www.maledatimes.com ‹‹ተበቺሣ››በብርሃኑ ተዘራ - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

‹‹ተበቺሣ››በብርሃኑ ተዘራ

By   /   January 6, 2013  /   Comments Off on ‹‹ተበቺሣ››በብርሃኑ ተዘራ

    Print       Email
0 0
Read Time:24 Minute, 24 Second
 ‹‹ተበቺሣ››
‹‹ተበቺሣ››
02 JANUARY 2013 WRITTEN BY  

‹‹ተበቺሣ››

  • ብዙዎች በብርሃኑ ተዘራ ከሚለው ይልቅ “ላፎንቴን” በሚል ስያሜ የሚያውቁት ብርሃኑ ተዘራ ሙዚቃን የጀመረው በቀበሌ ኪነት ቡድን ውስጥ በመዝፈን ነው፡፡

ለ17 ዓመታት ያህልም ታደለ ሮባና ብርሃኑ የማይነጣጠሉ ሙዚቀኞች የሚል ስያሜ አትርፈው ነበር፡፡ ከዓመታት በፊትም ነበር የየብቻቸውን መንገድ በመምረጥ በግል ነጠላ ዜማዎቻቸው ብቅ ብቅ ማለትም የጀመሩት፡፡ በዚህም ብርሃኑ “ያምቡሌ፣ አንበሳው አገሳ፣” የመሳሰሉ ሙዚቃዎችን በመዝፈን በቀላሉ አድማጭ ጆሮ ውስጥ መግባት የቻሉና የተወደዱ ዘፈኖችንም መሥራት ችሏል፡፡

ለሙዚቃ ሕይወቱም ሆነ ለዜማ አወጣጡ የድቁና ህይወቱ የተወሰነ አስተዋፅኦ እንዳደረገለት የሚናገረው ብርሃኑ ሰሞኑን “ተበቺሣ” የሚል አዲስ አልበሙን በአዲስ ዓይነት የአዘፋፈን ሥልት ለገበያ አቅርቧል፡፡ ይሄ አልበም የሁለት አሥርት ዓመታትን የሙዚቃ ጉዞ ዕድገት፣ የዕድሜ ለውጥ እንዲሁም ብስለት ያሳየ እንደሆነ ብርሃኑ ያምናል፡፡ አልበሙን በተመለከተ ከጥበበሥላሴ ጥጋቡ ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡

ሪፖርተር፡- አልበምህ “ተበቺሣ” የሚል መጠሪያ ተሰጥቶታል ምን ማለት ነው?

ብርሃኑ፡- “ተበቺሣ” ኦሮምኛ ቃል ሲሆን በቀጥታ ሲተረጐም አጫዋች ማለት ነው፡፡ ዘፈኑን የሠራነው ወሎ (ከሚሴ) አካባቢ በሚጫወቱት መንገድ ነው፡፡ ከሚሴ አካባቢ የኦሮሞና የአማራ ባሕል የተቀላቀለበት ነው፡፡ ዘፈኑ የወሎን ልጅ የሚያወድስ ዘፈን ሲሆን ለየት ባለ መልኩ ኦሮምኛ ራፕም ተካትቶበታል፡፡

ሪፖርተር፡- በሙዚቃው ብዙ ዓመት ቆይተሃል እናም በዓመታት ውስጥ ያለህን ለውጥ በመመልከት ወደ አገር ባሕል ዘፈኖች የመጠጋት ነገር አሳይተሃል ይባላል? ይህን አስተያየት እንዴት ትመለከተዋለህ?

ብርሃኑ፡- ሁልጊዜም ዘፈን እንደየዘመኑ ይሄዳል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ እድሜ መስተዋት ነው፡፡ እኛ ሙዚቃ ከጀመርን ከ17 ዓመት በላይ ሆኖናል፡፡ ከታደለም ጋር ላፎንቴን በሚል ስምም ስንሠራ ረጅም ጊዜ ሆኖናል፡፡ የመጀመሪያ ካሴታችንን በ1988 ዓ.ም. ነው ያወጣነው፡፡ ያኔ እንጫወት የነበረው የዱሮ ዘፈኖችን በአዲስ መልክ በማቀናበር ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ደግሞ ወደየራሳችን ሥራዎች መጥተን አራት አልበሞችን አውጥተናል፡፡

