www.maledatimes.com “ዘጠኝ ቁጥር” ክንፉ አሰፋ - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

“ዘጠኝ ቁጥር” ክንፉ አሰፋ

By   /   January 3, 2013  /   Comments Off on “ዘጠኝ ቁጥር” ክንፉ አሰፋ

    Print       Email
0 0
Read Time:21 Minute, 9 Second

በኪም ጆንግ ዘመነ-መንግስት በችጋር እና በእርዛት ይጎሳቆል የነበረ አንድ የሰሜን ኮረያ ወጣት ብቻውን በአደባባይ ወጥቶ የኪም ጆንግ ኢልን መንግስት ይረግማል።

 “የምንበላው የለም! የምንለብሰው የለም!… ታርዘናል፤ ደህይተናል! ኪም ጆንግ ከስልጣን ይውረድ!”…

ወጣቱ ብቻውን ሲጮህና ሲቃወም የተመለከቱ የኮምኒስቱ ፓርቲ የደህንነት አባላት ወጣቱን አፍነው ወስደው፣ ጨለማ ክፍል ውሰጥ ይወረውሩታል። ለሁለት ቀን ያህል በርሃብ ከቀጡት በህዋላም የጥይት ውርጅብኝ በጆሮው ላይ በማጮህ አስፈራርተው ይለቁታል። በእስር ቤቱ ይተኮስ የነበረው እውነተኛው ሳይሆን የልምምድ ጥይት ነበርና በእስረኛው ላይ የስነ-ልቦና እነጂ የአካል ጉዳት አላደረሰበትም።

ወጣቱ ከእስር እንደተለቀቀ ወደ ቤቱ አልተመለሰም። ይልቁንም ቀድሞ ወደተያዘበት አደባባይ እንደገና በመሄድ አሁንም ተቃውሞውን ቀጠለ።

“ቀለሃ እንኳን አልቋል…ጥይትም የለንም! ኪም ጆንግ ይወረድ!”

ኪም ጆንግ ሰሜንዋን ኮርያ በባዶ ሆድ የኒውክለር ባለቤት አደረጋት።

አንባገነን መሪዎች ሁሉ ቅድሚያ የሚሰጡት የራሳቸው ባዶ ክብር እና ዙፋኑ ላይ የመቆየቱ ስልት ላይ እነጂ ስለ ዜጋቸው መራብ እና መራቆት ግድ አይላቸውም።  ለኪም ጆንግ ኮርያን የኒውክለር ባለቤት የማድረጉ ተግባር የኮርያ ኩራት ነው። ለራሳቸው ዜጋ ክብር ሳይሰጡ ለሃገር ክብር የማስብ ግብዝነት!? ይህ እኛም ጋ ያለ አባዜ ነው። ከስምንት ሚሊዮን ህዘብ በላይ በምግብ ገና ራሱን ሳይችል ስለ ተአምራዊው የሁለት ድጅት ኢኮኖሚ እድገት ይነግሩናል።

ሃይለማረያም ደሳለኝ ደግሞ የኢትዮጵያ ህዘብ አሁን ጤፍ መብላት መጀመሩን ነው ሰሞኑን ያበሰሩን።  ሕዝቡ ጤፍ መብላት የጀመረው መካከለኛ የሚባለው የህብረተሰቡ ክፍል ጨርሶወኑ ጠፍቶ ዝቅተኛ ገቢ ካለው ክፍል በተቀላቅለበት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እድገት ላይ ነው።  ያን ምስኪን ህዝብ መለስ ዜናዊ እነዲሁ እንደቀለዱበት አለፉ፤ አሁን ደግሞ እነ…።

በ2011 ኪም ጆንግ 2ኛና የሊቢያዉ ኮ/ል ሙአመር ጋዳፊ ከምድራችን ለመጨረሻ ጊዜ ሲሰናበቱ አለማችን የተሸከመቻቸው አምባገነን መሪዎች ቁጥር ወደ ስምንት ዝቅ ማለቱን አለም-አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ዘግበው ነበር። የመንግስት ስልጣን ጨብጠዉ ሰብኣዊ መብቶችን በመርገጥና የፖለቲካ ጭቆና በማድረስ ላይ ከነበሩት ከስምንቱ ጨካኝና ራስ ወዳድ መሪዎቸ አነዱ የነበሩት አቶ መለስ ዜናዊ ባሳለፍነው የፈረንጆቹ አመት ሲያርፉ የአለማችን አንባገነን መሪዎቸ ቁጥር እንደገና በአንድ ተቀንሷል የሚል ተስፋ በብዙዎች ዘንድ ነበር።

 

 

 

 

 

በአቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ መምጣት በሃገራችን የፍትሃዊ ስርዓት የመስፈን ተስፋ መጣሉ ስህተት እንደነበር አሁን ብዙዎች ይስማማሉ።  ቀድሞውንም ተስፋ የተጣለባችው ያሁኑ ጠቅላይ ሚ/ር ቢያንስ ሲቪል ናቸው፣ ፊደል ቆጥረዋል፤ የእምነት ሰው በመሆናቸው ቢያንስ ተቃዋሚን አያሳድዱም፣ ዜጎችን አይገደሉም፣ አያስሩም፣ ፕሬሱን አያፍኑም…  ከሚል የተሳሳተ ግምት የተነሳ ነበር። ግና በህ.ወ.ሓ.ት. ካድሬዎች ከፊትና ከሗላ ተከበው ያሉ አቅመ-ቢስ ግለሰብ ለውጥ ያመጣሉ ብሎ ማሰቡ በእርግጥም የዋሕነት ነበር።

የአቶ መለስ ዜናዊ ከዚህ አለም በሞት መለየት በህ.ወ.ሓ.ት. ካድሬዎች ቁርጥ መሆኑ እንደተረጋገጠ፤ አቶ በረከት ስምዖን ኤስ.ቢ.ኤስ. አውስትራሊያ ራዲዮ ላይ ቀርበው አነድ በወቅቱ ግራ ያጋባ መግለጫ መስጠታቸው ይታወሳል። “…መለስ በቅርብ ጊዜ ወደ ስራው ይመለሳል።” ነበር ያሉት አቶ በረከት። የአቶ መለስ ወደ ‘ዙፋን’ መመለሻ ቀንም ተቆርጦ ነበር በአቶ በረከት የተነገረው። ታዲያ የዚህ መግለጫ ቅኔ ሰምና ወርቅ በወቅቱ ለብዙዎች ቱረጁማን ሳያስፈልገው አልቀረም ነበር።  የቀድሞው ጠቅላይ ሚ/ር በተባለላቸው ቀን ወደ ስራቸው አልገቡም። እንዲያውም የእረፍታቸው ዜና አስቀድሞ እንዲታወጅ ተደረገ።
ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገሮች ላይ የምርምር መጣጥፎችን የሚያቅርቡት ሚስተር ሬኔ ለፎርት “መለስ ከመቃብርም ሆነው እየገዙ ነው። ይህ ግን እስከመቼ ይዘልቃል?” ሲሉ የጻፉት ጥናታዊ መጣጥፍ የአቶ በረከት አባባልን በትክክል ገልጾታል።

በአቶ መለስ ዜናዊ  መቀመጫ ላይ ጉብ ብለው የህ.ወ.ሓ.ት.ን የፖለቲካ ድራማ በዋና ተዋናይነት እነዲጫወቱ የተመረጡት አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ – አቶ መለስን ለመተካት ሳይሆን ለማስመሰል ብዙ ጊዜ አልወሰደባቸውም። ከእንግሊዝኛ አነጋገራቸው በስተቀር ሁሉንም የአቶ መለስ ባህርይ ተላምደውና ተላብሰው ብቅ አሉ።  አሁንም “መለስ ዜናዊ አልሞተም!’  የሚሉ የህ.ወ.ሓ.ት. ካድሬዎች ሲያጋጥሙን እየቃዡ ነው ልንል እንችል ይሆናል። ካድሬዎቹ ግን አልተሳሳቱም።

 

መለስ አልሞቱም። የሃይለማርያምን ስጋ ለብስው ተመልሰዋል።  እለት – ተለትም ሳይበረዙና ሳይደለዙ እያየናቸው ነው።

የመለስ ዜናዊ ውርስና ቅርስ ሳይበረዝ.፤ ሳይቀለስ ተግባራዊ ለማድረግ ቃል መግባታችው በተሰማ በዙም ሳይዘገይ  “የመለስ ዜናዊን አጀነዳ ለማስፈጸም እንጂ የራሴ የሆን ሃሳብም ሆነ እቅድ የለኝም።” ሲሉ እቅጩን ተናግረዋል አቶ ሃይለማርያም። ይህ ንግግራችው ቃል ብቻ ሆኖ አልቅረም። በተግባርም የአቶ መለስ ኮፒ ሆነው ተገኝተዋል። ከፓረላማ አቀማምጥ እስከ ድንፋታቸው – ከውሃ አጎነጫጨት እስከ ፖልቲካ ፌዛቸው … ሁሉንም ኮፒ አድርገው ሲያበቁ በህዝቡ ላይ መቀለዳቸውን ቀጥለውበታል። የፌዙን ስታየል እንኳን አልቀየሩትም።
“ስኳር የተወደደው ሕዝቡ ስኳር መጠቀም ስለጀመረ ነው።” ብለው ነበር ሟቹ መሪ በህዝቡ ላይ የቀለዱት። የባለ ራእዩን መሪ ጉዳይ ለማሰፈጸም እንጂ የራሴ የሆን ሃሳብም ሆነ እቅድ የለኝም ያሉን አቶ ሃይለማረያም፤ “የጤፍ ዋጋ የጨመረው ሕዘቡ ጤፍ መብላት ስለጀመረ ነው።” ብለው ቢቀልዱ ታዲያ ምንም አይደንቅም።

“በኢትዮጵያ የፖለቲካ እስረኛ የለም!”  ሲሉም በፓረላማ ተደምጠዋል።  በአቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ የፓረላማ ድንፋታ የተበሳጩ ካሉ የዋሆች መሆን አለባቸው። በኦቶ መለስ ዘመን ለታማኝ የፓርላማ አባላት የተመረጡ ጥያቄዎች ይታደላሉ። አሁን ግን ጥያቄዎቹ ከነ መልሱ ነው ለአቶ ሃይለማርያም የሚዘጋጁላቸው።

 

 

 

“የሰንጋ ዋጋ ለምን በእጥፍ ጨመረ?” ብሎ አንድ ደፋር የፓርላማ አባል ቢጠይቃቸው ኖሮ፤ አቶ ሃይለማርያም ምንም ሳያንገራግሩ፤ “ሕዘቡ በነፍስ-ወከፍ ሰንጋ ጥሎ መብላት ስለጀመረ ነው።” እንደሚሉ ጥርጥር አይኖርም። የመኪና ዋጋ ለምን ጣራ እንደወጣ ቢጠየቁም፣ ያልተጻፈ የማያነብቡት ጠ/ሚ፣  “የኢትዮጵያ አርሶ አደር መኪና መንዳት ስለጀመረ ነው።” ሊሉን ይችላሉ።

 

ጤፍ በልቶ የማያውቀው ሕዘብ አሁን መብላት ስለጀመረ ነው ሲሉ አፌዙ?  ይህ በ17ኛው ክፍለ-ዘመን የነበረችውንና በሗላም አብዮቱ የበላትን የፈረነሳይ ንግስት የማሬ አነቶኔትን ፌዝ ያስታውሰናል። ታላቁ የፖለቲካ ፈላስፋ ጂን-ጃክዌስ ሩሶ ስለዚህች ታሪካዊ ንግስት ሲጽፍ፤ የፈረንሳይ ገበሬዎች ዳቦ አጣን ማለታቸውን ስትሰማ ንግስት ማሬ አነቶኔት ‘ለምን ታዲያ ኬክ አይበሉም?’ ማለቷ አነባገነን መሪዎች ከሕዝቡ ምን ያህል እንደሚርቁ አመላክቷል። የኛዎቹም ገዢዎች ከሰፊው ድሃ ህዘብ በእጅጉ ስለሚርቁ ከታች ያለውን እውነታ ከራሳቸው የኑሮ ሁኔታ ጋር ያመሳስሉታል።

 

“ጠቅላይ ምኒስትሩ” በራሳቸው አንደበት የሰው አጀንዳ የተሸከምኩ ባለ አደራ ነኝ ካሉ በሗላ ምንም አዲስ ነገር መጠበቅ አይገባም።  ልክ አንድ ደራሲ በምናቡ የፈጠረውን ገጸ-ባህርይ እንዲላበሱ ተደርገው እንደሚቀረጹ እንደ ካርቱን (አሻንጉሊት) ፊልም ነው ሰውየውን ማየት ያለብን።

 

ይልቅ ‘የመለስ ራዕይ’ እና ‘የመለስ ቅርስ’ የሚሉት ነገር ነው አሁን ህዝቡን እያሰለቸ የመጣው።  በኢ.ቲ.ቪ. እነደሚያሳዩን ከሆነ የአቶ መለስ ቅርስ፣ ውርስ እና ራዕይ እጅግ በጣም ብዙና መጠነ-ሰፊም ነው። የመንገድ እና ህንጻ ግንባታ፣ የአባይ ግድብ፣ ኮብል ሰቶን … የመሳሰሉትን የዓለም ባነክ እዳ ፐሮጀክቶች የመለስ ቅርሶችና ራዕዮች ናቸው ቢባሉ ጥቂቶችንም ቢሆን ሊያሳምኑ ይችሉ የሆናል።  ነገር ግን የአክሱም ሃውልት በየት አድረጎ መጥቶ የመለስ ቅርስ እና ራእይ ሊሆን እንደሚችል ደጋፊዎችንም ሳይቅር ግራ ሳያጋባ የሚቀር አይመስልም።  በአቶ በርከት የሚመሩት ብሄራዊ መገናኛ ብዙሃኑ በዚህም  አያበቁም። የላሊበላ ቤተ ክርስትያናት፣ የፋሲለደስ ግንብ፣ ታሪካዊው የሶፈመር ዋሻዎች… ወዘተ ከባለ ራእዩ መሪ ጋር ተቆራኝተው ለህዝብ እንዲቅርቡ እየተደረገ ይገኛል።ዛሬ ደግሞ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ለአፍሪካ ዋንጫ ማለፍ የባለ ራእዩ መሪ ስራ ውጤት እንደሆነ ነው እየተነገረ ያለው።

 

እ.ኤ.አ. በ 1970ዎቹ ካምቦዲያ በአምባገነኑ ፖል ፖት እጅ ስር ወድቃ በነበረበት ዘመን፤ የካምቦዲያ ህዘብ ሃይማኖቱ፣  ፍቅሩ፣  ታዛዥነቱና ከበሬታው ‘አንካር ፓደቫት’ ተብሎ በሚጠራው የካመር ሩዥ ቡድን ብቻ እንዲሆን የጠበቀ መመርያ አውጥተው እንደነበር ይታወሳል።

 

ካመር ሩዥ በካምቦዲያ ህዝብ ጫንቃ ላይ በሃይል ተፈናጥጦ ሲያበቃ “ፖል ፖት የሁላችሁም እናት እና አባት ነው። ከሱ ሌላ ማፍቀር ክልክል ነው።” የሚል መመርያ ነበር ያወጡት።

ዛሬ የኢትዮጵያ ሁለመና መለስ ዜናዊ ሆነዋል። ለፈጣሪ ብቻ የሚሰጠው ዘላለማዊ ክብርንም በአቶ ሃይለማርያም በኩል ተችረዋል። ለነገሩ ለነአቶ በረከት የመኖር እና ያለመኖር ዋስትና የሚሆን በመገናኛ ብዙሃን የሚለቀቅ ፕሮፓጋንዳ ውጭ አንዳች ነገር ሊኖር አይችልም።

 

የፖለቲካ አቡጊዳን የቆጠረ ማንም ሰው መለስ ዜናዊን ከቶውንም ባለ ራዕይ መሪ ሊያደርጋቸው አይችልም።  የጆርጅ ኦርዌልን “Animal Farm” እና “Ninety Eighty Four” መድብል አኝከው ሲያበቁ ይህንን ጽንሰ-ሃሳብ በኢትዮጵያ ላይ በትክክል ለመተግበር ከመሞክር ውጭ በህይውት ዘመናቸው አቶ መለስ ምንም ራእይ አልነበራቸውም። ይህንን ወደፊት ታሪክ በሰፊው የሚያወሳው ጉዳይ ይሆናል።

 

ለአሁን ግን በአቶ ሃየለማርያም ደሳለኝ ላይ ሰሞኑን በተለቀቀች አነዲት ቀልድ ጽሁፌን ላብቃ።

 

 

አቶ ሃየለማርያም ደሳለኝ በሽተኞችን ለመጠየቅ የአእምሮ በሽተኞች ሆስፒታል ይሄዱና ከታካሚ በሽተኞች ጋር መነጋገር ይጀምራሉ።

 

“አነተ ማን ትባላለህ?” አቶ ሃየለማርያም ደሳለኝ አንዱን ታካሚ ጠየቁ፣

 

“ስምንት ቁጥር። ” የአእምሮ  በሸተኛው መለሰ።

(በሸተኞቹ ስማቸውን ስለማያስታውሱ በቁጥር ነውና የሚታወቁት)

 

“በጣም ጎብዘ ልጅ፣ እኔንስ ታውቀኛለህ?” አቶ ሃየለማርያም ደሳለኝ እንደገና ጠየቁት፣

 

“ዘጠኝ ቁጥር!”  አላቸውና አረፈው።

 

ራስን መካድና ሌላን ለመምሰል የመሞከር አባዜን ከአእምሮ መታወክ በሽታ ጋር የሚያመሳስሉ ጥቂቶች አየደሉም።

 

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 12 years ago on January 3, 2013
  • By:
  • Last Modified: January 3, 2013 @ 11:59 pm
  • Filed Under: Ethiopia
  • Tagged With:

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar