዩታል፡፡ ግፊያና ትርምሱን ለመቻል  ጠንከር ያለ ሰውነት፣ ዘለግ ያለ ቁመና ያስፈልጎታል፡፡ አለበለዚያ ደቀቅ ያለ ሰውነት ይዘው ከግፊያው መካከል የምፈልገውን ገዝቼ እወጣልሁ ማለት ዘበት ነው፡፡ ካልሆነ ቀድሞ መገኘት ነው፡፡ አልያም ግፋያው ሲቀንስ ለሊት ላይ ወጣ ማለት ነው፡፡ አንዳንዴ እንደውም የሚገበዩት አዳራሽ ውስጥ ከሆነ አየር በማጣት ሊታፈኑ ስለሚችሉ ጎመን በጤና ብለው መውጣት ነው፡፡ አለበለዚያ በጤናዎ የሚተማመኑ መሆን አለቦት፡፡       ስለ ምግብ ከተነሳ እዚህ ሀገር የማይበላ የቅጠላ ቅጠልና የፍራፍሬ አይነት የለም፡፡ እነዚህን የቅጠላ ቅጠልና የፍርፍሬ አይነቶች በክፍል5 እናያለን፡፡ ተባብለን ነበር በክፍል 4የተለያየነው፡፡ክፍል 5 እንሆ፡፡    እኛ ሀገር በልጅነት ጢባጢቢ የምንጫወትበት ቅጠል ሳይቀር እንደ ጎመንና ቆስጣ ተከሽኖ ይቀርብልዎታል፡፡  ከፈለጉ እንደ ስጋ በጥሬ፡፡ ደግሞም የሚመገቡትን ምግብ እንዲያጣጥምሎት እንደ አፒታዘር ተውቦ አጠገቦ ይቀመጥሎታል፡፡ ከፈለጉት እያነሱ በጉራሻዎ መካከል ማጣጣም ብቻ ነው፡፡ የሀገሮትን የአመጋገብ ዘይቤ በምናቦ እየሳሉ ምን ያህል ምርት እንዳባከኑ ባያስቡ መልካም ነው፡፡ እንቢ ብለው ማሰቦን ካላቆሙ  በንዴት ሰውነትዎ ማለቁ ነው፡፡ ከዛ ይልቅ ለማያውቀው ሰው ያዩትን የሰሙትን ማሰማትና የሚችሉን ያቅሞትን ታሪክ ሰርቶ ማለፍ ነው፡፡
ከመጣፈጡ የተነሳ ባለማወቅ አፈር ላይ እያንከባለሉ የተጫወቱበት፣ አረም እያሉ ከጎመንና ከሰላጣ መካከል ነቅለው ከግቢዎ ጦሴን ብለው የወረወሩትን ቅጠል ባሰቡ ቁጥር ምነው አስቀድሜ ይህቺን ሀገር ባወኳት በለው በንዴት መንገብገቦ አይቀርም፡፡    በምድር ላይ የሚበቅሉ ሳርና ቅጠላ ቅጠሎች እንዲህ እንደዋዛ  በንቀት የሚታዩና ተመርጠው የሚወረወሩ እንዳይመስሎት፡፡ ሁሉም ቅጠላ ቅጠል በህይወቶ ውስጥ ትልቅ ቦታ አላቸው፡፡ ሁሉም የስራ ድርሻ ተከፋፍለው ለእያንዳንዱ በሽታ ፈዋሽ ናቸው ተብለው ተመድበው ቦታ ቦታቸውን ይዘዋል፡፡ ለደም ግፊት፣ለጨጓራ፣ ለጉበት፣ ለኩላሊት፣ ለፊት ጥራት፣ ለቆዳ ጥራት፣ ለፀጉር ብቻ ለማንኛውም የህመም አይነት መዳኛ አልያም መከላከያ ወይም ደግሞ እንዳይብስ ማስታገሻ……፡፡      ምን አልባት አበባንም ቢሆን እርሶ የሚያውቁት ለቤት ማስዋቢያ፣ ለጊቢ፣ ለሰው ስጦታ ለመስጠት ይሆናል እዚህ ግን አድርቀው ካስቀመጡት በኋላ እንደ ጭማቂ ይጠቀሙታል፡፡ ለእርሶም ከቀረበ እያጣጣሙ ያወራርዱታል፡፡ እንዳውም አበባ መትከል በሽታዎ ከሆነ እንደ ወረደ የአበባ ጭማቂ ለመጠጣት ዶማ ይዘው  ጓሮ ጓሮ ማለት ይጀምራሉ፡፡ ምድር ከምታበቅላቸው ነገሮች ምንም የማይበላና የማይጠጣ የለም፡፡ ሁሉም አገልግሎት ይሰጣሉ እንጂ ዝም ብሎ ያለጥቅም መሬት የሚያክል ነገር ላይ በቅለው ውሃ አባክነው ማዳበሪያ ተሻምተው በከንቱ ተነቅለው አይወረወሩም፡፡     ፍራፍሬውም እንደዚሁ፡፡ የማያዩት የፍራፍሬ አይነት የለም፡፡ በምድር ላይ መፈጠራቸውን የማያውቁት ፍራፍሬ ሲያዩ አይኖት በግርምት ይፈዛል፡፡ ሀገሪቷን ሲመለከቱ አርንጓዴ ነገር ለማየት በጠኔ ይሞታሉ፡፡ ከየት አመጡት ብለው አእምርዎን በጥያቄ ማጣደፉ አስፈላጊ ይሆናል፡፡
በዝናብ እንዳይሉና ጥያቄውን ቀለል እንዳያደርጉት፡፡ ደግሞ ክረምትና በጋው መቼ እንደ ሆነ አያውቁትም፡፡ አንዴ እራቁቶትን የሚያስኬሄድ ሙቀት ሌላ ጊዜ ደግሞ እሳት አጠገብ አይደለም እንደ ብረት ድስት ከላይ ቢጣዱ ሙቀት የማይሰማዎት ወቅት ይሆናል ፡፡ በአመት ለአንድ ሳምንት ከዘነበ ታድለዋል፡፡ ቢዘንብም ከተማ ውስጥ ነው፡፡ እንደውም እንደ እኛ ሀገር ዝናብ ሲያካፋ መጠለያ ፍለጋ  ሰዉ ሲራወጥ አያዩትም፡፡ እልቁንም ከቤት የነበረ  ሰው ሳይቀር የዝናቡን በረከት ለማግኘት በየመንገዱ ሲኮለኮል ያዩታል፡፡
አቅመ ደካሞች ቁራናቸውን እየቀሩ ፀሎት ያደርጋሉ እንጂ ደግሞ ጀመረው እኝኝ ሊል ነው ብለው አይነጫነጩም፡፡ይሄ ሊገርሞትም ሊደንቆትም ይችል ይሆናል፡፡ ለዝናብ ያላቸውን ጉጉትና ፍቅር ኤተው እንደው ስለ ዝናብ ትንሽ ወሬ ካነሱባቸው እናንተ ሀገር ዝናብ አለ? የሚል ጥያቄ  ይቀርብሎታል፡፡ በዚህን ሰዓት  ግፊቶት እዳይነሳ  በደንብ ተቋቁመው እንኳን ዝናብ ሰማይም የለንም ብለው መመለሱ በሽታዎ እንዳይበረታ ይረዳዎታል፡፡  ታድያ ደግሞ ከፈጣሪም እንዳይጣሉ ዞር ብለው ቱ..ቱ ይቅር በለኝ ማለትን እንዳይረሱ፡፡ ምክንያቱም እኛ ሀገር ያለውን ዝናብ ስለሚያውቁት ደግሞ እንደነርሱ እንዳያደርገን በመስጋት፡፡
የአትክልትና ፍራፍሬው ከየት መጣ የሚለው ጥያቄ መልስ አያገኝም፡፡ እርሶም መልስ ፍለጋውን ትተው እንደውም በበረሃ በተቃጠለች ሀገር  አርንጓዴ ለማት አይኖቾት በእረሃብ እየሞቱ እንደዚህ አይነት የአትክልትና የፍራፍሬ አይነት በማየቶት ጉብዝናቸውን ሲያደንቁ ውለው ያድራሉ፡፡ ይህንን ስሎት ከውጭ የሚያስገቡት የታሸጉ ገና ሲታዩ እኛ የእዚህ ሀገር ዜጎች አይደለንም ብለው እራሳቸው ለራሳቸው ምስክር የሚቆሞ መገዛት አቅሞት ባይችል እንኳን በመጠየቅ ፍላጎቶትን ሞልተው እንዲሄዱ ማራኪነታቸው ከእሩቅ የሚጣራ አትክልትና ፍራፍሬዎችን እንደ ጉድ ያያሉ፡፡
የእዚህ ሀገር ዝናብ ሲዘንብ መንገዱ ሁላ ወንዝ ይሆናል፡፡ እግረኛ ከሆኑ እንግዲህ ከቁመትዎ ዘለግ  ካሉ ወገቦት ደረስ፣ አጭር ከሆኑ አንገቶት ደረስ ተውጠው መሻገር ነው፡፡ በእዛላይ እየጠራረገ የሚሄደው ቆሻሻ ከልብሶት እየተለጠፈ ተሻግረው ሲጨርሱ ቆሻሻውን ለማርራገፍ  ቀጣይ ስራ አለቦት ማለት ነው፡፡
ጉዞው ቀጥላል፡፡  የትራፊክ መብራት ያለበት ቦታ ለመድረስ ጢቂት ቀርቶኛል፡፡ መኪናዎች ተተረማምሰው ያለ ረድፍ ቆመዋል፡፡ በቦታው የትራፊክ ፖሊሶች አሉ፡፡ የትራፊክ መብራቱ ስለተበላሸ አርንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ የሚያበሩት አንፖሎች ስራቸውን አቁመው እረፍት ላይ ናቸው፡፡ እርስ በእርሳቸው ተቆላልፈው የቆሙት መኪናዎች አንተ ልቀቅልኝ እኔ ልለፍ እያሉ በፉክክር ጥሩንባቸውን ያስጮሃሉ፡፡  ከእያንዳንዱ መኪና መስኮት የወጡ አንገቶችና የሚለፈልፉ ድምፆችን ያያሉ ይሰማሉ፡፡ ገሚሱ ይሳደባል ገሚሱ በትህትና ይለምናል ሌላው ደግሞ አንደበቱ እንደዘጋ አይኖቹን ብቻ ከግራ ወደ ቀኝ እየላከ የሚሆነውን በዝምታ ያያል፡፡ ሁሉም ግን ፉክክር ይዘዋል፡፡ የስራ ሰዓት እንዳረፍድ ነው ይህ ሁላ ጩኸት፡፡  የእዚህ ሀገር የስራ ሰዓት ስንት ሰዓት እንደሆነ ለማወቅ በጣም ይቸገራሉ፡፡ አንዱ 3ሰዓት ሌላው 4ሰዓት ደግሞ ማልዶ የሚነሳም አለ፡፡ ታድያ የትኛው ነው ተክክለኛው የስራ መግቢያ ሰዓት የሚለው ነገር መልስ ለማግኘት ከባድ ነው፡፡
እንደዚህ አይነት ነገር ሰምተው ወይም አይተው አያውቁ ከሆነ ዛሬ ልንገሮት፡፡ የትራፊክ ፖሊስ ባለበት ቦታ መኪናዎች እርስ በራሳቸው ተቆላፍፈው ይቆማሉ፡፡ ልክ ከላይ እንደገለፅኩት አይነት ማለት ነው፡፡ ሁሉም እኔ ልለፍ ነው የሚለው፡፡ የትራፊክ ፖሊሶች በአንድ ቦታ 2እና3 ያያሉ፡፡ የወጡት ወደ ስራ ብለው ከቢሮው ፈርመው ቢሆንም እነርሱ ግን ተሰብስበው የሚያወሩት የግል ወሬ ነው፡፡ እንዳንዱ በጫት የተወጠረ ጉንጩን እያሻሸ ሲጋራ በላዩ እየማገ ስለሚሆነው ነገር ደንታም የለውም፡፡  የበላይ ተቆጣጣሪያቸውም ብቅ ቢል ሞተሩ ላይ እንደተቀመጠ ከሚያወሩት ወሬ አዳምጦ አስተያየት መስጠት ካለበት ሰጥቶ ከራሱም ትንሽ ወሬ ጨምሮላቸው ሞተሩን አስነስቶ የመሰነባበቻ ሰላምታ ሰጥቷቸው ፈትለክ ነው፡፡       የእርሶና የሌሎች መኪናዎች እርስ በራሳቸው ተሳስረው ቆመው ቢውሉ ደንታቸው አይደለም፡፡ አንዳንዴ እንደውም ከመብራቱ ብዙ እርቀው ያሉ ባለ መኪናዎች ለጊዜው የትራፊክ ፖሊስ ሆነው ወርደው ሲያሰተናብሩ ያያሉ፡፡ አይግረሞት እርሱም ተራ ደርሶት ሲሄድ ሌላው ደግሞ ወርዶ ሲያስተናብር ያዩታል፡፡ ደሞዙን የሚበላው ግን……፡፡       በዚህ ቦታ የሚፈጠረው ግጨት ብዛት ተቆጥሮ አያልቅም፡፡ ምክንቱም ብዙ በመቆም ትግዕስቱ ያለቀበት ሁላ ትንሽ ክፍተት ሲያገኝ ለማምለጥ ስለሚጣደፍ ነው፡፡ ለነገሩ እነኛስ ሀገር ቢሆን እንደ መንግስተ ሰማያት መግቢያ የትራፊክ ህግ በጠበቀበት ሀገር የሚደርሰው አደጋ ይህ ነው የማይባል አሰቃቂና ዘግናኝ ነው፡፡ ስለዚህም እነዳንዴ አያምጣው ነው እንጂ ህግ ምን አባቱ እንድንል  የሚያደርገን ይህ ሀገር ነው፡፡     እዚህ ሀገር ህግ ፈፅሞ ምን እንደሆነ የሚያውቁት አይመስለኝም፡፡ ግን የሆነ ነገር ገርሞት እንዴ ይህ እኮ እኛ ሀገር ቢሆን ህጉ እንደዚህ ስለሚል ብለው ስለ ህግ ቢያወሩ እኛም ሀገር አለ ይልና ግን ማንም እንደማያከብረው አያይዞ ይነግሮታል፡፡ ታድያ በወረቀት ላይ የሰፈረው ለምን ይሆን ብለው አይጨነቁ ምክንያቱም እነርሱስ ቢሆን መች ተጨንቀውለት፡፡
ሌላው ደግሞ የመኪናዎን አፍንጫ ከፊቶት ካለ መኪና  መቀመጫ ጋር አጣብቀው ነው የሚቆሙት፡፡ በእርሶና በሌላው መኪና መካከል ባለው ክፍተት አየር እንኳን የሚያልፈው ተጣቦ ነው፡፡ ስለዚህ ወደፊት የለ ወደ ኋላ ነቅነቅ እላለሁ ካሉ የመኪናዎን የፊት ጥርስ ማራገፎት አይቀሬ ነው፡፡       በዚህ ሰዓት ብዙ አይነት ስድቦችን፣ ድበድባና ጩኸቶችን መስሚያዎት እስኪዝል ይሰማሉ አይኖቾት እስኪደነዝዙ ያያሉ፡፡ ታድያ እርሶ የፊልሙ ተመልካች ከሆኑ በምናቦት የሚስሉት ነገሮች በጣም ብዙ ናቸው፡፡ በድንጋይ ተፈንክቶ ደሙ ከትከሻው ላይ የሚወርድ፣ ጃንቢያ እየተባለ በሚጠራው ከደረታቸው ላይ ሰክተው የሚሄዱት ቢላ በሚመስለው ስለት ጎኑ ተወግቶ ቀይ ነገር ከጎኑ ሲፈስ …….፡፡ ምናልባት እዚህ ደረጃ ላይደርሱ ይችላሉ፡፡ ግርግርና ወከባውን ግን ሲያዩ ደም መፍሰስ ብቻ ሳይሆን የብዙ ሰው ህይወት የጠፋ ይመስሎታል፡፡ በነገራችን ላይ የዚህ ሀገር ሰዎች ለደም ትልቅ ክብር አላቸው፡፡ ሲደባደቡ አይደለም የሚቆረቆር ደም ቀይ ነገር ካዩ ጉድ ፈላ እንደ እብድ ነው የሚያደርጋቸው፡፡ ለምን ነስር ነስሮት አይሆንም፡፡ ተደባድበው ቀይ ነገር ከደበደቡት ሰው ከማንኛውም የሰውነት ክፍል ላይ ካዩ በመቆም እንዳይጃጃሉ ማምለጡ ነው የሚያዋጣዎት፡፡ አለበለዚያ እንደ ጉንዳን መንጋ ከተወረሩ መውጫ የሎትምና፡፡ እዛ ቦታ ላይ በምን ኮድ ተጠራርተው አልያም ተግባብተው ይሆን በማያውቁት መንገድ ደም የፈሰሰው ሰው ዘመድ በአንዴ አንድ ሺህ ሲሆኑ ያያሉ፡፡ እርሶ የዘመድ ቆጠርውን ትተው እግሬ አውጭኝ ማለቱ መፍትሄ ነው፡፡               የተጨናነቀውን የመኪና ብዛት ሲያዩ ምንም መጨናነቅ የለቦትም የቀሮት ትንሽ መንገድ ከሆነ ወርደው በእግሮት ቢሄዱ እመክሮታለሁ፡፡ እሩቅ ከሆነና በእግር የማይሞከር ከሆነ ካሎት ፀሎት አድርገው በሞተር ከባስ የዘለለ ሳንቲም ከኪስዎ ከሌላ ምን ማድረግ እንዳለቦ ልንገሮ ሄደ አልሄደ ደረስኩ አልደረስኩ ረፈደ አልረፈደ ብለው በሃሳብ ከሚያብዱ ወፍጮ ቤትና ትራንስፖርት ላይ የምትመጣዋ ታፋጯ እንቅልፍ ከመስኮት ላይ ደገፍ ብለው ማስነካት ነው፡፡ ስጋት አይግባዎ፡፡ እስኪጠግቡ ተኝተው  አንድ ሁለት ህልም በላዩ ላይ ጨምረው ተነቃቅተው ይነሳሉ፡፡ እንጂ የማይጠግቡ መስሎት ከመተኛት እንዳይቦዝኑ፡፡ አንባቢ ከሆኑ ደግሞ ታድለዋል በተለይ የሚያነቡት መፅሐፍም ሆነ መፅሄት ልብ አንጠልጣይ ከሆነ ልቦ ለበኋላ ሳይንጠለጠል ጨርሰው የሚናደዱም ከሆነ ተናደው ታሪኩ እርሶ እንደሚፈልጉት ከሆነ ያለቀው ተደስተው ጣጣዎን ጨርሰው ይወርዳሉ ታድያ ልብ ማለት ያለቦት ነገር በዚህ አሰልቺ መንገድ ላይ አሰልቺ ነገር ለማየትም ሆነ ለመስማት እንዳሞክሩ አቅሞት አይችልማና፡፡             ይኸው ቆመናል ከተጨናነቁት መኪናዎች ጋር፡፡ ለዛሬ በእዚህ እንሰነባበትና በክፍል 6 የመጨረሻ የጉዞ ቅኝቴን አብረን እናያለን፡፡                                          ቸር እንሰንብት፡፡ ፀሐይ በየነ

See More

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 12 years ago on December 17, 2012
  • By:
  • Last Modified: December 17, 2012 @ 6:20 pm
  • Filed Under: Ethiopia
  • Tagged With:

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar