www.maledatimes.com የባቡሩ ሃያ ምዕራፎች - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

የባቡሩ ሃያ ምዕራፎች

By   /   January 6, 2013  /   Comments Off on የባቡሩ ሃያ ምዕራፎች

    Print       Email
0 0
Read Time:24 Minute, 36 Second
የባቡሩ ሃያ ምዕራፎችFEATURED
 WRITTEN BY  

  • መኪኖች በአዲስ አበባ መንገዶች ተቀጣጥለው መቆም ከጀመሩ ሰነባብተዋል፡፡ ታክሲዎች በመንገድ ሥራ እያሳበቡ የራሳቸውን ታሪፍ ማውጣትና ማስከፈል ካመጡም ረፈድ ብሏል፡፡

የሥራ መግቢያና የስብሰባዎች መጀመርያ ሰዓት በስምምነት ወደኋላ መሸጋሸግ ይታይባቸው ከያዘ ውሎ አድሯል፡፡

ይህ ሁሉ ከመንገድ ቁፋሮዎች ጋር እየተያያዘ በመንገድ እንደቆሙ ማርፈድ ስለበዛ፣ የአዲስ አበቤውን ሆደ ሰፊነት በግንባታ ያሰለቹት ቻይኖቻችንና መንግሥት ይማጠናሉ፡፡ የከተማው ነዋሪ ለእስካሁኑ ትዕግስቱ ምስጋና ሲቸረው መስማት፣ በየግንባታ ቦታው የተለጠፉ የምስጋና መልዕክቶችን ማንበብ ወግ ሆኖ ይታያል፡፡

ከግንባታዎቹ አውራ የሆነው የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ትራንዚት ፕሮጀክት ይጠቀሳል፡፡ ከሁለት ዓመት በኋላ ይጠናቀቃል ተብሎ የሚጠበቀው ይህ ፕሮጀክት በዚህ ዓመት ስድስት ወራት ሥራው የሃያ ምዕራፍ ያህል (20 በመቶ) የተጓዘበትን ሥራ በማስመልከት ባለፈው ሐሙስ፣ ታኅሳስ 15 ቀን 2005 ዓ.ም. ለጋዜጠኞች የጉብኝት ጊዜ ተሰናድቶ ነበር፡፡ በመስክ የባቡሩ የሥራ ሒደት ምን ደረጃ ላይ እንዳለ ለማሳየት ያለመ ነው፡፡

ከመነሻው እስካሁን
በአዲስ አበባ የተንሰራፋውን የትራንስፖርት ችግር ይፈታል ብሎ መንግሥት በተደጋጋሚ ሲናገርለት የቆየው የቀላል ባቡር ትራንስፖርት በይፋ ሥራው እንደሚጀመር ያሳወቀው በ2001/2002 ዓ.ም. ነበር፡፡ ያገባቸዋል፣ ይመለከታቸዋል የተባሉ መሥርያ ቤቶች ሁሉ እንዲያውቁት ብቻ ሳይሆን ዝግጅት እንዲያደርጉበት ተነግሮ ሥራው መጀመሩን የሥራው ኃላፊዎች ይናገራሉ፡፡ በኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ደቦ ቱንካ እንዳስታወቁት፣ ለፕሮጀክቱ መንግሥት 475 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልገው፣ ይህንንም ገንዘብ ከቻይና የኤክስፖርት ኢምፖርት (Ex-Im) በብድር ማግኘቱን ያስታወሱ ሲሆን፣ ለቅድሚያ ክፍያው መንግሥት 15 በመቶ (72 ሚሊዮን ዶላር ገደማ) በመክፈሉ ፕሮጀክቱ የገንዘብ ችግር እንደሌለበት ተናግረዋል፡፡ ከአምናው የጥር ወር ጀምሮም እስከ ጥር ወር 2007 ዓ.ም. ባለው ጊዜ መሠረት ሙሉ በሙሉ የሥራው ኮንትራት ተሰጥቶት ሥራውን የጀመረው የቻይና ተቋራጭ ሲአርኢሲ ነው፡፡ በሦስት ዓመት ውስጥ እንዲጠናቀቅ የሚጠበቀው ይህ ፕሮጀክት፣ አንዱን ዓመት ተጉዞ አሁን ሁለት ዓመታትን ይጠብቃል፡፡ ኮንትራክተሩ ሙሉ ጣጣው ያለቀለትን ሥራ ለመንግሥት ያስረክባል (ውላቸው ‹‹Turnkey›› በተሰኘው ማዕቀፍ ስለሆነ ዲዛይን ሠርቶ፣ ገንብቶ ቁልፍ የማስረከብ ዓይነት ነውና)፡፡

የባቡሩ መስመሮች በአራቱ ዋና ዋና አቅጣጫዎች ማለትም በሰሜን ደቡብ፣ በምሥራቅ ምዕራብን ይዞ አዲስ አበባን በ34 ኪሎ ሜትር ክልል ውስጥ እንደሚሸፍን ይጠበቃል፡፡ ከሰሜን ወደ ደቡብ አቅጣጫ ያለው የባቡሩ መስመር መነሻውን ዳግማዊ ምኒልክ አደባባይ አድርጎ፣ አውቶቡስ ተራን (ሰባተኛን-አብነትን) ይዞ ወደ መስቀል አደባባይ ይዞራል፡፡ ከመስቀል አደባባይ ወደ ደቡብ አቅጣጫ ሲያቀናም ቃሊቲን መዳረሻው ያደርጋል፡፡ ይህ የሰሜን ደቡብ የባቡሩ መስመር በጥቅሉ 16.9 ኪሎ ሜትር ይሸፍናል፡፡ ከምሥራቅ ወደ ምዕራቡ አቅጣጫ የሚዘረጋው መስመር ርዝመቱ 17.35 ኪሎ ሜትር ነው፡፡

ከሲኤምሲ አያት መንደር በመገናኛ አድርጎ መስቀል አደባባይ ይደርስና ጦር ኃይሎችን ይዘልቃል፡፡ በመካከሉ ግን ከመስቀል አደባባይ እስከ ልደታ ባለው ርቀት ሁለቱ መስመሮች የ2.6 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የጋራ ሐዲድ ይጠቀማሉ፡፡ የሰሜን ደቡቡ ከላይ ከጊዮርጊስ መጥቶ በአውቶቡስ ተራ ዞሮ በልደታ በኩል መስቀል አደባባይ ሲመጣ፣ የምሥራቅ ምዕራቡ ከሲኤምሲ አያት መንደር መገናኛን ይዞ ወደ መስቀል አደባባይ መጥቶ የሚገናኙበት የጋራ ሐዲድ ከስድስት ሜትር በላይ ከፍታ ባለው የባቡር ድልድይ ላይ የሚገነባ ነው፡፡

የባቡሩ ሐዲዶች አንዴ መሬት ለመሬት ሌላ ጊዜም በድልድይ ላይ እንደሁም በዋሻ ውስጥ የሚዘረጉ ናቸው፡፡ ከአያት እስከ እስጢፋኖስ ባለው ርቀት ባቡሩ መሬት ለመሬት (13 ኪሎ ሜትር ያህል)፣ በ12 ሜትር ስፋት፣ በሁለት አቅጣጫ ሲጓዝ፣ እንደቦታው ልዩነት ከፍታውም እየተለያየ ከእስጢፋኖስ እስከ ልደታ በድልድይ ላይ ፉርጎዎቹን ያግተለትላል፡፡ ከምኒልክ አደባባይ እስከ ሀብተጊዮርጊስ ድልድይ በዋሻ ውስጥ ይጓዝና ከሀብተጊዮርጊስ እስከ አንዋር መስጊድ ባለው ርቀት ደግሞ ድልድይ ላይ ይወጣል፡፡ ከእነዚህ መንገዶች በተቀረው ላይ መሬት ለመሬት በ10 ኪሎ ሜትር ርቀት እንደሚጓዝ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚውም፣ የፕሮጀክቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ በኃይሉ ስንታየሁ ተናግረዋል፡፡

ከሃያ ምዕራፎች አንዳንዶቹ
በ2002 ዓ.ም. የፀደቀውን የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ተከትሎ የመንገድ አካፋዮችን ይዞ የሚዘረጋው የባቡሩ መስመር፣ 22 የባቡር ጣቢያዎችን ይዞ መንገደኞችን እንደሚያስተናግድ የምሥራቅ ምዕራቡን መስመር ከሚመሩበት የአያት አካባቢ ካምፓቸው ሆነው የገለጹት አቶ በኃይሉ፣ መንገደኞች በመሬት፣ በድልድዮች ላይና በዋሻ ውስጥ የሚስተናገዱባቸው ባቡር ጣቢያዎችም እንደሚገነቡ አስረድተዋል፡፡ በመሬት ላይ የሚገነባው ጣቢያ ወይም ፌርማታ ተሳፋሪዎች ከመንገድ ማቋረጫው በአራት አቅጣጫ ወደ ባቡር ጣቢያ ይመጡና ወደሚፈልጉት ይጓዛሉ፡፡ በድልድይ ላይ ካለው የባቡር ሐዲድ ስምንት ያህል ባቡር ጣቢያዎች ይገነባሉ፡፡ ወደእነዚህ ጣቢዎች መንገደኞች እንዲወጣጡ፣ ደረጃዎች፣ አሳንሰሮችና መሰል ደጋፊዎችን ይጠቀማሉ፡፡ አካል ጉዳተኞች፣ ሕፃናትና አቅመ ደካሞች ታስበዋል ተብሏል፡፡ በመሬት ውስጡ የዋሻው ጣቢያም ከአሳንሰር በተጫማሪ የአደጋ ጊዜ መውጫዎችን ጨምሮ የአየር ማቀዝቀዣም ይኖሩታል፡፡

የባቡሩ ፉርጎዎች ወይም መኪኖች ለመጀመርያው ዙር 41 ያህል ከቻይና እንደሚመጡ ይጠበቃል፡፡ የባቡሩ ሁለተኛው ምዕራፍ ተስፋ የተጣለውው ግን የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን የሚገጣጥማቸው መኪኖች ላይ ነው፡፡ የቀላል ባቡሩ መኪኖች (ሦስቱ በአንድ ላይ የተያያዙ ይመስላሉ) 64 መቀመጫዎች ሲኖሯቸው፣ በአንድ ካሬ ሜትር ስፋት ላይ እስከ ስድስት ሰዎች እንዲያቆሙ ይታሰባል፡፡ በዚህ ስሌት መሠረት በአንድ ጊዜ ከ270 ሰዎች በጠቅላላው ማጓጓዝ ይችላሉ፡፡

የአያት ሲኤምሲ ግንባታ ሥፍራ ከፍተኛውን ክፍል ይዞ ከአያት አደባባይ እስከ መገናኛ ድረስ ባቡሩ በመሬት ለመሬት ይጓዛል፡፡ ከመገናኛ አደባባይ በውስጥ በኩል፣ በ22 ማዞርያ አደባባይ ሥር ሾልኮ በኡራኤል ቤተ ክርስቲያን አደባባይ ሥር አድርጎ እስከ እስጢፋኖስ ቤተ ክርስቲያን በመሬት ላይ የሚመጣበት ይህ የምሥራቅ ምዕራብ ባቡር መስመር ነው፡፡ ከእስጢፋኖስ እስከ ልደታ ኮካ ኮላ ድረስ በድልድይ ላይ ያቀናና እስከጦር ኃይሎች በመሬት ላይ ይጓዛል፡፡ ከአያት አደባባይ ጀምሮ የመሬት ቁፋሮ፣ የአፈር ሙሊት፣ የፍሳሽ ማስወገጃና የማገጃ ግንብ ሥራዎች እየተካሄዱ ይገኛሉ፡፡ የሲቪል ግንባታ ከሚጠይቀው 32 ኪሎ ሜትር ርዝመት ውስት በ12 ኪሎ ሜትሩ ላይ ሙሉ ሥራ መጀመሩን አቶ በኃይሉ አያት አደባባይ ላይ ቆመው ገልጸዋል፡፡ እስከ 30 ሜትር ጥልቀት ቁፋሮ የሚደረግበት፣ በዋሻ ውስጥ ባቡሩ የሚያልፍበት የአራዳው ባቡር መስመር የአርማታ ሥራዎቹን ወደማከናወኑ የተቃረበ ሲሆን፣ በ15 ሜትር ጥልቀት እስካሁን የተካሄደው ቁፋሮ፣ ማዘጋጃ ቤቱን፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያንንም ሆነ የአፄ ምኒልክ ሐውልትን እንዳያዛባ በሚያደርግ የግንባታ ሒደት እየተካሄደ መሆኑ ተገልጿል፡፡ ዳርና ዳሩ በአርማታ ብረትና በሲሚኒቶ እየተገረፈ አፈር እንዳይናድ ጥበቃ እንደሚደረግ አቶ በኃይሉ ያስረዳሉ፡፡

በመስቀል አደባባይ የባቡሩን ድልድዮች የሚሸከሙ ምሰሶዎችን የሚያጠናክሩ አቃፊዎች እየተገነቡ ይገኛል፡፡ ጥልቀታቸው  እስከ አስር ሜትር በአማካይ እየተቆፈረ ዙርያቸውን በአርማታ ብረትና በሲሚንቶ የተገነቡት የምሰሶ አቃፊዎቹ ግንባታ እንዳበቃም የምሰሶ ተከላው እንደሚጀመር ተገልጿል፡፡

በአንድ ሰዓት በአራቱም አቅጣጫ በድምሩ ከ60 ሺሕ በላይ ተሳፋሪዎችን የሚያስተናገዱት 41 የባቡር ፉርጎዎች፣ በሰዓት 70 ኪሎ ሜትር የመጓዝ አቅም አላቸው፡፡ በኤሌክትሪክና በባቡር ሞተር የሚታገዘው ጉዟቸው፣ ተሳፋሪን የሚያስተናግዱት በኤሌክትሮኒክስ ካርድ አማካይነት ይሆናል፡፡ ተሳፋሪው ለሚጓዝበት ርቀት ወደባቡሩ ሲሳፈርም ሆነ ሲወርድ፣ ካርዷን ወደተዘጋጀላት መሣርያ እያስነካ የታሪፉን መጠን አስቆርጦ ይጓዛል፡፡ በእያንዳንዱ 600 ሜትር ርቀት የባቡር ጣቢያዎች የሚኖሩ ሲሆን፣ ከስድስት ደቂቃ ላልበለጠ ጊዜም ተሳፋሪዎች ተራ ጠብቀው ወደሚፈልጉበት አቅጣጫ በባቡር እንደሚጓዙ አቶ በኃይሉ አስታውቀዋል፡፡

አንዳንድ ሥጋቶች 
ፕሮጀክቱን በአማካሪነት የሚቆጣጠረው የስዊድኑ ስዊሮድ ኩባንያ ሲሆን፣ ከሠራተኛ ደኅንነት ጀምሮ ፕሮጀክቱ በጊዜ ሰሌዳው መሠረት እየተከናወነ ስለመሆኑ ቁጥጥር ያደርጋል፡፡ የኩባንያው ተቆጣጣሪ መሐንዲስ አቶ ኢዮብ ተሰማ እንዳስታወቁት፣ በእስካሁኑ የፕሮጀክቱ ጉዞ የታየ አሳሳቢ ችግርም ሆነ መጓተት አልተከሰተም፡፡ በሠራተኞችና በኅብረተሰቡ ላይም የደረሰ አደጋም ሆነ ጉዳት ሳይኖር እየተካሄደ እንደሚገኝና ከ15 እስከ 30 ሜትር ጥልቀት የሚደርስ ቁፋሮ ያለምንም አደጋ መጠናቀቁ የግንባታ ጥራትን መሠረት አድርጎ ስለተሠራ እንደሆነም አስታውቀዋል፡፡

ነገር ግን በአራዳው የዋሻ ቁፋሮ ሲሳተፉ ከነበሩ ሠራተኞች አንዳንዶቹ በአደጋ መከላከያ ጭምብሎችና የእጅ ጓንቶች እንዲሁም በተገቢው መጫሚያና አልባሳት የማይታገዙ ከመሆናቸው ባሻገር ለቆዳ መቁሰል የተጋለጡም ይገኙበታል፡፡ የደመወዝ ክፍያ በጊዜው የማይፈጸምላቸው የአራዳው ምድብ አንዳንድ ሠራተኞችም ታይተዋል፡፡ የደመወዝ ችግር በመስቀል አደባባዩ ግንባታም ተንፀባርቋል፡፡ ያነጋገርናቸው አንዳንድ ሾፌሮችም የገና በዓልን ያለደመወዝ ለማሳለፍ ሥጋት ውስጥ የወደቁበት አጋጣሚ ተከስቷል፡፡ ለሁለት ሳምንት ያህል ደመወዝ ሳይከፈላቸው በመዘግየቱ ቅሬታቸውን የገለጹት ሠራተኞቹ፣ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ኃላፊዎች ቅሬታቸውን ሰምተውታል፡፡ ሠራተኞቹ ከቻይኖቹ ይልቅ ጣታቸውን ባስቀጠራቸው ኤጀንሲ ላይ ቀስረዋል፡፡ የፕሮጀክቱ ኃላፊ አቶ በኃይሉ ምንም እንኳ እስካሁን እንዲህ ያለውን ነገር ከዚህ በፊት እንዳልተመለከቱትና የቀረበላቸውም ቅሬታ እንደሌለ ቢገልጹም፣ እንዲህ ያሉት ጉዳዮች በቸልታ እንደማይታለፉ አሳስበዋል፡፡

ፕሮጀክቱ በታሰበለት የጊዜ ሰሌዳ እንደሚጠናቀቅ ተቆጣጣሪ መሐንዲሱም ሆኑ የፕሮጀክቱ ሥራ አስኪያጅ እንዲሁም ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚው ይናገራሉ፡፡ የወሰን ማስከበር፣ የማሳለጫ ግንባታዎች አለመጀመር፣ ከለገዳዲ ግድብ በመገናኛ በኩል ወደከተማይቱ የሚዘልቀው የውኃ መስመር አለመነሳት (በስምንት ወራት እንዲነሳ ታስቦ ወደ አሥር ወር መዝለቁ) ዋና ዋና ሥጋቶች ናቸው፡፡ በሜክሲኮ፣ በቄራ መገንጠያ፣  በልደታ፣ በኡራኤል፣ በ22 ማዞርያና በመገናኛ መስመሮች ላይ ለተሽከርካሪዎችና ለባቡሩ ማሳለጫ እንዲሆኑ የሚገነቡ ናቸው፡፡ የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን ይህ ሥራ የሚመለከተው ቢሆንም እስካሁን የየትኛውም ማሳለጫ ግንባታ አልተጀመረም፡፡

እነዚህን ሥጋቶች የሚጋራው የቻይናው ኮንትራክተር China Railway Group Limited (CREC)፣ የተሰጠው የፕሮጀክት ማጠናቀቂያ ጊዜ አጭር መሆኑን ገልጾ፣ እንዲህ ያሉ እክሎች ባልተፈቱበት ወቅት ፕሮጀክቱን በተባለው ጊዜ ለማጠናቀቅ ከባድ እንደሚሆንበት ያስታወቀው፣ በምክትል የፕሮጀክት ኃላፊው ሳይ ኩዊንሀው በኩል ነበር፡፡ ይህንን ሥጋት በተወሰነ ደረጃ ኮርፖሬሽኑ እንደሚያውቀው የገለጹት አቶ በኃይሉ፣ ሆኖም በተባለው ጊዜ ከመጠናቀቅ ወደኋላ እንደማያደርገው ገልጸዋል፡፡

እንዲህ እየሆነ እስካሁን 20 በመቶው ጠቅላላ የፕሮጀክቱ ሥራ የተጠናቀቀው የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ፕሮጀክት፣ በመጪዎቹ ስድስት ወራት ውስጥ ቀሪውን 20 በመቶ ሥራ አጠናቅቆ የበጀት ዓመቱን 40 በመቶ ሥራ ያገባድባል፡፡ በታሰበው መንገድ መጓዝ ከቻለ ደግሞ ከሁለት ዓመት በኋላ ተጠናቅቆ ለሕዝብ አገልግሎት ክፍት ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 12 years ago on January 6, 2013
  • By:
  • Last Modified: January 6, 2013 @ 3:48 pm
  • Filed Under: Ethiopia
  • Tagged With:

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar