www.maledatimes.com እኔ ኢትዮጵያዊ እስላም ነኝ! (ከይመሩ ሙሄ) - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

እኔ ኢትዮጵያዊ እስላም ነኝ! (ከይመሩ ሙሄ)

By   /   December 19, 2012  /   Comments Off on እኔ ኢትዮጵያዊ እስላም ነኝ! (ከይመሩ ሙሄ)

    Print       Email
0 0
Read Time:8 Minute, 0 Second

 ዜግነቴና እምነቴ

የመጣ ከናት ካባቴ፣

ከትውልድ ትውልድ ተወራርዶ፣ የተቀበልኩት አደራ

ሃላፊነት የተጫነብኝ፣ እንዳስተላልፍ በተራ፤

ነውና ማባከን ጊዜ፣ ያልተሰበረን መጠገን መጣር

ለከላሸና ላክራሪ ሴራ፣ እጄን የማልሰጥ የማልበገር፤

እኔ ኢትዩጵያዊ እስላም ነኝ፣ ዜግነቴ የማይጠረጠር

ሃይማኖቴን የማላስደፍር፣

ባህሌ ነው ተባብሮ መኖር

ከክርስቲያን ወገኖቼ ጋር።

አስተዳደጋችንን ሲቃኙት፣ ልዩነቱ የማይታይ ጎልቶ

በመፈቃቀር ተውጦ፣ በመከባበር ተሞልቶ።

ፊደል የቆጠርኩ በአባ

ባቆምም መለዕክተ ሳልገባ፣

ቁንጥጫቸውን ቀምሼ

በኩርኩማቸው ተምሼ

ከአለንጋቸው ተቋድሼ

ከፊደሌ ላይ ዓይኖቼን ሥጌ

ያነበብኩ ድምፄን ከፍ አድርጌ፤

እኔ ኢትዩጵያዊ እስላም ነኝ

ከክርስቲያን ጓደኞቼ ብዙ የጋራ ታሪክ ያለኝ።

ዘንግ አሽለምልሜ፣ አዥጎርጉሬ

በጥምቀት በዓል ጨፍሬ አብሬ

ዙሪያ ገጥመው ሳዱሎቹ፣ ‘ናሆሉ ናሆይ ሆሎሉ’

በተዋበ ዜማቸው ሲሉ፣

ከክርስቲያን ጓደኞቼ

ተጋፍቼ ተሻምቼ

‘ሰኪ በጀግና ሞት’ በመለፈፍ

ሎሚ ያሰካሁ በዘንጌ ጫፍ፤

ታቦት ተከትዬ የነጎድኩ

ሥርዓት ውበቱን እያደነቅኩ፤

ያማኙን ሥሜት ሲነካ፣ የቀሳውስቱ ውብ ዝማሬ

እኔም የረካሁ አብሬ፣

የከበሮአቸው ድምታ

የተዋሃደ ከልቤ ትርታ፣

ፅናፅላቸው ሲቀለባበሥ

ፅናሃሃቸው ሲል መለሥ ቀለሥ

ሚዛን ጠብቆ ሲነዛ ጭሥ፣

አየሩ ሲታወድ በእጣን ከርቤ

የረካሁ በትንፋሼ ስቤ፤

ምን አስለፈው ከኛ እኩል

ምን ያጋፋዋል በኛ በዓል

ያልተባልኩ ያልተነሳሁ ፊት

እኔ ኢትዮጵያዊ እስላም ነኝ፣ ወደኃላም ሆነ ወደፊት።

ጨክና መክና ተፈጥሮ፣ በወቅቱ ሲጠፋ ዝናብ

መርገፍ ሲጀምር እንደቅጠል፣ ሰውና ከብቱ በረሃብ፤

ወይም እናት መሬት ተንቀጥቅጣ

መቆሚያ መቀመጫ ሲታጣ፣

መሄጃ ማምለጫ ሲጠፋ

መሬት በመሬት ላይ ሲደፋ፣

ክርስቲያን ወገኔ ሲማለል

ከፈጣሪው ጋር ሲሸማገል

እያለ ‘ኑሮ! ፈጣሪ ኑሮ!

ምን መዓት አመጣህብን ዘንድሮ!!’

ድምፄን ያሠማሁ አብሬ፣ ከመሃላቸው በመንበርከክ

ምህረት የለመንኩ ከአምላክ፣

ስለሆነ ሕልውናችን ተገምዶ የተሣሠረ

የተጣበቅን የማንቀረፍ፣ አንድነታችን የጠነከረ፣

እኔ ኢትዮጵያዊ እስላም ነኝ

ከክርስቲያን ወገኖቼ፣ አብሮ መኖር የተወሃደኝ።

በቡሄ ያኖጋሁ ጅራፍ

ከኮረብታ ላይ ቆሜ ካፋፍ፣

በግርፊያ የተፋለምኩ፣ ከክርስቲያን አብሮ አደጎቼ

‘የከርሞ ሰው ይበለኝ’ ያልኩ፣ ተተላትዬ ደምቼ አድምቼ፣

‘ቡሄ ና ቡሄ በሉ!’ ያልኩ፣ የሠበሰብኩ ጅምልምል ዳቦ

ከክርስቲያን ጓደኞቼ፣ የተካፈልኩ ሂሣብ ታሥቦ፤

ሌላ መሆን የማልችል ፣እኔ ኢትዮጵያዊ እስላም ነኝ

ያላሠለሠ ጥረት ቢደረግ፣ ከወገኖቼ ማንም አይለየኝ!!

በአዲስ ዘመን መለወጫ፣ በዋዜመ መስከረም አንድ

የፈነጨሁ አብርቼ ችቦ፣ እስኪሆን ድረሥ የዶጋ አመድ

‘ኢዮሃ አበባዬ’ ያልኩ፣ በማስከተል ‘መስከረም ፀባዬ’

‘ዓመት ዐውዳመት’ን ያስተጋባሁ፣ የቀለጠ እልልታዬ!

እኔ ኢትዮጵያዊ እስላም ነኝ፣ ኢትዮጵያ ናት ሀገሬ ቤቴ

ምንጊዜም ኮሪ በባህሌ፣ በታሪኬ፣ በሃይማኖቴ።

የሠላም አኗኗራችን፣ አብነት የተጎናፀፈ

በዓለም የተቀናበት፣ ብዙ አድናቆትን ያተረፈ፣

ከክርስቲያን ወገኖቼ፣ ደሜ ደማቸው የተዋሃደ

ጣምራነታችን ሥር የሠደደ፣

እኔ ማለት እነሱ፣ እነሱ ማለት እኔ

የማልጠፋ ከጎናቸው፣ የማይጠፉ ከጎኔ፣

ኢትዮጵያ ማለት እኛ ባንድ ላይ

እኔ ክፉ ካሰብኩባቸው፣ እራሴን መጉዳት አይሆንም ወይ?!

ስለዚህ ትርጉም የለውም፣ በአሸባሪነት እኔን መክሰሥ

ሠብአዊ መብቴን በመግፈፍ፣ ሕገመንግሥቱን በመጣሥ

ሴራ ጠንሥሰሀል በማለት፣ የሸሪዓ ሕግ ለማንገሥ፤

ኢትዮጵያና የሸሪዓ ሕግ

እንደማይሆኑ ድርና ማግ፣

ጠንቅቄ የማውቅ የገባኝ

የባህሌ ውጤትም የሆንኩ፣ እኔ ኢትዮጵያዊ እስላም ነኝ፤

እስልምናና ዐረብነት፣ ልዩነቱን የማውቅ አሳምሬ

ለኢትዮጵያዊነቴ የምሞት፣ ሃይማኖቴንም አስከብሬ፤

የክርስቲያኑ ወገኔ

ግማሽ አካሉ በመሆኔ

የምኩራራ የምጀነን፣ የምመካ የምኮፈሥ!

እኔ ኢትዮጵያዊ እስላም ነኝ፣ ተጀምሮ እስኪጨረሥ!!!

* * *

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 12 years ago on December 19, 2012
  • By:
  • Last Modified: December 19, 2012 @ 6:26 pm
  • Filed Under: Ethiopia, POEMS
  • Tagged With:

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar