www.maledatimes.com የብላቴናዎን ተማፅኖ ይቀበሉኝ ይሆን?የተማፅኖ ደብዳቤ(፩) - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

የብላቴናዎን ተማፅኖ ይቀበሉኝ ይሆን?የተማፅኖ ደብዳቤ(፩)

By   /   January 6, 2013  /   Comments Off on የብላቴናዎን ተማፅኖ ይቀበሉኝ ይሆን?የተማፅኖ ደብዳቤ(፩)

    Print       Email
0 0
Read Time:13 Minute, 12 Second

የተማፅኖ ደብዳቤ(፩)

ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሪዎስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ

ሀገረ አሜሪካ

የብላቴናዎን ተማፅኖ ይቀበሉኝ ይሆን?

ከሁሉም አስቀድሜ ልጁ እንድሆን ፀጋውን ያደለኝና ለነገሮቼ ሁሉ መትባት ያለዋጋ የፈቀደውን ቸሩ ፈጣሪዬ፣ ኃያሉ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ፡፡ እንዲሁም እናቱና እናቴን ተወዳጇን ድንግል ማርያምን አመሰግናለሁ፡፡ ያለ እርሷ በከንቱ የምባዝን መፃተኛ መሆኔን በተረዳ ነገር አውቄዋለሁና፡፡

ቅዱስ አባቴ ብፁዕ አቡነ መርቆሬዎስ!

እኔ እጅግ ባልገባኝና ባልተገባኝ ነገር ውስጥ ገብቼ በከንቱ የምናውዝ ነገርግን እግዚአብሔር ባወቀ በልቤ የተረዳሁትን ነገር ሳልናገረው ብቀር ለፀፀት እንዳይዳርገኝ የፈራሁት ከንቱ ሃሳቤ አስጨንቆኛልና እነሆ ዛሬ ለእርስዎ ልናዘዘው የተዳፈርኩ የምድር ድውይ የሆንኩ ልጅዎ ወልደአረጋዊ የጣፍኩልዎትን መልዕክት የገደፍኩትን አሟልተው፣ ያወላገድኩትን አቃንተው፣ ያቆረፈድኩትን አለስልሰው ይረዱልኝ ዘንድ በህያው በእግዚአብሔር ስም እጫማዎ ስር ወድቄ እማጠናለሁ፡፡

እግዚአብሔር ባወቀ እውነተኛውን የልቤን ሃሳብ ያመላክትልኝ፡፡ አሜን!

ቅዱስ አባቴ !

ባለፉት ፳ ዓመታት በዚህ በዕርግና ዘመንዎ መራራውን የስደት ፅዋ በዚህ በአላውያን ሃገር መጎንጨትዎ እንኳንስ ለእኛ ለኢትዮጵያውያን የተዋህዶ ልጆችዎ ይቅርና ከህሊናው ጋር ለሚኖር የሰው ዘር በሙሉ ለዘወትር ሰላምን ይነሳል፡፡ የስደትዎን አስከፊነት ዛሬ ከእኛ ከኢትዮጵያውያን በተለይም እለት በእለት ወላጆቻችን፣ ቤታችን፣ ወገኖቻችንና፣ ሃገራችን እየናፈቁን በወጣንበት የስደት ጎዳና ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ሳንመለስ የመቅረታችንን መርዶ በቅንድቦቻችን ተሸክመን ለምንከራተት ለእኛ ይልቁንም በየአረብ ሃገራቱ ለምንደየነው ለመፃተኞቹ ለእኛ ይበልጥ የተረዳን ፍዳ ነው፡፡ ስለሆነም የዘወትር ፀሎታችንና ምኞታችን እግዚአብሄር አምላክ በማያልቅ ምህረቱ ጎብኝቶን ይህ መራራው የስደት ዘመንዎ አክትሞና ስደትዎን የስደት ዳርቻ አንዲያደርግልንና ልጆቿ የሚሰበሰቡላት ታላቅ ሃገር ኢትዮጵያና ቅድስት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ያድለን ዘንድ ነው፡፡

በአለፉት ፫ ዓመታት በሁለቱ ሲኖዶሶች መካከል ሲደረግ የቆየው የእርቅና የሽምግልና መንገድ እጅግ እያዘገመ ቢሄድም በተለይም በቅርቡ ለሶስተኛ ጊዜ በዳላስ/ቴክሳስ የተደረገው የአባቶቻችን ውይይት እጅግ ተስፋ ሰጪ እንደነበር እረዳለሁ፡፡ ይሁንና በጥባጭ እያለ ማን ጥሩ ይጠጣል እንዲሉ በዚህም በዚያ ተብሎ የምንቋምጥለት እርቀ ሰላም ሳንካ እንደገጠመው እያየንና እየሰማን ነው፡፡

ይልቁንም ልዑካኖቹ በአብዘኛው ጉዳዮች ላይ ቢስማሙም የመጠላለፊያው አዙሪት “በእርስዎ ወደ ቀደመ መንበርዎ መመለስና አለመመለስ” ጉዳይ ላይ ብቻ እንደታነቀ ተረድተናል፡፡ እውነት ነው የእርስዎ ወደ ቀደመ መንበርዎ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መመለስ ለእኔ እንደ አንድ ክርስቲያን የማይናወጥ አቋሜ ነው፡፡ ምክንያቱም እውነቱ ያለው የእርስዎ በግፍ ከመንበርዎ መነሳትና ለከፍው የስደት ኑሮ መዳረግዎ ላይ ነውና ነው፡፡

ነገር ግን ስለ ቤተክርስቲያናችን እና ስለመንጋዎ ሰላም፣ ፍቅርና፣ አንድነት ይልቁንም እጅግ ይልቁንም የጠላትን ሴራ፣ ወጥመድና፣ አሽከላ ከመበጣጠስ አንፃር እውነተኛውን እውነት ለታለቁ አላማ ሲባል እንዲህ ቢመለከቱት ይጠቅም ይሆናል በማለት እኔ ሃጢያት ያጎሳቆለኝ ልጅዎ በታላቅ አክብሮትና ትህትና እጫማዎ ስር በመውደቅ እንደሚከተልው አቅርባለሁ፡-

ቅዱስነትዎ !

በሚከተሉት ዐበይት ምክንያቶች በመነሳት፡-

፩ኛ. አሁን ያለንበት ዘመን እርስዎ ከ፳ ዓመታት በፊት ከሚያውቁት በሁሉም መልኩ እጅግ የተወሳሰበና የተለወጠ በመሆኑ፣

 

፪ኛ. ያ! በዘመነ ፕትርክናዎ አብዝተው የሚያውቁት አስቸጋሪው ቢሮዎ ዛሬ በተንኮሉም ይሁን በመጠላለፉ እራሱን አዘምኖና                ይልቁንም በዘር ተደራጅቶ የለየለት የዝርፊያ አውድማ በመሆኑ፣

፫ኛ. እርስዎም ላለፉት ፳ ዓመታት ከማንኛውም የአስተዳደራዊ እንግልትና ማህበራዊ ውጣውረድ እራስዎን አግልለው በብህትውናው ብቻ ተወስነው በመቆየትዎ፣

 

በአጠቃላይ በነዚህና በሌሎች ተዛማጅ በሆኑ ምክንያቶች በመነሳት የሚከተሉትን ሁለት የተማፅኖ ሃሳቦች በፍርሃት ለማቅረብ እወዳለሁ፡፡

፩ኛ. አስቀድሞም ሊሆን እንደሚገባው በመንበሩ እርስዎ ተቀምጠው ቅዱስ ሲኖዶሱን በመምራት፣ ጳጳሳትን በመሾም፤ በቡራኬና በመሳሰሉት ለእድሜዎና ለጤንነትዎ በሚስማሙ አባታዊ አገልግሎቶች ላይ በመሳተፍና በፀሎትዎ እየባረኩን ከዕድሜ ቢቆዩልንና ፣

 

፪ኛ. አድካሚውንና አስቸጋሪውን የአስተዳደር ስራውን ግን ሁለቱም ሲኖዶሶች በአንድነት ሆነው አዲስ በሚያዘጋጁት የምርጫ        መስፈርት መሰረት   ከመካከላቸው እራሳቸው መርጠው ለሚያቀርቡልዎ እንደራሴ ቅዱስነትዎ ባርከው ስልጣንዎትን ቢያጋሩና የቤተክርስቲያኗም ውስብስብ የአስተዳደር ችግር በሚመረጡት እንደራሴዎ እልባት እንዲያገኝና እንዲሳለጥ ቤተክርስቲያናችንም ዘመኑ የሚጠይቀውን ሐዋሪያዊ ብቃት እንድትላበስ ቢያደርጉልን፤ ሲሆን ሁላችንም እንዲያም ካለ ለአብዛኛው ልጆችዎ የሚያስማማና የሚያስደስት ታላቅ አባታዊ እርምጃ ይሆናል ብዬ አምናለሁ፡፡

ስለዚህ እባክዎ ቅዱስ አባታችን በቀረዎት እድሜ እኛን የአደራ ልጆችዎን በሙሉ ፍቅርዎ ቢባርኩንና ቢመርቁን፤ እኛም እንደ ልጅነታችን በአንድነት እንድናገለግልዎት እድል ቢሰጡን ይህንም በማድረጋችን እኛ ልጆችዎ በአንድነት እርስዎን እያስቀደምን እግዚአብሔርን በፍቅር ሆነን ብናመልከውና ብናስደስተው፤ በአንፃሩም ጥንተ ጠላታችንንም ዳግመኛ ድል ልንነሳውና ልናዋርደው ይገባናል ስል እኔ ሃጢያተኛው ልጅዎ ወልደአረጋዊ በእውነት በመንፈስ ጫማዎ ስር ወድቄ አማፅንዎታለሁ፡፡

በመጨረሻም እኔ ደካማና አላዋቂ ነኝ፡፡ የተሰማኝንና ያመንኩበትን ሁሉ በቅንነትና በእውነት እንደ አቅሜ ለማስፈር ሞክሪያለሁ፡፡ እናም በዚህ ተማፅኖ ውስጥ ያለዕውቀት በስህተት ያጠፍሁት ነገር ቢኖር እባክዎ ቅዱስ አባቴ በህያው በእግዚአብሕር ስም በደሌን ሁሉ ይቅር ይሉኝ ዘንድ በሚዎዷት በድንግል ማርያም ስም ተማፅኘዎታለሁ፡፡

እግዚአብሔር አምላክ የምህረት ፊቱን ከተቅባዝባዥ ልጆቹ ላይ አይመልስብን!

ወለተኪሮስን (ነብስ ይማር) በፀሎትዎ ያስቡልኝ!

እግዚአብሔር ይስጥልኝ!

ታህሳስ 29, 2005 ዓ.ም

 

 

 

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 12 years ago on January 6, 2013
  • By:
  • Last Modified: January 6, 2013 @ 11:00 pm
  • Filed Under: Ethiopia
  • Tagged With:

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

Skip to toolbar