በወቅቱ እንጫወተው የነበረው አዳዲስ የአዘፋፈን ሥልቶችን ራጋ፣ ዳንስ ሆልም ነበር የምንሠራው ለየብቻ ነጠላ ዜማዎችን መሥራት ከጀመርን በኋላ የብሔር ብሔረሰቦች ስልቶችን መጫወት የደቡብ ዘፈን በሆነው “ያምቡሌ”ሀ ብዬ ጀመርኩ፡፡ ከዚያ በኋላ “አንበሳው አገሣ” ከማዲንጐ ጋር በኦሮምኛም የተጫወትኩት ዘፈን አለኝ፡፡ ዘፈኖቹን ለወጣቱ እንዲሁም ለሌላውም እንዲስማማ አድርገን ነው የምንሠራው፡፡ እዚህ አዲሱ ሲዲዬ ላይም ሰው ባልለመደኝና በፊት በማያውቀኝ መልኩ መጥቻለሁ፡፡ ቀስ ያሉ ዘፈኖች አሉኝ፡፡ በቀደሙት ሥራዎች ላይ ወደ ጭፈራ የማድላት ነገር ነበር፡፡ በዚህ አልበም ላይ የተካተቱት “የዋህ”፣ “ተወዳጅ”፣ “ዛሬም እወድሻለሁ” የሚሉት ረጋ ያሉ ዘፈኖች ናቸው፡፡ በእንደዚህ ዓይነት የአዘፋፈን ሥልት ሠው አያውቀኝም፡፡ ግን አሁን ለራሴ በሚስማማና በድምጼ መጠን የሚስማማውን ነገር አስቤ ሠርቻለሁ፡፡ የካሴቱ አጠቃላይ ሐሳብ አንድ ቦታ ላይ ያረፈ አይደለም፡፡ የተለያዩ ሐሳቦች ነው ያሉት፡፡

ለምሳሌ ተበቺሣ ከቃሉ ጀምሮ ኦሮሞኛ ነው፡፡ ኦሮምኛ ራፕ አለው፡፡ እንደገና እዚህ አልበም ላይ ባሕላዊውን ማሲንቆና ክራር ተጠቅሜያለሁ፡፡ ሁሉም የሙዚቃ መሣሪያ አይነቶች ሳክስፎን፣ ቤዝ፣ ሊድ አለ፡፡ ወጣት ሙዚቀኞችን አሳትፌያለሁ፡፡ ከዘፈንኩት ውስጥ ፍቅር፣ አባባሎች፣ ተስፋ ሰጪ ጉዳዮች፣ ጥሩነት፣ ከዚህም በተጨማሪ አገራዊ ስሜትን የሚቀሰቅሱ ሀገራዊ ጉዳዮችም በዚህ አልበም ከተካተቱት ውስጥ የተወሰኑት ናቸው፡፡ እንደተለመደው ለሠርግም የሚሆኑ አጫዋች ዘፈኖችም አሉበት፡፡ “ሻሎም” የሚለው ዘፍን ደግሞ የተወሰነ የሂብሪው ግጥሞች ተካትቶበታል፡፡ ያጀበኝም አቪ የሚባል እስራኤላዊ ሙዚቀኛ ነው፡፡ መጀመሪያ ጉጉት የሚሆነው መታወቅ ነው፡፡ ሙዚቃ ስጀምር ያ ስሜት እኔም ላይ ነበር፡፡ በጥልቀት ታስቦ ግጥም፣ ለዜማና ለሙዚቃ ቅንብር ምን ዓይነት መሆን አለበት የሚባልበት ጊዜ አልነበረም፡፡ በዚያ ሰዓት ላይ ዕውቅናን የመፈለግ ነው አሁን ደግሞ ዕውቅናው እጃችን ላይ መጥቷል፡፡

እንደገናም ብዙ ዓመት በሙዚቃው ሠርቻለሁ፡፡ ብዙ ዓመት በተሠራ ቁጥር እየበሰሉ መምጣት አለ፡፡ በአለባበሴ፣ በስታይሌ ሁሉ እዚህ ሲዲ ላይ ተለይቻለሁ፡፡ ዱሮ ልጅ ሆነን ዱላ ይዘን፣ ከኋላችን ውሻ፣ ትልልቅ የአንገት ሠንሠለት አድርገን ፎቶ የምንነሳበት ጊዜ ነበር፡፡ ይሄ ሁሉ ነገር በእድሜያችን የሆነ ጉዳይ ነው፡፡ አሁን በዚህ ወቅት ደግሞ ሰከን ስል እኔን የሚመስል፤ ብርሃኑ በዚህ እድሜው ምን ይመስላል የሚለውን የሚያሳይ ነገር አድርጌያለሁ፡፡ በሥራዬ ላይ ያሳየሁት ብስለት ምንድን ነው? እዚህ ደረጃ ላይ ስደርስ ሠው ከእኔ ምን ይጠብቃል? ሞቅ ያለ ሙዚቃ መጫወት ብቻ አይደለም፡፡ ሲዲ ከባድ ነገር ነው ብዙ ኃላፊነቶች አሉ፡፡ አንደኛ እኔና ታደለ ለብዙ ዘመናት አብረን ዘፍነናል፡፡ ተነጥዬ ስወጣ ምን ይዤ መምጣት አለብኝ? ሙሉ ካሴት መሥራት የሚችል አቅም ይዠ መምጣት አለብኝ በማለት ግጥሙም፣ ዜማውም፣ ሙዚቃውም እንዲሁም የአዘፋፈኔ መንገድ ላይ ሁሉ ከበፊቱ ጨምሬ በደንብ ተስተካክዬ የመጣሁበት ጊዜ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡

ይህንን መልስ ደግሞ ያገኘሁት መቼ ነው ካሴቱን ካወጣሁ በኋላ ብዙ ሠው እየደወለ በሰጡኝ አስተያየት መሠረት ከጠበኩት በላይ እንደሠራሁ ነግረውኛል፡፡ ብዙ ጊዜ ሞቅ ባሉ ሥራዎች የሚያውቀኝ ሕዝብ ሲዲውን በተለየ መንገድ አግኝቶታል፡፡ ዘፈኑ በወጣ በሳምንት ውስጥ ይህንን መልስ አግኝቻለሁ፡፡ ይህ የሚያስተምረኝ ሁልጊዜ ሰው በዕድሜ ሲገፋ፤ መብሰል ሲመጣ ጥንቃቄም አብሮ ይመጣል፡፡ ጉዞየንም ዕድገቴንም የሚያሳይ ሥራ ነው እላለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ሁልጊዜም አንድ አልበም ላይ የተወሰኑ ነጠላ ዜማዎች ገንነው የመውጣት ነገር አለ፡፡ የትኞቹ ዘፈኖች ገንነው ወጡ?

ብርሃኑ፡- እንደ አባባል “የዋህ ምን ይሆናል” የሚለው ዘፈን የብዙዎችን ስሜት በመንካት ብዙዎች ውስጥ ገብቷል፡፡ ቤላ፣ ተበቺሳና ጎንደር የመሳሰሉት ዘፈኖች ተወደዋል፡፡ የተለያዩ ሰዎች የተለያዬ ዘፈኖችን ወደውልኛል፡፡ ከሠው ሠው ይለያያል፡፡ ግን ከአልበሙ ውስጥ አምስት ዘፈኖች ጐልተው የወጡ ይመስለኛል፡፡ ቤላ፣ ተበቺሳ፣ ጐንደር፣ የዋህ፣ የአገሩ ዘፈን ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- ጊዜው ለሙዚቀኞች ፈታኝ ነው፡፡ በተለይም ከአልበም ሽያጭና ከሕገወጥ ቅጅ ጋር ተያይዞ ገበያው አንተን አላስፈራህም?

ብርሃኑ፡- ራሴ ነኝ አልበሙን ያሳተምኩት፤ የሚያከፋፍለውም ቮካል ሪከርድስ ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ የትም ቦታ ላይ አስገዳጅ ሁኔታዎች የሚያጋጥሙበት ጊዜ አለ፡፡ ዱሮ በማሣተም የሚታወቁት እነ ኤሌክትራ፣ አምባሰል አሁን ተቀይረው የማሳተሙን ሁኔታ አዲካ ይዞታል፡፡ ግን አሁንም የሚያከፋፍሉት ቮካልና ኤሌክትራ ናቸው፡፡ አዲካ ማስታወቂያውን ስለያዘ ዘፋኞቹ ለማስታወቂያው ሲሉ አብረው ይሠራሉ፡፡ እንዲሁም ከብዙ ድርጅቶች ጋር የስፖንሰር ሺፕ የማግኘት እድሉ ሠፊ ስለሆነ በዚያ ዓይነት መስመር ውስጥ ገብቶ ነገሮች ይዞታል፡፡ አዲካ ብቻውን ኃላፊነቱን ሲይዝ ብዙ ዘፋኞች ወደ አዲካ ሄዱና አዲካ ጋር ወረፋው በዛ ያንን ደግሞ እኔ ከሰራሁበት ጊዜ አንጻር ሥራዬን ለማውጣት ከእነዛ በፊት ጊዜ ወረፋ የያዙ ሲዲዎች በጠቅላላ ገብተው ካለቁ በኋላ ነው እኔ መግባት የምችለው፡፡ ይህን ሳስበው ጊዜው ስለማይጣጣምልኝ ጊዜዬን ጠብቄ ቶሎ ማውጣት እንዳለብኝ ወሰንኩኝ፡፡

ዘፈን አንዴ ከተሠራ በኋላ ሲቀመጥ አሠልቺ ነው የሚሆነው፡፡ አንደኛ ከዘመኑ ሊርቅ ይችላል፡፡ ሐሳብ ሊወራረስ ይችላል እኔ ጋር ያለው ሐሳብም ሌላ ሠው ጋር ሊኖር ይችላል፡፡ ስለዚህ ዋናው ነገር መቅደም ነው፡፡ ይህን ይህን አስቤ በራሴ ማድረግ አለብኝ አልኩኝ፡፡ አከፋፋይም አገኘሁኝ፡፡ ለእኔ አድካሚ ነበር ብዙ ነገሮችን ሠርቼበታለሁ፡፡ ማስታወቂያ መሥራቱ የተለያዩ ቢል ቦርዶችን በግሌ ነው ያሰራሁት ከተማ ውስጥ ወደ 11 ያህል ቢልቦርዶችን ሳሠራ ሁለት ብቻ ነው ስፖንሠር ያገኘሁት፡፡ ፖስተርና በራሪ ወረቀቶች አሉ፡፡ ያወጣሁት ወጪ በጣም ብዙ ነው፡፡ ዋናውን ሲዲ እንዲሸጥ ብዙ ነገር አሟልተናል፣ የሙዚቀኞቹ ፎቶግራፍ አለ፡፡ የተመረጡ ግጥሞች ተካትተውበታል፡፡

የወጪየን ውጤት ግን አሁን እያየሁት ነው፡፡ በጣም ጥሩ ነው፡፡ ጥሩ ሥራ ከተሠራ ሥራው በራሱ ይተዋወቃል፡፡ ራሱን ያስተዋውቃል፡፡ የሥራው ውጤት ነጋሪው ደግሞ ሕዝቡ ነው፡፡ ያወጣሁት አጠቃላይ ወጪ ከ600-800 ሺሕ ብር ይደርሳል፡፡ ግን አልፈራም፡፡ ምክንያቱም ዋናው ነገር መሞከር ነው፡፡ ገበያውንም ቢሆን አውቀዋለሁኝ፡፡ ያወጣሁትን ወጪ ሕዝቡ ተረድቶ የጥበብ አጋዥ መሆኑን አሳይቶ የዋናውን ሲዲ የመግዛት ሁኔታ ይኖራል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ያ ደግሞ ካልሆነ ሥራው ስኬታማ ሆኖ ነገ በኮንሰርትም እንደማገኘው አውቃለሁ፡፡ ነገር ግን ደረጃውን የጠበቀ ሥራ ይዤ መምጣት አለብኝ ብዬ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ያሰቡትን ለማሳካት ብዙ ፈተናዎች አሉ፡፡ ይሄንንም አውቃለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ምን ያህል ባለሙያዎችን አሳተፍክ? ምን ያህል ጊዜስ ወሰደብህ?

ብርሃኑ፡- ሠርቶ ለማጠናቀቅ ሁለት ዓመታት ያህል ፈጅቶብኛል፡፡ በዚህ አልበም ከተካተቱት ውስጥ አንድ ሦስት ዘፈኖች ከስድስት ዓመት በፊት የሰራኋቸውን አካትቻለሁ፡፡ የተሳተፉት ስድስት ባለሙያዎች በማቀናበር፣ ማስተሪንግ አበጋዝ እና ክብረት ናቸው፡፡ ከዚያም በተጨማሪ ቤዝ ጊታር ፋሲል ውሂብ አለበት፡፡ ሊድ ጊታር ሮቤል መሐሪ እንዲሁም መሠንቆ በማጀብ በአጠቃላይ ወደ ሀያ የሚሆኑ ባለሙያተኞች ተሳትፈውበታል፡፡

ሪፖርተር፡- በዜማም የተወሰኑትን አንተ ነህ የሰራሃቸው ድሮም ዜማ ትሠራ ነበር?

ብርሃኑ፡- ድሮም ዜማ እሞክር ነበር፡፡ ግጥምም አስተካክላለሁ፡፡ ብዙዎቹ እዚህ አልበም ላይ የተሳተፉት ወጣቶች ናቸው፡፡ በወጣቶች ማመን ራሱ ትልቅ ነገር ነው፡፡ ብዙ ጊዜ አልበሞች ላይ ተደጋጋሚ ሠዎች ናቸው የሚሰሩት፡፡ ከበፊትም እኔና ታደለ ሆነን አዳዲስ ልጅ በማውጣት እንታወቃለን፡፡ ሙሉ ካሴቴን ስሠራ በአዲስ ልጆች ነው፡፡ ከእነዚህም ውስጥ አንዱ ኢዮኤል መሐሪ አምስት ሥራ ነው የሰጠሁት፡፡ እኔ ለወጣቶችና ለአዲሶች ዕድል በመስጠት አምናለሁ፡፡ በዚህም ሥራ አዳዲሶቹን ከታዋቂ ሙዚቀኞች ጋር አንድ ላይ መሥራታቸው ሞራላቸውን ከፍ ያደርገዋል ብየ አምናለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- በቅንብርስ ደረጃ ምን አዲስ ነገር አለ?

ብርሃኑ፡- ብዙ ሙዚቃ መሣሪያዎችን ቤዝ ጊታር፣ አልቶ ሣክስ፣ ሶፕራኖ፣ ቴነር፣ ሊድ ጊታር በቀጥታ ባለሙያተኞቹ ገብተው በቀጥታ ነው የተቀረፀው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የአገራችንን ሙዚቃ ክራርንም አካትቻለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- አልበምህን ለማስተዋወቅ ቀጣይ ኮንሠርቶች አሉህ?

ብርሃኑ፡- ሲዲዬ ሰሞኑን በይፋ ከጥምቀት በፊት ይመረቃል፡፡ ከዚያ በኋላ በአሜሪካ፣ አውሮፓ፣ አውስትራሊያ፣ ካናዳም ኮንሠርቶች ይኖሩኛል፡፡ ከአዳዲሶቹም ሥራዎች ጋር የአዳዲስ መንፈስ ይኖራል፡፡

ሪፖርተር፡- ታደለ ለምን በዚህ አልበም አልተሳተፈም?

ብርሃኑ፡- ከታደለ ጋር በፍቅር ነው ያለነው፡፡ አራት አልበም አብረን ሠርተናል፡፡ ከዚያ በኋላ አራት ነጠላ ዜማዎች ሠርተናል፡፡ በዛም ምክንያት ተጣልተዋል የሚሉ ወሬዎች ነበሩ፡፡ እንዳልተጣላን ለማሳየት “በሽሽታን ዘሌ” የሚል ስልጥኛ ዘፈን አብረን ሠርተናል፡፡ ታደለም አሁን የራሱን አልበም ጨርሷል፡፡ እንደገና ደግሞ ለወደፊት አንድ ነጠላ ወይም ሙሉ አልበም የምንሰራበት አጋጣሚ ይኖራል ብዬ እገምታለሁ፡፡ ያለንን ተቀባይነት ደግሞ እናየዋለን፡፡ እዚህ ሲዲ ላይ በአጋጣሚ ሆኖ ታደለ አልተሳተፈም፡፡ ሁለታችን በምንሠራበት ጊዜ በጣም ጥሩ ነበር፡፡ ለብቻም መሥራቱም መጥፎ ነገር አይደለም፡፡ መሞከሩም ጥሩ ነው፡፡

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 12 years ago on January 6, 2013
  • By:
  • Last Modified: January 6, 2013 @ 4:01 pm
  • Filed Under: Ethiopia
  • Tagged With:

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar